Saturday, 16 May 2015 10:03

በዲሞክራሲ ዝም ማለትም ይቻላል! የኢሮብ አዛውንት

Written by 
Rate this item
(14 votes)

“ጮሃ የማታውቅ ወፍ እለቁ እለቁ ትላለች” - ሀገርኛ ተረት
አንዳንድ ታሪክ ሲውል ሲያድር እንደ ተረት ይወራል፡፡ ኢሮብ ትግራይ ውስጥ የምትገኝ አንዲት ወረዳ ናት፡፡ ተራራማ መልክዐ - ምድር ያላት ስትሆን ኢሮብ የሚባል ብሔረሰብ ይኖርባታል፡፡ የነደጃች ሱባጋዲስ (ማሸነፍን አበልፃጊ እንደማለት ነው) አገር ናት፡፡
በዚች አገር የሚታወቀው አንድ የነዋሪው ልማዳዊና ባህላዊ ጠባይ፣ መቻል፣ መታገሥና ሁሉን እኩል ማስተናገድ ነው፡፡ ህንፃም ልጅ ቢሆን፡፡ በሠርግ ወቅት የሚታደል ማንኛውም ነገር እንኳ ለልጅም እኩል ይደርሳል፡፡ ከተማይቱ ለጦርነት አመቺ ከሆኑት እንደ አሲምባ ተራራ እና አይጋ (ሻቢያ በጣም የተመታበት ቦታ) አሊቴና (ዳውሃን) ዓይነት ቦታዎች አካባቢ በመሆንዋ የደርግ ጦር፣ የኢዲዩ ጦር፣ የኢህአፓ ጦር፣ የህወሓት ጦር፣ አንዳንዴም የህዝባዊ ግንባር ጦር ወዘተ ኃይሎች እንደመተላለፊያ በየጊዜው እየመጡ ይሰፍሩባት ነበር ይባላል፡፡
ህዝቡ እነዚህን ኃይሎች በአግባቡ፣ ሳያጋጭና ሳያጣላ፤ አንዱን በፊት ለፊት አንዱን በጀርባ/ በጓሮ አስተናግዶ ኮሽ ሳይልበት ይሸኛቸዋል፡፡ ለኢሮብ ውይይት ዋና ባህል ነው፡፡ ህዝቡ የአገር ሽማግሌ ይኖረዋል፡፡ የእድር ዳኛ፣ የማህበር መሪ፣ የጎበዝ አለቃ ወዘተ እንደሚባለው ዓይነት የበሰሉ፣ ብልህነት የተዋጣላቸውና ህዝቡ እህ ብሎ የሚያዳምጣቸው አባት (አቦይ) ይኖሩታል፡፡
በአንድ ወቅት በዚሁ በኢሮብ አካባቢ ከፖለቲካ ንቅናቄ ድርጅቶች አንዱ ይመጣል፡፡ ህዝቡን ሰብስቦ እንደተለመደው ሰበካ ያደርጋል፡፡ ህዝብን ወክለው አቦይ ንግግር ያደርጋሉ፡፡ ጥያቄም ይጠይቃሉ፡፡
የንቅናቄ ቡድኑ አባላት በአቦይ ንቃትና አንደበተ ርቱዕነት ይደመማሉ፡፡ አቦይን በንቅናቄው ፖለቲካ ቢያጠምቋቸው የኢሮብ ህዝብ ላይ ትልቅ የፖለቲካ ተፅዕኖ ሊፈጥሩ እንደሚችሉ ገመቱ፡፡
ስለዚህም፤ አቦይን ለአሥራ አምስት ቀናት ወስደው የፖለቲካ ፕሮግራማቸውን ቢያስተዋውቋቸው ትልቅ ሥራ እንደሚሰሩላቸው ወሰኑ፡፡ አቦይን ይዘዋቸው ሄዱ፡፡ አቦይ ውይይቱን ተካፈሉ፡፡ ግምገማውን አዳመጡ፡፡ ትምህርቱን ቀመሱ፡፡
“አቦይ እየገባዎት ነው?” ይላል አንዱ ካድሬ፡፡
“አሳምሬ” ይላሉ አቦይ፡፡
ሌላው ሰበካውንና ገለፃውን ይጨርስና፣
“እህስ አቦይ! እየተከታተሉ ነው ትምህርቱን?”
“እንዴታ!” ይላሉ አቦይ፡፡
ሌላው ይቀጥላል፡፡
“አቦይ ዓላማችን ገባዎት?”
“አዎን”
“ፕሮግራማችን በዝርዝር ፍንትው ብሎ ታየዎት?”
“እጅግ! እጅግ!” ይላሉ፡፡
የአሥራ አምስቱ ቀን የአቦይ ንቃት ፕሮግራም አለቀ፡፡ ከዚያ አለቃው ካድሬ፤
“ይበሉ እንግዲህ አቦይ፣ ወደ ኢሮብ ጎሣ ይሂዱና እስካሁን የተማሩትን ያስተምሩ” አሉ፡፡
አቦይ አመስግነው ወደ ኢሮብ ተመለሱ፡፡
የኢሮብ ህዝብ ተሰብስቦ ጠበቃቸውና፤
“እሺ አቦይ ምን ተምረው መጡ?” አላቸው
አቦይም እንዲህ መለሱ፣
“ይገርማችኋል ወገኖቼ፣ የተማርኩት ስለዲሞክራሲ ነው፡፡ እናም በጣም ያስደሰተኝ ነገር በዲሞክራሲ ዝም ማለትም ይቻላል!” ብለው አጠቃለሉ፡፡
*       *      *
ብልህ ህዝብ ብልህ ዘመን ይሰራል፤ ይላሉ አበው፡፡ የተነሳበትን ቦታና ሁኔታ የማያውቅ ህዝብ የት እንድደደረሰ ለመገንዘብም ልብና ልቡና ያንሰዋል፡፡ የህዝብን ዐይን ይገልጣሉ፣ ያንቀሳቅሱታል የሚባሉ ማህበራት፣ ድርጅቶችና ፓርቲዎች፣ የነቁ፣ የተቡ፣ ሥነ - ምግባር የተላበሱና ከሁሉም በላይ አርቀው ማስተዋል የሚችሉ ሊሆኑ ይገባል። ታግለው የሚያታግሉ፣ ነቅተው የሚያነቁና የተደራጀ ህዝብ የሚከተላቸው መሆንም አለባቸው፡፡ ሥርዓትን መውለድ፣ ሥርዓታዊ አስተዳደርን ማበልፀግ አለባቸው፡፡ ገብረ ህይወት ባይከዳኝ ያሉትን እዚህ ላይ መጥቀስ አግባብነት አለው፡-
“አዕምሮ የሌለው ህዝብ ሥርዓት የለውም፡፡ ሥርዓት የሌለው ህዝብም የደለደለ ኃይል የለውም፡፡ የኃይል ምንጭ ሥርዓት ነው እንጂ የሠራዊት ብዛት አይደለም፡፡ ሥርዓት ከሌለው ሰፊ መንግስት ይልቅ ትንሽ ከተማ ሞያ ትሰራለች፡፡”
ሥርዓታዊ አስተዳደር ሲባል፣ ከሁሉም በላይ ገዢም ተገዢም የሚዳኙበትና የሚያከብሩት ደንብ ማለት ነው፡፡
ህዝብን የማያዳምጥ ፓርቲም ሆነ መንግስት ዕድሜ አይኖረውም፡፡ እኔ ያልኩት ብቻ ነው ትክክል ማለትም ብዙ መንገድ አያስኬድም፡፡
ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ እንዲህ ይሉናል፡- “እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ደሀና ደካማ ሀገሮች ትልቁ አደጋ እንዲህ ያለ መንግስት ዘፈኔን ካልዘፈናችሁ፣ እስክስታዬን ካልወረዳችሁ እያለ ክብራቸውን ከመንካትም አልፎ ማለቅያ ወደ ሌለው ጦርነትና ውጥረት ውስጥ እንዳያስገባቸው ነው፡፡ በአሜሪካ ዳፋ ኢትዮጵያ ከዐረቦችና ሙስሊሞች ጋር ተጣላች ማለት፤ ከውጪም ከውስጥም በእሳት ስትለበለብ ኖረች ማለት ነውን፡፡ (ምን ዓለምን? የት ደረስን? ወዴትስ እያመራን ይሆን?)
ትውልዶች ያለሙት ዒላማ በየለውጡ ኩርባ (turning point) መመርመር አለበት፡፡ ምን ምን የሰመረ ነገር ታየ? ምን አጋጣሚ ተሳተ? ምን ምን ሥተት ተሰራ? ምን ላይ ፈር ቀደድን? ምን ላይ ባቡሩ ሐዲዱን ሳተ? ማለት ይገባል፡፡
የሄድንበት መንገድ አንዱ ችግር ቃልና አፈፃፀም አለመጣጣማቸው ነው፡፡ “በተለይ መብትን በተመለከተ፡፡ በሕገ - መንግሥት የተረጋገጡ መብቶች በተግባር ሲሻሩ ይታያሉ፡፡” ይላሉ ፀሐፍት በተደጋጋሚ፤ ስለ አፈፃፀም ችግር ሲያወጉ፡፡
ማንም ይፈፅመው ማን፤ ከየትኛውም ሀረግ ጋር ይጠላለፍ፤ ሙስናን መዋጋት ሌላው ግዴታችን ነው፡፡ እነ እገሌ ካሉበት ሙስናውን ማጋለጥ አደገኛ ነው እያሉ ገሸሽ ማለት ይሄው እዚህ አድርሶናል፡፡
“ኢትዮጵያ አንዴ በመደብ ስትመራ፣ አንዴ በብሔረሰብ ስትመራ ቆይታ፣ ወደፊት እጣ ፈንታዋ ከነዚህ ሁሉ የከፋው የሃይማኖት ጦርነት እንዳይሆን የብዙ ተመልካቾች ሥጋት ነው!” ይላሉ ፀሐፍት፡፡ የሃይማኖትን አያያዝ ማወቅ ዋና ነገር መሆኑ ብቻ ሳይሆን ከጀርባው ያሉትንም ኃያላን ነቅቶ ማየት እጅግ ወሳኝ ነገር ነው፡፡ ጠንቀቅ እንበል፡፡
የሀገራችን ሌላው አስገራሚ ነገር ህዝብ ያደነቀውና ሆይ ሆይ ያለለት ታጋይ (ልክም ይሁን አይሁን) ሲገል ቆይቶ አንድ እክል ከገጠመው እንዳልነበር መረሳቱ ነው፡፡ ያላንተ ማናለን ሲባል የነበረ ታጋይ፣ መሪ ወይም ንቁ ሰው፤ ሲታሰር ወይም ካገር ሲወጣ ከአዕምሮአችን ጨርሶ ለመውጣት ሁለት ሳምንት አይፈጅበትም፤ ፈፅሞ ይረሳል፡፡ ያውም ምን አቅብጦት እዛ ነገር ውስጥ ገባ? ተብሎ ካልተተቸ ነው! ይሄ እንግዲህ ከዓመታት በፊት የተሰውለትን ሳይጨምር ነው!
ሌላው በእስከዛሬው መንገዳችን ያየነው ጉዳይ፣ የጠቅላይ ገዢነት አመለካከት ነው፡፡ በዝግ ባህላችን ላይ ይሄ ሲታከልበት “በደምባራ በቅሎ፣ ቃጭል ጨምሮ ነው!” ከዚህ ይሰውረን!
ፕሮፌሰር ባህሩ በዚያው ፅሑፋቸው፤ “ሁሉን አውቃለሁ ከማለት የሌሎችንም ሀሳብ ለማዳመጥ ዝግጁ መሆን፣ ሁሉንም ጠቅልዬ ልያዝ ከማለት ለመጋራት መዘጋጀት፣ ከሁሉም በላይ በስሙ የምንገዳደልበት ሰፊ ህዝብ የሚበጀውን አሳምሮ እንደሚያውቅ ተገንዝበን ከሱ መሬት የቆነጠጠ እውቀት ለመማር ዝግጁ መሆን ይኖርብናል፡፡” … በኢኮኖሚውም ረገድ፡፡ “የተማረ የሰው ኃይላችንን ተንከባክቦ መያዝ፣ ለግሉ ክፍለ ኢኮኖሚ ሰፊ ዕድል መስጠት የዕድገታችን መሰረት ነው… ከእርሻ ኢኮኖሚ ያገኘነው ቋሚ ድህነትንና ተደጋጋሚ ረሀብን ብቻ ነው፡፡ የትም ያላደረሰንን በጥቃቅን የገበሬ ማሳዎች ላይ የተመሰረተውን የእርሻ ኢኮኖሚ ትተን ወደ ኢንዱስትሪያል ኢኮኖሚ በፍጥነት የምንሸጋገርበትን ስልት ስናወጣ ነው የምናድገው” ይሉናል፡፡ የሰብዓዊ መብቶችም ሆኑ የዲሞክራሲ መብቶች በልካችን እንዲሰፉ የታሰበ እለት “መላው ቀለጠ!” “ገደደ!” ማለት ብቻ ነው የሚተርፈን፡፡ የመናገርና ሀሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት የምንታገልለት፣ ሳናሰልስ የምንጮህለት፣ መቼም ወደ ኋላ የማንልበት ጉዳይ ቢሆንም፣ የማይጥመን ነገር ካለ፣ የአቦይን በሳል አስተሳሰብም እንጋራለን “በዲሞክራሲ ዝም ማለትም ይቻላል!” እንላለን፡፡  

Read 4528 times