Saturday, 15 August 2015 15:47

በአውሮፕላን ተደብቆ ስዊድን የገባው ኢትዮጵያዊ ጥገኝነት ጠየቀ

Written by 
Rate this item
(38 votes)

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሰራተኛ ነው ተብሏል

   ከአዲስ አበባው ቦሌ አለማቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ተነስቶ ወደ ስዊድን ስቶክሆልም በመብረር ትናንት ማለዳ አርላንዳ አውሮፕላን ማረፊያ በደረሰው የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን የእቃ መጫኛ ክፍል ውስጥ ተደብቆ የተጓዘው ኢትዮጵያዊ ጥገኝነት መጠየቁን ቢቢሲ ዘገበ፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሰራተኛ እንደሆነ የተነገረለትና በሃያዎቹ እድሜ ክልል ውስጥ እንደሚገኝ የተገለጸው ወጣቱ፣ አውሮፕላኑ ማረፉን ተከትሎ ሰራተኞቹ ጭነት ሊያራግፉ በሩን ሲከፍቱ ክፍሉ ውስጥ ተደብቆ እንደተገኘ የጠቆመው ዘገባው፣ ወዲያውኑ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውሎ በተደረገለት የጤና ምርመራ ምንም አይነት የጤና ችግር እንደሌለበት መረጋገጡን ገልጿል፡፡
ለስምንት ሰዓት ያህል በርሮ አርላንዳ አውሮፕላን ማረፊያ ጣቢያ በደረሰው አውሮፕላን ተደብቆ የተገኘው ወጣቱ፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሰራተኛ መሆኑን የሚያሳይ የደረት ላይ መታወቂያ ማድረጉን ዘገባው ጠቅሶ፣ ወደ ስቶክሆልም ኢሚግሬሽን ቢሮ ተወስዶ ጥገኝነት መጠየቁንም አመልክቷል፡፡
የአርላንዳ አውሮፕላን ማረፊያ ጣቢያ ምክትል መኮንን የሆኑት ስቴፋን ፋርዲክስ፤ ወጣቱ ምንም አይነት የወንጀል ድርጊት ፈጽሟል ተብሎ እንደማይጠረጠር ገልጸው፣ በስዊድን አውሮፕላን ማረፊያ ጣቢያዎች መሰል ድርጊት ተፈጽሞ እንደማያውቅና የአሁኑ የመጀመሪያው እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

Read 6153 times