Saturday, 20 June 2015 10:43

ሣር የምትበላው በቅሎ ሄዳ ልጓም የምትበላው መጣች

Written by 
Rate this item
(11 votes)

ከዕለታት አንድ ቀን የዱር አራዊት ንጉሥ “አያ አምበሶ ታሟል እና ሄደን እንጠይቀው” ብለው የዱር አራዊት እመት ጦጢትን ይነግሯታል፡፡
እመት ጦጢትም፤
“እስቲ እናንተ ቀደም ብላችሁ ሂዱ፡፡ እኔ፤ አያ አምበሶ የሚመገበውን ምግብ ለማዘጋጀት የሚጠቅመውን ራሺን ልሸማምት” አለቻቸው፡፡
የዱር አራዊቱ ወደ አያ አምበሶ ሄዱ፡፡ ጦጢት ወደ ኋላ ቀርታ ዝም ብላ የሚሆነውን ታዳምጥ ጀመር፡፡
የዱር አራዊቱ አያ አምበሶ ጋ ደርሰው፣
“አያ አምበሶ ተሻለዎ ወይ?” ይላሉ፡፡
አያ አምበሶም፤
“ኧረ እየባሰብኝ ነው የመጣው፡፡ እርጅናም በጣም እየተጫነኝ ነው፡፡ በዛ ላይ የሚያስታምመኝ አንድም እንስሳ አጠገቤ የለም፡፡ ደግም ምግብ እንደልቤ አልበላም” አለ፡፡
ሁሉም ደንግጠው “ምን ብናደርግ ይሻላል?” ተባባሉና “ምን ዓይነት ምግብ ያምርዎታል?” ሲሉ ይጠይቃሉ፡፡
አያ አምበሶ፤ “በየቀኑ የሚያምረኝ ሥጋ ዓይነቱ ይለያያል
አንድ ቀን የድኩላ ያምረኛል፡፡
ሌላ ቀን የጎሽ ያምረኛል፡፡
ደሞ ሌላ ቀን የቀጭኔ ሥጋ እንደጉድ ያምረኛል፡፡  
ደሞ አንዳንድ ሰሞን የነብር ሥጋ ያስፈልገኛል፡፡ ይሄን ካላገኘሁ የምድን አልመሰለኝም” አለ፡፡ የዱር አራዊቱ ደግመው ተሰበሰቡና፤
“ጎበዝ ምን እናድርግ?” ተባባሉ፡፡
ሁሉም፤ “ጦጣ መላ አታጣም፡፡ ሄደን እንጠይቃት” አሉ፡፡
ከአያ አምበሶ ጊዜ ቀጠሮ ወሰዱ፡፡ ሀሳባቸውን በደምብ አብስለው እስኪመጡ ተራ ገብተው ሊያስታምሙ ተስማሙ፡፡
ጦጢት እንዳደፈጠች ዛፉዋ ላይ ሆና ትጠብቃለች፡፡ ወደ እሷው ዘንድ ሄዱና፤
“እመት ጦጢት አያ አምበሶ ግራ - የሚያጋባ ጥያቄ አቀረቡልን፡፡ ይኸውም ከየአንዳንዱ እንስሳ በዓይነት በዓይነቱ ምግብ ያምረኛል አሉ፡፡ ይህን እናድርግ ካልን በቀን በቀን አንድ አንድ እንስሳ ይታረድ እንደማለት ነው?” አሏት
እመት ጦጢትም፤
“ይሄ መቼም ዐይናችን እያየ እያንዳንዳችን በየተራ እንሙት ማለት ነው፡፡ ስለዚህ የሚሻለው አንድ ሆነን፣ በአንድ ድምፅ፣ ፈትልና ቀስም ሆነን፤ ይሄ የማይሆን ምኞት ነው፡፡ የታመመ፣ ወይም ጊዜው የደረሰ እንስሳ ካገኘን እናቀርብልዎታለን፡፡ አለበለዚያ ግን ምንም የምንረዳዎት ነገር የለም፤ እንበል፡፡ ግን አንድ ልብ ይኑረን!” አለች፡፡ የዱር አራዊቱ በጦጣ ሀሳብ ተስማሙ፡፡
እንደተባባሉት ዋና ተናጋሪ መርጠው ለአያ አምበሶ የወሰኑትን ውሳኔ ገለጡ፡፡
አያ አምበሶ፤ በየቀኑ ምን ምን የምግብ ዓይነት መርጠው ይሰጡኝ ይሆን? እያለ በጉጉት ሲጠብቅ የወሰኑትን ሲሰማ፤ ባለበት በድን ሆኖ ቀረ፡፡ በዚያው ህይወቱ አለፈ፡፡
*    *     *
አለቃ ምንዝሩን የሚያጠቃበት፣ ሥርዓቱን ለግል ጥቅሙ ለማዋል የሚሯሯጥበት፣ አልፎ ተርፎም የደጋፊዎቹን ህልውና ሳይቀር የሚያናጋበት ሁኔታ ከፈጠረ ጤና አይኖርም፡፡ ሥርወ - መንግሥቱም የረጋ አይሆንም፡፡ ዛሬ በሚሊዮንና በቢሊዮን ብር የሚቆጠር ፕሮጀክት፣ ህንፃ፣ ፋብሪካ ወዘተ የሚወራበት አገር ነው ያለን፡፡ የህዝቡ ኑሮ ግን ፈቀቅ አላለም፡፡ ምናልባት የህንድ ዓይነት ጥቂቶች ከዝሆን ጥርስ የተሰራ ፎቅ ማማ ላይ ያሉ የናጠጡ ሀብታሞች ከአናት የተቀመጡባት፣ በአንፃሩ ህልቆ መሳፍርት ድሆች የጉስቁልና ህይወት የሚመሩባት አገር እንዳትሆን መስጋታችን አልቀረም፡፡ ማባሪያ የሌለው ምዝበራና ሙስና ጓዳ - ደጁን ሞልቶት፣ በህጋዊ መንገድ ያልተገኘ ብልፅግና ሥር የሰደደበት ሁኔታ እያለ ዕድገት ማምጣት ከባድ ነው፡፡ ሀንቲግተን ዘመናዊነትና ሙስና በሚለው ሀተታው፤ “ሙስና የባለሥልጣናት ጠባይ ሲሆን፤ ከተለመደው ህግ በማፈንገጥ ሥልጣንን ለግል ጥቅም ማዋል ነው … በእርግጥም ሙስና ስኬታማ ፖለቲካዊ ተቋም አለመኖር ምልክት ነው!” ብሏል፡፡
የሲቪል ተቋማት አለመኖር (Civic Society) የዲሞክራሲ መዳከም ምልክት መሆኑን የፖለቲካ ሊቃውንት ይናገራሉ፡፡ ይህን መሰል ተቋማት ብዙ ያስፈልገናል። ለውጥ በመጣ ቁጥር አዳዲስ ሹማምንትን ማየት የተለመደ ነው፡፡ የምናያቸው ሹማምንት ፊት ካየናቸው የተሻሉ እንዲሆኑ እንመኛለን/እንናፍቃለን፡፡ ያንን ካላገኘን “ሣር የምትበላው በቅሎ ሄዳ ልጓም የምትበላው መጣች” የሚለው ተረት ዕውን እንዳይሆን ያሰጋል!! ከዚህ ይሰውረን!

Read 6388 times