Saturday, 15 August 2015 15:41

የኢትዮጵያ ሴቶች ማኅበራት ቅንጅት ለእንቁጣጣሽ የመኪና ስጦታ አዘጋጀ

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(2 votes)

• ከ120 በላይ ሰዎች ተሸልመዋል
• የSMS ሎተሪ እስከ ጳጉሜ 2 ተራዝሟል

 የኢትዮጵያ ሴቶች ማኅበራት ቅንጅት (ኢሴማቅ)፤ ለእንቁጣጣሽ የ375ሺ ብር የመኪና ብር ስጦታ ማዘጋጀቱን አስታወቀ፡፡ ነሐሴ 10 ይጠናቀቅ የነበረው 8400 የአጭር ጽሑፍ መልዕክት (SMS) የሎተሪ ዕጣ እስከ ጳጉሜ 2 ቀን 2007 ዓ.ም ተራዝሟል፡፡
ለኢትዮጵያ ሴቶች ማህበራት ቅንጅት ማዕከል የህንፃ ማስገንቢያ ታስቦ ሃምሌ 25 ቀን 2006 ዓ.ም ተጀምሮ የነበረው የ8400 የአጭር መልዕክት ጽሑፍ ሎተሪ፣ ከህዳሴው ግድብ የገንዘብ ማሰባሰቢያ 8100 የአጭር መልዕክት ጽሑፍ ሎተሪ ጋር በመገጣጠሙ፣ ከ6 ወር እንቅስቃሴ በኋላ መቋረጡን ኢሴማቅ አስታውሷል፡፡
በድጋሚ ከግንቦት 8 ቀን 2007 ጀምሮ የአጭር መልዕክት ጽሑፍ ሎተሪው ሲካሄድ መቆየቱን ጠቁሞ፣ ቀኑ በማጠሩ ከብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር ድርጅት በተገኘ ፈቃድ እስከ ጳጉሜ 2 እንደተራዘመ ተገልጿል፡፡
የሎተሪ ጨዋታው ጊዜ በመራዘሙ በአዲስ መልክ የእንቁጣጣሽ ገጸ በረከት ይዘን ቀርበናል ያሉት የኢሴማቅ ዳይሬክተር፤ የሽልማቶችን ብዛትም ጨምረናል ብለዋል፡፡ አሸናፊዎች የልብስ ማጠቢያ ማሽን፣ ላፕቶፕ፣ ቴሌቪዥን፣ ሞተር ሳይክል፣ ፍሪጅና ሳምሰንግ ሞባይል እየተሸለሙ መሆናቸውን የጠቆሙት ዳይሬክተሯ፤ በመጨረሻም የመኪና ሽልማቱ ዕጣ ይወጣል ብለዋል፡፡
የሎተሪ ዕጣ 8400 እንደገና ከተጀመረ ወዲህ ጥሩ ውጤት እያሳየና ዕድለኞችም እየተሸለሙ ነው ያሉት ዳይሬክተሯ፣ በየቀኑ ከሚበረከቱ ሳምሰንግ ሞባይሎች 85 ሰዎች፣ በየሳምንቱ ከሚሰጡ ቶሺባ ላፕቶፖች 7 ሰዎች፣ በየሳምንቱ ከሚሸለሙ 21 ኢንች ቴሌቭዥኖች 13 ሰዎች፣ በየ15 ቀኑ ከሚበረከቱ ዌስት ፖይንት ልብስ ማጠቢያ ማሽኖች 7 ሰዎች፣ በየሁለት ሳምንቱ ከሚሰጡ ሞተር ሳይክሎች 8 ሰዎች፣ በየ15 ቀኑ ከሚበረከቱ ፍሪጆች 9 ሰዎች መሸለማቸውን ገልፀው በሎተሪው አጋማሽ የሚወጣውን የቤት መኪና ዕጣም በሆሳዕና መምህራን ኮሌጅ አስተማሪ የሆኑት አቶ መሃሪ ዋኬሮ እንደተሸለሙ ተናግረዋል፡፡
ሎተሪው ብዙ ጥቅሞች እንዳለው ጠቅሰው ለሕንፃው ግንባታ የሚያስፈልገው 47 ሚሊዮን ብር ባይሞላም የኢሴማቅን ማንነት በኅብረተሰቡ ዘንድ ለማስተዋወቅ በእጅጉ እንዳገዘና ስለማህበሩ የበለጠ ግንዛቤ ለመፍጠር እንዳስቻለ ዳይሬክተሯ ጠቁመዋል፡፡

Read 1748 times