Saturday, 11 July 2015 11:37

የጦማሪያኑና ጋዜጠኞቹ መፈታት ድብልቅልቅ ስሜት ፈጥሯል - ደስታና ስጋት

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(17 votes)

• መንግስት የክሱ መቋረጥ የኦባማ ተጽዕኖ ውጤት አይደለም አለ
• ለክሱ መቋረጥ ምክንያት አለመቅረቡ መልሶ ለመክሰስ ያመቻል ተባለ
• 6 የኦሮሞ ተወላጅ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችም ሰሞኑን ተፈተዋል

     መንግሥት ከአንድ ዓመት በፊት በሽብር ጠርጥሬያቸዋለሁ ብሎ ክስ ከመሰረተባቸው ጋዜጠኞችና ማሪያን መካከል የአምስቱን ክስ አንስቶ ሰሞኑን ከእስር የለቀቀ ሲሆን ቀሪዎቹ ክሳቸው ይቀጥላል ብሏል፡፡ በሌላ በኩል ሽብርተኛ ድርጅትን በሙያ በመርዳት በሚል 5 ዓመት የተፈረደባት ጋዜጠኛና መምህርት ርዕዮት አለሙ ከ4 ዓመት ከ1 ወር እስር በኋላ ከትናንት በስቲያ በአመክሮ ደብዳቤ ከእስር ተለቃለች፡፡
ረቡዕ አመሻሽ ላይ በድንገት ከእስር የተለቀቁት ጋዜጠኛ ተስፋለም ወልደየስ፣ አስማማው ኃ/ጊዮርጊስ፣ ኤዶም ካሣዬ እንዲሁም ጦማሪያኑ ማህሌት ፋንታሁን እና ዘላለም ክብረት ሲሆኑ ጦማሪያኑ አቤል ዋበላ፣ በፍቃዱ ሃይሉ፣ ናትናኤል ፈለቀ እና አጥናፍ ብርሃኔ ክሳቸው ይቀጥላል ተብሏል፡፡ ተለቀቁት ጋዜጠኞች አንዱ የሆነው ተስፋለም ወልደየስ፤ መለቀቁ ቢያስደስተውም ቀሪ ወዳጆቹ አሁንም እስራቸው መፅናቱ ብዥታ እንደፈጠረበት ለአዲስ አድማስ ተናግሯል፡፡ “ደስታችን ሙሉ አይደለም፣ የተደባለቀ ስሜት ነው እየተሰማን ያለው” ብሏል ጋዜጠኛ ተስፋለም፡፡ በመንግስት አሸባሪ ተብለው ከተሰየሙ የተለያዩ ድርጅቶች ጋር ግንኙነት ፈጥረዋል የሚል የሽብር ክስ ቀርቦባቸው የነበሩት ጋዜጠኞቹ፤ አቃቤ ህግ ማስረጃ አቅርቦ በማስረጃውና በክሱ ቀጣይ ሂደት ላይ ፍ/ቤት ብይን ለመስጠት ለሐምሌ 13 ቀን 2007 ዓ.ም ቀጠሮ ሰጥቶ እንደነበር ይታወሳል፡፡ በሌላ በኩል ሽብርተኛ ድርጅቶችን በሙያ መርዳት በሚል ክስ ከ15 ዓመት የእስራት ፍርድ በይግባኝ ወደ 5 ዓመት እስር ዝቅ የተደረገላት ጋዜጠኛና መምህርት ርዕዮት አለሙ፤ የአመክሮ ጊዜዋ ቢጠበቅላት ኖሮ ባለፈው ጥቅምት ወር ትፈታ እንደነበረ ጠቁማ “ጥፋትሽን እመኚ” ተብላ
እሺ ባለማለቷ፤ ሙሉ የእስራት ጊዜዋን ጨርሳ ልትወጣ 11 ወራት ሲቀራት ከትላንት በስቲያ
በድንገት ከእስር መለቀቋን ለአዲስ አድማስ ገልፃለች፡፡በሌላ በኩል ከአዲስ አበባ እና የፊንፊኔ ዙሪያ ኦሮሚያ ከተሞች ማስተር ፕላን ጋር በተገናኘ ተቃውሞ አስነስተዋል የተባሉ 6 የኦሮምያ ክልል የተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ተማሪዎችም ከ1 አመት ከ3 ወር እስር በኋላ ሰሞኑን እንደተለቀቁ ታውቋል፡፡ ከዩኒቨርሲቲዎቹ በፖሊስ ተወስደው ታስረው ከነበሩት ተማሪዎች መካከል አዱኛ ፌሶ፣ ቢሊሱማ
ዳመና፣ ሌንጂሣ አለማየሁ፣ አብዲ ከማል፣ የአገር ሰው ወርቁ እና ቶፊክ ራሺድ ከ1 አመት በላይ በወህኒ ቤት ቢቆዩም በብዙዎቹ ላይ ክስ አልተመሰረተም ተብሏል፡፡የጋዜጠኞቹ ጦማሪያኑ መፈታት ከህግ አንፃር
የጋዜጠኞቹና ጦማሪያኑ የህግ አማካሪና ጠበቃ የሆኑት የህግ ባለሙያው አቶ አመሃ መኮንን፤ በ5ቱ
ታሳሪዎች መፈታት ጉዳይ ላይ ለአዲስ አድማስ በሰጡት ማብራሪያ፤ በህጉ ፍትህ ሚኒስቴር በማንኛውም ሰአት የጀመረውን ክስ የማቋረጥ ስልጣን እንዳለው ጠቅሰው፣ በፊት በነበረው አሰራር የወንጀለኛ መቅጫ ህጉን መነሻ በማድረግ፣ ክስ ለማንሳት ፍ/ቤትን ማስፈቀድ ይጠየቅ እንደነበረ ተናግረዋል፡፡ ፍ/ቤቱ ካመነበት ብቻ ክሱን ያነሳ ነበር ያሉት የህግ ባለሙያው፤ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ የወጡት አዳዲስ ህጎች የቀድሞውን ሽረው ለፍትህ ሚኒስቴር ክስ የማንሳት ስልጣን ሰጥተውታል ይላሉ፡፡ አዲሱ አዋጅ፣ የፍትህ ሚኒስትሩ ካመነበት ክሱን ያነሳል ብሎ ክስ የማንሳትን ስልጣን ለሚኒስትሩ ይሰጣል የሚሉት አቶ አመሃ፤ በተቃራኒው ፍ/ቤት “ክሱን ለምን አነሳህ?” የሚል ጥያቄ ፍትህ ሚኒስቴርን እንዲጠይቅ አለመደረጉን ይገልፃሉ፡፡ ሙሉ ለሙሉ ክስ የማንሳት ስልጣን ለፍትህ ሚኒስቴር የመሰጠቱ ጉዳይ በሚገባ መተርጎም ያስፈልገዋል ያሉት አቶ አመሃ፤ ሚኒስቴሩ በፈለገ ሰአት ክስ እያነሳና በፈለገ ጊዜ ደግሞ ክሱን እንደገና እያንቀሳቀሰ ዜጎችን መብት የማሳጣት አቅም ሊሰጠው አይገባም የሚል አተያይ አለኝ ብለዋል፡፡ ፍትህ ሚኒስቴር ይሄን ስልጣን ተጠቅሞ “ከዚህ ቀደም ለጊዜው ክሳችንን አንስተናል” ካለ በኋላ፣ በድጋሚ ክሱን የቀጠለበትን የጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ የክስ ሂደት ያስታወሱት የህግ ባለሙያው፤ “በወቅቱ ተጨማሪ ምርመራ ለማድረግና ጠንካራ ክስ ለማደራጀት የሚል ምክንያት አቅርቦ አቃቤ ህግ ክሱን አንስቶ የነበረ ቢሆንም ኋላ ላይ ያንኑ ክስ በድጋሚ ሊያቀርብ ችሏል” ሲሉ ያስረዳሉ፡፡ “አዋጁ አላግባብ እየተተረጎመ በመሆኑ ነው እንጂ ፍትህ ሚኒስቴር ሲያሻው ክስ አቋርጦ ሲፈልግ ክሱን ማንቀሳቀስ አይችልም፤ ክሱን ሲያቋርጡ ምክንያታቸውን እንዲያቀርቡም በፍ/ቤት መጠየቅ አለባቸው” ብለዋል - ጠበቃው፡፡ ጋዜጠኞቹና ብሎገሮቹም ጉዳይ የአቃቤ ህግን ማስረጃ ይከላከሉ ወይስ በነፃ ይሰናበቱ በሚለው የህግ ሂደት ላይ ብይን ለመስጠት ለሐምሌ 13 ቀን 2007 ዓ.ም ተቀጥሮ ሳለ በድንገት 5ቱ ሲለቀቁ፣ የተለቀቁበት ምክንያት በግልፅ አልተብራራም ያሉት ጠበቃው፤ በዚህም የተነሳ ጋዜጠኞቹና ብሎገሮቹ ላይ በፈለጉት ጊዜ ክሱን ሊያንቀሳቅሱ ይችላሉ የሚል ስጋት ይፈጥራል፤ ክሱ የተነሳበት ምክንያት ባልታወቀበት ሁኔታ መተማመኛ ማግኘት አይቻልም ብለዋል፡፡ “መንግስት በፈለገ ሰአት አስሮ ባሻው ጊዜ መልቀቁ እስከመቼ ይቀጥላል” ሲል የሚጠይቀው ጋዜጠኛው፤ የተፈቱት ልጆች በአሁን ሁኔታው ነገ ተመልሰው እስር ቤት የማይገቡበት ምክንያት አይኖርም ብሎ ሙሉ ለሙሉ መተማመን አይቻልም” ብሏል፡፡ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮችም የህግ ባለሚያውን ስጋት ይጋራሉ፡፡ የመላ ኢትዮጵያውያን አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ፕሬዚዳንት አቶ አበባው መሃሪ፤ “የጋዜጠኞቹና ጦማሪያኑ መለቀቅ መልካም ቢሆንም ከእስር የተለቀቁበት መንገድ መንግስት ባሻው ጊዜ መልሶ ስላለማሰሩ ዋስትና አይሆንም” ብለዋል፡፡ የኢዴፓ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ወንደወሰን ተሾመ በበኩላቸው፤ ጋዜጠኞቹና ጦማሪያኑ መፈታታቸው መልካምና አስደሳች መሆኑን ጠቅሰው፣ የቀሩትም ቢሆኑ መፈታት አለባቸው የሚል አቋም አለን ብለዋል፡፡ “የኦባማ ወደ ኢትዮጵያ ለመምጣት ማቀድ በራሱ ተፅዕኖ ሳይፈጥር እንደማይቀር ጥርጣሬ አለን” ያሉት አቶ ወንድወሰን፤ የዳያስፖራው ሰሞነኛ ተፅዕኖም ቀላል ግምት የሚሰጠው አይደለም ይላሉ፡፡ የፖለቲካ ሳይንስ መምህሩና የመድረክ አመራር ዶ/ር መረራ ጉዲና በሰጡት አስተያየት፤ “የጦማሪያኑና የጋዜጠኞቹም ሆነ የሌሎች ፖለቲከኞች እስር በምዕራባውያኑ ሚዲያዎች መነጋገሪያ መሆኑን ተከትሎ እዚህ ያሉት የአሜሪካ አምባሳደር በመንግስት ላይ ተፅዕኖ ሳያሳርፉ አይቀርም የሚል ግምት አለኝ” ብለዋል፡፡ “ጋዜጠኞቹና ጦማሪያኑ በመፈታታቸው ደስ ብሎኛል፤ እንኳን ደስ ያላችሁ የሚል መልዕክቴ
ይድረሳቸው” ያሉት ዶ/ር መረራ፤ “መንግስት ምንም እንኳ እነሱን ቢፈታም የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን ጨምሮ ሌሎች በኦሮሚያ ክልል ያሉ ወጣቶችን እያሰረ ነው” ብለዋል፡፡ “ወከባና እንግልቱም ከምርጫው በኋላ ተጠናክሮ ቀጥሏል” የሚሉት ምሁሩ፤ “አንዱን መፍታት አንዱን ማሰር የኢህአዴግ ባህሪ ነው” ይላሉ፡፡ “የጦማሪያኑና ጋዜጠኞቹ ከእስር መለቀቅን እንደ ቋሚ የፖሊሲ ለውጥ ማየት አያሻም” የሚሉት ምሁሩ፤ ለኦባማ እጅ መንሻ የተደረገም ሊሆን ይችላል ብለዋል፡፡ የፍትህ ሚኒስቴር የ5ቱን ጋዜጠኞችና ጦማሪያን ከእስር መለቀቅ አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙሃን በላከው መግለጫ፤ በህግ በተሰጠው ክስን የማቋረጥ ስልጣን የጋዜጠኛ ተስፋለም ወልደየስ፣ አስማማው ሃ/ጊዮርጊስ፣ ኤዶም ካሣዬ እንዲሁም የጦማሪያኑ ማህሌት ፋንታሁን እና ዘላለም ክብረት ክስን ማቋረጡን ጠቅሶ፣ የቀሪዎቹ 4 ተከሳሾች ክስ ይቀጥላል ብሏል፡፡ አለማቀፍ ሚዲያዎችን ጨምሮ የተለያዩ አስተያየት ሰጪዎችና ፖለቲከኞች፤ የጋዜጠኞቹ መፈታት በቅርቡ ኢትዮጵያን ይጐበኛሉ ተብሎ የሚጠበቁት የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ተፅዕኖ ውጤት መሆኑን እየገለፁ ሲሆን መንግስት በበኩሉ፤ የክሱ መቋረጥና የታሣሪዎቹ መፈታት የፕሬዚዳንቱ ተፅዕኖ ውጤት አይደለም ብሏል፡፡ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ እውነቱ ብላታ፤ የፍትህ ሚኒስቴር በህግ በተሰጠው ስልጣን በፈለገው ጊዜ ክስ ማቋረጥ እንደሚችል ጠቅሰው፤ “ለፍትህ ሚኒስቴር ክስ የማቋረጥ ስልጣን የሰጠው ህግ የወጣው ኦባማ ስለሚመጣ አይደለም፤ አስቀድሞም ያለ ነው” ብለዋል፡፡ አክለውም፤ “መንግስት በየትኛውም መንገድ ቢሆን የሀገር ሉአላዊነትን ጉዳይ ለድርድር አያቀርብም፤ ክሱ የተነሳው በማንም ተጽእኖ አይደለም፤ ፍትህ ሚኒስቴር ባለው ስልጣን ብቻ
የተነሳ ነው” ብለዋል - ሚኒስትሩ ለአዲስ አድማስ በሰጡት ማብራሪያ፡፡

Read 7994 times