Saturday, 20 June 2015 09:46

ዛሚ እና የብሮድካስት ባለሥልጣን እየተወዛገቡ ነው

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(7 votes)

ሬዲዮ ጣቢያው ሊታገድ እንደሚችል ማስጠንቀቂያ ደርሶታል

    በዛሚ 90.7 ሬድዮ በሚተላለፈው የኢትዮፒካሊንክ ፕሮግራም በሚቀርበው “ውስጥ አዋቂ” የተሰኘ ዝግጅት በተደጋጋሚ ስሜ ጠፍቷል ያለው አርቲስት ዳንኤል ተገኝ፤ ለኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን አቤቱታ ማስገባቱን ተከትሎ ዛሚ ሬዲዮ እና ባለስልጣኑ እየተወዛገቡ ነው፡፡ በተለያዩ ፊልሞች እና የቴሌቪዥን ድራማዎች ላይ በመተወን የሚታወቀው አርቲስት ዳንኤል ተገኝ፤ በሬዲዮ ጣቢያው የሚተላለፈው ኢትዮፒካሊንክ ፕሮግራም ከ1 ዓመት ከ8 ወር በፊት ጀምሮ የስም ማጥፋት ዘመቻ እንደከፈተበት ይናገራል፡፡ “ወደ 6 በሚሆኑ ፕሮግራሞቻቸው ያልሆንኩትን ሆነ፣ ያላደረኩትን አደረገ እያሉ ስሜን ሲያብጠለጥሉ ቆይተዋል” የሚለው አርቲስቱ፤ በተደጋጋሚ ጉዳዩን ለብሮድካስት ባለስልጣን ማመልከቱንና ባለስልጣኑም የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ ለአዘጋጆቹ እንደፃፈ ለአዲስ አድማስ ገልጿል፡፡ ጉዳዩን በተመለከተ ከአርቲስቱ ተደጋጋሚ አቤቱታ የቀረበለት ብሮድካስት ባለሥልጣንም ከሁለት ሳምንታት በፊት በፕሮግራሙ “የውስጥ አዋቂ” ዝግጅት ላይ የእግድ ደብዳቤ ማውጣቱን የሚገልፀው አርቲስቱ፤ ጣቢያው እገዳውን ሳይቀበል ለአዘጋጆቹ ሽፋን እየሰጠ እግዱን ተግባራዊ ሳያደርግ ቀርቷል ብሏል፡፡ ለሁለተኛ ጊዜም የብሮድካስት ባለሥልጣን የስራ አመራሮች እና አቤቱታ አቅራቢውን ጨምሮ አርቲስት ዮሐንስ አፈወርቅ፣ አርቲስት በኃይሉ ከፍያለውና ጋዜጠኛ አብርሃም ግዛው እንዲሁም የአርቲስቱ ጠበቃ አቶ መልካሙ ሆነው በጉዳዩ ላይ ተሰብስበው መምከራቸውንና የብሮድካስት ባለሥልጣን አመራሮችም “ከዚህ በኋላ ህግን የማስከበር ጉዳይ የኛ ነው፤ ለኛ ተዉልን” እንዳሏቸው አርቲስቱ ለአዲስ አድማስ አብራርቷል፡፡ ነገር ግን ፕሮግራሙ አሁንም
እየተላለፈ ነው ብሏል፡፡ “ገና የአንተን ስም አጠፋዋለሁ፤ እዚህች ሃገር ላይ ሠርተህ አትኖርም” የሚል ዛቻና ማስፈራሪያ ሠንዝረውብኛል” ያለው አርቲስቱ፤ ጉዳዩ በብሮድካስት በኩል እልባት የማያገኝ ከሆነ ለጠቅላይ
ሚኒስትር ፅ/ቤት አቤቱታውን እንደሚያቀርብ፤ ወደ ፍ/ቤት ቀርቦም ክስ ለመመስረት እየተሰናዳ
መሆኑን ገልጿል፡፡ በጉዳዩ ላይ የፕሮግራሙን አዘጋጆች በስልክ ለማነጋገር ያደረግነው ተደጋጋሚ ሙከራ ባይሳካም የጣቢያው ስራ አስኪያጅ አቶ ዘሪሁን ተሾመ፤ በአርቲስቱ ምክንያት ከብሮድካስት ባለሥልጣን ጋር
የተፈጠረውን ውዝግብ ለመፍታት ከባለስልጣኑ የቦርድ ኮሚቴ ጋር እየተወያዩ መሆኑን ጠቅሰው፤
“ፕሮግራሙን አግዱ፤ አለበለዚያ እርምጃ ይወሰድባችኋል፤ እናግዳችኋለን” የሚል መልዕክት እንደመጣላቸውም ጠቁመዋል፡፡ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ አንድን ፕሮግራም ካላገዳችሁ በሚል ጣቢያውን አግዳለሁ ማለቱ በህግ አግባብ  የማያስኬድ ነው ያሉት አቶ ዘሪሁን፤ አንድን የሚዲያ ተቋም የማገድ ስልጣንም የለውም ብለዋል፡፡ ጣቢያው በአሁን ሰዓት መደበኛ የእለት ተእለት ተግባሩን እያከናወነ መሆኑን አቶ ዘሪሁን ጠቁመው፣ “በሚዲያ ህጉ ተበደልኩ የሚል አካል ጉዳዩን ወደ ፍ/ቤት መውሰድ የሚችልበት የህግ
አግባብ እያለ አርቲስቱ በዚህ መንገድ መሄዱም ተገቢ አይደለም፤ እኛም ይሄን መሰሉን አካሄድ አናስተናግድም” ብለዋል፡፡ “አንድን ፕሮግራም በማያሳምን ምክንያት የምናግድ ከሆነ ተገቢ አይሆንም፤ ፕሮግራሙንም አናግድም” ብለዋል አቶ ዘሪሁን፡፡ ጉዳዩ የሚመለከታቸውን የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን ሃላፊዎችን በስልክ ለማነጋገርም ሆነ በአካል ቢሮአቸው ሄደን ለማግኘት ያደረግነው ተደጋጋሚ ሙከራ ስብሰባ ላይ ናቸው በመባላችን ሳይሳካልን ቀርቷል፡፡

Read 4840 times