Saturday, 11 July 2015 11:27

ኮርያ ሆስፒታል በአገልግሎት አሰጣጥና በሰራተኞች አስተዳደር ቅሬታ ቀረበበት

Written by  ከጋዜጣው ሪፖርተር
Rate this item
(2 votes)

ሆስፒሉ ቅሬታውን አስተባብሏል

   የሚዮንግ ስንግ አጠቃላይ ሆስፒታል (ኮሪያ ሆስፒታል) በአገልግሎት አሰጣጡና በሰራተኞች አያያዙ
ላይ ችግሮች እንዳሉበት የገለፁ የሆስፒታሉ ሰራተኞች፤ በኢትዮጵያውያን ሰራተኞች ላይ የሚፈፀሙ በደሎችና አድልዎችን የሚቃወሙ ሰራተኞች ከስራቸው እንደሚባረሩ ተናገሩ፡፡ በሆስፒታሉ ውስጥ
የሚከናወኑ ህገ ወጥ ስራዎችን የሚቃወሙ ሰራተኞችም ከስራ ይወገዳሉ ብለዋል፡፡ ኢትዮጵያውያን ዘማቾች በኮሪያ ዘመቻ ወቅት ያደረጉትን አስተዋፅኦ ለማሰብ እ.ኤ.አ በ2004 ዓ.ም በደቡብ ኮሪያውያን የተመሰረተው ሆስፒታሉ፤ በዘመናዊ መሳሪያዎችና ከፍተኛ ዕውቀት ባላቸው ባለሙያዎች እየታገዘ አገልግሎት ሲሰጥ መቆየቱን ሰራተኞቹ ያስታውሳሉ፡፡ ሆኖም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአገልግሎት አሰጣጡ ላይ ችግሮች እየታዩ መምጣታቸውን የሚናገሩት ሰራተኞቹ፤ ተገልጋዩ ህብረተሰብ ከፍተኛ ዋጋ ከፍሎ ለሚያገኘው የህክምና አገልግሎት ምንነቱን ለመረዳት የማይቻልና በኮሪያ ቋንቋ የተፃፉ መርፌና መድኀኒቶች እንደሚታዘዙለት ይናገራሉ። ይህንን ለመቃወም የሞከረ ታካሚ፤ “ምን ዓይነት ህክምና መስጠት እንዳለብን ካወክ ለምን መጣህ” የሚል ጥያቄ በማንሳት፣ ህክምናውን ከእነአካቴው ይነፈጋል ብለዋል፡፡በሆስፒታሉ የሚሰሩ ኢትዮጵያውያን ሰራተኞች በደቡብ ኮሪያውያኑ የሥራ ኃላፊዎች አድልዎና ጫና ይደረግባቸዋል የሚሉት ሰራተኞቹ፤ ለመብታቸው ለመከራከር የሚሞከሩ ኢትዮጵያውያን ራተኞችም ከስራ እንደሚባረሩ ተናግረዋል፡፡በሃይማኖት ልዩነት ሳቢያ በሰራተኞች ላይ አድልዎና መገለል እንደሚፈፀም የሚናገሩት  ሰራተኞቹ፤ ሰራተኛው ያለፍላጎቱ የእነሱን ሃይማኖት እንዲከተል መገደዱንም ገልፀዋል፡፡ በሆስፒታሉ የሰራተኞች ማህበር የሚባል ነገር እንደሌለም ተናግረዋል፡፡ ሆስፒታሉ በምግብ መድኀኒትና ጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለስልጣን ታውቀውና  ተመርምረው ወደአገር ውስጥ እንዲገቡ ከሚፈቀድላቸው መድኀኒቶች ውጪ ሌሎች መድኀኒቶችን ወደ አገር ውስጥ እንደሚያስገባ
የጠቆሙት ሰራተኞቹ፤ መድኀኒቶቹ ሙሉ በሙሉ በኮሪያ ቋንቋ የተፃፉና ምንነታቸው የማይታወቅ
ሲሆን በከፍተኛ ዋጋ ለህመምተኞች የሚሸጡና በሃኪሞች የኮድ ትዕዛዝ የሚሰጡ ናቸው ብለዋል፡፡ ጠቅላላ የቀዶ ጥገና ስፔሻሊስትና የሆስፒታሉ ምክትል ሜዲካል ዳይሬክተር ዶ/ር ሰለሞን በቀለ በሆስፒታሉ አሰራር ላይ የሚነሱ አቤቱታዎችን አስመልክተው ሲናገሩ፤ በሆስፒታሉ አልፎ አልፎ የሚነሱ አንዳንድ ቅሬታዎች መኖራቸውን ጠቁመው፣ እነዚህ ቅሬታዎች ግን የሆስፒታሉን የአሠራር ሥርዓት ካለመገንዘብ የተነሳ የሚከሰቱ ናቸው ብለዋል፡፡ ለዚህም እንደምሳሌ የሚጠቅሱት በሆስፒታሉ የሚሰጠውን የፈጣን ክሊኒካል አገልግሎት ነው፡፡ በዚህ አገልግሎት ተጠቃሚ ለመሆን የሚፈልግ ሰው ከመደበኛው የካርድ አገልግሎት ሦስት እጥፍ ያህል ከፍሎ ተራ ሳይጠብቅ በቀጥታ ወደ ሃኪሙ የሚገባበት አሠራር መኖሩን ጠቁመው፣ አሠራሩ ለሁሉም ታካሚ በግልፅ የሚነገርበት መንገድ ባለመኖሩ ቅሬታዎች ሲፈጠሩ ተመልክተናል ብለዋል፡፡ ሆስፒታሉ አሠራሩን የማስተካከል እርምጃ እንደሚወስድና ሁሉም ተገልጋይ አሠራሩን በግልጽ አውቆ እኩል የሚስተናገድበት መንገድ እንደሚመቻችም ምክትል ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል፡፡ በሠራተኞች አስተዳደር ላይ የተነሱ ቅሬታዎችን በተመለከተም ችግሮች ሙሉ በሙሉ የሉም
ለማለት እንደሚቸገሩ የገለፁት ኃላፊው፤ በሆስፒታሉ ውስጥ ለተቋቋመው የዲሲፒሊን ኮሚቴ ቅሬታዎችን በማቅረብ የእርምት እርምጃ ማስወሰድ ይቻላል ብለዋል፡፡ በሆስፒታሉ ውስጥ በሃይማኖት ልዩነት ሳቢያ ይፈፀማል የተባለውን አድልዎ በተመለከተም፤ የሆስፒታሉ ሠራተኞች በሃይማኖት ሳቢያ አድልዎና መገለል ይፈፀምባቸዋል የሚለውን ቅሬታ በተደጋጋሚ የሚሰሙ ቢሆንም በግልጽ ሲፈፀምያዩት አድልዎ አለመኖሩን ተናግረዋል፡፡ ቀደም ሲል የሆስፒታሉ ሠራተኞችም ሆኑ ለአገልግሎት የሚመጡ ህሙማን የሃይማኖት ትምህርትና ሰበካ ይደረግላቸው እንደነበር ያስታወሱት ዶክተሩ፤ አሁን ግን ሙሉ በሙሉ መቅረቱንና በሳምንት አንድ ቀን ቅዳሜ ቅዳሜ ለሚፈልግ ሠራተኛ ብቻ በፍላጎት ትምህርትና ሰበካው እንደሚሰጥ አስረድተዋል፡፡ ከመድሃኒት አቅርቦት ጋር በተያያዘ የተነሳውን ችግር በተመለከተ ሲናገሩም፤ በሆስፒታሉ የአገልግሎት ጊዜያቸው ያለፉ መድሃኒቶችን እንደማይጠቀሙ ገልፀው፣ በኮሪያ ቋንቋ የተፃፉ
መድሃኒቶች አገልግሎት ላይ የሚውሉበትን አግባብ አብራርተዋል፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ እንደልብ
ተፈልገው የማይገኙ መድሃኒቶች ሲሆኑ ጥቅም ላይ ይውላሉ በማለት፡፡ እሱም ቢሆን የምግብ መድሃኒትና የጤና ክብካቤ አስተዳደር ቁጥጥር ባለስልጣን ተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያ ስለተሰጠ ከመጠቀም መታቀባቸውን ገልፀዋል፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የምግብ፣ መድሃኒትና ጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለስልጣን፤ በሆስፒታሉ ውስጥ ይከናወናሉ የተባሉ ህገወጥ ተግባራትንና ከባለስልጣን መ/ቤቱ ዕውቅናና ፈቃድ ውጪ ወደ አገር ውስጥ ገብተው ጥቅም ላይ ይውላሉ የተባሉትን መድሃኒቶች በተመለከተ ለሆስፒታሉ ተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያዎችን እንደፃፈ ለማወቅ ተችሏል፡፡ ሆስፒታሉ የጤና አገልግሎት ለመስጠት ታስቦ የተቋቋመ እንደመሆኑ፣ ከጤና አገልግሎቶች ውጪ ለተገልጋዩ ህብረተሰብ የሃይማኖት ሰበካ መተላለፍ እንደማይገባው ጠቁሞ፣ ይህ ህገወጥ ተግባርም በአስቸኳይ እንዲቆም በፃፈው ማስጠንቀቂያ አስታውቋል፡፡ ሆስፒታሉ በመድሃኒት አገልግሎት አሰጣጡ ላይ ተገቢውን ቁጥጥርና ክትትል አያደርግም ያለው የባለስልጣን መ/ቤቱ የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ፤ በመድሃኒቶቹ ላይ ስለመድሃኒቱ የሚገልፁ ጽሑፎች በኮሪያ ቋንቋ የተፃፉ መሆናቸው ስለመድሃኒቱ አገባብና ጥራት በቂ መረጃ እንዳይኖር አድርጓል ብሏል፡፡ አንዳንድ የመድሃኒት ማዘዣ ወረቀቶች በኮድ መፃፋቸው ከሆስፒታሉ መድሃኒት ለመግዛት የማይፈልጉ ወይም የማይችሉ ታካሚዎችን ችግር ውስጥ እንደሚጥላቸውና ወደ ሃኪማቸው ጋ ተመልሰው በድጋሚ ለማፃፍ እንደሚገደዱ ጠቅሶ፣ ይህም ትክክለኛ አሠራር አለመሆኑን በመግለጽ አፋጣኝ የማሻሻያ እርምጃዎች ሊወስዱ እንደሚገባ ባለስልጣን መ/ቤቱ በማስጠንቀቂያ ደብዳቤው ገልጿል፡፡    

Read 5164 times