Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 28 January 2012 11:59

“ጀግናው” ኢቴቪ መተጋተግ ቢቀርበትስ?

Written by 
Rate this item
(0 votes)
  • “ከኤርትራ ጋር በአዝማሪ እንዳንጣላ”
  • ኢህአዴግ “ሙያ በልብ ነው” ቢል ይሻለዋል!

በአሜሪካ የሚገኘው ናሳ የተባለው የሳይንስ ምርምር ተቋም አባላት ትልቅ ፌሽታ ላይ ናቸው፡፡ የፌሽታው ምክንያት ምን መሰላችሁ? ትልቅ ሳይንሳዊ ስኬት ተቀዳጅተናል ብለው ነው የሚጠጡትና የሚጨፍሩት፡፡ ጠርሙስ ሻምፓኝ እየተከፈተ ሳለ ግን የሳይንቲስቶቹ ሃላፊ ሞባይል ድንገት ይጮሃል፡፡ ሃላፊው ቁጥሩን ያይና በደስታ ፊቱ በርቶ ሁሉም ፀጥ እንዲሉ ይነግራቸዋል፡፡ “ከአሜሪካ ፕሬዚዳንት ቢሮ ነው የተደወለልኝ” አለ ሃላፊው በስሜት ተጥለቅልቆ፡፡ ከዚያም በትዕዛዝ የተፈበረከችለትን ቀይ ሞባይሉን ጆሮው ላይ አድርጐ ፕሬዚዳንቱን ማነጋገር ጀመረ፡፡

“ሚስተር ፕሬዚዳንት” አለ ሃላፊው ሁለመናው ጥርስ በጥርስ ሆኖ፡፡ “ቢሊዮን ዶላሮችን ከፈጀ የ15 ዓመታት እልህ አስጨራሽ ምርምር በኋላ ማርስ ላይ ማሰብ የሚችል ፍጡር አግኝተናል”ሃላፊው ከዚህ በኋላ ለሰከንድ ያህል ምንም አልተናገረም፡፡ ቀስ በቀስም ፊቱ ላይ የነበረው ፈገግታ እየከሰመ መጣ፡፡ በመጨረሻም ኮሶ ያጠጡት ይመስል ፊቱን አጨፍግጐ መናገር ጀመረ - ለፕሬዚዳንቱ፡፡  “የማይቻል ነገር እኮ ነው…ኧረ አንችልም…ፈጽሞ አይቻልም ስልዎ…እሺ በቃ እንሞክራለን ሚስተር ፕሬዚዳንት”

ስልኩን ዘጋና አፍጠው በጉጉት ወደሚጠባበቁት ባልደረቦቹ እያየ፣ ፕሬዚዳንቱ ያዘዙትን ነገራቸው፡፡ “ፕሬዚዳንቱ በማርስ ላይ ለተቀዳጀነው ሳይንሳዊ ድል እንኳን ደስ አላችሁ …” ሳይንቲስቶቹ አላስጨረሱትም፡፡ በሁካታና በፉጨት የምርምር ክፍሉን ቀወጡት፡፡ የቡድኑ ሃላፊ በጭብጨባ እንደምንም ዝም አሰኛቸውና፤

“ጓደኞቼ፤ ፕሬዚዳንቱ ሌላም ያሉት ነገር አለ”

የምርምር ቡድኑ አባላት ፕሬዚዳንቱ አሉት የተባለውን ለመስማት አሰፍስፈዋል፡፡

“ፕሬዚዳንቱ በማርስ ላይ የተገኘውን ሳይንሳዊ ስኬት በአሜሪካ ምክር ቤት (ኮንግረስ) እንድትደግሙልኝ እፈልጋለሁ” ብለዋል፡፡

ከመቅጽበት ክፍሉ በተቃውሞ ተናወጠ፡፡

“የማይሆነውን! እንኳን በ15 ዓመት በዕድሜ ልክ ምርምርም አይገኝም” አለ - አንዱ ሳይንቲስት፡፡

ሌላኛው ሳይንቲስት ሻምፓኙን ጐንጨት ካደረገ በኋላ፤ “ኮንግረስ ውስጥ ማሰብ የሚችል ፍጡር?  ፈጽሞ አይሞከርም!” አለ፤ ተስፋ በሚያስቆርጥ ቅላፄ፡፡

የናሳ የምርምር ቡድን ሃላፊ ጉሮሮውን ጠራርገና፤

“እንግዲህ ፕሬዚዳንቱ ውለዱ ብለዋል፤ ለዛሬ ግን ፌሽታችንን እንቀጥል” አለ፡፡ ከዚያም ለጊዜውም ቢሆን ሁሉም ወደ ፌሽታው ተመለሰ፡፡

እኔና እናንተም እንግዲህ ለጊዜውም ቢሆን የአሜሪካን ም/ቤት (ኮንግረስ) ትተን ወደ አራት ኪሎው ማዘዣ ጣቢያችን እንመለስ፡፡ አራት ኪሎን ስጠራ ግር አላችሁ እንዴ? ቤተመንግስቱን ማለቴ እኮ አይደለም - ፓርላማውን ነው፡፡ እኔ የምለው ፓርላማውን ስታስቡ ቀድሞ ወደ አዕምሮአችሁ ከች የሚለው ምንድን ነው? (ጥያቄው ተቃዋሚዎችንና ደጋፊዎቻቸውን አይመለከትም)

ፓርላማ ስል አንድ ነገር ትዝ አለኝ፡፡ ባለፈው ሰሞን “የሁለት ምርጫዎች ወግ” የሚለውን “ዝነኛ” መጽሐፍ የፃፉት የቀድሞው የማስታወቂያ ሚኒስትር፣ ያሁኑ የኮሙኒኬሽን ጽ/ቤት ሚ/ር አቶ በረከት ስምኦን በ ”Meet Etv” ላይ በእንግድነት ቀርበው ነበር፡፡ (በገዛ ቤታቸው የምን እንግድነት ነው አላችሁ እንዴ?)

ስህተቱ ከእኔ ነው፡፡ በእንግድነት አልነበረም የቀረቡት፡፡ በኢቴቪ መስኮት ብቅ ያሉት ለቃለመጠይቅ ነበር - በ”ሁለት ምርጫዎች ወግ” ዙሪያ፡፡

የፕሮግራሙ አዘጋጅና አቅራቢ ተፈራ ገዳሙ ከሰነዘራቸው ጥያቄዎች ውስጥ ትኩረቴን የሳበው “ፓርላማው በኢህአዴግ አባላት መሞላቱ ከብዝህነት (pluralism) አኳያ ተጽእኖ አልፈጠረም ወይ” የሚለው ነበር፡፡

ልብ በሉ ጥያቄውን ቃል በቃል አላሰፈርኩትም፤ መንፈሱን ነው (ጥያቄ መንፈስ አለው እንዴ?)

ተፈራ ገዳሙ ትንሽ ደፈር ቢል ኖሮ ጥያቄው እንዲህ ሊሆን ይችል ነበር፡፡ “የመድብለ ፓርቲ ሥርዓት እንከተላለን ትላላችሁ፤ ፓርላማው ውስጥ ግን ተቃዋሚዎች የሉም፡፡ እንዴት ነው ነገሩ?” (ሙግት መሰለ አይደል?) የሆኖ ሆኖ ተጠያቂው ጠያቂው የፈለገው ሳይገባቸው አልቀረም፡፡ ኧረ በደንብ ገብቷቸዋል፡፡ እናም ፍርጥርጥ አድርገው መለሱት፡፡

አቶ በረከት እንዳሉት ብዝህነት ማለት የተቃዋሚ ፓርቲዎች መኖር ሳይሆን የአገሪቱን ህዝቦች የሚወክሉ አባላት በፓርላማው ውስጥ መኖር ነው፡፡ እነሱ ደግሞ በም/ቤት ውስጥ አሉ፡፡ (ያልተጠበቀ መልስ ማለት ይሄ ነው!)

እርግጥ ነው በፓርላማው ብሔር ብሔረሰቦች ተወክለዋል፡፡ ግን ሃሳባቸው አንድ ነው - በኢህአዴግ የተቃኘ፡፡ ከኢህአዴግ የተለየ ሃሳብስ የት ነው የሚስተናገደው? እኔ እሳቸውን ብሆን ግን እንዲህ እል ነበር፡፡ “ተቃዋሚዎች ከፓርላማ የወጡት እኮ በምርጫ ተዘርረው ነው!” (አይሻልም?) እኔ የምለው ግን ኢህአዴግ ስንት ዓመት ሙሉ “ጠንካራ ተቃዋሚ ፓርቲ እፈልጋለሁ” ሲለን የነበረው “ሲፎግረን” ነው ማለት ነው?  መቼም እኛንም እንደ ዶ/ር ነጋሶ ከሸወደን በጣም እንታዘበዋለን፡፡ (በአብዮታዊ ዲሞክራሲ አጠቃቀስኩ ብሎ “ነጭ ካፒታሊዝም” እከተላለሁ ብሏቸው ነው አይደል?)

ሰሞኑን ኢህአዴግ ከመሬት ሊዝ አዋጁ ጋር በተያያዘ ከነዋሪዎች ጋር ባደረገው ውይይት አንድ ቅሬታ ተሰንዝሮበት እንደነበር ሰምቻለሁ፡፡ አዋጅ ከወጣ በኋላ ህዝብን ለውይይት መጥራት ስህተት ነው የሚል፡፡ “ስማርቱ” ኢህአዴግም ስህተቴን አምኛለሁ ብሎ በአጭሩ ተገላገለ፡፡ በዚህ የቀኑ ወገኖች ምን አሉ መሰላችሁ? “ኢህአዴግ ስህተቱን ያምናል እንጂ አያርምም” እኔ ደግሞ ምናልባት ያመነ ይድናል ሲባል ሰምቶ ይሆናል አልኩኝ፡፡ (ቅን ግምት ነው አይደል?)

እኔ የምለው በኢቴቪ ላይ የሚቀርበውን መተጋተግ ትከታተላላችሁ? የቴሌቪዥን ዋና ሥራው እኮ ለውጭ መንግስታት ምላሽ መስጠት የሆነ ነው የሚመስላችሁ፡፡

በመሬት መቀራመት (Land grabbing) ዙሪያ፣ ስለታሰሩት የስውዲን ጋዜጠኞች፣ ስለነፃ ፕሬስ ጥሰት፣ የአገራችንን መጥፎ ገጽታ እየመረጡ ስለሚዘግቡ ዓለማቀፍ ሚዲያዎች፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰትን በተመለከተ ሪፖርት የሚያደርጉ ተቋማት፣ ወዘተ ለሁሉም ምላሽ ይሰጣል - “ጀግናው” ኢቴቪ፡፡ ያውም በዘለፋና በፍረጃ የታጀበ የማያዳግም ምላሽ፡፡ እኔ ግን መተጋተግ ብየዋለሁ፡፡ አንዳንድ የኢህአዴግ ካድሬዎች ይሄን መተጋተግ የአገሪቱን በጐ ገጽታ ለመገንባት ነው ሲሉ ሰምቼ ግራ ግብት አለኝ፡፡ በመተጋተግ ገፅታ ይገነባል እንዴ? ሌላው የገረመኝ ደግሞ ኢህአዴግ እኛን (ህዝቦቹን) ኪራይ ሰብሳቢ፣ ፀረ ልማት፣ ፀረ ሰላም፣ ወዘተ እያለ እንደሚፈርጀን የውጭ መንግስታትንና ተቋማትንም እንዲሁ ለመፈረጅ መዳዳቱ ነው፡፡ (ጀምሮታል እኮ!)

እስቲ የመሬት ወረራ ወይም መቀራመት (Land grabbing) ከሚለው እንጀምር፡፡ ኢህአዴግ የ5 ዓመቱን የዕቅድና ትራንስፎርሜሽን ዕድገት ተግባራዊ ለማድረግ ሲል ለውጭ ኢንቨስተሮች ሰፋፊ የእርሻ መሬቶችን በሊዝ እየሰጠ ይገኛል፡፡ (“አበጀሁ” ያለችው ዘፋኝ ማን ነበረች?) እስካሁን እንኳ ለህንድ፣ ለፓኪስታን፣ ለሳኡዲ ወዘተ ባለሀብቶች መስጠቱን (በስጦታ ግን አይደለም በሊዝ ነው) መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ይሄ ታዲያ ምን ክፋት አለው? ምንም! ችግሩ ግን ምን መሰላችሁ? ክፋት አለው የሚሉ ፀረ-ልማቶች ተከስተዋል፡፡ ከእነዚህ ወገኖች መካከል አንዳንድ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮችና የምዕራብ መንግስታት ይገኙበታል፡፡ እነዚህ ወገኖች የአገር ተወላጆችን ከገዛ መሬታቸው የሚያፈናቅል የመሬት ወረራ ነው ሲሉት ኢህአዴግ በበኩሉ “ልማት ነው” ብሎታል፡፡ ምኑን አላችሁኝ እንዴ? የእርሻ መሬቶችን ለኢንቨስተሮች በሊዝ መስጠትን ነዋ! ይሄን በተመለከተ እኔ ፍርድ ለመስጠት አልቸኮልኩም፡፡ ዓላማዬ አይደለማ! (ደግሞስ ምን አገባኝ!) በዚህ የተነሳ ግን መተጋተግ ያስፈልጋል እንዴ?

በነገራችን ላይ የመሬት ወረራ እየተፈፀመ ያለው በውጭ ባለሀብቶች ሳይሆን በአንዳንድ የኢህአዴግ “ኪራይ ሰብሳቢ” ባለስልጣናት ይመስለኛል፡፡ እንዴ… ሥልጣናቸውን ከለላ አድርገው እኮ መሬቱን ጨፈጨፉት (የመረጃ ምንጩ ኢህአዴግ ነው)

እዚሁ ጋዜጣ ላይ እንዳነበብኩትም ኢህአዴግ የመልካም አስተዳደር (good governance) ሠራዊት ይሆኑኛል ብሎ የሾማቸው አንዳንድ ከንቲባዎችና የከተማ አስተዳደሮች (የክልል ፕሬዚዳንቶችም አይጠፉም) የሙስና ሰራዊት ሆነው ወህኒ ቤት ተልከዋል! (ለፍቶ መና!)

እነዚህ የመተጋተግ ፕሮግራም በኢቴቪ የሚያቀርቡትም እኮ የልማታዊ ጋዜጠኝነት ሠራዊት ይፈጥራሉ ተብለው ነበር፡፡ እነሱ ግን የዘለፋና የፍረጃ ጋዜጠኝነት ሰራዊት ፈጥረው ገላገሉት - ኢህአዴግን!! ወደ መሬቱ እንደመስ (ዞሮ ዞሮ ወደ መሬት ነው ወደ አፈር ይባል የለ!) እናላችሁ ኢህአዴግ “ልማት” ያለውን የእርሻ መሬቶች ለውጭ ኢንቨስተሮች የመስጠት እንቅስቃሴ አንዳንድ ወገኖች “የመሬት ወረራ” በሚል ተቃውሞአቸውን እያሰሙ እንደሆነ ከኢቴቪ ሰማሁኝ፡፡ የአሜሪካ ድምጽና የጀርመን ሬዲዮ ላይ የቀረቡ ዘገባዎችም ተጠቅሰዋል - በኢቴቪ በተደጋጋሚ በተላላፈ ፕሮግራም ላይ፡፡ የፕሮግራሙ ዓላማ በመሬት ወረራ ዙሪያ ሚዛናዊ ዘገባ ማቅረብና ያልጠሩ ሃሳቦችን ማጥራት ቢሆን ደግ ነበር፡፡ ግን አይደለም፡፡ ዓላማው መተጋተግ ነው የሚመስለው፡፡

ባይገርማችሁ ሳይቸግራቸው ልማቱን “የመሬት ወረራ ነው” ያሉት የውጭ አገር መንግስታት “እኔ ከሞትኩ ሠርዶ አይብቀል” የሚል ተረት ተተርቶባቸዋል፡፡ ልብ በሉ! ለውጭ መንግስታት ጥብቅና መቆሜ ሳይሆን የዘለፋና የፍረጃ ስትራቴጂ ይጠቅመናል ወይ እያልኩ ነው፡፡ (እንደ ኢህአዴግም እንደ አገርም) ያውም ደግሞ ለዕድገታችን ድጋፍ ከሚሰጡን መንግስታት ጋር፡፡

የዘለፋና የፍረጃ ስትራቴጂ ዋናው ችግር ምን መሰላችሁ? ጠላት ያበዛል፡፡ እኛ ደግሞ በቂ ታሪካዊ ጠላቶች ስላሉን አዳዲስ ጠላቶች የመፍጠር ትጋት አያስፈልገንም፡፡ (ትጋቱ ለልማት ይዋል!)

ማሳሰቢያ - ይሄን ምክር በአክብሮት የምለግሰው ለኢቴቪ ሳይሆን ለኢህአዴግ ነው፡፡ ኢቴቪማ በምክር የሚመለስ ተቋም እንዳልሆነ በ”ሳይንስ” ተረጋግጧል፡፡ (ምናልባት ፀባይ ማረሚያ ይመልሰው ይሆናል!)

በሽብርተኝነት ተከሰውና ጥፋተኝነታቸው በፍ/ቤት ተረጋግጦባቸው እስር የተበየነባቸው የሁለት ስውዲናውያን ጋዜጠኞች ጉዳይም አለ፡፡

እንግዲህ ገና ሲያዙ ጀምሮ የስውዲን መንግስትና ምዕራባውያን በዚህ ደስተኞች አልነበሩም (እንዴት ይሆናሉ?) ስለዚህ የፕሬስ ነፃነት ጥሰት ተፈጽሟል፤ ጋዜጠኞቹ ይፈቱ ወዘተ የሚል አቤቱታ አስተጋቡ፡፡ ኢቴቪ ለዚህም ጉደኛ ምላሽ አዘጋጅቷል (አናውቃችሁም እንዴ የሚል ቅላፄ ያለው) “እመቤት ፍትህ” በተሰኘ ፕሮግራሙ የምዕራብ መንግስታት ለምን ያህል ጊዜ በየአገሮቻቸው ላይ የፕሬስ ነፃነትን እንደጣሱ ከነማስረጃው እየጠቀሰ ሲወርፋቸው ሰንብቷል - “ጀግናው” ኢቴቪ፡፡ አሁንም ምዕራባውያን ትክክል ናቸው አይደሉም የሚል ነገር አልወጣኝም፡፡

ኢህአዴግም ግን ትክክል አይመስለኝም፡፡ የስውዲን ጋዜጠኞቹን በተመለከተ ህጋዊ ነው ብሎ ያመነበትን በህጋዊ መንገድ ከፈፀመ በኋላ የምን የፕሮፓጋንዳ ጋጋታ ነው! (ቅዳሴው ሲያልቅበት ቀረርቶ አከለበት ሆነ እኮ!)

ይሄን የምለው የምዕራባውያንን እጅ ጠባቂ ድሆች ስለሆንን እንዳይመስላችሁ! (ድሆች ብንሆንም እኮ ኩሩ ነን!) በነገራችን ላይ አውሮፓ ህብረት በዓመት የሚሰጠን ድጋፍ 100 ሚ. ዩሮ ይደርሳል (ለጠቅላላ ዕውቀት ያህል ነው!)

አያችሁ…ይኼ አዝማሚያው የማያምር የስድብ፣ የፍረጃና የዘለፋ ስትራቴጂ በአፋጣኝ ካልተቀየረ “የመንገዶቻችን እናት” የምንላት ወዳጃችን ቻይናም አንድ ቀን ከቀንደኛ ጠላቶች ጐራ ልትፈረጅ ትችላለች፡፡ ይሄ ደግሞ ውለታቢስ ሊያስብለን ይችላል፡፡ እናም ለጠብ አንቸኩል ባይ ነኝ፡፡ የባሰ ዕለት እኮ ጠቡ ራሱ በራችን ድረስ ከች ይላል፡፡

ያኔ እስኪወጣልን እንተጋተጋለን፡፡ በዚህ አጋጣሚ ከኢህአዴግ መዝገበ ቃላት ውስጥ “የአገሪቱ ጠላቶች”፣ “ፀረ - ልማት”፣ “ፀረ - ሰላም”፣ “ፀረ - እድገት” የሚሉ አሉታዊ ቃላት ተፍቀው በአዎንታዊ ቃላት እንዲተኩ እፈልጋለሁ (እመኛለሁ ማለቴ ነው!)

ለምሳሌ ግብር በዝቶብናል ለሚሉ ነጋዴዎች መልሱ “ፀረ - ልማት” በሚል መፈረጅ ሳይሆን ችግሩን በቅጡ መርምሮ መፍትሔ ወይም ማብራሪያ መስጠት ነው፡፡ የመሬት ሊዝ አዋጁ ትክክል አይደለም የሚል ሁሉ ጥቅም የቀረበት “ኪራይ ሰብሳቢ” ነው ማለት አይደለም፤ እንደኔ አዋጁ ያልገባው ሊሆን ይችላል፡፡ ለኢትዮጵያ መጥፎ ገጽታ የሚፈጥር ዘገባ ያሰራጨ ዓለማቀፍ ሚዲያ የአገሪቱ ታሪካዊ ጠላት ላይሆን ይችላል - (የተሳሳተ መረጃ ደርሶት ቢሆንስ?) መፍትሔው ታዲያ በጐ ምስል የሚፈጥር ዘገባ እንዲያቀርብ በመረጃ ማሳመን እንጂ ዘለፋ ወይም ፍረጃ አይደለም፡፡

አደራ ኢቴቪ! እኔን ደሞ “የውጭ መንግስት ተላላኪ” እንዳትሉኝ! (አይደለሁማ) በነገራችን ላይ ኢህአዴግም ሁሌም መናገር ያለበት አይመስለኝም፡፡ አንዳንዴ እኮ “ሙያ በልብ ነው” ቢል ይሻለዋል፡፡

አንድ ወዳጄ አንድ ባለታክሲ ነገረኝ ብላ ያጫወተኝን ላጫውተችሁ፡፡ ወዳጄ በታክሲው ተሳፍራ ስትሄድ የቴዲ አፍሮ አዲስ ነጠላ አልበም እየተሰማ ነበር፡፡ “ማነው ይሄ?” ስትል ጠየቀች፡፡

ባለታክሲውም “ቴዲ ከኤርትራ የቦከመው ዘፈን ነው፤ አብርሃምም ቦክሟል ይላሉ… ኧረ ጣጣ እንዳያመጡብን”

ወዳጄ “የምን ጣጣ?”

ባለታክሲው “ወደብ ሲሉ ወደብ ሰጠናቸው… አሁን ደግሞ በአዝማሪ እንዳንጣላ ነው የምፈራው”

እንግዲህ ባለታክሲው ከፈረደባት ኤርትራ ጋር “ዘፈን ሰርቃችሁኛል” በሚል ጦርነት ውስጥ እንዳንገባ ሰግቶ መሰለኝ፡፡ ደግነቱ ዘፈኑ የኤርትራ መንግስት ሳይሆን የግለሰብ ወይም የህዝቡ ነው፡፡

በመጨረሻ ለፕሮፖዛል ያልበቃች ትንሽ ሃሳቤን ልንገራችሁና እንሰነባበት፡፡ ምን አሰብኩ መሰላችሁ? በኢቴቪ ከፍረጃ ወይም ከዘለፋ የፀዳ ዘገባ ያቀረበ ጋዜጠኛ ይሸለማል ቢባል ጥሩ ይመስለኛል፡፡ አያችሁ እንዲህ አይነት ማበረታቻ (Incentive) ካልተዘጋጀ ጋዜጠኞቹ ከትግተጋ የሚወጡ አይመስለኝም፡፡ ዓመል ነዋ!

 

Read 4009 times Last modified on Saturday, 28 January 2012 12:10