Saturday, 27 June 2015 08:13

ከእትብት ጋር የወጣ አመል፣ ከከፈን ጋር ይቀበራል

Written by 
Rate this item
(9 votes)

ከአይሁዳውያን ተረት ውስጥ እንዲህ የሚል ይገኝበታል፡፡
ከዕለታት አንድ ቀን አንድ ብቸኛ ጫማ ሰፊ በአንድ ከተማ ይኖር ነበር፡፡ የዚያ ጫማ
ሰፊ አንድ ደንበኛ ጫማ ሊያሰራ መጥቶ ሳለ፤
“ጫማዬን በትክክል አልሰፋህልኝምና አልከፍልህም” ይለዋል፡፡
ጫማ ሰፊውም፣
“ከዚህ በላይ ልሰፋልህ አልችልም፡፡ የሰፋሁልህን ያህል ልትከፍለኝ ይገባሃል” አለው፡፡
“አልከፍልም”
“ትከፍላለህ!”
ግብ ግብ ገጠሙ፡፡ ጫማ ሰፊው ደምበኛውን በመዶሻ አናቱን ብሎ ገደለው፡፡
ተይዞ እከተማው ዳኛ ፊት ቀረበ፡፡
የከተማው ዳኛም፤
“ደምበኛህን ሆነ ብለህ በመዶሻ መትተህ በመግደልህ ሞት ይገባሃል፡፡ ይኸውም ሞት
በስቅላት መልክ የሚፈፀም ይሆናል፡፡” ሲሉ ፈረዱ፡፡ ፍርዱ ባደባባይ ተነበበ፡፡ ፍርዱን
ከሚያዳምጠው ህዝብ መካከል አንድ ሰው ተነስቶ፤
“የተከበሩ ዳኛ! እነሆ በከተማችን አለን የምንለውን አንድ ጫማ ሰፊ እንዲገደል
ፈርደዋል፡፡ ሆኖም ያለን ብቸኛ ጫማ ሰፊ እሱ ስለሆነ ከእንግዲህ ማን ጫማችንን
ይሰራልናል? ለህዝቡ ሊታሰብለት ይገባል!”
ሲል ሀሳብ አቀረበ፡፡ ሌሎችም ሰዎች በተራ በተራ እየተነሱ፤
“አስተያየት ይደረግልን”
“አስተያየት ይደረግልን”
“ያለን እሱ ብቻ‘ኮ ነው ምን ይውጠናል?” አሉ፡፡
የህዝቡ ሁኔታ የከተማው ዳኛ ሀሳባቸውን እንደገና እንዲያጤኑ አደረጋቸውና፤
“የከተማችን ህዝብ ሆይ በሀሳባችሁ እስማማለሁ፡፡ ያላችሁትም ዕውነት ነው፡፡ አንድ
ልብስ ሰፊ ቢኖረን እሱኑ መግደል ትክክል አይሆንም፡፡ በከተማችን ሁለት ጣራ ሰሪዎች
ናቸው ያሉት፡፡ ስለዚህ ከሁለቱ አንደኛው እንዲሞት ወስኛለሁ! ፍርዱ በስቅላት የሚፈፀም
ይሆናል!” ሲሉ ፈረዱ፡፡
* * *
አንዱን አድን ብሎ አንዱን ከሚያስገድል፣ በፍርደ - ገምድልነት ከመፍረድና በህዝብ
ከመገፋት ይሰውረን! በትናንሽ ጠብ - ያለሽ በዳቦ ከመናቆርም ያድነና፡፡ የፍርድ ሂደት
በቲፎዞና በግፊት ከሆነ የህግ መንፈስ ጨርሶ ጥያቄ ውስጥ መውደቁ አይቀሬ ነው፡፡ ህግ
ስነ-ሥርዓት አክብሮ የሚኖር ዜጋ ወገናዊነትንና ፍርደ - ገምድልነትን መቃወሙ ያለ፣
የነበረና ወደፊትም የሚኖር ነው፡፡
“ለመቶ አምሣ ጌታ
ስታጠቅ ስፈታ
ነጠላዬ - አለቀ በላዬ”፤ ያለችው ጭሰኛ ይሄንኑ የፍትህ መዛባትና የጌታ - የሎሌ ግንኙነት
አባዜ ስትግልጥ፣ ብሶቷንም ስታሰማ ነው፡፡ ዜጋ ቅሬታውንና በደሉን ማሰማቱ፣ ምንም
ቢዘገይ፣ አይቀርምና የፍትሕ አካላት ለሚያዛቡት ማናቸውም ፍርድ ተጠያቂነታቸው
አሌ አይባልም፡፡
በየትኛውም ሥርዓት ውስጥ ሥልጣን ላይ የሚቀመጡ ሹማምንት ከየት እንደመጡ፣
የት እንዳሉና ወዴት እንደሚሄዱ የዘነጉ ዕለት የጥፋት ህይወታቸው ይጀምራል፡፡ የበለጠው
ጥፋታቸው ደግሞ ጥፋታቸውን አለማመናቸው ነው፡፡ ከዚያ ቀጣዩ ደግሞ የአብዬን ወደ
ዕምዬ ማላከካቸው ነው፡-
ሥልጣን ላይ ያሉ ሰዎች የሚዋረዱት በሚሰሩዋቸው ስህተቶች
አይደለም፡፡ ይልቁንም፤ ስህተቶቻቸውን በሚይዙበት መንገድ
ምክንያት ነው” ይለናል ሮበርት ግሪን፡፡ (The way they deal with
their mistakes እንዲል)
“የአብዬን እከክ ወደ እምዬ ልክክ” የሚለው አባባል፣ Scapegoat የሚሉት በእንግሊዝኛ
መሰረታዊ - አመጣጡ በዕብራውያን ምክንያት ነው ይባላል፡፡ ይኸውም ለተሰራ ጥፋት
የፍየል መስዋዕት በማድረግ አገራቸውን ለማዳን ይሞክሩ በነበረበት ዘመን ነው፡፡ ከዚያም
ቢሆን ይሰውረን የዲሞክራሲ ጠር ነውና! ዲሞክራሲ እንደየአገሩ ፈሊጡም፣ አካሄዱም
እንደሚለያይ ማስተዋል ዋና ቁም ነገር ነው፡፡
ፋሪድ ዘካሪያ እንዲህ ይለናል፡-
… የበለጠ “ዲሞክራሲ” አለ በሚባልበት በአሜሪካ ሥርዓት ከዚህ
ቀደሙ የበለጠ ሥርዓተ - ነገሥታት (dynasties) አይተናል፡፡ የተከበሩ
ሹማምንት አይተናል፡፡ ሆኖም የፖለቲካ ፓርቲዎች እየተዳከሙ
ሲሄዱ፤ ሀብታም መሆን እና/ ወይም ዝነኛ መሆን፤ ለከፍተኛ ተመራጭ
ሹማምንት ተራ፣ የአዘቦት ጉዳይ ይሆናል፡፡
እኛ ሀገርም ከፊውዳሊዝም አብራክ ወጥቶ፣ በሶሻሊዝም አቋርጦ፣ አሁን ከካፒታሊዝም
ጋር በመፈጣጠም፣ እንውለደው እያልን የምናማምጠው ዲሞክራሲ፣ ከሌላ ከማናቸውም
አገር የተለየ ቢሆን አይገርምም፡፡ ተዋንያኑ አዋላጆች ግን ዛሬም እኛ ነን፡፡ የእኛ ማንነት
ደግሞ ንጥረ ነገሩ አንድ ነው፡፡ ታሪካችን፣ ባህላችን፣ ፖለቲካችን መሰረቱ አንድ ነው፡፡
ድንገት በአንድ ጀንበር አይለወጥም - “ከእትብት ጋር የወጣ አመል፣ ከከፈን ጋር ይቀበራል”
የሚባለው ተረት ዕውነት የሚሆነው ለዚህ ነው

Read 7859 times