Saturday, 27 June 2015 08:22

ት/ቤቱ ልጆቻችንን እርዳታ መለመኛ አድርጐብናል ሲሉ ወላጆች ከሰሱ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(4 votes)

“ድርጊቱን የፈፀሙት በውጭ አገር የሚገኙ ግለሰቦች ናቸው” - ት/ቤቱ

     ከቢ አካዳሚ በተባለ የአፀደ ህፃናትና ህፃናት ማቆያ ት/ቤት ልጆቻቸውን እየከፈሉ የሚያስተምሩ ወላጆች፤ “እኛ ሳናውቅ ልጆቻችን በድረ ገፅ መለመኛ ተደርገውብናል” ሲሉ ያማረሩ ሲሆን ት/ቤቱ በበኩሉ፤ ድርጊቱን የፈፀሙት በውጭ ሀገር የሚገኙ ግለሰቦች ናቸው ብሏል፡፡ በአዲስ አበባ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ፣ ወረዳ 02/03 የሚገኘው ከቢ አካዳሚ፣ የልጆቻችንን ፎቶግራፎች በድረገፆች እየተለጠፈ የእርዳታ ማሰባሰቢያና መለመኛ አድርጐብናል ያሉት ወላጆች፤ ራሳቸውም መለመኛ ከመሆን እንዳላመለጡ ይናገራሉ፡፡ “እኛም አልቀረልንም፤ የአንዳንድ ወላጆች ፎቶግራፍም ለመለመኛነት ውሏል” ብለዋል፡፡ ት/ቤቱ አፀደ ህፃናትን ጨምሮ የህፃናት ማቆያ (ዴይኬር) አገልግሎት የሚሰጥ ሲሆን በአፀደ ህፃናት ለሚማሩ ልጆቻቸው በወር 500 ብር፣ በማቆያ ለሚገለገሉ ህፃናት ደግሞ በወር 600 ብር እንደሚከፍሉ ወላጆች ለአዲስ አድማስ አስረድተዋል፡፡ “በልጆቻችን ላይ የተፈፀመው ድርጊት በእጅጉ የስነ ልቦና ጉዳት አድርሶብናል” ያሉት የወላጅ
ተወካዮቹ፤ ጉዳዩን ካወቁ በኋላ ለህግ አካላት ቢያመለክቱም ቀና ምላሽ ሳያገኙ መቆየታቸውን ጠቁመው ባለፈው ረቡዕ ለክፍለ ከተማው አስተዳደር ማመልከታቸውን ይናገራሉ፡፡ የክፍለ ከተማው አስተዳደርም ጉዳዩ በወረዳ 2 በኩል እንዲታይ ወስኖ፣ በትናንትናው እለት ወረዳው ለፍትህ ቢሮ ክስ ማቅረቡን የወላጅ ተወካዮች ገልፀዋል፡፡ ወላጆቹ ባሰባሰቧቸው የድረ - ገፅ መረጃዎች ላይ የህፃናቱ ፎቶግራፍ ከሙሉ የማንነት መግለጫ ጋር ተቀምጦ፣ በትይዩ ለትምህርት ፕሮጀክቱ የገንዘብ ድጋፍ እንዲያደርጉና እርዳታ እንዲለግሱ
ጐብኚዎችን የሚጠይቅ የተማፅኖ መልዕክት ሰፍሯል፡፡ Kobiacademy.org በሚለው ድረ ገጽ ላይም ተማሪዎች በህብረት የተነሷቸው እንዲሁም የወላጆች መምህራንና የተማሪዎች የተናጠል ፎቶግራፎች መለጠፋቸውን ጠቁመው በእንግሊዝኛ “Donate Now!” (አሁን ይርዱ) የሚል መልዕክት መቀመጡን ወላጆች ገልፀዋል፡፡
የአፀደ ህፃናት ተማሪ የሆነች ልጅ ያላቸው አቶ መላ የተባሉ ወላጅ፤ የልጃቸው ፎቶግራፍ በተናጠል ከአጭር የማንነት መግለጫና የእርዳታ ጥያቄ ጋር በድረገፁ መቀመጡን ጠቁመው የራሳቸውም ፎቶግራፍ “ከወላጆች አንዱ፤ አቶ መላ ገ/ሚካኤል” ከሚል መግለጫ ጋር ተለጥፏል፡፡በድረገፁ ላይ አካዳሚው በአሜሪካ የተደራጀ ኮሚቴ እንዳለው መጠቆሙንና የኮሚቴው ተግባርም ስትራቴጂክ እቅድና ግብ መንደፍ እንዲሁም፤ የምክርና የእርዳታ ማሰባሰብ ስራዎችን እንደሚሠራ ተገልጿል ብለዋል - ወላጆች፡፡ በኮሚቴው ውስጥም ትውልደ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያን ያልሆኑ ግለሰቦች እንዳሉበት በፎቶግራፍ ከተደገፉ የማንነት መግለጫዎች ተረድተናል ያሉት ወላጆች፤ ኮሚቴው በዋናነት የእርዳታ ማሰባሰብ ስራ እንደሚሠራ መጠቀሱንም ይገልፃሉ፡፡
ጉዳዩን የሰሙት ከወር በፊት ከት/ቤቱ አካባቢ መሆኑን የጠቆሙት ሌላዋ ወላጅ ወ/ሮ ፍቅርተ፤ መረጃውን ከሰሙ በኋላ ለተወሰኑ ወላጆች በመጠቆም፣ በጋራ ሆነው የት/ቤቱን አስተዳደር ቢያነጋግሩም አስተዳደሩ ቀና ምላሽ እንዳልሠጣቸው ያስረዳሉ፡፡ ከቀናት በኋላ ግን አስተዳደሩ ወላጆችን ስብሰባ ጠርቶ “ልጆቻችን መለመኛ ሆኑ የምትሉ ወላጆች ኮሚቴ ምረጡና ትከሳላችሁ” ብለዋቸው አራት አባላት ያሉት የወላጆች ኮሚቴ መዋቀሩን ይገልፃሉ። ኮሚቴውም ተሰብስቦ ለመክሰስ የሚያስችለውን ቃለ ጉባኤ በሚያረቅበት ወቅት የት/ቤቱ አስተዳዳሪ
አቶ ሚካኤል፤ “እኛ ሳናውቅ ውጭ ያሉ ሰዎች የፈፀሙት ድርጊት ነው፤ እኔም ከእናንተ ጋር ከሳሽ ነኝ” ማለታቸውን የኮሚቴው አባላት ይናገራሉ፡፡ የድርጅቱ ባለቤትና ስራ አስኪያጅ አቶ ሚካኤል ተክሌ ስለጉዳዩ ለአዲስ አድማስ በሰጡት አስተያየት፤ “ድርጊቱ የተፈፀመው ከዚህ አይደለም፤ ውጭ ሀገር ካለው ጋር የተያያዘ ነው፤ ከኛ ጋር አይገናኝም፤ ስለጉዳዩ እንደማናውቅም በማስረጃ አስደግፈን ለወረዳው አመልክተናል” ብለዋል፡፡  

Read 3664 times