Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 28 January 2012 11:25

ፍርድ ቤቱ በእነኤልያስ ክፍሌ ክስ ከ14 ዓመት እስከ ዕድሜ ልክ እስራት ፈረደ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ኤልያስ ክፍሌ  በሌለበት ዕድሜ ልክ፣ዘሪሁን ገ/እግዚአብሔር 17 ዓመት፣ውብሸት ታዬ 14 ዓመት፣ሒሩት ክፍሌ 19 ዓመት እና ርእዮት አለሙ 14 ዓመት እስራት ተፈርዶባቸዋል

ችሎት በአሜሪካን አገር የሚገኘው የኢትዮጵያን ሪቪው ድረ-ገጽ አዘጋጅ ኤሊያስ ክፍሌ፤ በተከሰሰባቸው ሦስት ክሶች ጥፋተኛ መባሉን በማውሳት፣ ተከሳሹ በዋና ወንጀል አድራጊነት ካልተያዙ የውጭና የሀገር ውስጥ አባሪዎቹ ጋር ተካፋይ በመሆን ከግንቦት 7፣ አርበኞች ግንባር፣ ኦሮሞ ነጻ አውጪ ግንባር (ኦነግ)፣ ኦጋዴን ብሔራዊ ነጻ አውጪ ግንባር (ኦብነግ)፣ ጋር በመደራጀትና በኤርትራ መንግሥት በመታገዝ የጋራ ህቡእ ትጥቃዊና በሽብር የተደገፈ ሁሉን አቀፍ ትግል የማድረግ ጥምረት በመፍጠር፣ ሕገ መንግሥቱንና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን በተደራጀ የሽብር ድርጊት ለማፍረስና የሀገሪቱን መሠረተ ልማቶች ለማውደም፣ ባለሥልጣናትን ለመግደል እንቅስቃሴ አድርጓል ብሏል፡፡

ፍርድ ቤቱ አያይዞ እንዳለው፤ ኤልያስ ክፍሌ በአንደኛው ክስ የጸረ ሽብርተኝነት አዋጅ ቁጥር 652/2001 አንቀጽ 3(6) መተላለፍ ከ15 ዓመት እስከ ዕድሜ ልክ እሥራት ያስቀጣዋል፣በሁለተኛው ክስ የጸረ ሽብርተኝነት ዐዋጅ አንቀጽ 7 መተላለፉ ከ20 ዓመት እስከ ዕድሜ ልክ እስራት ያስቀጣዋል፣ በሦስተኛው ክስ የጸረ ሽብርተኝነት ዐዋጅን አንቀጽ 9 በመተላለፉ ደግሞ ከ10 ዓመት እስከ ዕድሜ ልክ የሚያስቀጣው ሲሆን ፍርድ ቤቱ የወንጀሉን ክብደትና አፈጻጸም ሲመረምር ተከሳሹ ለወንጀል ድርጊቱ ገንዘብ እየሰበሰበ ሰው በመመልመልና በህቡእ በማደራጀት በመንቀሳቀሱ፣ ወንጀሉን ከባድ ያደርገዋል ብሏል፡፡ በዚህም ምክንያት በአሜሪካን አገር በሚገኘው የኢትዮጵያን ሪቪው ድረ-ገጽ ባለቤት ኤልያስ ክፍሌ ላይ፤ በአንደኛው ክስ ዕድሜ ልክ እሥራት፣ በሁለተኛው ክስ 25 ዓመት ጽኑ እስራት፣ በሦስተኛው ክስ ደግሞ 13 ዓመት ጽኑ እስራት በመፍረድ በአጠቃላይ ተከሳሹ በሌለበት የዕድሜ ልክ ጽኑ እስራት  ፍርድ ሰጥቶበታል፡፡

ሁለተኛ ተከሳሽ የአብዴፓ ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ ዘሪሁን ገብረእግዚያብሔር በአንደኛው ክስ ከ15 ዓመት እስከ ዕድሜ ልክ ወይም ሞት የሚያስቀጣ፣ በሁለተኛው ክስ ከ20 ዓመት እስከ ዕድሜ ልክ እስራት፣ በሦስተኛው ክስ ደግሞ ደረጃ ባይወጣለትም ከ5 ዓመት እስከ 15 ዓመትና በገንዘብ እስከ መቶ ሺህ ብር ሊያስቀጣ እንደሚችል ፍርድ ቤቱ በፍርድ ውሳኔው ዝርዝር አስረድቷል፡፡

ፍርድ ቤቱ የወንጀሉን ድርጊትና አፈጻጸም መመልከቱን በመግለጽ፤አቶ ዘሪሁን ሰዎችን በገንዘብ በመደለል፣ በህቡእ በመንቀሳቀስና በመመልመል በመሳተፉ ወንጀሉን በመካከለኛነት  መድቦታል፡፡ በአንደኛው ክስ 20 ዓመት፣ በሁለተኛው ክስ 20 ዓመት ከስድስት ወር፣ በሦስተኛው ክስ 10 ዓመት ጽኑ እስራት በአጠቃላይ መነሻ ቅጣቱ 25 ዓመት ጽኑ እስራት መሆኑን በፍርድ ውሳኔው በንባብ አሰምቷል፡፡

የዐቃቤ ሕግ የቅጣት ማክበጃ በክሱ ላይ የቀረበ በመሆኑ እንዳልተቀበለው ያስታወቀው ፍርድ ቤቱ፤ በአንጻሩ የተከሳሹን የቅጣት ማቅለያ በመቀበልና ተከሳሹ የቤተሰብ አስተዳዳሪና ቀደም ሲል ጥፋት የሌለበት መሆኑን ግምት ውስጥ በማስገባት ቅጣቱን በሦስት እርከን ዝቅ አድርጎ በእርከን 34 ላይ በማሳረፍ እና ይህም ከ15 እስከ 18 ዓመት ጽኑ እስራት የሚያስቀጣ በመሆኑ፣ ተከሳሹ እጁ ከተያዘበት ጊዜ ጀምሮ የታሰረው ታስቦ 17 ዓመት ጽኑ እስራት፣ ከ50 ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣት ጋር ተፈርዶበታል፡፡

የዐቃቤ ሕግ ሦስተኛ ተከሳሽ የአውራምባ ታይምስ ጋዜጣ ምክትል ዋና አዘጋጅ ጋዜጠኛ ውብሸት ታዬ፤ በአንደኛው ክስ ከ15 ዓመት እስከ ዕድሜ ልክ ወይም ሞት፣ በሁለተኛው ክስ ከ10 እስከ 15 ዓመት፣ በሦስተኛው ክስ ከ5 እስከ 15 ዓመትና መቶ ሺህ ብር የሚያስቀጣ በመሆኑ የወንጀሉ አፈጻጸም ሰዎችን እየረዳ በህቡእ መንቀሳቀስ በመሆኑ ቅጣቱ ዝቅተኛ በሚባል ደረጃ ተወስኖበታል፡፡በዚህም መሠረት በአንደኛው ክስ 17 ዓመት ጽኑ እስራት፣ በሁለተኛው ክስ 6 ዓመት፣ በሦስተኛው ክስ 7 ዓመት በመፍረድ በጠቅላላው 25 ዓመት ጽኑ እስራት መነሻ ቅጣት ሆኖ ተወስኗል፡፡

ዐቃቤ ሕግ ያቀረበው የቅጣት ማክበጃ የወንጀል ድርጊቱን በማቋቋሚያነት የተያዘ በመሆኑ ፍርድ ቤቱ ሳይቀበለው ቀርቷል፡፡በአጻሩ የተከሳሹን የማቅለያ ሐሳብ በመቀበል በ5 እርከን ዝቅ እንዲል ተደርጎ እርከን 32 ላይ ተወስኗል፡፡በዚህ እርከን መሠረት ከ13 እስከ 15 ዓመት ከ8 ወር የሚያስቀጣ ሲሆን ጋዜጠኛ ውብሸት እስከ አሁን የታሰረው ታስቦ 14 ዓመት ጽኑ እስራትና 33 ሺህ ብር እንዲቀጣ ተወስኗል፡፡

አራተኛ ተከሳሽ የሆነችው ወ/ሮ ሒሩት ክፍሌ፤ በሦስቱም ክሶች ጥፋተኛ መሆኗን ያወሳው ፍርድ ቤቱ፤ በአንደኛው ክስ ከ15 ዓመት እስከ ዕድሜ ልክ እስራት፣ በሁለተኛው ክስ ከ5 እስከ 10 ዓመት ጽኑ እስራት፣ በሦስተኛው ክስ ከ5 እስከ 15 ዓመትና ከመቶ ሺህ ብር በማይበልጥ የሚያስቀጣ ሲሆን ወንጀሉ ሽብር ለማድረግ ሰዎችን መመልመልና ማደራጀት በመሆኑ በመካከለኛ ደረጃ በመመደብ በእርከን 34 ላይ ወድቆ፤ በአንደኛው ክስ 20 ዓመት ጽኑ እስራት፣ በሁለተኛው ክስ 7 ዓመት ጽኑ እስራት፣ በሦስተኛው ክስ 10 ዓመት ጽኑ እስራት በመፍረድ 25 ዓመት ጽኑ እስራት የቅጣቱ መነሻ ተደርጓል፡፡

ነገር ግን ዐቃቤ ሕግ ለቅጣት ማክበጃነት ተከሳሿ ከዚህ ቀደም በሌላ ወንጀል ተከሳ  ሦስት ዓመት ታስራ እንደነበር የሚገልጽ ማስረጃ በማቅረቡ፣ ቅጣቱ በአንድ እርከን ከፍ እንዲል ተደርጎ፣ በአንፃሩ ተከሳሿ የታማሚ ወንድሟን ልጆች የምታሳድግ እና የቤተሰብ አስተዳዳሪ መሆኗን በመግለጽ ለቅጣት ማቅለያነት ያቀረበችው የቅጣት አስተያየት ተቀባይነትን አግኝቶ  ቅጣቱ በ3 እርከን ዝቅ እንዲል እንዲልና እርከን 35 ላይ  እንዲቆም አድርጎታል፡፡ በዚህም መሰረት ጥፋቱ ከ16 ዓመት ከ6 ወር እስከ 19 ዓመት ከ6 ወር የሚያስቀጣ መሆኑን ፍርድ ቤቱ በመግለጽ ተከሳሽዋ እስከ አሁን የታሰረችው ታሳቢ ሆኖ በ19 ዓመት ጽኑ እስራት እንድትቀጣ ተወስኗል፡፡

አምስተኛ ተከሳሽ ርእዮት ዓለሙ፤ በሦስቱም ክሶች ጥፋተኛ መሆኗን በፍርድ ውሳኔው ያስደመጠው ፍርድ ቤቱ፤ በአንደኛው ክስ ከ15 ዓመት ጽኑ እስር እስከ ዕድሜ ልክ እስራት ወይም ሞት፣ በሁለተኛው ክስ ከ5 እስከ 10 ዓመት ጽኑ እስራት፣ በሦስተኛው ክስ ከ5 እስከ 15 ዓመት ጽኑ እስራትና ከመቶ ሺህ ብር በማይበልጥ የገንዘብ ቅጣት ያስቀጣል፡፡ ፍርድ ቤቱ የወንጀሉን አፈጻጸም ሲመረምር፤ የሽብር ድርጊት ለሚሰራ ድርጅት ድጋፍ በመስጠትና መረጃ በመስጠት በመሆኑ በዝቅተኛ ደረጃ በመመደብ በአንደኛው ክስ በ17 ዓመት፣ በሁለተኛው ክስ በ6 ዓመት፣ በሦስተኛው ክስ በ7 ዓመት ጽኑ እስራት በመወሰኑ በአጠቃላይ 25 ዓመት ጽኑ እስራት የመነሻ ቅጣት እንዲሆን ተወስኗል፡፡

ፍርድ ቤቱ የዐቃቤ ሕግ የቅጣት ማክበጃን የክስ ማቋቋሚያ በመሆኑ ባለመቀበል፤ የተከሳሽ ጠበቆች ያቀረቡትን በመቀበል የፍርድ ውሳኔው በ5 እርከን ዝቅ ብሎ ወደ ቅጣት እርከን 32 ላይ በመውደቁ፣ ከ13 እስከ15 ዓመት ከ8 ወር የሚያስቀጣ ሲሆን አጠቃላይ ሁኔታዎች ታስበውና እስከ አሁን የታሰረችው ታሳቢ ተደርጎ፣ 14 ዓመት ጽኑ እስራትና 33 ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣት ተፈርዶባታል ሲል ፍርድ ቤቱ ገልፆል፡፡ከዚህ የእስራትና የገንዘብ ቅጣት በተጨማሪም፣ ሁሉም ተከሳሾች ለአምስት ዓመታት ከሕዝባዊ መብቶቻቸው እንዲታገዱ መወሰኑን ፍርድ ቤቱ አስታውቋል። ፍርድ ቤቱ የቅጣት ውሳኔውን አሰምቶ እንደጨረሰ ጋዜጠኛ ውብሸት ታዬ “አጠቃላይ ሁኔታው የሚያሳዝንና የሚያሳፍር ነው። ከጥርጣሬ ባሻገር ምንም ዓይነት ማስረጃ ባልቀረበበት ሁኔታ ነው የፈረዳችሁብን” በማለት የፍርድ ቤቱ ውሳኔ አግባብ  አለመሆኑን በመጠቆም ቅሬታውን ገልጿል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አብዴፓ) ሊቀ መንበር አቶ ዘሪሁን ገብረእግዚያብሔር በበኩላቸው፤ “እኔ ጥፋተኛ አይደለሁም፣ ለሰላማዊ የፖለቲካ ትግል በተቃዋሚ ፓርቲ በመሰለፌ ነው ይሄ ቅጣት የተወሰነብኝ፤ ታሪክ ነፃነቴን ወደፊት ያረጋግጣል” በማለት ለፍርድ ቤቱ ቅሬታቸውን ያሰሙ ሲሆን የቀኝ ዳኛው ሙሉጌታ ኪዳኔ ተከሳሾቹ ዝም እንዲሉ እና ቅሬታ ካላቸው ይግባኝ መጠየቅ እንደሚችሉ በመግለፅ ቆጣ ብለው ማሳሰቢያ ሰጥተዋል፡፡

ከውሳኔው በኋላ አስተያየታቸውን ለአዲስ አድማስ የሰጡት የ2ኛ፣ የ3ኛ እና የ4ኛ ተከሳሾች ጠበቃ አቶ ደርበው ተመስገን፤ “ውሳኔውን ይግባኝ የምንልበት ስለሆነ አሁን ምንም ለማለት ያስቸግራል፡፡ ነገር ግን የተሰጠው ፍርድ እኔንም ያሳዝነኛል፡፡

እነዚህ ሰዎች ሊሠሩ የተነሱት ጋዜጠኝነትና ፖለቲከኛነት ነው፡፡ ይሄ ደግሞ በዚህ ደረጃ ማስቀጣቱ ያሳዝነኛል ያስደነግጠኛል፡፡ ይሄንን ውሳኔ በፍፁም አልጠበቅኩም፤ ከደንበኞቼ ጋር ተነጋግሬ ይግባኝ ጠይቅ ካሉኝ እጠይቃለሁ” ብለዋል፡፡ የሕግ ባለሞያ መሆናቸውን የተናገሩት የርእዮት አባት አቶ አለሙ ጌቤቦ በበኩላቸው፤ ቀድሞውኑ ዐቃቤ ሕግ በርእዮት ላይ ያቀረበው ክስ እንድትከላከል ብይን የሚያሰጥ ነው ብለው እንደማያምኑ በመግለጽ፤ ፍ/ቤቱ እንድትከላከል በሰጠው ብይን መሰረት ግን የዐቃቤ ሕግን ክስ የሚያፈርስ መከላከያ አቅርባ እንደነበር ተናግረዋል፡፡ከዚህም አንጻር የፍርድ ቤቱ ውሳኔ እንዳልተዋጠላቸው በመግለጽ፤ ‹‹ዐቃቤ ሕግ ቅጣቱን ያቀረበው ‹‹ወይም›› በሚል በአማራጭነት የወንጀል ሕግን አንቀጽ 684/1 ጠቅሶ ነው፡፡ፍ/ቤቱም የሚከብደውን በመያዝ ነው የወሰነው›› ብለዋል፡፡ እንዲያም ሆኖ ቅሬታቸው በቅጣቱ ላይ ሳይሆን ጥፋተኛ በመባሏ ላይ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በመጨረሻ የተከሳሽ ቤተሰቦች ሐዘናቸውን በእንባ እየገለጹ በፖሊስ ታጅበው  ከሚወጡት ተከሳሾች ጋር የማጽናኛ ቃላት እየተለዋወጡ ተሰነባብተዋል፡፡

 

 

Read 11569 times Last modified on Saturday, 28 January 2012 15:21