Saturday, 06 June 2015 13:58

ኢህአዴግ በምርጫው ማግስት የሚያስፈልጉት ጥንቃቄዎች!

Written by  ዮሃንስ ሰ.
Rate this item
(4 votes)

የአደጋ ምንጮች- የዋጋ ንረት-የሃብት ብክነት-ሙስና-የብር ህትመት-አክራሪነት-ዘረኝነት
                   
       ኢህአዴግ በዘንድሮው ምርጫ አሸንፌያለሁ ብሎ፣ እንዳለፉት አስር አመታት በተመሳሳይ አቅጣጫ መቀጠል የሚችል መስሎ ከታየው ተሞኝቷል። በአገሪቱና በአለም ዙሪያ ብዙ ነገሮች ተቀይረዋል። የዋጋ ንረትን ብቻ አስታውሱ። በ2003 ዓ.ም እና ከዚያም በፊት እንዳደረገው፣ ዛሬ አለቅጥ የብር ኖት እያተመ የዋጋ ንረትን ቢያባብስ...ብላችሁ አስቡት። የከፋ ትርምስ ሳይፈጠር፣ እንደያኔው የምናመልጥ ይመስላችኋል? ኢህአዴግ፣ ከእንግዲህ እጅጉን ካልተጠነቀቀ በቀር፣ ለራሱም ለአገሪቱም መዘዙ ብዙ ነው። በኢኮኖሚ ቀውስ ሰበብ በተለኮሱ ችግሮች አማካኝነት፣ ስንቱ አገር ወደ ሲኦልነት እየተቀየረ እንደሆነ’ኮ እያየን ነው - የዘረኝነት ግጭትና የጭፍን እምነት አክራሪነት እየታከለበት። እነዚህ ነገሮች እርስበርስ የተሳሰሩ መሆናቸውን በማሳየት፣ የጥንቃቄ ሃሳቦችን ለማቅረብ እሞክራለሁ።
ከኢኮኖሚ እንነሳ። እንደ ኤሌክትሪክ ማመንጫ ግድብ፣ የአስፋልት መንገድ፣ እንዲሁም የጂቡቲ የባቡር መስመር ግንባታዎች ውለው አድረው ጠቃሚ አገልግሎት መስጠታቸው የማይቀር ቢሆንም፤ ባለፉት አመታት ለግዙፍ ፕሮጀክቶች በመደበው ከፍተኛ የገንዘብ መጠን፣ በርካታ የሃብት ብክነትንና ስራ አጥነትን፣ የዋጋ ንረትንና የሙስና አደጋን እንዳባባሰ ኢህአዴግ መረዳት አለበት። የነፋስ ተርባይኖች ተከላንና የስኳር ፕሮጀክቶችን በምሳሌነት መጥቀስ ይቻላል።
በምርጫው ዋዜማ የተመረቀውን ጨምሮ፣ እስከዛሬ ለኤሌክትሪክ ማመንጫ የነፋስ ተርባይኖች ከፈሰሰው 15 ቢሊዮን ብር ውስጥ፣ ቢያንስ ቢያንስ 10 ቢሊዮን ብር ያህሉ በከንቱ የባከነ ነው። ምክንያቱም፣ ከእነዚህ የአዳማና የመቀሌ ጣቢያዎች የሚመነጨውን ኤሌክትሪክ፣ በአማካይ በሦስት ቢሊዮን ብር ወጪ የሃይል ማመንጫ ግድብ በመገንባት መተካት ይቻላል። የግንባታ ወጪው እጅግ በዛ ቢባል አምስት ቢሊዮን ብር አይደርስም። ከ10 ቢሊዮን ብር በላይ ሃብት በከንቱ ባክኗል ማለት ነው።
ይሄ፣ አንዳንዶች እንደሚያደርጉት ያለ በቂ መረጃ፣ ኢህአዴግንና መንግስትን ለማጥላላት ወይም ለማሳጣት ተብሎ የሚቀርብ ትችት አይደለም። ለነገሩ፣ ይህንን ትችት የሚሰነዝር ተቃዋሚ ፓርቲ ሰምቼ አላውቅም። በዚያ ላይ፣ ራሱ የኤሌክትሪክ ሃይል ኮርፖሬሽን ሊክደው የማይችል ሃቅ ነው። ኮርፖሬሽኑ ለዚህ ትችት ምላሽ ሲሰጥ፣ መረጃዎቹን አላስተባበለም። የነፋስ ተርባይኖች አነስተኛ የኤሌክትሪክ መጠን ለማመንጨት ከፍተኛ ወጪን እንደሚጠይቁ ኮርፖሬሽኑ አምኖ፣ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እያደገ ስለሆነ ወጪውን የመሸፈን አቅም እንዳላት ያረጋግጣል ሲል ነው ምላሽ የሰጠው።
አስገራሚው ነገር፣ እስካሁን በከንቱ የባከነው ሃብት ያነሰ ይመስል፣ “አይሻ” ተብሎ ለተሰየመ ሌላ የነፋስ ተርባይን ፕሮጀክት ከ20 ቢሊዮን ብር በላይ ተጨማሪ ገንዘብ ለመመደብ ታቅዷል። ይህንንም ፕሮጀክት፣ አምስት ቢሊዮን ብር በማይደርስ ወጪ፣ በሃይል ማመንጫ ግድብ መተካት ይቻላል። 15 ቢሊዮን ብር ያህሉ በከንቱ እንደሚባክን አስቡት። ይሄ እንዴት የጤንነት ሊሆን ይችላል? ለማን ነው ይሄን ሁሉ ሃብት በከንቱ የምንገብረው? ለአካባቢ ጥበቃ ቡድኖች?
እንደሚታወቀው፣ የግልገል ጊቤ 3 የሃይል ማመንጫ ግድብ ግንባታ እስከ ዛሬ የተጓተተው በአካባቢ ጥበቃ ቡድኖች ተፅእኖ ነው። ከአውሮፓና ከአፍሪካ ልማት ባንክ ብድር እንዲከለከል ባካሄዱት አለማቀፍ ዘመቻ፣ የግድቡ ግንባታ ለአመታት ተጓቷል። “ግድቡ፣ ነባር አኗኗርንና የአካባቢ ገፅታን ይቀይራል” በሚል ግንባታውን የሚቃወሙት የአካባቢ ጥበቃ ቡድኖች፣ አካባቢያችንን ከመንካትና ግንባታ ከማካሄድ ታቅበን፣ ነባር የድህነት አኗኗራችን ታቅፈን እንድንኖር ነው የሚፈልጉት። ጠ/ሚ መለስ ዜናዊ፣ “የአካባቢ ጥበቃ” ቡድኖችን፣ “የድህነት ጠበቃ” በማለት የሰየሟቸው ወደው አይደለም። እና እነዚህ የአካባቢ ጥበቃ ቡድኖች እንዲደሰቱ ብለን፣ እስካሁን በነፋስ ተርባይን ስም የባከነው 10 ቢሊዮን ብር አንሶ፣ በ“አይሻ ፕሮጀክት” እንደገና 15 ቢሊዮን ብር በከንቱ ማባከን አለብን? እነሱ ጣዖት ናቸው እንዴ የምንገብርላቸው? ይታያችሁ--ኢትዮጵያውያን የሕዳሴ ግድብን በመደገፍ ባለፉት አራት አመታት ለቦንድ ግዢ ያበረከቱት ሃብት ሁሉ፣ ለነፋስ ቢበተንና በከንቱ ቢጠፋ አስቡት። ግን እሱ ይሻል ነበር። 7 ቢሊዮን ብር ገደማ ብቻ ነዋ። ኧረ፣ የድሃ አገር ሃብትን በከንቱ ማባከን ይብቃ።
የእስካሁኑ ብክነትም እንዲሁ መረሳት አለበት ማለቴ አይደለም። የጊዜ ጉዳይ እንጂ፣ በዚህ ከፍተኛ ብክነት ውስጥ የተሳተፉ ሃላፊዎች ተጠያቂ መሆናቸው የማይቀር ነው። ከእንግዲህ ግን፣ በእቅድ ደረጃ ላይ ያሉትን ፕሮጀክቶች ጨምሮ፣ ተጨማሪ ብክነት መፈፀም በጭራሽ ይቅር የማይባል ትልቅ ጥፋት ይሆናል። ኢትዮጵያ፣ በድህነት የሚሰቃዩና ከድህነት ለመውጣት የሚፍጨረጨሩ ሚሊዮኖች የሚኖሩባት፣ ገና በቋፍ ላይ ያለች አገር ናት። “ድህነት ዋና ጠላታችን ነው፤ የአገሪቱን ህልውና የሚያጠፋ ነው” በማለት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተናገሩት ከምር አይደለም እንዴ? “ኢትዮጵያ በድህነት ለብዙ ዘመናት ዘልቃለች” የሚል መከራከሪያ እንደማያዋጣ ሲገልፁ፤ ሰዎች ከድህነት ጋር ተኮራምተው የሚቀመጡበት ዘመን እንዳበቃና በዛሬው ዘመን ድህነት የፀናባቸው አገራት ይበታተናሉ፣ ይጠፋፋሉ ብለው ነበር። ኢትዮጵያ ውስጥ ስለ ድህነት ስናወራ፤ በላያችን ላይ እሳት እየወረደብን እንደሆነ መቁጠር እንደሚኖርብንም ጭምር ነው የተናገሩት። ታዲያ በዚሁ እሳት ስር ያለ ድሃ አገር ውስጥ፣  የ10 ቢሊዮን ብሮች ሃብትን በከንቱ ማባከን፣ በራስ ላይ እንደመፍረድ አይቆጠርም?
የስኳር ኮርፖሬሽን በየአመቱ በአማካይ 10 ቢሊዮን ብር እንዲሁም በፓርላማ የቢሊዮን ብሮች በጀት እየተመደበላቸው ለአመታት የተጓተቱ የስኳር ፕሮጀክቶችንም መመልከት ይቻላል። የተንዳሆ ፕሮጀክትን ጨምሮ አንዳንዶቹ ለአስር አመታት የተጓተቱ መሆናቸው ሲታሰብ፣ ለወለድ ክፍያ ብቻ የቢሊዮን ብሮች ብክነት እንደሚያስከትል ግልፅ ነው። ይህም ብቻ አይደለም። የተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ በጊዜው ባለመጠናቀቁ በአንድ አመት ብቻ የመቶ ሚሊዮን ብር ስኳር አገዳ በከንቱ እንዲቃጠል ተደርጓል። ከዚያ ወዲህ የአምናንና የዘንድሮንም አስቡት። በዚያ ላይ፣ የፌደራል ኦዲተር መስሪያ ቤት ባደረገው ምርመራ፣ በበርካታ ቢሊዮን ብሮች ተገዝተው የሚመጡ የግንባታ እቃዎች ለምን አገልግሎት እንደዋሉ ማወቅ እንደማይቻል ገልጿል። በሌላ አነጋገር፣ ለሙስና የተመቸ ሜዳ ሆኗል። በሃብት ብክነት ላይ ሙስና ይጨመርበታል ማለት ነው።
ይህን ትችት አንብቦ ከተጨባጭ መረጃዎች ጋር እያመሳከረ ከመመዘን ይልቅ፣ “ኢህአዴግ ተሰደበብኝ”፣ “መንግስት ተነካብኝ” ብሎ የአካኪ ዘራፍ ፉከራ ለማዥጎድጎድ የሚነሳ ጭፍን ደጋፊ እንደሚኖር አያጠራጥርም። “መረጃ ገደል ይግባ፤ ኢህአዴግ የሚነግረኝን ብቻ ነው የማዳምጠው” የሚል ከሆነ ምን ይደረጋል? ምናልባት ራሱ ኢህአዴግ፣ “የዲሞክራሲ ግንባታ በኢትዮጵያ” እንዲሁም “የኢንዱስትሪ ልማት ስትራቴጂ” በሚል ያሳተማቸውን መፃህፍት ገለጥ ገለጥ አድርጎ ለማንበብ ቢሞክርስ? እነዚሁ መፃህፍት ውስጥ፣ ስለ ሃብት ብክነትና ስለ ሙስና የተፃፉ ነገሮች አሉ።
ነገሩ እንዲህ ነው። መንግስት የቢዝነስ ስራ ውስጥ ሲገባ፣ የሃብት ብክነት እንደሚፈጠር ራሱ ኢህአዴግ አይክደውም። ደርግ የአገሪቱን ኢኮኖሚ ያንኮታኮተው በምን ምክንያት ሆነና? ኢኮኖሚውን በሙሉ ካልተቆጣጠርኩ ብሎ የቢዝነስ ስራ ውስጥ በመግባቱና ኮርፖሬሽኖችን በማቋቋሙ ነው። ኢህአዴግ፣ የሃብት ብክነትን መከላከልና ኢኮኖሚን ማሳደግ የሚቻለው በግል ኢንቨስትመንት እንደሆነ በማተት ባሳተማቸው መፃህፍት፣ “የግል ኢንቨስትመንት የኢኮኖሚ እድገት ዋና ሞተር ነው” ሲል ይገልፃል። ይህም ብቻ አይደለም። መንግስት የቢዝነስ ስራ ውስጥ ሲገባ፣ ከሃብት ብክነት በተጨማሪ ሙስና እንደሚስፋፋ የሚተነትኑ እነዚሁ የኢህአዴግ መፃህፍት፣ “ሙስና መንግስታዊ ስርዓቱን የሚያጠፋ አደጋ ነው” በማለት አሳሳቢነቱን ይዘረዝራሉ።
ጭፍን ደጋፊዎች ይህንን ሲያነቡ ምን እንደሚሉ እንጃ። ያነበቡት ነገር በተግባር ምን እንደሚመስል የሚያሳይ ተጨባጭ መረጃ ሲቀርብላቸውስ? ኢህአዴግ በፅሁፍ የገለፃቸው ጥፋቶችና አደጋዎች ናቸው በተግባር የተከሰቱት። መንግስት ባለፉት አስር አመታት በቢዝነስ ስራዎች ላይ ለመንሰራፋት ያደረጋቸው ዘመቻዎች፣ የአስር ቢሊዮን ብሮች ሃብትን ለብክነት ከመዳረግ አልፎ የሙስና አደጋን እንዳባባሰ ታይቷል።
ምን ለማለት ፈልጌ ነው? በቃ፣ በእውነታ ላይ የተመሰረተ እንጂ ጭፍን ደጋፊነት አያዋጣም። ነገርዬው፣ የህልውና ጉዳይ ነዋ። በዚያው ልክ፣ በእውነታ ላይ የተመሰረተ ተቃዋሚነት እንጂ ጭፍን ተቃዋሚነትም አያዋጣም። “እገሌ ወረዳ፣ እንቶኔ ዞን መንገድ አልተገነባም” እያለ ቀኑን ሙሉ ኢህዴግን ሲያማርር የዋለ ጭፍን ተቃዋሚ፣ አመሻሽ ላይ “የመንገድ ግንባታ ተመረቀ” የሚል ዜና ሲሰማ “ለቁጥጥርና ለአገዛዝ እንዲመቸው መንገድ ይገነባል፤ ቅኝ ገዢዎችም ዋና ስራቸው መንገድ መገንባት ነበር” ብሎ ያንቋሽሻል - የስካር ውዥንብር በሚመስል ስሜት።
ግን ምን ዋጋ አለው? ጭፍን ድጋፍና ጭፍን ተቃውሞ፣ ማንንም አይጠቅምም - ተያይዞ ለመጥፋት ካልሆነ በቀር። ደግሞስ፣ ከእውነታ ጋር ፀብ ገጥሞ ምን ትርፍ ይገኛል? የተገነባው መንገድ፣ በጭፍን ተቃውሞ ምክንያት፣ ምንነቱ ተቀይሮ ዘንዶ ወይም እባብ አይሆንም። በ10 ቢሊዮን ብሮች የሚቆጠረው የሃብት ብክነትና አስፈሪው የሙስና ደመናስ? በጭፍን ድጋፍና በጭብጨባ ብዛት አገሩ ቢጥለቀለቅ እንኳ፣ እስከዛሬ የተፈፀመው ሙስና ጨርሶ እንዳልተፈፀመ ተደርጎ ሊቆጠር አይችልም፤ እስከ ዛሬ የባከነው ሃብትም ተመልሶ አይመጣም።
ይልቅስ፣ በጭፍን የድጋፍ ስሜት መነዳት ማለት፣ የብክነትና የሙስና ጥፋቶች ይበልጥ እንዲባባሱ መንገድ እንደመጥረግ ነው የሚቆጠረው። መዘዙ ደግሞ ብዙ ከመሆኑ የተነሳም፣ “ለአገሪቱ የሕልውና አደጋ ነው” ቢባልም ማጋነን አይደለም። የሃብት ብክነትና ሙስና ሲባባስ፣ ከዚሁ ጋር አብረው የሚመጡ የጥፋት አጀቦች በርካታ ናቸውና።
ባለፉት አስር አመታት እንዳየነው፣ በአገሪቱ ኢኮኖሚ ውስጥ የመንግስት ቁጥጥርና ድርሻ እያበጠ የሃብት ብክነት ሲስፋፋ፣ በተቃራኒው የዜጎች የኢኮኖሚ አቅም እየደከመ፣ የግል ኢንቨስትመንት እየጠበበ ይመጣል። የስራ እድል ይቀንሳል። አንድ በሉ። በተለይ በተለይ፣ ዩኒቨርስቲና የቴክኒክ ተቋማት ውስጥ የተማሩ ወጣት ተመራቂዎች፣ የስራ እድል ማግኘት ሲያቅታቸው፣ አደጋው ቀላል አይደለም።
ሁለተኛ፣ መንግስት የሃብት ብክነቱን ለመሸፈን፣ ቅጥ ወደሌለው የገንዘብ ሕትመት እየገባ፣ ኢኮኖሚውንና የዜጎችን ኑሮ ማናጋቱ የማይቀር ነው። ከአዲሱ ሚሌኒየም ወዲህ የተከሰቱ ከፍተኛ የዋጋ ንረቶችን ማስታወስ ትችላላችሁ። በተለይ በ2003 ዓ.ም በስድስት ወራት ውስጥ በርካታ ቢሊዮን ብሮች ታትመው ስለመጡ፣ በአገሪቱ ውስጥ የሚንቀሳቀሰው የብር መጠን በ50% እንደጨመረ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለፓርላማ ባቀረቡት ሪፖርት ገልፀዋል - የዋጋ ንረቱ የተፈጠረው በመንግስት ምክንያት እንደሆነ በማመን።
በእርግጥ፣ መንግስት አብዛኛውን ጊዜ ጥፋቱን እንዲህ በግልፅ አያምንም። የዋጋ ንረት በተከሰተ ቁጥር፣ ጥፋቱን በቢዝነስ ሰዎች ላይ በማላከክ ነው የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ የሚያጧጥፈው። ደግሞም ይሳካለታል። ቢዝነስን እንደ ቅዱስ ስራ የማይቆጥርና የማያከብር ኋላቀር ባህል ውስጥ፣ አብዛኛው ሰው የመንግስት ፕሮፓጋንዳ በመደገፍና የቢዝነስ ሰዎችን በማውገዝ፣ የመንግስት ቁጥጥር እንዲስፋፋ ይጎተጉታል። አሳዛኙ ነገር፣ በሽታን ለመፈወስ ያንኑን በሽታ ደጋግሞ መጨመር መፍትሄ አይሆንም። ውጤቱም፣ ያው... የባሰ የምርት እጥረት፣ የገበያ ግርግርና የኢኮኖሚ ምስቅልቅል ነው። “የእድገት ዋና ሞተር” የተባለውን የግል ቢዝነስ ከስር ከስሩ እንደመናድ ቁጠሩት - ወደ ሶሻሊዝም ቅኝት የሚንፏቀቅ የቅይጥ ኢኮኖሚ ቀውስ በማለት ልንሰይመው እንችላለን። ይህም ብቻ አይደለም።
የሃብት ብክነትና ሙስና፣ የስራ እጦትና የኑሮ ውድነት ሲደማመሩ (በሌላ አነጋገር በሶሻሊዝም ቅኝት የአገር ኢኮኖሚ ሲቃወስ)፤ ምስቅልቅሉን የሚያባብሱ ሌሎች ሁለት የኋላቀርነት ቅኝቶች እየጎሉ ይመጣሉ። የኋላቀር ባህል አንዱ መለያ ባህርይ፣ ሰዎችን በትውልድ ሃረግ የሚፈርጅና የግል ማንነትን የሚያዋርድ የብሔረተኝነት ወይም የጎሰኝነት ቅኝት ነው። ነባር ቅኝት ቢሆንም፣ የቅኝት ጩኸት እየጨመረና እየበረከተ የሚመጣው መቼ እንደሆነ አስተውሉ። ሌላኛው የኋላቀር ባህል መለያ ባህርይ፣ የሰውን አእምሮና ሕልውና የሚያዋርድ የጭፍን እምነት ቅኝት ነው - የሃይማኖት አክራሪነት። የዚህኛው ነባር ቅኝት ጩኸት የሚጨምረውና የሚበረክተውስ መቼ ነው?
ባለፉት ስድስት አመታት የዋጋ ንረት የተባባሰባቸው ጊዜያትን መለስ ብላችሁ አስታውሱ። የቢዝነስ ጥላቻን ከሚያባብስ የሶሻሊዝም ሽታ በተጨማሪ፣ የየአካባቢውና የአየሩ ጠረን ሁሉ ይቀየራል፤ በዘረኝነት እና በጭፍን እምነት የታወደ ይመስላችኋል። በሶሻሊዝም ቅኝት የቢዝነስ ሰዎችን ከሚያወግዝ መዝሙር ጋር፣ የቀንና የማታው ዜማ ሁሉ፣ በዘረኝነትና በጭፍን እምነት ቅኝት ይታፈናል። በደርዘን የሚቆጠሩ የአፍሪካና የአረብ አገራት፣ መውጪያ መግቢያ ወደሚያሳጣ ትርምስና እልቂት እየገቡ ያሉት በእነዚሁ ሦስት የጥፋት ቅኝቶች ሳቢያ ነው።
ይሄ... እኛ ላይ ሊደርስ የማይችል የሩቅ ማዕበል ወይም ብልጭ ብሎ የሚጠፋ ጊዜያዊ ሽውታ እንዳይመስላችሁ። ሌሎቹ አገራትም እንደዚህ ነበር የሚያስቡት - እስኪገቡበት ድረስ። ነገርዬው፣ የሩቅ ማዕበል ሳይሆን፣ እኛው ላይ እያንዣበበ የሚገኝ የእሳት ማዕበል ነው። በሰሞነኛ ግርግር የሚረግብ ጊዜያዊ ሽውታ ሳይሆን፣ ማብቂያው የማይታወቅ ትርምስ ነው።
በአጭሩ፣ ነገርዬው የመኖርና ያለመኖር ጥያቄ ነው። ይህን በመገንዘብ፣ (1) ለእውነታ፣ ለአእምሮና ለሃሳብ ነፃነት ክብር የሚሰጥ ትክክለኛ የሳይንስ አስተሳሰብ እንዲዳብር፤ (2) ለብልፅግና፣ ለምርታማነትና ለንብረት ባለቤትነት ክብር የሚሰጥ ተገቢ የነፃ ገበያ ስርዓት እንዲስፋፋ፤ እንዲሁም (3) ለሕይወት እርካታ፣ በግል ብቃት አርአያ ለሚሆኑን ጀግኖች እና ለግል ማንነት ክብር የሚሰጥ ቅዱስ የስልጣኔ ባህል እንዲሰፍን መጣጣር የእያንዳንዱ ሰው ሃላፊነት ነው። ማንም ቅን ሰው ሊያደርገው የሚገባ ነው - ምሁራንና ተማሪዎች፣ የቢዝነስ ሰዎችና ሰራተኞች፣ አርቲስቶችና አትሌቶች ... ፖለቲከኞችና ፓርቲዎች።
ተቃዋሚ ወይም ደጋፊ የመሆን ጉዳይ አይደለም። ነገሩ ለሁላችንም የህልውና ጉዳይ ነውና። ነገር ግን፣ ስልጣን የያዘው ፓርቲና ባለስልጣናቱ፣ ከሌሎቻችን የከበደ ሃላፊነት አለባቸው። ለሚፈፅሙት ጥፋትም፣ ተጠያቂነታቸው የዚያኑ ያህል ከባድ ነው። እናም፣ ኢህአዴግ የአገሬውን እና በአለም ዙሪያ ያለውን ሁኔታ በማገናዘብ፣ ወደ ተሻለ አቅጣጫ ለመገስገስ መትጋት እንዲሁም ካንዣበበው አደጋ ለማምለጥ መፍጠን ይኖርበታል። የጥፋት ጎዳናን ለማስወገድ እጅጉን መጠንቀቅ ይገባዋል። ለምሳሌ፣ በ10 ቢሊዮን ብሮች ከሚቆጠር የሃብት ብክነትና ከተመሳሳይ የጥፋት ጨዋታዎች እርም ብሎ መራቅ ይኖርበታል። አለበለዚያ፣ ራሱንም፣ አገሪቱንም ለከባድ አደጋ ያጋልጣል።

Read 1928 times