Saturday, 15 August 2015 15:44

ሂዩማን ራይትስ ዎች ለኢትዮጵያ የመረጃ ጠለፋ ቴክኖሎጂ ሸጧል ያለውን ተቋም ከሰሰ

Written by 
Rate this item
(10 votes)

ተቋሙ ከኢትዮጵያ ጋር መስራቴን  ሙሉ ለሙሉ አቋርጫለሁ ብሏል

አለማቀፉ የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች ሂዩማን ራይትስ ዎች ለኢትዮጵያ የመረጃ ጠለፋ ቴክኖሎጂዎችን ሸጧል፤ ለደህንነት ባለሙያዎች ስልጠና በመስጠት የዜጎች መብቶች እንዲጣሱ እገዛ አድርጓል ያለውን “ሃኪንግ ቲም” የተባለ የጣሊያን ተቋም በጉዳዩ ዙሪያ በቂ ምላሽ አልሰጠም፣ የመብቶች ጥሰቶችን ለማስቆምም እርምጃ አልወሰደም ሲል ከሰሰ፡፡
ሃኪንግ ቲም ለተለያዩ አገራት መንግስታት የመረጃ መጥለፊያ ቴክኖሎጂዎችን በመሸጥና ለባለሙያዎች ስልጠና በመስጠት፣ መንግስታት የዜጎችን ሰብአዊ መብቶች እንዲጥሱ እገዛ ያደርጋል ያለው ሂዩማን ራይትስ ዎች፣ በኢትዮጵያ ሲከናወን የቆየውን የመረጃ ጠለፋና የመብቶች ጥሰት በተመለከተ ምላሽ እንዲሰጠው ቢጠይቅም በቂ ምላሽ ሊሰጠው እንዳልቻለ ከትናንት በስቲያ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡
ተቋሙ ጉዳዩን በተመለከተ ምርመራ ለማድረግም ሆነ የኢትዮጵያ መንግስት ቴክኖሎጂውን በመጠቀም በዜጎቹ ላይ የሚያደርሰውን የመብቶች ጥሰት ለማስቆም ምንም አይነት ተጨባጭ እርምጃ አልወሰደም ሲል የከሰሰው ሂዩማን ራይትስ ዎች፣ ሃኪንግ ቲም ለኢትዮጵያ የደህንነት ባለሙያዎች የግለሰቦችን ኮምፒውተሮች ሰብረው መግባት የሚችሉበትን ስልጠና መስጠቱን እንደቀጠለና ቀጣይ ስምምነቶችን ለማድረግ እንቅስቃሴ ጀምሮ እንደነበር የሚያረጋግጡ መረጃዎችን በሃምሌ ወር እንዳገኘ አስታውቋል፡፡
ሃኪንግ ቲም ለኢትዮጵያ መንግስት የሸጣቸው የመረጃ መጥለፊያ ቴክኖሎጂዎች ከቫይረስ መከላከያ ፕሮግራሞች አቅም በላይ እንደሆኑና በቀላሉ ወደ ግለሰቦች ኮምፒውተሮች በመግባት መረጃዎችን እንደሚወስዱ የጠቆመው ሂዩማን ራይትስ ዎች፣ ከተቋሙ ኢሜይል አፈትልከው የወጡ መረጃዎችም ተቋሙ በሚያዝያ ወር ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ከ700 ሺህ ዶላር በላይ የሚገመት አዲስ የቴክኖሎጂና የስልጠና ስምምነት ለመፈጸም ሲያደርጉት የነበረው እንቅስቃሴ ሳይሳካ መቅረቱን ያመለክታሉ ብሏል፡፡
ሃኪንግ ቲም ጉዳዩን በተመለከተ ምላሹን እንዲሰጥ ባለፈው ሃምሌ ወር ላይ ከሂውማን ራይትስ ዎች ለቀረበለት ጥያቄ በሰጠው ምላሽም፣ የሚያመርታቸው ሶፍትዌሮች የሚንቀሳቀሱት በእሱ ሳይሆን በገዙት ደንበኞቹ መሆኑን ጠቁሞ፣ ቴክኖሎጂው ለስለላ ተግባር ስለመዋሉ የሚያውቀው ነገር እንደሌለ ገልጾልኛል ያለው ሂዩማን ራይትስ ዎች፣ ከተቋሙ አፈትልከው የወጡ መረጃዎች ግን የኢትዮጵያ መንግስት የስለላ ተግባራት የሰብአዊ መብቶችን የሚጥሱ መሆን አለመሆናቸውን ለማጣራት በርካታ አጋጣሚዎች እንደነበሩት የሚያመለክቱ ናቸው ብሏል፡፡
ተቋሙ በዚሁ ምላሹ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ያለውን ግንኙነት በ2015 የመጀመሪያዎቹ ወራት ሙሉ ለሙሉ አቋርጫለሁ ማለቱንም ሂውማን ራይትስ ዎች ጠቁሟል፡፡

Read 3937 times