Saturday, 28 January 2012 11:45

የፋሲል ቤተመንግስትን በትወና

Written by  መልካሙ ተክሌ (melkamutekele@gmail.com)
Rate this item
(1 Vote)

ታሪክ ፀሃፊው ተክለፃድቅ መኩሪያ ስለ ንጉስ ፋሲል ቤተመንግስት አገነባብ ሲገልፁ አፄ ፋሲል ቤተ እስራኤሎችንና ሕንዶችን እንዳስተባበሩ ያወሳሉ፡፡ ፀሃፊው “የኢትዮጵያ አንድነት ከአፄ ልብነድንግል እስከ አፄ ቴዎድሮስ” በተሰኘ የታሪክ መፅሃፋቸው እንዳሰፈሩት፤ “ግንበኞች ሰብስበው (ፖርቱጊዞች አሉበት የሚሉ አሉ)፤ በጐንደር ከተማ እስከዛሬ የፋሲል ግንብ እየተባለ የሚታየውን ቤተመንግስት አሠሩ፡፡ ያሰራሩንም አኳኋን ከሌሎቹም እየተማከሩ ዓይነቱን የሰጡ ራሳቸው ናቸው ይባላል፡፡ ቤተመንግስቱም ተሠርቶ ካለቀ በኋላ ዙርያውን ሰፊ ግንብ አሰሩ፤ በዙሪያውም አብያተክርስትያናት አሳነፁ፡፡ በዚህም ቤተመንግስት የንጉሡ ለብቻ የጳጳሱ ለብቻ ግብር ማብሊያውና ችሎት ማስቻያውም እየተለየ በየክፍሉ ስለተሰራ በጣም አምሮ ነበር፡፡ ይኸውም ያን ጊዜ አፄ ፋሲል ያሰሩት ቤተመንግስት እላይ እንዳልነው “የፋሲል ግንብ” እየተባለ ታሪካዊ የሆነ ምልክቱ ስማቸውን እያስጠራ እስከ ዛሬ ይታያል፡፡” ብለዋል፡፡

ከሁለቱ ነገሥታት በተጨማሪ አፄ በካፋ እና ሌሎችም ከፋሲል ወዲህ የነገሡ ነገሥታት የየራሳቸውን የታሪክ አሻራ ትተው አልፈዋል የሚሉት ደራሲው፤ ሁሉም ጐንደርን “ጐንደር” ለማሰኘት ጉልህ ድርሻ ቢኖራቸውም ቤተመንግስት አልሰሩም ብለዋል በመፅሃፋቸው፡፡ በሕይወት ዘመኔ ለመጀመርያ ጊዜ አዲስ አበባ ብሔራዊ ቤተመንግስት ስገባ የገጠመኝን ማስታወሱ ተገቢ ነው፡፡ ገና የቤተመንግስቱ ውጭ በር ላይ እንደደረስኩ ጠባቂ ወታደሮች መግባት የምችለው ስሜ ከተጋበዙ እንግዶች ዝርዝር ውስጥ መኖሩ ሲረጋገጥ ብቻ መሆኑን ነገሩኝ፡፡ ተረጋገጠ፡፡ በእጅና በኤሌክትሮኒክስ መሳሪያ ከተፈተሽኩ በኋላ ካሜራና መቅረፀ-ድምፄን ከፍቼ በማብራት እንዳሳይ ተጠየቅኩ፡፡ ከዚህ በኋላ ወደ አዳራሽ ከመግባቴ በፊት እንደገና በሩ ላይ ተመሳሳይ ፍተሻ ተደረገልኝ፡፡ ባለፈው ጥር 13 ቀን 2004 ዓ.ም ወደ ጐንደሩ ቤተመንግሥት ሳመራ እንደ ብሄራዊ ቤተመንግስት እንኳንስ በተደጋጋሚ ልፈተሽ ማንም “አባ ከና” አላለኝም፡፡ የጥምቀት ሰሞን በመሆኑ በግርግሩ ምክንያት ውጭ በር ላይ የቆመውን ቃፊር እግር ሳላውቅ ረግጬው ነበር፡፡ የተረገጠውን ቃፊር ይቅርታ ብጠይቅም እሱ ግን ሰማሁም ለማሁም አላለም፡፡ ቀጥ ብሎ መቆም ብቻ፡፡ በአፄ ፋሲል ዘመን የነበሩ የቤተመንግስት ጠባቂ ወታደሮች ሐሞተ ኮስታራ እንደነበሩ ለመጠቆም ይሆን?

ሠርጋቸው የደመቀላቸው ሙሽሮች

ኮስታራውን ጠባቂ አልፌ በፋሲል ግቢ ካሉ ቤተመንግስቶች አንዱ ወደሆነው ወደ ፋሲል ቤተመንግስት አመራሁ፡፡ በጐንደር በአማተር ከያኒነት የተደራጁ ወጣቶች፤ ሕይወት በፋሲል ቤተመንግስት ምን ይመስል እንደነበር ለማሳየት ደፋ ቀና እያሉ ነበር፡፡ እነሱንና ቤተመንግስቱን አይቼ ስመለስ ሙሽሮች ከነእድምተኞቻቸው “ሙሽራዬን” ሲያስነኩት ደረስኩ፡፡ በፕሮግራሙ መርሃ ግብር ላይ የጐንደር ባህላዊ ሰርግ ምን ይመስል እንደነበር የሚያሳይ ትርዒት እንደሚቀርብ ማንበቤን አስታወስኩ፡፡ በነገራችን ላይ አንዲት አውስትራሊያዊትና አንድ ኢትዮጵያዊ በእለቱ የሰርጋቸውን የፎቶ ሥነ ስርዓት ያከናወኑ ሲሆን በተመሳሳይም ከአስር በላይ ጥንዶች የሰርጋቸውን የፎቶግራፍ ሥነሥርአት በታሪካዊው የፋሲል ግቢ አከናውነዋል፡፡ ልብ በሉ በግቢው ለትርኢት ሲባል አማተር ከያንያኑ በእግረኛና ፈረሰኛ ጠባቂነት ተከፋፍለው የምርምር የአፄ ፋሲል ዘመን አስመስለውት ነበር፡፡ በዚህ ሻምላ የታጠቀ ኮስታራ የአፄ ፋሲል ወታደር በወዲያ ደግሞ ፈረሰኛ ይታያል፡፡ በዚህ መልካም አጋጣሚ የጥንዶቹ ሠርግ ደመቀ፡፡ እንዴት ደስ ይላቸው!

ታሪክን በትወና

ወጣቶቹ የጐንደር ከያንያን ከ379 አመት እስከ 343 ዓመት ወደ ኋላ ተጉዘው የአንድን ንጉሥ ቤተመንግስት የሠላሳ ስድስት ዓመታት ዜና መዋእል ከፊል ገጽታ አሳምረው አሳይተዋል፡፡ የእለቱ ተመልካች ቁጥር በጣሙን አነሰ እንጂ ታሪክን በትወና ማዳረስ በተቻለ ነበር፡፡

በእለቱ ከታዩት የፋሲል ቤተመንግስት ትዕይንቶች አንዱ የነበረው የፍትህ ሥርአት ነው፡፡ ያኔ ከሳሽ ክሱን ለአፈንጉሱ ወይም ለአጥቢያ ዳኛው በቃል ያመለክትና እሳቸው በቀጠሩት ቀን በቃል (”እሰጥ አገባ”) ይሟገታል፡፡ የጐንደር ወጣቶች ይህ ምን እንደሚመስል ክሽን አድርገው በትወና ጥበብ አሳይተውናል፡፡ ግንቡ ሠገነት ላይ ንጉሡና ንግሥቲቱን እንዲሁም ሹማምንቱንና ወታደሮቹን የወከሉ ወጣቶች የወቅቱን አለባበስ (የአቅማቸውን ያህል) ተከትለው ተቀምጠዋል፡፡ ከታች መሃሉ ላይ አፈንጉሡ ከነጋሻ ጃግሬዎቻቸው ቆመዋል፡፡ በቀኝ መሃል ላይ ተከሳሽ፣ በግራ በኩል ደግሞ ከሳሽ አሉ፡፡ ከእያንዳንዳቸው ጀርባ ደጋፊዎቻቸው ተቀምጠዋል፡፡ ነጋሪት ተጐሰመ፡፡ ሕዝብ ተሰበሰበ፡፡ አዋጅ ነጋሪም አፄ ፋሲል መንገሳቸውን ተናገረ፡፡ ቀጥሎ ንጉሡና ንግሥቲቱ በዙፋን ተሰየሙ፡፡ እነሱ ሳይቀመጡ መቀመጥ አይቻልም፡፡

የአፄ ፋሲል ዘመን ሰንደቅ ዓላማስ?

ጋዜጠኞች ፎቶግራፍ ለማንሳትና ድምጽ ለመቅረጽ ከወዲያ ወዲህ ሲሯሯጡ ታዳሚው ትዕይንቱን በቅጡ እንዳይመለከት አውከውት ነበር፡፡ ተዋንያኑ ስለተጠቀሙባቸው አልባሳት (costume) አንዳንድ ነገር ማለት እፈልጋለሁ፡፡ የወንዶቹ ጫማ የዛሬ 343 ዓመት የነበረ ነው ተብሎ የሚታሰበውን ይመስላል፡፡ የሴቶቹ ጫማ ግን ፈፅሞ አይቀራረብም፡፡ ኮንጐ ጫማ ነው፡፡ ይኼ ጫማ በኢትዮጵያ መደረግ የጀመረው የኢትዮጵያ ጦር ወደ ዲሞክራቲክ ኮንጐ ከዘመተበት ከዛሬ ሃምሳ ሁለት ዓመት ወዲህ  እንጂ ከሦስት መቶ አመት ወዲህ አይደለም፡፡ የዚያን ወቅት አይነት ፈትል ማግኘት ያዳገታቸው ወጣቶች፤ ትወናቸውን  በአቡጀዴ ተወጥተውታል፡፡ በአፄ ፋሲል ጊዜ የነበረ ድባብ ለቤተመንግስቱ ለመፍጠር ተዋናዮቹ ወይም አዘጋጁ የአሁኑን የኢትዮጵያ ባንዲራ ተጠቅመዋል፡፡ የድሮን ታሪክ አሳያለሁ የሚል የጥበብ ባለሙያ ለፋሲል ዘመን መቼት አሁን ፌደራል መንግስቱ የሚጠቀምበትን ባንዲራ መጠቀም አግባብ ይሆን? የወጣቶቹ ዋና አስተባባሪ ስለዚሁ ሲያስረዳ “የፌደራሉ መንግስት አርማ የሌለበትን ሰንደቅ ዓላማ መጠቀም ስለማይቻል ነው” ብሏል፡፡ እንዴት ነው ነገሩ? በትያትርና በፊልም ሥራዎች ላይ የቀድሞ ባንዲራን መጠቀም የሚከለክል ደንብና ህግ ከየት መጣ? እኔ በበኩሌ ይሄን አላውቅም፡፡ ካለም አግባብ አይመስለኝም፡፡

የተካፈልኩበት ግብር ቤት

የዘመኑን ስርአት ለማሳየት ተፍ ተፍ ያሉት ወጣቶች፤ በወቅቱ ነገሥታት እንዴት ግብር እንደሚያገቡ (ሰው እንደሚያበሉ) አሳይተዋል፡፡

በዚሁ ግብዣ ላይ ኢትዮጵያዊ ባህል አስገድዶኝ ላጐርሰው የሞከርኩት በቅርቤ የነበረ “የፋሲል እልፍኝ አስከልካይ ወታደር” ጭራሽ እንዳላየኝ ሆኖ አሳፍሮኛል፡፡ ወይ የፋሲል ጊዜ! መጠጥ አዳዮች የተጣራ የቤተመንግስት ጠጅ ሲያድሉ ደግሞ ጠጅ ስለማልደፍር “ኮካኮላ” ጠይቄ ነበር፡፡ ለካስ በፋሲል ጊዜ ኮካ አልነበረም፡፡

 

 

Read 5384 times Last modified on Saturday, 28 January 2012 11:50