Saturday, 04 July 2015 10:26

ከርከሮ አንዲት ፀጉር አለችው፤ እሷን ለማጥፋት ይተሻሻል

Written by 
Rate this item
(15 votes)

ከዕለታት አንድ ቀን እመት ጦጢት ምግብ ስትሰራ እንስሳት አገኟትና፤
“እመት ጦጢት?”
“አቤት” አለች፡፡
“ሽሮና በርበሬ ማን ያመጣልሻል?” አሏት፡፡
“ባሌ” አለች
“ከየት ያመጣል?”
“ሠርቶ፣ ወጥቶ፣ ወርዶ”
“ሰርቆስ እንደሁ የሚያመጣው በምን ታውቂያለሽ?”
“አምነዋለሁ”
“ቂቤስ ከየት አመጣሽ?”
“ባሌ አመጣልኝ”
“ከየት ያመጣል?”
“ሰርቶ፣ ወጥቶ - ወርዶ”
“ሰርቆስ እንደሁ በምን ታውቂያለሽ”
“ባሌን አምነዋለሁ”
“ከዕለታት አንድ ቀን ሌላ ጦጢት ይዞብሽ ቢመጣስ?”
“ተገላገልኳ! አጋዥ አገኘሁ፡፡ እሷ ምግብ ትሰራለች፤ እኔ እሱን አቅፌ እተኛለሁ”
“እስከ ዛሬ ጦጣ ብልጥ ናት ሲባል ነበር፡፡ ለካ አንደኛ ደረጃ ጅል ነሽ?!”
“ጅልስ እናንተ፡፡ እየሰረቃችሁ መዋችላሁ አንሶ ወደሌላ ለማዛመት ሌብነት፣ ከቤት - ቤት ይዛችሁ የምትዞሩ!! በሉ ሌብነታችሁን ሌላ ቤት ይዛችሁልኝ ሂዱ!” ብላ ከቤት አስወጣቻቸው፡፡
*   *   *
እንደ ጦጣ አለመመቸት ብልጥነት ብቻ ሳይሆን ብልህነትም ነው!
ጥርጣሬ፣ ቅጥፈትና ሌብነት አንድ ህብረተሰብ ውስጥ ሲነግሥ ዕድገት መቀጨጩ አሌ አይሉት ነገር ነው፡፡ የተዋሃደውን ለመነጣጠል፣ የተጋባውን ለማፋታት፣ የተደራጀውን ለመበታተን መሞከርን ያህል እኩይ ተግባር ያጥጣል። የተማረው እንዳልተማረ ይናቃል፡፡ የመንገዱን መነሻ እንጂ መድረሻውን አለማስተዋል የዕለት የሰርክ ህፀፅ ይሆናል፡፡
ሮበርት ግሪን፤
“ፍፃሜውን የማትገምተው ነገር አትጀምር” ይለናል፡፡
ያቀድነው ዕቅድ ከየት ያስጀምረናል? ወዴት ያመራናል? ወዴትስ ያደርሰናል? ግብዐቶቹ ምን ምንድናቸው? ብሎ በቅጥ በቅጡ እያዩ መከታተል፤ እናም እፍፃሜ ሳይደርስ ሌላ ምዕራፍ አለመጀመር፣ በተለይ ትግል ውስጥ ለገባ ቡድን፣ ስብስብ፣ ማህበር ወይም ድርጅት፤ ዋና ነገር ነው፡፡ ሁለተኛው በቂ ዝግጅት ማድረግ ነው። ባጭሩ በአገርኛ ግጥም፡-
“ቀድሞ ነበር እንጂ፣ መጥኖ መደቆስ
አሁን ምን ያደርጋል፣ ድስት ጥዶ ማልቀስ” የሚለውን ማስታወስ ነው፡፡
“ሌሎች አዝመራውን ስለሚሰበስቡት ሰብል ማለም ከንቱ ህልም ነው፡፡ ይልቅ ራስህ መጨረሻውን የምትጨብጠውን ህልም ዛሬውኑ አልም!” ይላሉ አበው፡፡
ህልማችን ዕውን እንዳይሆን እፊታችን የሚደቀኑትን እንቅፋቶች ለይቶ ማስቀመጥ፣ እንቅፋቶቹን አልፎ ለመሄድ የሚገባውን ያህል አቅም መፍጠርና ጉልበትን ማጠራቀም፤ ሳይታክተን ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ፣ በፅናት መጓዝ፤ ያስፈልጋል፡፡ ምንጊዜም ቢሆን ሙሉ በሙሉ ማሸነፍና ሙሉ ለሙሉ መሸነፍ አለመኖሩን፣ ማመንና ይልቁንም፤ ጠንካራና ደካማ ጎን ሁሌም መኖሩን ማስተዋል የተሻለ ዕውነታ ነው፡፡
ሁኔታዎች ተለዋዋጭ መሆናቸውንና አዲስ አሸናፊ ምንጊዜም መብቀሉን ለአፍታም አለመዘንጋት ነው፡፡ ተስፋ አለመቁረጥ የሚመነጨው ከዚህ ዕሳቤ ነው። ያለ ሁሌም የሚኖር ይመስለዋል፤ ይላሉ አበው፡፡ ሆኖም ያልፋል፤ ማለታቸው ነው። የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የፍትህ አካላት፣ የአስተዳደር ወኪሎች እና ፍርድ ቤቶችም ጭምር፣ ከህብረተሰብ ጋር የሰፋ ግንኙነት መፍጠርና በመዋቅርም፣ በመንፈስም የበለጠ ዲሞክራሲያዊነት እንዲኖራቸው መጣር፤ ዛሬ የዓለም ሁሉ ትጋት ነው፡፡ ከዚህ የድርሻችንን መውሰድ ነው፡፡ ክሊንተን ሮዚተር የተባለው ምሁር፤ “አገር ያለ ዲሞክራሲ፣ ዲሞክራሲ ያለ ፖለቲካ፣ ፖለቲካ ያለ ፓርቲዎች አይኖርም” ይለናል። ይህን እንዲሰራ ለማድረግ ግን ቀና ልቡና ይጠይቃል፡፡ ጤናማ ፓርቲና ጤናማ ፖለቲካዊ ስነ - ልቦናም እነዚህ ውስጥ ወሳኝ ናቸው፡፡ ያሉት ቀና ፓርቲዎች እጅግ ጥቂት ናቸው፡፡  ያሉንን የፖለቲካ ፓርቲዎች ካመናመንንና ካጠፋናቸው     “ከርከሮ አንዲት ፀጉር አለችው፣ እሷን ለማጥፋት ይተሻሻል” የሚለውን ተረት በታሳቢነት ያዝን ማለት ነው፡፡

Read 6399 times