Saturday, 11 July 2015 11:35

የመኢአድ የአመራር ውዝግብ ዳግም አገረሸበት

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(7 votes)

     የአመራር ሽኩቻው በምርጫ ቦርድ እልባት አግኝቶ ወደ ምርጫ ውድድር የገባው የመላ ኢትዮጵያውያን አንድነት ድርጅት (መኢአድ)፤ በድጋሚ የአመራር ውዝግብ የተነሳበት ሲሆን ፕሬዚዳንቱ አቶ አበባው መሃሪ ስልጣናቸውን እንዲለቁ ተጠይቀዋል፡፡ አቶ አበባው በበኩላቸው፤ “አሁን ጠቅላላ ጉባኤ የመጥራት እቅድ የለኝም፤ መሪ የሚመርጠው ጠቅላላ ጉባኤው ብቻ ነው” ብለዋል፡፡ “መኢአድን በቁርጠኝነት እንታደግ” በሚል የተቋቋመው ኮሚቴ፣ የማዕከላዊ ም/ቤት አባል የሆኑትን አቶ ፀጋዬ እሸቴ፣ አቶ ይርዳው ሽፈራው እና አቶ መላኩ መሰለን በዋና ሰብሳቢነት፣ ም/ሰብሳቢነትና ፀሐፊነት ያካተተ ሲሆን ፓርቲው ከ1997 ወዲህ ከገባበት የአመራር ችግርና ድክመት ለማላቀቅ ቆርጦ የተነሳ ኮሚቴ መሆኑን የኮሚቴው ፀሐፊ አቶ መላኩ መሰለ ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡ በአመራር ችግር ምክንያት የሚጠበቅበትን ውጤት ማስመዝገብ አልቻለም የሚሉት አቶ መላኩ፤ “በተለይ ፕሬዚዳንቱ በ2007 ምርጫ የፓርቲውን መሰረታዊ አቋም የሚገዳደሩ ግድፈቶችን ፈፅመዋል፣ በግድ ወደ ምርጫው ውድድር እንድንገባም አድርገዋል” ይላሉ፡፡ በዚህም የተነሳ ፕሬዚዳንቱ በመኢአድ አላማ ሙሉ ለሙሉ አምነው እየተጓዙ ስለመሆናቸው ጥርጣሬ አለን ያሉት አቶ መላኩ፤ ሐምሌ 14 ቀን 2007 ዓ.ም ስልጣን ከያዙ ሁለተኛ አመታቸው ስለሆነ ፓርቲውን እንዲለቁ የላዕላይ ምክር ቤት አንድ ሶስተኛ የሚሆኑ አባላት ተፈራርመው ጠቅላላ ጉባኤ ለመጥራት ወስነዋል ብለዋል፡፡ “መኢአድን በቁርጠኝነት እንታደግ” በሚል የተቋቋመው ኮሚቴም በዋናነት ግብ አድርጎ የተነሳው ድርጅቱን ለማዳንና ወደ ቀድሞ አቋሙ ለመመለስ ነው ብለዋል፡፡ ፓርቲው ፕሬዚዳንት አቶ አበባው መሃሪ፤ ጠቅላላ ጉባኤውንም ሆነ ስራ አስፈፃሚውን ሳያማክሩ በግላቸው ከኢራፓና ኢዴፓ ጋር የሚያደርጉትንም እንቅስቃሴ በፅኑ እንደሚቃወሙ የኮሚቴው አባላት ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡ ፕሬዚዳንቱ አቶ አበባው በበኩላቸው፤ የሥልጣን ፍላጎትና ጥመኝነት እንደሌላቸው ጠቁመው፣
ሥልጣን መልቀቅ ካለብኝ የፓርቲው ደንብ በሚያዘው መንገድ ብቻ እለቃለሁ ሲሉ አስረድተዋል፡፡ ሐምሌ 14 ጠቅላላ ጉባኤ ለመጥራት ፓርቲው እንዳላቀደ የጠቀሱት ፕሬዚዳንቱ፤ ጉባኤው መቼ ይጠራ የሚለውን ስራ አስፈፃሚው ገና እየተወያየበት ነው ብለዋል፡፡  ከኢዴፓ እና ኢራፓ ጋር አብሮ ለመስራት የሚያስችል ስምምነት ላይ አለመድረሳቸውን የገለፁት አቶ አበባው፤ አንዳንድ የጋራ የሆኑ ጉዳዮች ላይ መግለጫ ያወጣነው ስራ አስፈጻሚው በወሰነው መሰረት እንጂ በኔ የግል ውሳኔ አይደለም ሲሉም አስተባብለዋል፡፡

Read 3748 times