Saturday, 28 January 2012 14:25

ሞውሪንሆ በበርናባኦ አንገት ደፍተዋል

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

ከ2 የውድድር ዘመናት በፊት በአለማችን ከፍተኛው የአሰልጣኝ ደሞዝ 12 ሚሊዮን ዶላር በማግኘት ሪያል ማድሪድን ማሰልጠን የጀመሩት ጆሴ ሞውሪንሆ በቀጣይ የውድድር ዘመን ከክለቡ ጋር መቀጠላቸው አጠያያቂ ሆነ፡፡ ሪያል ማድሪድ ሞውሪንሆን ለመተካት የአርሰናሉን አርሴን ቬንገርና የጀርመን ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ ጆአኪም ሎውን ዋናዎቹ እጩዎች አድርጓል፡፡ የሞውሪንሆ ቆይታ አጣብቂኝ ውስጥ የገባው በባርሴሎና አልሸነፍ ባይነት እና የኤልክላሲኮ የበላይነት ጋር በተያያዘ ነው፡፡ የክለቡ ደጋፊዎች በተደጋጋሚ በቡድኑ አጨዋወት ደስተኞች አይደሉም፤ በባርሴሎና በሚወሰድበት ብልጫም ተማረዋል፤ በአሰልጣኙ አወዛጋቢ ተግባራትና በክለቡ ከሚገኙ ስፔንያውያን ተጨዋቾች ጋር ፈጥረዋል በሚባለው አለመግባባት ተሰላችተዋል፡፡

የሞውሪንሆን ቆይታ አጠራጣሪ ያደረጉ ምክንያቶችም እነዚሁ ናቸው፡፡ በሳምንቱ አጋማሽ ላይ ደግሞ ለሞውሪንሆ የተቃውሞ መልእክት ያስተላለፉት የማድሪድ ክብር ፕሬዝዳንት አልፍሬዶ ዴስቲፋኖ ናቸው፡፡ ዲ ስቴፋኖ ማድሪስታኖች በበርናባኦ የሞውሪንሆን እቅድ አልወደድነውም፤ ከባርሳ ጋር በተደረገ ጨዋታ የሞውሪንሆ ከልክ ያለፈ የመከላከል ጨዋታና አጠቃላይ ባህርይ ማድሪድን አዋርዷል በማለት ማርካ በተባለ ጋዜጣ ቋሚ አምደኛነታቸው ፅፈዋል፡፡ ስቴፋኖ በፅሁፋቸው ማድሪድ የተሻለ ስኬት ያስመዘገቡ አሰልጣኞችንም አሰናብቷል ብለው ማስጠንቀቃቸው የሞውሪንሆ የበርናባኦ አገዛዝ የመጨረሻው ምእራፍ ላይ መድረሱን ያመለከተ ተብሏል፡፡ አሁን የስፔን ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ የሆኑት ዴልቦስኬ እንኳን ሁለት የሻምፒዮንስ ሊግና 2 የላሊጋ ዋንጫ ሰብስበው በዋዛ መሰናበታቸውን ያስታወሱት የክብር ፕሬዝዳንቱ ዴስቲፋኖ፤ ሞውሪንሆ ባርሴሎናን ማሸነፊያ ፎርሙላ ማጣቱን በበርናባኦ ጨዋታ ተናዝዟል ይህ መስተካከል ይኖርበታል በማለትም ማሳሰቢያ ሰጥተዋል፡፡የ48 ዓመቱ ጆሴ ሞውሪንሆ ቢሆን በቀጣይ ዓመት በሪያል ማድሪድ ስለመቆየታቸው እርግጠኛ አለመሆናቸውን በመናገራቸውም ስንበታቸውን የማይቀር አድርጎታል፡፡ በሪያል ማድሪድ ደጋፊዎች ዚነዲን ዚዳንና ሮናልዶ ተቃውሞ ሲገጥማቸው አውቃለሁ ያሉት ሞውሪንሆ በበርናባኦ እየደረሰባቸው ያለው ተቃውሞ እንደማያሳስባቸው ይናገራሉ፡፡ በሪያል ማድሪድ የ100 ዓመት ታሪክ ከ30 በላይ አሰልጣኞች በሙሉ ኃላፊነት የሰሩ ሲሆን ከፍተኛውን ስኬት ያስመዘገቡት ለክለቡ 15 ዓመታትን ያገኙት ሚግዌል ሙኖዝ ናቸው፡፡ ሚግዌል ከሪያል ማድሪድ 9 የላሊጋና 2 የሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫዎች አግኝተዋል፡፡ ጆሴ ሞውሪንሆ በክለቡ የስልጠና ታሪክ በሠሩባቸው ያለፉት 2 የውድድር ዘመናትና 1 የኮፖዴለሬይ ዋንጫ ብቻ ቢያገኙም 85 ጨዋታ አድርገው በ65 አሸንፈው፣ በ11 አቻ ወጥተውና በ9 ጨዋታ ተሸንፈዋል፡፡ በዚህ ቆይታቸው የባርሴሎናን የበላይነት መግታት ቢሳናቸውም በየጨዋታው ቢቆዩም 70.47% አሸናፊነት በማስመዝገብ የክለቡ ከፍተኛ ባለድል የሆኑ አሰልጣኝ ናቸው፡፡

 

Read 2080 times