Monday, 27 July 2015 10:12

ድመት አይጥ እንዲይዝ ተብሎ ችቦ አይበራለትም! የጉራጌ ተረት

Written by 
Rate this item
(15 votes)

 አንዳንዴ ፈረንጆችን ከእኛ የሚለያቸው ስለ ሰማይ ቤትም ለመቀለድ መቻላቸው ነው፡፡ የሚከተለው ተረት አንድ ምሣሌ ነው፡፡
ከዕለታት አንድ ቀን አንድ ጠበቃ ይሞትና ወደ ሰማይ ቤት ይሄዳል፡፡ በገነት በራፍ ላይ ቅዱስ ጴጥሮስ ያገኘዋል፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ የሁሉም ሰው ኃጢያት መዝገብ በእጁ ነውና የጠበቃውን ስም ፈልጎ ያገኘዋል፡፡ ከዚያ የሰራውን ኃጢያት ዝርዝር ያያል፡-
1ኛ. አንድን ከአየር መበከል ጋር ተያይዞ የተከሰሰን ሰው በመከላከል ጥብቅና ቆሟል
2ኛ. ደህና ገንዘብ ይከፈልሃል ስለተባለ ብቻ በግልፅ በነብስ ግድያ የተከሰሰን ነብሰ ገዳይ በመከላከል ጥብቅና ቆሟል፡፡
3ኛ. አብዛኛዎቹን የጥብቅና ደምበኞቹን ከልኩ - በላይ አስከፍሏል፡፡
4ኛ. አንዲትን የዋህ ሴት ለሌሎች ወንጀለኞች ጥፋት ማምለጫ ሰበብ እንድትሆን በመፈለግ፤ እንዲፈረድባት አድርጓል፡፡
ጠበቃው ይህን ክስ በመቃወም ተሟገተ፡፡ ክሶቹን በሙሉ ተቀበለና አንድ መሟገቻ ግን ይዞ ቀረበ፡-
“አንድ የምፅዋት ስጦታ ለነዳያን በህይወቴ አንዴ ሰጥቻለሁ” አለ፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ መዝገቡን አየና፤
“አዎን አዎን ስምህ አለ፡፡ ለአንድ ጎዳና ተዳዳሪ አሥር ሳንቲም ሰጥተሃል! ለአንድ ሊስትሮ ደግሞ አንድ ሳንቲም ሰጥተሃል! ትክክል ነኝ?” ጠበቃው ግራ የተጋባ መልክ እየታየበት፤ “አዎን!” አለ፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ አጠገቡ ወዳለው መልዐክ አየ፡፡
“ይሄን ልጅ አሥራ አንድ ሳንቲሙን ስጠውና ወደ ገሀነም አስገባው!” አለው፡፡
*       *     *
በሰው ላይ ግፍ ማስፈረድ፣ አላግባብ ገንዘብ መዝረፍ፣ የአብዬን እከክ ወደ እምዬ ልክክ ማድረግ፣ የማታ ማታ ማስጠየቁ አይቀሬ ነው፡፡
በርካታ ሌብነት፣ በርካት ግፍ፣ በርካታ የማጭበርበር ተግባር ፈፅመን ስናበቃ፣ ቅንጣቷ ደግነቴ ትመዝገብልኝ ማለት ግብዝነት እንጂ ብልጠት አይሆንም፡፡ ዕድሜያችንን ሙሉ የሰራነው ተንኮል እየታወቀ፣ አንድ ቀን የመፀወትኩትስ? ብሎ መከራከር ዐይናውጣነት ከመሆን በቀር ከፍርድ አያድንም! ዐረቦች “ሌባው በሰረቀው ሳይሆን ሳይሰርቅ በተወውም ይታወቃል” ይላሉ፡፡
የሀገራችን ፖለቲከኞች ነገር ለተፎካካሪ የሚመችና የተጋለጠ ነው፡፡ “ብቅል አስጥታ ነበር፤ እሽ ብትል እንዴት ጥሩ ነበር” ተብሎ ሁሌም የሚታለፍ ፌዝ መሳይ ነው፡፡
የሀገራችን ኢኮኖሚም ጥቂቶች ከዝሆን ጥርስ (Ivory - Power) ላይ ሆነው የሚነጩበት፣ ብዙሃኑ ትቢያ ላይ የሚተኙበት ዓይነት እየሆነ ነው፡፡ ቱርኮች “አንዱ በይ አንዱ የበይ ተመልካች የሆነ ዕለት የዓለም መጨረሻ መጣ ማት ነው” ይላሉ፡፡ እንደዚያም ቢባል አይገርምም፡፡
የመሰረተ - ልማት ሂደቱ ደግ ነው ቢባልም፤ በዙሪያው ያለው ሙስና ቀለም በተቀባ ቆርቆሮ እንደሚሸፈን ቆሻሻ ቦታ ሊሆን አልቻለም፡፡ የሚያስደንቀው ሌቦቹ ቀና ብለው የሚሄዱበት፣ ተመዝባሪዎቹ የሚያቀረቅሩበት ሁኔታ መሆኑ ነው፡፡
የካፒታሊዝምን ነገረ - ሥራ ሳንመረምር ተቀብለን አንድምታዎቹ በፖለቲካችንም፣ በኢኮኖሚያችንም፣ በማህበራዊ ኑሯችንም ሲንፀባረቁ መማረራችን አስገራሚ ነው፡፡ ዲሞክራሲ ልሙጥ በሆነ ህብረተሰብ ውስጥ ፋይዳው ከሲታ ነው፡፡ የሚወዳደር፣ የሚፎካከር፣ የሚከራከር፣ የሚታገል፣ የሚደራደር ህብረተሰብን ግድ ይላል፡፡ “ሞኝ ሸንጎ ተሰብስ አገኘሽ፣ ቁርስ የሌለው ቡና አፈላሽ” አይነት ከሆነ ጉዞው ዘገምተኛ ይሆናል፡፡ ቢያንስ “ምቀኛ አታሳጣኝ” የሚለውን አገርኛ ባህላዊ አነጋገር ማስተዋል ይጠቅማል፡፡
ኃያላን መንግሥታት ዐይን ቢጥሉብን ፍፅምና ያለን ሊመስለን አይገባም፡፡ ሁሉም የየራሱ ገበታ እንዳለው አንርሳ፡፡ ዞሮ ዞሮ ራስን ችሎ እንደመገኘት የመሰለ ነገር የለም! “ተሸፋፍነው ቢተኙ፣ ገልጦ እሚያይ አምላክ አለ” የሚለውን ተረት አንርሳ፡፡ የኢኮኖሚ ችግርን መባባስ መደበቅ አይቻልም፡፡
ምድረ - በዳውን እየማተርን የበረሀ - ገነት (oasis) አየን ብንል ራስን ከማታለል በቀር ሌላም መላ የለው፡፡ ያለን አለን፣ የሌለን የለንም፡፡ የማንኖረውን ኑሮ እየኖርን ነው ብለን ብንኩራራና ብንቦተልክ ኑሯችን አጋልጦ እርቃናችንን ያሳየናል!
ሥራችን የሆነውን ኃላፊነት ሳንወጣ ከሁሉም በላይ ደግሞ፤ ሌላው ላይ መላከክ ሀገራችን በየጊዜው የሚያጋጥማት የፖለቲካ ጨዋታ ነው፡፡ ሁሉ ወቃሽ ሁሉ ከሳሽ ሆነና የየራሱን ግዴታ የሚያይበት ዐይን ጠፋ፡፡ “ሁሉም ፈረስ ላይ ከወጣ፣ ማን መንገድ ይምራ?” እንደሚለው የወላይትኛ ተረት ነው፡፡ የጠያቂው ብዛት የተጠያቂውን ደብዛ ያጠፋዋል! ይህ መፈተሽ ያለበት የፖለቲካ ችግራችን ነው፡፡
“ድመት አይጥ እንዲይዝ ተብሎ ችቦ አይበራለትም” የሚለው የጉራጌ ተረት ሁሉም በየራሱ ሥራ መፈተሽና መጠየቅ እንደሚገባው ነው የሚያሳየን፡፡ ይህንን ልብ እንል ዘንድ ልብ ይስጠን!

Read 7689 times