Saturday, 30 May 2015 11:54

ሰማይ እንዳንወጣ ራቀብን፣ ምድርን እንዳንጠቀልል ሰፋብን

Written by 
Rate this item
(15 votes)

 

 

 

(ሰማይ ከይንድይብ ረሐቐና፣ ምድሪ ከይንጥቐልል ገፊሑና)

 ከዕለታት አንድ ቀን በአንድ ሩቅ አገር የሚኖር አንድ ባለፀጋ ንጉሥ ነበር፡፡ 5 ልጆች አሉት፡፡ ዕድሜው ወደሞት እየተቃረበ ሲመጣ ዙፋኑን ለማን እንደሚሰጥ ግራ ይጋባል፡፡ በመጨረሻ ግን አምስቱንም ልጆቹን ይጠራና፤

“ውድ ልጆቼ! እነሆ ሰው ነኝና እንደንጉሥ ብኖርም እንደሰው መሞቻዬ ደረሰ፡፡ ከመካከላችሁ ለአንዳችሁ ዙፋነ -መንግሥቴን መስጠት የግድ አለብኝ፡፡ ለዚህ የመረጥኩት መንገድ እናንተን ማወዳደርና የተሻለ ውጤት ያመጣ ሥልጣነ - መንግሥቴን እንዲወርስና ሁላችሁንም በእኩል - ዐይን እያየ፣ ሳያዳላ፣ ሥርዓቱን ጠብቆ እንዲያስተዳድር፤ ሌሎቻችሁም ወንድማችሁን አንድም እንደወንድምነቱ፤ አንድም እንደመሪያችሁ አድርጋችሁ በቀና ዐይንና በፍቅር እያገዛችሁት እንድትተዳደሩና አገራችሁን እንድትጠብቁ ማድረግ ነው፡፡”

ልጆቹ በአባታቸው ማርጀትና መድከም ቢያዝኑም፤ ሌላ ምርጫ ስለሌላቸው፤

“የመወዳደሪያ ጥያቄው ምንድን ነው?” ሲሉ ጠየቁ፡፡

ንጉሡም፤

“እያንዳንዳችሁ፤ በየበኩላችሁ እስከዛሬ ደግ ሠርተናል የምትሉትን እጅግ ትልቅ ነገር አምጡና ንገሩኝ፡፡ የተሻለ ደግ ነገር የሰራውን ልጅ መርጬ እኔ ዳኝነት እሰጣለሁ፡፡ አሁን ሂዱና ነገ ከነግ - ወዲያ ተመለሱ” ብለው አሰናበታቸው፡፡

ልጆቹም ወደየክፍላቸው ሄዱ፡፡

በየፊናቸው ካሰቡበት  ከሁለት ሶስት ቀን በኋላ ሁሉም ወደአባታቸው ተመለሱ፡፡

ንጉሡም፤

“እህስ እጃችሁ ከምን? ምን ምን ደግ ሥራ ይዛችሁልኝ መጣችሁ?” ሲል ጠየቀ፡፡

የመጀመሪያው፣ የበኩር ልጃቸው፣

“ንጉሥ ሆይ፣ አንድ ቀን በሠፈራችን ከፍተኛ የቤት ቃጠሎ ደርሶ አይቼ አንዲት ልጃገረድ ቤት ውስጥ ልትቃጠል ስትል ለነብሴ ሳልሳሳ ገብቼ ተሸክሜ አውጥቼ አድኛታለሁ” አለ፡፡

ሁለተኛው ልጅ ቀጠለ:-

“ንጉሥ ሆይ፤ አንድ አዛውንት ዐይናቸው፣ በቅጡ የማያይ ናቸውና ገደል አፋፍ ላይ ተንጠልጥለው አይቼ፤ ሰው “ጉድ! ጉድ!” እያለ ሲተራመስ እኔ አፋፉን ወርጄ ከሥር ተሸክሜ አወጣሁዋቸው፡፡ ነብሳቸው ዳነ” አለ፡፡

ሶስተኛው ልጅ ደግሞ የሚከተለውን ተናገረ:-

“ንጉሥ ሆይ፤ እኔ ደግሞ አንድ ነብስ ያላወቀ ህፃን ከቤቱ ደጃፍ ካለ አውራ ጐዳና ላይ እየዳኸ ሲሄድ፤ ታኮ ያልተደረገለት ከባድ መኪና ወደኋላ እየተንሸራተተ መጥቶ ሊደፈጥጠው ሲል፣ ከሩቅ እየሮጥኩ ደርሼ ከጐማው ስር አፍሼ አውጥቼ አድኜዋለሁ”

አራተኛው ወንድምም፤

“ንጉሥ ሆይ፤ እኔም አንዲት አሮጊት መንገድ ላይ ወድቀው፣ የወደቁበት ድንጋይ ጭንቅላታቸውን መቷቸው ደም ሲፈሳቸው ደርሼ፤ ተሸክሜ ወደአቅራቢያው ጤና ጣቢያ ወስጄ አሳክሜ አድኛቸዋለሁ!” አለ፡፡

የመጨረሻው ወንድም እንዲህ አለ:-

“ንጉሥ ሆይ! እኔ ያደረግሁት ቀላል ነገር ነው፡፡

አንድ ቀን አንድ ከዚህ ቀደም በድሎኝ ተጣልተን፣ ተደባድበን የነበረ ሰው፤ ውሃ ውስጥ ገብቶ፣ እየሰመጠ ሳለ እኔ ደረስኩ፡፡ ሰውዬው “እባክህ በድዬሃለሁና ከመሞቴ በፊት ይቅርታ አድርግልኝ?” አለኝ፡፡ እኔም ወዲያው ልብሴን አወላልቄ ውሃው ውስጥ ገብቼ እየቀዘፍኩ በዋና ይዤው ወጣሁ - ዳነ!”

ንጉሡም፤

“ልጆቼ ሆይ! ሁላችሁም የፈፀማችሁት ወደር የሌለው መልካም ነገር ነው፡፡ የመጨረሻው ትንሹ ልጄ ግን ለበደለው ሰው ይቅርታ ማድረጉን፣ ያንንም በተግባር ማሳየቱን የሚያህል ትልቅ ነገር አይገኝም፡፡ እሱ መንግሥቴን ይውረስ፡፡ እናንተ ደግሞ ምንም ሳትመቀኙት የተለመደውን የደግነት እገዛችሁን ለግሱት!” ብለው ልጆቻቸውን አሰናበቱ፡፡

                                       ***

ይቅር - ባይነት የደግነት ሁሉ የበላይ ነው! ከእኔ ይቅር ማለት ታላቅ ፀጋ ነው፡፡ ብጐዳም እኔ ልለፈውና የጋራ ህልውናና ደህንነታችን፣ የጋራ ቤታችን በጠነከረ ሁኔታ ይቆይ ማለት፤ አርቆ አስተዋይነት ጭምር ነው፡፡ የመጨረሻ ትንሹ ልጅ ጠላቱን “እንዳሰመጠ ይቅር!” ማለት አቅቶት አይደለም! ለጠላቱ ሳይቀር ትምህርት ሊሰጥ የሚችል ልባዊ ደግነት ስላለው ነው! ይህን መቀዳጀት ወደፍፁም ፍቅር፣ ያለሂሳብ ወደሚሰጥ ፍቅር መጠጋት ነው! በአንፃሩ በስሌት የሚሰጥ ደግነትና ፍቅር፣ ዛሬ ይሄን ባደርግለት ነገ ይሄን ይከፍለኛል የሚባል ዓይነት ፍቅር ወይም ደግነት፤ ዞሮ ዞሮ ወደ ንግድ የሚገባ ነው! ዲሞክራሲም የዚህ ዓይነት ባህሪ አለው፡፡ ያለሂሳብ ስንሰራው ደግነት አለው፡፡ መስዋዕትነትን ይጠይቃል፡፡ በሚታሰብ ትከፍለኛለህ ሲባል ግን ዞሮ መግቢያው ንግድ ነው፡፡ ያ ንግድ ደግሞ በዋጋው የሚነገድ አይደለም፡፡ “ዋናውን ከመለሰልኝ ይበቃኛል” በሚል ተጀምሮ፤ “ባመጣሁበት ውሰደው” እየተባለ ሥንጥቅ ይተረፍበታል፡፡ ውሎ ሲያድር ደግሞ የተትረፈረፈ ጥቅም ለማግኘት ደባልቆ መሸጥ ይመጣል፡፡ ቅቤው ሙዝ ይገባበታል፣ የማሩ ጠጅ የስኳር ጠጅ ይሆናል፡፡ (በአራዳ ቋንቋ “የተወጋ” ነው ይባላል)

ከዚህም አልፎ የእኔን ሸቀጥ ብቻ ግዛ ወደማለት ይሸጋገራል - የተወጋም ቢሆን ዲሞክራሲም “የተወጋ ዲሞክራሲ” የሚሆንበት ሰዓት አለ፡፡ ለሠራነው ዲሞክራሲ ዋጋ ከመጠየቅ አልፈን “የተወጋም” ቢሆን፡፡ “የእኔን ዲሞክራሲ ብቻ ተቀበል” ማለት ይመጣል፡፡ (የእኔን ሸቀጥ ብቻ ግዛው ወደሚል ንግድ እንደመሸጋገር ማለት ነው) ውስጡ ቅድመ ሁኔታ እንደረድራለን - መመሪያ፣ ደንብ፣ ህግ፣ ዓለም አቀፍ የንግድ ውል እያልን፡፡ “ንፁህ የማር ጠጅ ነው” የሚል ማስታቂያ እንለጥፋለን እንደማለት ነው፡፡

ከዚያ ይህን ካልገዛህ ህልውና የለህም ወደማለት እናድጋለን፡፡ እጅ መጠምዘዝ እንጀምራለን የሚገርመው፤  ይህ ሁሉ የሚሆነው “ስለዲሞክራሲ” ሲባል ነው፡፡ ስለሰው ልጆች መብት ሲባል ነው! ያለንበት ዓለም ይህን እሳቤ ከፍ አድርጐ “ጐሎባላይዜሽን” ይለዋል፡፡ በዚህ እንፈራረማለን፡፡ የብድር ግዴታ እናስፈርማለን፡፡ የዚህ ሁሉ ውስጡ፣ የዚህ ሁሉ ቡጡ፣ የዚያው የተወጋ ዲሞክራሲ፣ የዚያው በልካችን የተሰፋ ዲሞክራሲ፤ “በነፃ መስፋፋት” ነው፡፡ የዚያው “የመልካም አስተዳደር” መስፈን ማንሰራፋት ነው፡፡ የዚያው “የፍትሕና እኩልነት” ዜማ “የተሻሻለ ቅንብር በእገሌ ሙዚቃ ቤት” እየተባለ መለፈፍ ነው፡፡ ከጥንታዊት ግሪክ ዲሞክራሲ እስከዛሬው “ዲሞክራሲ” የሄድንበት መንገድ “የንግድ ህግን” የተከተለ ነው፡፡ ለትርፍ የተቀነበበ በመሆኑ መቼም ቢሆን ሙስና አያጣውም! እርግጥ ሙስናው ዝማሬ - ቃናው፣ ቅኔ ዘረፋና አቋቋሙ፣ ይለያያል፡፡ እንደየአገሩ የውጪ ምንዛሬ መጠኑም ይለያያል፡፡ እንጂ ውስጠ ነገሩ አንድ ነው፡፡ “የናይጄሪያው ይከፋል፣ የኬንያው ትንሽ መለስ ያለ ነው፡፡ የኢትዮጵያው ጠየም ይላል፡፡ የሱዳኑ በጣም አልለየለትም ወዘተ” እንበል እንጂ ሙስና ሙስና ነው!! ሁሉም በዲሞክራሲ ስም፣ ሁሉም በሠፊው ህዝብ ስም፣ ሁሉም በፍትሐዊነት ስም፣ ሁሉም በነፃና አድልዎ - አልባ ምርጫ ስም፣ ሁሉም ቡድን በሰላም ስም የሚፈፅመው ምዝበራ ነው፡፡ ግለሰብ ሠራው፣ ቡድን ሠራው፣ ፓርቲ ሠራው፣ መንግሥት ሠራው አያጨቃጭቅም፡፡ የሙስና ቦቃ የለውም፡፡ ስለዲሞክራሲ ስናወራም የአሜሪካ ተፅዕኖ፣ የእንግሊዝና የጀርመን ተፅዕኖ ያመጣው ወዘተ ማለትም አያዋጣም፡፡ ዞሮ ዞሮ “ለአምጪው እንዲከፈል ህግ ያስገድዳል” ይላልና መጽሐፉ! ሀገራችን ከላይ ካልነው የዲሞክራሲ ሂደት ውጪ አይደለችም፡፡ በእርግጥ የራሷ ንቅሳት፣ የራሷ ክትባት፣ የራሷ ዕትብት አላት፡፡ ውስጧ ስንገባ ጓዳ ጐድጓዳዋ ብዙ እንደመሆኑ ኢኮኖሚያዊ ፖለቲካዊ፣ እና ማህበራዊ ጣጣ - ፈንጣጣዋ ያለ ነው፡፡ ኢኮኖሚያዊና ኢኮኖሚስቷ፣ ወርቁ ቢጠፋ ሚዛኑ አይጥፋ የሚባል ዓይነት ነው፡፡ ማህበራዊ ኑሮዋና ነዋሪዋ የባሰ አታምጣ የሚል ነው፡፡ ፖለቲካዋና ፖለቲከኛዋ “ሰማይ እንዳንወጣ ራቀብን፣ ምድርን እንዳንጠቀልል ሰፋብን” የሚል፤ ራስ ሳይኖረው ትራስ ፍለጋ የሚዞር ምሁር ነው!

ስለሆነም፤ ከፊሉ የሞተ ፈረስ ይጋልባል፤ ከፊሉ የሌለ ፈረስ አለኝ ይላል፣ ከፊሉ ያገኘውን ፈረስ ከመጋለብ ይልቅ አፉን ይዞ ይጐትታል፡፡ ደግሞ ከፊሉ፣ መውደቁን ረስቶ ፈረሱ ብቻውን እየሮጠ፤ አለሁ እየጋለብኩ ነው” ይላል፡፡ ከፊሉ ሲመቸው የሚጋልብ ሳይመቸው የሚተኛ ነው፡፡ ከፊሉ ደግሞ ከፈረሱ ይልቅ ራሱ ያልተገራ ሆኖ ይደነባበራል፡፡ አንዳንዴ ጋላቢው ፈረሱ፤ ተጋላቢው ባለፈረሱ ይሆናል፡፡ ብዙ ዘመን ጋልቤያለሁ የሚለው ደግሞ ራሱም ማርጀቱን፣ ፈረሱም መገጣጠቡንና ማነከሱን፣ ማለክለኩንና አረፋ መድፈቁን ሳያስተውል “መጭ!” ይለዋል፡፡ ከዚህ ሁሉ ይሰውረን! የተሻለ ቀን እንመኝ!

 

 

 

Read 4428 times