Print this page
Saturday, 08 August 2015 09:11

የኮንዶሚኒየም ዕጣ ያልወጣው የቤቶቹ ግንባታ ባለመጠናቀቁ ነው ተባለ

Written by  ማህሌት ኪዳነወልድ
Rate this item
(10 votes)

       ባለፈው ሰኔ ወር መጨረሻ ላይ ለነባር 20/80 እና ለአዲስ 10/90 የጋራ መኖሪያ ቤቶች ዕጣ እንደሚወጣ ቢነገርም የቤቶቹ ግንባታ ባለመጠናቀቁ የዕጣ ማውጫውን ለማራዘም መገደዱን የቤቶች ልማትና አስተዳደር ኤጀንሲ አስታወቀ፡፡
የኤጀንሲው የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች የስራ ክፍል ሃላፊ አቶ ወንዳለ በፍቃዱ ለአዲስ አድማስ እንደተናገሩት፤ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት፣ 74ሺህ ቤቶችን ለማስተላለፍ ቢታቀድም የተላለፉት ግን 35ሺህ ብቻ ናቸው፡፡
አሁን ቤቶቹ በመጠናቀቅ ምእራፍ ላይ መሆናቸውን እቦታው ድረስ ሄደን አይተናል ያሉት  ኃላፊው ቤቶቹን በተረከቡ በአጭር ጊዜ ውስጥ፣ ከተቻለም በአዲሱ አመት መግቢያ ላይ እጣውን እንደሚያወጡ ተናግረዋል፡፡
የቤቶች ግንባታ ፕሮጀክት ጽ/ቤት የኮሙኒኬሽን ኃላፊ አቶ ካሳ ወልደሰንበት በበኩላቸው፤ ለቤቶቹ በወቅቱ አለመጠናቀቅ የተለያዩ ምክንያቶችን ጠቅሰዋል፡፡ ክረምት በመሆኑ የፈጠረው የመንገድ ችግር፣ ከበጀት መዘጋት ጋር ተያይዞ የተከሰተው የፋይናንስ እጥረት ተጠቃሽ ሲሆኑ በዋናነት ግን በኃይል መቆራረጥ ምክንያት መስኮቶችን ለመግጠም አለመቻላቸውና የቀለም አቅርቦት ችግር ፈተና እንደሆነባቸው ኃላፊው ገልፀዋል፡፡
የቤቶቹ ግንባታ ከ85 በመቶ በላይ መገባደዱን ሃላፊው ጠቁመው በርግጠኝነት የሚጠናቀቅበትን ጊዜ ለመግለፅ ግን እንደሚቸገሩ ተናግረዋል፡፡

Read 4248 times