Saturday, 15 August 2015 15:46

የበሬ ንግድ ያለደረሰኝ ማከናወን ተከለከለ

Written by 
Rate this item
(16 votes)

ማንኛውንም ከብት ያለ ንግድ ፈቃድ መሸጥ አይቻልም

በአዲስ አበባ የዳልጋ ከብት ግብይት ከትላንት ጀምሮ በደረሰኝ እንዲካሄድ የተወሰነ ሲሆን ማንኛውም የቁም እንስሳት የንግድ ግብይት ያለ ንግድ ፈቃድ ማከናወን እንደማይቻልም የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ አስታውቋል፡፡
የከብት ግብይቱ የሚካሄደው በ5 የገበያ ማእከላት፡- በጉለሌ፣ የካ ካራሎ፣ ንፋስ ስልክ፣ አቃቂና ኮልፌ ቀራኒዮ መሆኑን የገለፀው ቢሮው፤ ከእነዚህ ማእከላት ውጪ ምንም አይነት የቁም እንስሳት ንግድ ማካሄድ እንደማይቻል አስጠንቅቋል፡፡
የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ ገመቺሳ መላኩ ለአዲስ አድማስ እንደገለፁት፤ ለጊዜው የደረሰኝ ግብይት ሥርዓቱ የሚመለከተው የዳልጋ ከብት (በሬና ላም) ብቻ ቢሆንም ወደፊት የበግና ፍየል ንግድም በደረሰኝ እንደሚሆን ታውቋል፡፡
የልኳንዳ ማህበር ከግብር ጋር በተያያዘ ሂሳብ ማወራረድ በመቸገሩ ግብይቱ በደረሰኝ እንዲካሄድ በተደጋጋሚ መጠየቁን ኃላፊው ጠቁመው፣ የደረሰኝ ግብይቱ የማህበሩን ችግር እንደሚፈታ ይጠበቃል ብለዋል፡፡
የደረሰኝ  ግብይቱ ህገወጥ እርድን፣ የቤት ለቤት ማደለብንና መሰል ህገወጥ ተግባራትን ለመቆጣጠር እንደሚያስችልና የህብረተሰቡን ጤናም ለመጠበቅ እንደሚያግዝ የተገለፀ ሲሆን የቁም እንስሳት ንግድ ግብይት ሥርዓቱን ለማዘመንም ዓይነተኛ መፍትሄ ነው ተብሏል፡፡
እስካሁን በ5ቱ የገበያ ማእከላት የሚገኙ ነጋዴዎች የንግድ ፍቃድ እንዲያወጡ የተለያዩ ጥረቶች መደረጋቸውንና አብዛኞቹም የንግድ ፍቃድ እንዳላቸው የጠቆሙት አቶ ገመቺስ፤ ፈቃድ ሳያወጡ ተቀላቅለው እየሰሩ ያሉ ነጋዴዎችም ፍቃድ አውጥተው ወደ ህጋዊ ስርአት እንዲገቡ ይደረጋል ብለዋል፡፡ የደረሰኝ ቁጥጥር ስርዓቱንም የገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን እንደሚከታተለው ታውቋል፡፡

Read 4534 times