Print this page
Saturday, 15 August 2015 15:43

ለድርቅ አደጋ በተጋለጡ አንዳንድ አካባቢዎች ዝናብ መዝነብ ጀምሯል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(7 votes)

በሰኔና ሐምሌ ዝናብ ባልዘነበባቸውና ለድርቅ አደጋ በተጋለጡ አፋርና ወሎ እንዲሁም ሃረርና ድሬደዋ አካባቢ ሰሞኑን ዝናብ መዝነብ እንደጀመረ ምንጮቻችን ገልፀዋል፡፡
በድርቅ አደጋ በቀን እስከ 100 የቤት እንስሳት እየሞቱ በነበረበት የአፋር ክልል በአሁን ወቅት አስቸኳይ እርዳታና ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን የጠቆሙት ምንጮቹ፤ በተለይ ከሎጊያ እስከ ክልሉ ዋና መቀመጫ ሠመራና አካባቢው ተደጋጋሚ ዝናብ እንደዘነበ ተናግረዋል፡፡
ድርቅ ተከስቶባቸው ከነበሩ ቦታዎች አንዱ የድሬደዋና ሀረር ቆላማ አካባቢ ከባለፈው ሠኞ ጀምሮ መጠነኛ ዝናብ እየዘነበ ሲሆን በድሬደዋ ከተማ ጠንከር ያለ ዝናብ መዝነቡን ለማወቅ ተችሏል፡፡ በድሬደዋ ገጠራማ አካባቢዎች ግን አሁንም የዝናቡ ሁኔታ የሚጠበቀውን ያህል አለመሆኑን ምንጮች ለአዲስ አድማስ ጠቁመዋል፡፡
ከሰሜኑ የአገሪቱ ክፍሎች አንዱ በሆነውና ከፍተኛ የድርቅ ስጋት አንዣቦበት የነበረው ከሸዋሮቢት እስከ ወሎ ባለው መስመር በሣምንቱ ተደጋጋሚ ዝናብ መዝነቡን በአካባቢው የሚገኙ ምንጮች ጠቁመዋል፡፡
በምስራቅ ስምጥ ሸለቆ አካባቢ ተብሎ በሚታወቀው ከአዳማ እስከ መተሃራ ባለው አካባቢም በሳምንቱ የሚጠበቀውን ያህል ባይሆንም ዝናብ መዝነብ መቻሉን በአካባቢው የሚመላለሱ ምንጮቻችን ጠቁመዋል፡፡
የብሄራዊ ሜትሪዎሎጂ አገልግሎት ማክሰኞ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ፤ በሰኔና በሐምሌ ወር በሰሜን ምስራቅ፣ በመካከለኛው እንዲሁም በመካከለኛው ምስራቅ ስምጥ ሸለቆ አካባቢዎችና በምስራቁ የሀገሪቱ ክፍሎች ከመደበኛ በታች ዝናብ መዝነቡን ጠቅሶ በነሐሴ ወር በነዚህ አካባቢዎች የዝናቡ መጠን ሊጨምር እንደሚችል ተንብይዋል፡፡
በዘንድሮ ክረምት የተፈጠረው የዝናብ እጥረት የኤሊኒኖ ክስተት ውጤት መሆኑን የአየር ትንበያ ባለሙያው ዶ/ር ድሪባ ቆሪቻ ጠቅሰው፣ በፓስፊክ ውቅያኖስ አካባቢ የተፈጠረውን ሙቀት መጨመር ተከትሎ የዝናብ እጥረቱ መፈጠሩን ገልፀዋል። በነሐሴ ወር የዝናቡ ሁኔታ በሚፈለገው መጠን እንደሚዘንብና ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ብሄራዊ ሜትሪዎሎጂ በመግለጫው ጠቁሟል፡፡

Read 4109 times