Saturday, 01 August 2015 14:13

መንግሥት በቤተ ክርስቲያኒቱ የሙስና ወንጀሎች ላይ ርምጃ እንደሚወስድ አስታወቀ

Written by 
Rate this item
(15 votes)

  የሰንበት ት/ቤቶቹ እንቅስቃሴያቸውን አጠናክረው እን
                         ‹‹መልካም ዜጋ የምታወጣው ተቋም በሙስና መጎዳቷ ለሀገርም ጉዳት ነው”፤ ወንጀሉ ላይ መንግሥት መዋቅሩን                         ጠብቆ ይገባል፤ በሃይማኖቱ መሸፈን አይችሉም››        ዶ/ር ሺፈራው ተክለ ማርያም


        ከመልካም አስተዳደር ዕጦት እና ከተጠያቂነት ሥርዐት መጥፋት ጋር በተያያዘ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አስተዳደራዊ መዋቅር ውስጥ ሰፍኗል በተባለው ምዝበራ እና ሙስና  መንግሥት መዋቅሩን ጠብቆ ሕጋዊ ርምጃ እንደሚወስድ የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
ከትላንት በስቲያ ከአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት አመራሮች ጋር በተካሔደው ውይይት፣ መንግሥት ከሃይማኖት ተቋማት ጋር በሰላም እና በልማት ጉዳዮች ላይ አብሮ እንደሚሠራ የጠቀሱት የሚኒስቴሩ ከፍተኛ ሓላፊዎች፣ ‹‹ የሕዝብ ሀብት ለህዝብ ጥቅም መዋል አለበት፤ በሕዝብ ገንዘብ እንዲቀለድ አንፈልግም፤ መንግሥት ሰላምንና የሕግን የበላይነት ከማረጋገጥ አኳያ ደረጃውን ጠብቆና የሙስና ወንጀል መፈጸሙን አጣርቶ ርምጃ ይወስዳል፤›› ብለዋል፡፡
‹‹ሙዳየ ምጽዋቱን ማን ነው የሚጠቀምበት፤ ሕዝብ ይጥላል፤ ጥቂት ሰዎች መኪና እና ቤት ይሠሩበታል፤›› በማለት የአለመግባባት መንሥኤዎችን የዘረዘሩት ሚኒስትር ዴኤታው አቶ ሙሉጌታ ውለታው፣ የሚዘርፉት ሃይማኖት ሳይኖራቸው በሃይማኖት ስም የሚነግዱ ግለሰቦች እና አካላት እንደኾኑ ገልጸዋል፡፡ በሚፈጽሟቸው ወንጀል ነክ ጉዳዮችም ‹‹መንግሥት ለምን ጣልቃ ይገባል አይባልም፤ ከሀገረ ስብከቱ ጋር ኾኖ ይከታተላል፤ ወንጀለኛውን ይይዛል፤ ይቀጣል፤ ያጸዳል፤›› ብለዋል፡፡
የግልጽነት እና የተጠያቂነት አሠራር ዘመኑ የሚጠይቀው እና መንግሥትም በአቋም ያስቀመጠው መኾኑን ያወሱት ሚኒስትር ዴኤታው፣ የሀገረ ስብከቱ ሰንበት ት/ቤቶች ሙስናና ብልሹ አሠራር እንዲወገድ፣ መልካም አስተዳደር እንዲሰፍንና ሃይማኖት እንዲጠበቅ የጀመሩትን እንቅስቃሴ አድንቀዋል፡፡ ‹‹እንቅስቃሴአችኹን ከሁከት በራቀ፣ ስልታዊ በኾነና በሰላማዊ መንገድ ቀጥሉ፤ መንግሥትም ድጋፍ ያደርግላችኋል፤›› ሲሉም አበረታተዋቸዋል፡፡
የሰንበት ት/ቤት አባላት ሰላም ፈላጊዎች እንደኾኑ የገለጹት የአንድነቱ አመራሮች በበኩላቸው፣ ለቤተ ክርስቲያን ሰላም መደፍረስ ዋነኛ ምንጩ የመልካም አስተዳደር ዕጦት እንደኾነ አስረድተዋል፡፡ እንደ አመራሮቹ፣ ቅዱስ ሲኖዶሱ እና ቅዱስ ፓትርያርኩ ሙስናንና ብልሹ አሠራርን ለማስወገድና ተቋማዊ ለውጥን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ውሳኔዎችን በየጊዜው ቢያሳልፉም ትግበራው አስተዳደራዊ መዋቅሩን ከላይ እስከ ታች በኔትወርኪንግ በተቆጣጠሩ ሙሰኞች ስለሚታገት ተፈጻሚ ለመኾን አልቻለም፡፡
ሙሰኞቹ÷ በሙዳየ ምጽዋት፣ በስእለትና በስጦታ ምእመኑ የሚሰጠውን ገንዘብ ለራሳቸው ዓላማና ጥቅም እያዋሉ፤ የአድባራቱን መሬትና ሕንፃ ከዋጋ በታች እያከራዩ በቤተ ክርስቲያኒቱ ጥቅሞችና መብቶች ከገቢያቸው በላይ ሕገ ወጥ ሀብት ያካብታሉ፤ በሦስትና በአራት ሺሕ ብር ደመወዝ ኤሮትራከር ይገዛሉ፤ ሕንፃ ይሠራሉ፡፡
ይኹንና የተጠያቂነትና የግልጽነት አሠራር ባለመኖሩ ሲነቃባቸውና ተቃውሞ ሲበረታባቸው የበለጠ ወደሚዘርፉበት ቦታ በዕድገት እንደሚዘዋወሩ ጠቅሰው፣ ለዚኽም በጎጠኝነትና በጥቅም ትስስር ተሞልቷል ያሉት የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ፅ/ቤት ተጠያቂ ነው ብለዋል፡፡ “ሀገረ ስብከቱ ሌባን አሳልፎ አይሰጥም፤ በሹመት እና በዝውውር ጉቦ እየተከፈለ አብሮ ይበላል፤” በማለት የወቀሱት አመራሮቹ፣ “የሕዝብ ንብረት እየባከነ ስለኾነ መንግሥት ጣልቃ ይግባልን፤ የመንግሥት ባለሥልጣናት ሀብታቸው ተሰፍሮ ተቆጥሮ ይታወቃል፤ አሠራሩ እዚኽም ይምጣልን፤” ሲሉ አመልክተዋል፡፡
ሙሰኞችን በመቃወማቸውና እውነቱን በመናገራቸው አሸባሪዎች ተብለው ለእስር እንደሚዳረጉ  አመራሮቹ ጠቁመው፣  የጸጥታ አካላት ርምጃ ከመውሰዳቸው በፊት ኹኔታቸውን በሚገባ እንዲያጣሩና ፍትሐዊ አሠራር እንዲከተሉ ጠይቀዋል። ከአስተምህሮ ውጭ የኾኑ ግለሰቦችን የማጋለጥ ድርሻ የእነርሱ መኾኑን ገልጸው፣ በዚኽም በአክራሪነት መፈረጃቸው አግባብነት እንደሌለው ተናግረዋል፡፡
“አክራሪነትና ጽንፈኝነት በሃይማኖት ተቋማት ውስጥ መኖሩ የሚያከራክር አይደለም፤” ያሉት ሚኒስትሩ ዶ/ር ሺፈራው ተክለ ማርያም፣ ኾኖም ጥያቄው በሃይማኖት አጥባቂነት እስከተነሣ ድረስ ከአክራሪነት ስለሚያርቅና ከሙስና ስለሚጠብቅ የሚደገፍ መሆኑን ጠቁመው የፍረጃው አካሔድ ስሕተት መኾኑን አብራርተዋል። እንደ ሚኒስትሩ፣ የቤተ ክርስቲያኒቱ አስተምህሮ የማይፈቅደውን የአክራሪነት አስተሳሰብና ተግባር በሃይማኖት ሽፋን የሚያራምዱ ግለሰቦች ለተቋሙ ደኅንነት ሲባል መለየት አለባቸው፡፡
ሕዝብ ከተግባርም እንደሚማር ዶ/ር ሺፈራው ገልጸው፣ አትስረቅ እያሉ በሌላቸው ገቢ የሚልዮን ብር መኪኖችን የሚነዱ አካላት፣ ለሀገር መልካም ዜጋ የምታወጣውን ተቋም በማማሰን በሕዝብ ላይ ተጽዕኖ እየፈጠሩ ናቸው ብለዋል፡፡ ይህም ለሀገር የሚጎዳ በመኾኑ ድንጋይ በመወርወር ሳይኾን በምእምኑ ሰላማዊ እንቅስቃሴ በቀጣይነት መጋለጥ እንደሚገባቸው መክረዋል፤ የሰንበት ት/ቤት አባላትም ከቤተ ክርስቲያኒቷ አልፎ ለሀገርና ለዓለም የሚበቁ ሊቃውንቷን በማስተባበር ለመልካም አስተዳደር መስፈን የሚያደርጉትን ጥረት አጠናክረው እንዲቀጥሉ አሳስበዋል፤ መንግሥትም ‹‹መዋቅሩን ጠብቆ በወንጀሉ ላይ ይገባል፤ በሕግም ይጠይቃቸዋል፤ በሃይማኖቱ መሸፈን አይችሉ፤›› ሲሉ አስታውቀዋል፡፡
በሚኒስቴሩ የስብሰባ አዳራሽ በተደረገው በዚኹ የግማሽ ቀን ምክክር ማጠናቀቂያ ላይ፣ የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ እና የዋና ክፍል ሓላፊዎች የተገኙ ሲኾን ሚኒስትሩም “የወጣቶቹን ጥያቄ እንደ ቀላል አትዩት፤ በአስቸኳይ ፍቱ” ሲሏቸው ተደምጠዋል፡፡
ቀደም ሲል ሚኒስቴሩ፣ ከሀገረ ስብከቱ የአድባራት አለቆች፣ ካህናት እና ሰባክያነ ወንጌል ጋር ተመሳሳይ ምክክር ያደረገ ሲሆን፤ ይኸውም በቅርቡ በሃይማኖት ተቋማት በሰላም አብሮ መኖር እና ጤናማ ግንኙነቶች ማስፈንን በተመለከተ በጋራ እንደሚካሔድ ለሚጠበቀው ውይይት ቅድመ ዝግጅት እንደኾነ ተጠቁሟል፡፡

Read 6623 times