Saturday, 20 June 2015 11:12

መንግሥት አንዳንዴ የሚመራውን ህዝብ ይምረጥ! መንግሥት አንዳንዴ የሚመራውን ህዝብ ይምረጥ!

Written by  ኤልያስ
Rate this item
(13 votes)

ዶ/ር አሸብር ኢህአዴግን እንዴት ይታዘቡት? (ከአሁን በኋላማ!)
260ሺ የመዲናዋ ነዋሪዎች “ምርጫው ይለፈን” ብለዋል?!
ኢህአዴግን ያልመረጡት ከ400ሺ በላይ ነዋሪዎችስ? (ዜግነት አይለውጡ!)

   ብዙ ጊዜ ጦቢያችን ውስጥ አንድ ትልቅ አገራዊ ክስተት ከተፈፀመ በኋላ (ለምሳሌ እንደ ግንቦቱ ምርጫ ያለ!) ሀበሻ በእጅጉ የሚታወቀው በምን መሰላችሁ? የጨረሱ ቀልዶችን በመፍጠር ወይም በመኮመክ ነው። (በራሱ ላይ እኮ ነው!) እንዴ … በዚህ ዓይነቱ ኑሯችን … በዚህ አይነቱ አለመከባበራችን … በዚህ ዓይነቱ ዘረኝነታችን … በዚህ ዓይነቱ ጭፍንነታችን … አንድዬ በራሳችን ኑሮ የመቀለድ … ቀልዶም የመሳቅ … ስቆም ከጨፍጋጋው የዕለት ተዕለት ህይወታችን ለአፍታም ቢሆን የመላቀቅ ፀጋ ባያድለን ኖሮ ምን ይውጠን ነበር? ዝንተ ዓለም እሮሮ? ለነገሩ አበሻ ሁሌ “Happy” ነው (ይኮምካላ!) የቀድው ጠ/ሚኒስትር (ነፍሳቸውን ይማረውና!) በእኛ ነው የወጡት (ወይም እኛ በእሳቸው ነው የወጣነው!) እናላችሁ … እስቲ አንድ መራራ የምርጫ  ቀልድ ላስታውሳችሁ፡- (አይዟችሁ ከ2007 ሳይሆን ከ97 ነው!)
በ97 የምርጫ ቀውስ ጊዜ የጎዳና ነውጠኞችን (የቀለም አብዮተኞችም ያስኬዳል!) ከጥይት በፊት ውሃ በመርጨት ወደ ሰላማዊ ኑሮ እናምጣቸው የሚል የጋራ ውሳኔ ላይ ሳይደረስ የቀረ አይመስለኝም። (በኢህአዴግና የኒዮሊበራል መንግስታት ማለት ነው!) ከዚያስ? ውሳኔው ወደ ፈፃሚው የወርዳል፡፡ ወደ ፌደራል ፖሊስ!! ከፌደራል ፖሊስም ወደ አድማ በታኙ ኃይል! ከአድማ በታኙም ለምርጫው ከተለያዩ ክልሎች ተመርጦ ወደ መጣው የከተማ ዋዛ ፈዛዛ የማያውቅ ፌደራል! … እስቲ አስቡት የጎዳናን ነውጥ በውሃ ርጭት ሲበትን! … ሲባል  መጀመሪያ ቀልድ ሊመስለው ይችላል፡፡ የምር መሆኑን ሲያውቅ ግን እንዲህ አለ ተብሎ ተቀልዷል “እሺ ውሃው ይፍላ!” እኛ እንግዲህ እንዲህ ነው ስንቀልድ! (ሰው ኑሮውን ይመስላል አሉ!)
ከዋናው አገራዊ ምርጫ ዘግይቶ በቅርቡ የተካሄደው የቦንጋ ምርጫ ሁለት ዶክተሮችን ያፋጠጠ ነበር ተብሏል - በየሚዲያው እንደተዘገበው። ምርጫ ዋናው ሂደቱ ነው የምትሉ ፍጥጫው እንደመንግስት ኮሙኒኬሽን ፅ/ቤት ሚኒስትሩ አቶ ሬድዋን ሁሴን፤ ምርጫ ዋናው ሂደቱ ነው ለምትሉ ዓይነቶቹ ፍጥጫው ይማርካችሁ ይሆናል፡፡ አልዋሻችሁም… ለእኔ ግን ዋናው ሂደቱ ሳይሆን ውጤቱ ወይም ፈረንጆች እንደሚሉት ቆጠራው ነው፡፡ ዶ/ር አሸብር ወ/ጊዮርጊስ እንደኔ ዋናው ውጤቱ ነው የሚሉ ይመስለኛል። (ኢህአዴግን አትፎካከረኝ ብለውታላ!) እናም እስካሁን በታወቀው ውጤት መሠረት፤ ዶ/ር አሸብር 9ሺ ድምጽ ያገኙ ሲሆን ደህዴን/ ኢህአዴግን በመወከል የተወዳደሩት ዶ/ር መብራቱ ገ/ማርያም ደግሞ 44ሺ ድምጽ ማግኘታቸው ታውቋል (ኢህአዴግ “ደጋፊህ ነኝ” ተብሎም አይራራም እንዴ?)
በነገራችን ላይ ከ5 ዓመት በፊት እሳቸውም የኢህአዴግን ተወካይ ነው በዝረራ አሸንፈው ፓርላማ የገቡት፡፡ ግን ከኢህአዴግ ጋር የተወዳደሩትም ሆነ ኢህአዴግን ያሸነፉት ወደው ሳይሆን የግድ ሆኖባቸው እንደሆነ መግለፃቸው አይዘነጋም (አያድርስ እኮ ነው!) የዘንድሮ ምርጫ ከመዳረሱ ትንሽ ቀደም ብለው ለዚሁ ጋዜጣ በሰጡት ቃለምልልስ፤ ኢህአዴግ በምርጫው እንዳይፎካከራቸው አበክረው ጠይቀው ነበር፡፡ ለምን ሲባሉ? የፖሊሲው ሙሉ ደጋፊ ስለሆንኩ በእኔ የምርጫ ክልል ኢህአዴግ ተወዳዳሪ አይመድብብኝ ነው ያሉት (ሳይደባብቁ!)
ኢህአዴግ ደግሞ የ2002 ምርጫ ብድሩን መክፈል ሳይፈልግ የቀረ አይመስለኝም፡፡ ወይም ደግሞ ለእሳቸው ተማፅኖ ጆሮ አልሰጠ ይሆናል። (በምርጫው ጣጣ ተወጥሮ!) የሆኖ ሆኖ ግን የፖሊሲው ደጋፊ ስለሆንኩ በእኔ የምርጫ ክልል ኢህአዴግ ተወዳዳሪ አይመድብብኝ ቢሉም የቴፒ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንትና እንደሳቸው ምሁር የሆኑትን ዶ/ር መብራቱ ገ/ማሪያምን ነበር በደህዴን  በኩል ተፎካካሪ አድርጐ ገጭ ያደረገባቸው፡፡
ለኢህአዴግ ግን አንድ ወዳጃዊ ምክር በአደባባይ ብለግሰው እወዳለሁ (እንደማይቀበለኝ እኮ አውቀዋለሁ፤ ይውጣልኝ ብዬ እንጂ!) እናም … የደጋፊና የወዳጅ ጡር አለውና “በልማት ፖሊሲ ፍቅር ወደቅን፣ በዕድገት ስትራቴጂህ አበድን፤ ከነፍን” ለሚሉ አንዳንድ የጦቢያ ልጆች ጆሮና ቦታ ቢሰጣቸው ተገቢ ይመስለኛል። ይታያችሁ… በአዲስ አበባ ከ400ሺ በላይ ነዋሪዎች ኢህአዴግን አልመረጡም (ባቡሩን እኮ አይተውታል!) 260ሺዎቹ ደግሞ ምርጫ ጣቢያ ዝር አላሉም ተብሏል (ኢህአዴግ በ100ፐርሰንት ማሸነፉን አልዘነጋሁትም!) እንዲያም ሆኖ 186ሺ 875 ነዋሪ ሰማያዊ ፓርቲን መምረጡን እኛም ኢህአዴግም ያውቀዋል፡፡ አሁን ጥያቄው ይሄ ሁሉ የተቃዋሚ ድምፅ፣ የተአቅቦ ድምፅ፣ የኩርፊያ ድምፅ በማን ሊወከል ነው? (በፓርላማ ማለቴ እኮ ነው!) ይሄ የውክልና ጉዳይ እንጂ የጡር ጉዳይ አይደለም፡፡ ለነገሩ ኢህአዴግ ለደጋፊዎቹ (ወዶ ገቦቹን ማለቴ ነው!) ካልሆነ እንዴት ላልመረጠውና ላኮረፈው ሊሆን ይችላል (በሊማሊሞ ማቋረጥ ይችላሉ!)
ወደ ቦንጋ እንመለስ - ወደ “የሁለቱ ዶክተሮች ወግ!!” (የአቶ በረከት “የሁለት ምርጫዎች ወግ” ትዝ አለኝ!) አያችሁ… ዶ/ር አሸብር ቀድሞውኑ እኔ ያንተው ነኝና ተፎካካሪ አትመድብብኝ ያሉት ይሄንን ፈርተው ነው፡፡ (የፈሩት እኮ መሸነፍን ሳይሆን ፉክክሩን ነበር!) የማታ ማታም በምርጫው ሳይቀናቸው ቀረ፡፡ በእርግጥ የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢው ፕ/ር መርጋ በቃናና ለተቃዋሚ ፓርቲዎች እንዳሉት፤ “የዓለም መጨረሻ አይደለም፤ ከ5 ዓመት በኋላ ሌላ ምርጫ ይመጣል” ይሄን መቼም ዶ/ር አሸብርም አይጠፋቸውም፡፡ ማንም በእሳቸው ቦታ ቢሆን ግን ሌላው ሁሉ ቢቀር ኢህአዴግን ክፉኛ ይታዘበዋል (ዘመድን አይጣሉትማ!)
እኔ የምለው ግን… ኢህአዴግ አዳዲስ አባላትን እንዴት ነው የሚመለምለው? (ለሳቸው ሳይሆን ለራሴ ነው!) አያችሁ …በጊዜ ቦታ መያዝ ሳይሻል አይቀርም። (በሁለት ተከታታይ ምርጫዎች “በዝረራ” ሲያሸንፍ እያዩ መፋዘዝ ጅልነት ነው!) በነገራችን ላይ እኔ የኢህአዴግ አባል ለመሆን የተነሳሳሁት ሥልጣን ወይም ጥቅም አሊያም ኢህአዴግ ለብቻው የተቆጣጠረውን ፓርላማ ልቦርቅበት አምሮኝ እንዳይመስላችሁ። (በቃ የአሸናፊ ፓርቲ አባል መሆን ይምቸኛል! ስለሚያስደስተኝ ብቻ!) በየ4 ዓመቱ በሚመጣው የዓለም ዋንጫ ጊዜ እንኳ በጓደኞቼ ዘንድ የምታወቀው በግብ የሚመራውን ቡድን አይቼ ድጋፍ በመስጠት ነው (ፈርዶብኝ አሸናፊ እወዳለሁ!)
እስካሁን ባለው የምርጫ ቦርድ ውጤት መሰረት እንግዲህ ለቀጣዮቹ 5 ዓመታት በአራት ኪሎው የጦቢያ ፓርላማ፤ የተቃዋሚ ፓርቲዎችን ብቻ ሳይሆን የግል ተወዳዳሪም ላናይ ነው ማለት እኮ ነው (ፓርላማው ውስጥ የሚቀመጡት ታዛቢ ዲፕሎማቶችም እንዳይጠፉ ብቻ!)
አሁንም አንድ የወዳጅ ምክር ለኢህአዴግ ብለግሰው ደስ ይለኛል (እንደማይሰማኝ እኮ አሳምሬ አውቃለሁ!) ለነገሩ ሰማኝ አልሰማኝ “ወዶ ገብ ደጋፊ” ስለምሆን ፓርቲውን ከውድቀት ለመታደግ መለፍለፌን አልተውም፡፡ ከምሬ ነው .. ፓርቲውን  ያድነዋል ያልኩትን ሁሉ እተነፍሳለሁ፡፡ ምን መሰላችሁ …. ተቃዋሚዎች በምርጫው ላይ አለን የሚሉትን ቅሬታና ችግር (መጭበርበርን ጨምሮ) መስማት ክብር አያዋርድም፡፡ እንግዲህ አስቡት… በምክንያታዊነት እመራለሁ የሚለው የ97ቱ ቅንጅት ሰለባ የሆነው የሦስተኛው አማራጭ ቀያሽ ኢዴፓ እንኳን እንዲህ አምርሮ መግለጫ ሲያወጣ ሰምቼ አላውቅም፡፡ በምርጫው ኢ-ተዓማኒነት ዙሪያ እኮ ነው፡፡ (ኢህአዴግ በረዶዎቹን ተቃዋሚዎች እሳት ካስጫራቸውማ ለራሱ መፍራት አለበት!)
ይሄ የጡንቻ መፈታተሸ ጉዳይ አይደለም፡፡ መፍራት ደግሞ ለራስ ብቻ አይደለም … ለህዝብም … ለአገርም … ለጊዜያችንም … ለመርሃችንም … ለታገልንበት ዓላማም … (አገርም ነው፡፡ እናም ጠልቆ ማሰብ …. ከራስ መታረቅ… ትልቁን ስዕል ማየት … (ጦቢያን) ወይም ኢህአዴግ የህልውናዬ መሰረት ነው የሚለውን ዲሞክራሲን … ማስቀደም አለብን!!
በነገራችን ላይ እኔ ከዚህ (ከዘንድሮ ማለቴ ነው!) ምርጫ ደስ ያለኝ ምን እንደሆነ ታውቃላችሁ? “አንድም ዜጋ በምርጫው አይሞትም!” የሚለው መርህ በአንፃራዊነት በመሳካቱ ነው፡፡ (አሁን አሁን Bad news መሰማቱ ያሳፍራል!) ግን የምርጫው ድባብ እኮ ደስ አይልም ነበር፡፡ አንድ የሆነ ወቅት ላይ እኮ የምንዘጋጀው ለምርጫ ነው ለጦርነት አሰኝቶን ነበር? የወታደሩ መኪና.. የፖሊስ መግለጫ… የመንግስት ባለስልጣናት ማስፈራሪያ…የቦርዱ ኃይለቃል ወዘተ (ሃበሻ ስለሆንን ግን በራሳችን ቀልደን እንረሳዋለን!) የወደፊቱ ምርጫ ግን (አረረም መረረም… መካሄዱ አይቀርም ብዬ እኮ ነው!) ከፍርሃት የፀዳ፣ የምንናፍቀው ቢሆንልን እንመኛለን (ናፍቆቱ ቢቀር እንኳ የማንፈራው ከሆነ ይበቃናል!) አሁን ደግሞ ሰሞኑን የሰማኋትን በዘንድሮ ምርጫ ላይ የምታጠነጥን ሂሳዊ ቀልድ እነሆ፡፡ (ምርጫው የኛ፤ ቀልዱ የኛ!)
የምርጫው ዕለት ነው አሉ፡፡ ሦስት ወጣት ጓደኛሞች ድምፃቸውን ሰጥተው ከምርጫ ጣቢያ ከወጡ በኋላ “ማንን መረጥክ?” ይባባላሉ፡፡ ሁለቱ “ኢህአዴግን” አሉ። አንዱ ግን “እኔ ግን ሰማያዊን መረጥኩ” ይላቸዋል፡፡
ሁለቱ ጓደኛሞች አፋጠጡት፤
“እንዴት ሰማያዊን ትመርጣለህ? ምን ሲሰራ አይተህ ነው?” ይሉታል፡፡
“በቃ ሰማያዊ ይመቸኛል!” “ኧረ ሰርቶ ያሳየንን ኢህአዴግን ምረጥ” በመጨረሻ በአቻ ተፅዕኖ አሳመኑትና የሰጠውን ድምጽ ሊያስተካክል ወደ ምርጫ ጣቢያው ገባ፡፡ መግቢያ ላይ ወዴት ነው ተባለ (ዝም ብሎ ዘው የለማ!) “አይ ድምጽ ስሰጥ ተሳስቼ ማስተካከል ፈልጌ ነው”
“እንዴት ማለት?”
“ሰማያዊን መርጬ ነበር፤ በኢህአዴግ ላስተካክለው ፈልጌ ነው”
“በል ሌላ ጊዜ እንዳይደግምህ፤ ለዛሬ እኛ አስተካክለነዋል” ብለው መከረው ሸኙት!!
ይሄ እኮ ነው ምርጫውም የእኛ፣ ቀልዱም የኛ የሚያስብለው፡፡ (ቀልደን ይወጣልናል!) በነገራችሁ ላይ አንዳንዴ መንግስትም የሚመራውን ህዝብ ቢመርጥ ጥሩ ነው እላለሁ፡፡ በቃ የወደደውን መርጦ ይምራ፡፡ ሁልጊዜ በህዝብ ምርጫ ምን በወጣው? (እሱም ይየው የመራጭን ጣጣ ብዬ እኮ ነው!)

Read 4153 times