Print this page
Saturday, 01 August 2015 14:14

ጆሴፍ ፍራንሲስ ከ33 ዓመት ኑሮ በኋላ ኢትዮጵያን በሞት ተለያት

Written by  ማህሌት ኪዳነወልድ
Rate this item
(9 votes)

አስከሬኑ ከትላንት በስቲያ ወደ አገሩ ተሸኝቷል
                              
    ላለፉት 33 ዓመታት በኢትዮጵያ የኖረው ሕንዳዊው መምህርና የሕፃናት መጽሐፍት ደራሲ ጆሴፍ ፍራንሲስ፣ ባለፈው ማክሰኞ ማታ መኖሪያ ቤቱ በር ላይ ወድቆ ሕይወቱ አለፈ፡፡ አስከሬኑ ከትላንት በስቲያ ሐሙስ ወደ ትውልድ አገሩ ህንድ በክብር ተሸኝቷል፡፡
በ1974 ዓ.ም በ29 ዓመቱ ከተወለደበት ደቡብ ሕንድ ታሚላዱ ማዱሬ ክልል፣ በመምህርነት ሙያ ወደ ኢትዮጵያ የመጣው ጆሴፍ ፍራንሲስ፤ የዕድሜውን ግማሽ ኢትዮጵያ ውስጥ በማስተማርና የሕፃናት መጻሕፍትን በመጻፍ ነው ያሳለፈው፡፡
በትምህርት ሚኒስቴር ተመድቦ በወሎ ሓይቅ ማስተማር የጀመረው ጆሴፍ፤ በመቀጠልም በአዲስ አበባ በቦሌ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት በእንግሊዝኛ መምህርነት አገልግሏል፡፡ ለበርካታ ዓመታትም በግሪክ የማኅበረሰብ ት/ቤት የእንግሊዝኛ ቋንቋና ማኅበራዊ ሳይንስ ሲያስተምር ቆይቷል፡፡
ለኢትዮጵያ ታሪክ ልዩ ፍቅር እንደነበረው የሚነገርለት ሕንዳዊው መምህር፣ “የዐድዋ ጦርነት”፤ “ዐፄ ቴዎድሮስ”፤ “ዓለማየሁ ቴዎድሮስ - የኢትዮጵያ ልዑል”፤ “ድንቂቱ ኢትዮጵያ” የተሰኙ መጻሕፍትን አሳትሟል፡፡  የኢትዮጵያ ሕፃናት የአገራቸውን ታሪክ እንዲያውቁ የሚያግዝ በአቅማቸው የተዘጋጁ የታሪክ መፃሕፍት አለመኖሩን የተገነዘበው ጆሴፍ ፍራንሲስ፣ የመጀመሪያ የህፃናት መጽሐፉን “The Battle of Adowa - የዐድዋ ጦርነት” በሚል ካሳተመ በኋላ ከሦስት የማያንሱ የታሪክ መጻሕፍትን ለህፃናት አዘጋጅቷል፡፡
የመጨረሻ መጽሐፉ ደግሞ “የድንቂቱ ኢትዮጵያ ድንቃ ድንቆች” (This is Ethiopia፡ A book of Fascinating Facts) የተሰኘ ሲሆን በኢትዮጵያ ሊጎበኙ የሚገባቸውን ድንቅ ቦታዎች በመዘርዘር የሚያስተዋውቅ ነው፡፡ ጆሴፍ ሌላ አዲስ መጽሐፍ በማዘጋጀት ላይ እንደነበር ታውቋል፡፡
በኢትዮጵያ ፍቅር ተማርኮ እዚሁ የቀረው ጆሴፍ፤ ባለፈው ማክሰኞ በ62 ዓመቱ ኦሎምፒያ አደባባይ ከሚገኘው የአፓርትመንት ቤቱ በረንዳ ላይ ላፕቶፑን እንዳነገተና መነጽሩን እንደያዘ መሬት ላይ ወድቆ ሞቶ ተገኝቷል፡፡
ከቅርብ ወዳጆቹ አንዱ የሆነው ጋዜጠኛ ጌጡ ተመስገን፣ ስለ ጆሴፍ ሲናገር፤ “እኔ የኢትዮጵያ ልጅ ነኝ፤ ለሕንድ አልሠራሁም፤ ስለዚህም ሕንድ እኔን አታውቀኝም፤ ስሞት ወሎ ሐይቅ ወስዳችሁ እንድትቀብሩኝ!” ብሎ በዚያች በምትናፍቀው ሣቁ ንግግሩን ያጅባታል፤ ዛሬም ያቺን ሣቁን እናፍቃታለሁ፡፡ የመጨረሻ ሣቁንና የማይጠገብ ጨዋታውን ከመሞቱ ሁለት ቀናት በፊት ቦሌ በምትገኝ ግሮሰሪ ውስጥ ነበር የሰማሁት፤ የአሜሪካ ድምፅ ሬዲዮ ዘጋቢ መለስካቸው አምሃና ሌሎችም ታላላቅ እንግዶች ነበሩ፡፡ ለካ ጆሴፍ እየተሰናበተን ነበር፤ እየተለየን፤ አላወቅንም እንጂ፤” ሲል ጌጡ ከሕንዳዊው ጓደኛው ጋር ያሳለፈውን የመጨረሻ ቀን አስታውሷል፡፡
ጆሴፍ፤ ከ11 ዓመታት በፊት የመጀመሪያ መጽሐፉ “የዐድዋ ጦርነት” መውጣቱን ተከትሎ ከአዲስ አድማስ ጋዜጣ ጋር ባደረገው ቃለ - ምልልስ፤ ለታሪካዊ ቦታዎች ትልቅ ፍቅር እንዳለውና መጓዝ እንደሚወድም ገልፆ ነበር፡፡ በርግጥም ጆሴፍ ያልጐበኘው ታሪካዊ ስፍራ እንደሌለ የቅርብ ወዳጆቹ ይመሰክራሉ፡፡ የበርካታ የጥበብ ባለሞያዎች እና የጋዜጠኞች ባልንጀራ የነበረው ጆሴፍ፤ ድንገተኛ አሟሟቱ ለብዙዎቹ አስደንጋጭ ሆኖባቸዋል፡፡

Read 4317 times