Sunday, 10 May 2015 15:31

ህይወታችን እና የኢትዮጵያ እርምጃ

Written by  ተፈሪ መኮንን
Rate this item
(0 votes)

ታሪክ፤ ‹‹ህይወት እና እርምጃን›› መለስ ብሎ የማየት ጥበብ ነው፡፡ በዚህ ፅሁፍ፤ ሚያዝያ 27 የተከበረውን ‹‹የኢትዮጵያ አርበኞች መታሰቢያ›› በዓልን ሰበብ በማድረግ፤ ከ73 ዓመታት በፊት፤ ሮበርት ጋሌ ውልበርት (Robert Gale Woolbert) የተባለ ፀሐፊ፤ በ‹‹ፎሪን ፖሊሲ›› መፅሔት፤ ‹‹የኢትዮጵያ የወደፊት ዕጣ›› (The Future of Ethiopia) በሚል ርዕስ ባወጣው አንድ መጣጥፍ ያቀረበውን አስተያየት በመዳሰስ ታሪክን ለመዘከር ሞክሬያለሁ፡፡
ይኸው ፀሐፊ፤ ጁላይ 1936 ዓ.ም (እኤአ)፤ ‹‹The Rise and fall of Abyssinian Imperialism›› በሚል ርዕስ ያቀረበው ሌላ ፅሑፍ አለው፡፡ ኢትዮጵያ በጣሊያን ስትወረር ከፍ ሲል በተጠቀሰው ርዕስ ፅሁፍ ያቀረበው ይህ ፀሐፊ፤ ነፃነቷን ባገኘች ማግስትም ‹‹የኢትዮጵያ የወደፊት ዕጣ›› (The Future of Ethiopia) በሚል ርዕስ ሌላ ፅሑፍ አስነብቧል፡፡ ውልበርት፤ ኢትዮጵያን እንደ ‹‹አፍሪካ በቀል›› ኢምፔሪያሊስት ኃይል ይገልፃታል፡፡ እናም ፋሽስት ጣሊያን ኢትዮጵያን በወረረች ጊዜ፤ ‹‹የአፄ ኃይለስላሴ መንግስት መፈራረስ፤ በአፍሪካ አህጉር ውስጥ የመጨረሻ ሐገር በቀል ኢምፔሪያሊስት የሆነ አንድ መንግስት ግብዓተ መሬቱ ተፈፀመ›› በማለት ፅፎ ነበር፡፡
ውልበርት፤ ‹‹የዓለም ኃያል መንግስታት የሰሜን - ምስራቅ አፍሪካን በቀጥታ ከመቆጣጠር ይልቅ፤ የቱርክ፣ የግብፅ እና የአቢሲኒያ ኤምፓየሮች እንዲስፋፉ በማድረግ የአውሮፓን ስልጣኔ በተዘዋዋሪ መንገድ ሥር እንዲይዝ ለማድረግ መሞከር ይበጃል›› የሚል አመለካከት እንደ ነበረ ጠቅሶ፤ ብዙ ሳይቆይ የቱርክ ኤምፓየር መፈራረሱን እና የግብፅ መንግስት ግዛት እያስፋፋ ኑቢያን፣ ኮርዶፋን እና ስናርን እንደተቆጣጠረ ይገልጻል፡፡
ግብፅ ከዚህም በላይ ግዛቷን ለማስፋፋት ትፈልግ ነበር የሚለው ይኸው ፀሐፊ፤ በወታደራዊ ኃይል የናይል ወንዝ ምንጭን ለመቆጣጠር በነበራት ፍላጎት የነጭ አባይን (ኋይት ናይል) መነሻ ለመቆጣጠር ችላ እንደ ነበር፤ እንዲሁም የአውሮፓ እና የአሜሪካ የጦር መኮንኖችን በጦርነቱ እንደተጠቀመች ይናገራል፡፡ ለምሣሌ፤ ከ1869 እስከ 1878 ዓ.ም (እኤአ) ባሉት ዓመታት አርባ ዘጠኝ የሚደርሱ በአሜሪካ ‹‹ሲቪል ዋር›› (የነፃነት ትግል) ተሳታፊ የሆኑ ጀነራሎችን በጦርነቱ አሰልፋ ነበር፡፡  
ግብፅ፤ የአሜሪካ እና የአውሮፓ የጦር መኮንኖችን ተጠቅማም፤ ኢትዮጵያን መያዝ አልቻለችም፡፡ በሂደትም እየተዳከመች መጣች፡፡ ኢስማይል የተባለው የግብፅ ንጉስ፤ ግዛቱን የማስፋፋት እና ስዊዝ ካናልን የመገንባት ትልቅ ምኞቱን ለማሳካት፤ ሐገሪቱን ለአራጣ አበዳሪ ሊሸጣት ተቃርቦ ነበር፡፡ በዚህ ተነሳ ችግር ውስጥ ገባ። በመጨረሻም ግብፅ በ1882 ዓ.ም (እኤአ) ከእንግሊዝ እጅ ወደቀች፡፡ ሱዳንም ከእጇ ወጣች፡፡ በቀይ ባህር ዳርቻ፤ ከምፅዋ በስተደቡብ የነበራት ግዛትም በጣሊያን ተወሰደ፡፡ በዚህም፤ በአፍሪካ ኤምፓየር የመመስረት ፍላጎትዋ እንደ ጉም በኖ ጠፋ፡፡
ኢትዮጵያ ለቅኝ ገዢዎች ሴራ ሳትንበረከክ ቆየች። ሮበርት ጋሌ ውልበርት  ‹‹ኢትዮጵያ ነፃነቷን ጠብቃ ለመኖር የቻለችው፤ በአስቸጋሪ መልክዐ ምድር የምትገኝ ሐገር በመሆኗ ነው›› ቢልም፤ ነገሩን በዚህ ብቻ ወስኖ ለማለፍ አልሞከረም፡፡ እንደ ውልበርት ሁሉ፤ ሌሎች የአውሮፓ ቅኝ ገዢ ፀሐፊዎች፤ ‹‹ኢትዮጵያ በተራራ የተከበበች ሐገር በመሆኗ የተነሳ በጦር ለመውጋት የማትመች ስለሆነች ቅኝ ገዢዎች ሊቆጣጠሯት አልቻሉም›› ብለው ለመደምደም አልቻሉም፡፡ ስለዚህ የኢትዮጵያ ነገስታት የአመራር ብቃትን ለዓላማቸው አለመሳካት ምክንያት አድርገው ይጠቅሳሉ፡፡ ውልበርት፤ አፄ ዮሐንስ፣ ምኒልክ እና ኃይለስላሴ ልዩ የመሪነት ብቃት በተፈጥሮ የታደሉ መሆናቸውን ገልፆ፤ በተለይ አፄ ምኒልክ ከሌሎቹ ላቅ ያሉ መሆናቸውን ያነሳል፡፡
በዚህ የተነሳ የአውሮፓ ቅኝ ገዢዎች፤ ኢትዮጵያ የማትሞከር ሆናባቸው ተወት ሲያደርጓት ‹‹አልሰሜን ግባ በለው›› እንደሚባለው ሆኖ፤ አፍሪካን በመቀራመት ሂደት አርፍዳ የመጣችው ጣሊያን፤ በጉምዥት፣ ባለማመወቅ እና አማራጭ በማጣት ጭምር ኢትዮጵያን ለመያዝ ተመኘች፡፡ ሞከረች፡፡
በነፃነት ማግስት
ከፍ ሲል እንደገለጽኩት፤ በዚህ መጣጥፍ የማተኩረው፤ ሮበርት ጋሌ ውልበርት፤ ‹‹የኢትዮጵያ የወደፊት ዕጣ›› (The Future of Ethiopia) በሚል ርዕስ ባቀረበው ፅሑፍ ላይ ነው፡፡ ፀሐፊው ይህን ጽሁፍ ባሳተመ ጊዜ፤ ኢትዮጵያ ገና ነፃነት ማግኘቷ ነበር፡፡ የወደፊት ዕጣ ፈንታዋ ገና ግልፅ አልነበረም። ስለዚህ ‹‹ኢትዮጵያ ከአክሲስ ፓወር ቁጥጥር ነፃ ብትወጣም፤ አሁንም ነፃነቷ ፈተና እንደተጋረጠበት ነው›› ይላል፤ የፎሪን ፖሊሲ መፅሔት ፀሐፊው ሮበርት ጋሌ ውልበርት:: ውልበርት፤ የዛሬ 73 ዓመት በኤፕሪል 1942 እትም ላይ ባቀረበው መጣጥፉ፤ ‹‹የአክሲስ ኃይሎች›› ከሚባሉት ሦስት ሐገራት፤ (ጣሊያን፣ ጀርመን እና ጃፓን) አንዷ በሆነችው ጣሊያን፤ ‹‹በመጀመሪያ የተወረረች ሐገር ኢትዮጵያ ናት፡፡ ነፃነትን በመቀዳጀትም የመጀመሪያዋ ሐገር ነበረች›› ይላል፡፡
ሌሎች ‹‹በአክሲስ ፓወር›› የተወረሩ ከደርዘን በላይ ሐገሮች ነበሩ፡፡ ታዲያ ይህን ‹‹የአክሲስ ኃይሎችን›› እንቅስቃሴ ለመግታት ህብረት የፈጠሩ ሦስት ሐገሮች (አሜሪካ፣ እንግሊዝ እና ሩሲያ) ነበሩ፡፡ እነሱም ‹‹አላይድ ፓወር›› በሚል ይጠቀሳሉ፡፡ እናም ‹‹በአክሲስ ኃይሎች›› ቁጥጥር ሥር የነበሩት ሐገሮች፤ በ‹‹አላይድ ፓወር›› ድጋፍ ነፃ ወጡ፡፡ በ‹‹አላይድ ፓወር›› ትብብር በመጀመሪያ ነፃ የወጣችው ሐገርም ኢትዮጵያ በመሆኗ፤ ‹‹አላይድ ፓወር›› ነፃ እንዲወጡ ያገዟቸውን ሐገራት ጉዳይ በተመለከተ ላራመዱት ፖሊሲ የመሠረት ድንጋይ የሆነ ሥራ የተሰራው የኢትዮጵያን ጉዳይ ከመፍታት ጋር ተያይዞ ነበር፡፡ ሆኖም እንደ መፅሔቱ ዘገባ፤ የጣሊያንን ኃይል በማንበርከክ ዘመቻ ወሳኝ ኃይል የነበረው የኢትዮጵያ ህዝብ ነበር፡፡
‹‹አላይድ ፓወር››፤ ሐገራቱን መልሶ በመገንባት ሂደት ለተከተሉት አካሄድ እንደ ቀመር ሆኖ የሚያገለግል ፖሊሲ ሲነድፉ፤ የኢትዮጵያን ሁኔታ መሠረት አድርገው ነበር፡፡ ቀመሩን በመፍጠር ሂደትም ልዩ ጥንቃቄ አድርገዋል፡፡ ምክንያቱም፤ የ‹‹አላይድ ፓወር›› ፖሊሲ እና አሰራር በስደት በሚገኙ መንግስታት፤ እንዲሁም ‹‹በአክሲስ ፓወር›› ቁጥጥር ሥር ባሉ ሐገራት ህዝቦች እይታ ሥር መሆናቸውን ተረድተዋል፡፡ ይህን መረዳት ብቻ ሣይሆን፤ የተሳሳተ ሥራ በመሥራት ‹‹የአክሲስ ፓወር›› ሐገራት፤ ለፕሮፓጋንዳ የሚሆን ስንቅ እንዳያገኙ ሥጋት አድሮባቸው በጥንቃቄ መሄድን መርጠዋል፡፡    
በምሥራቅ አፍሪካ፤ የጣሊያን ፋሽስታዊ ኃይል የመጨረሻ የሽንፈት ፅዋውን የጨለጠው እኤአ ኖቬምበር 28፣ 1941 ዓ.ም ጎንደር ውስጥ በተካሄደ ጦርነት ነበር። በዚህ ጦርነት፤ የእንግሊዝ ኤምፓየር፤ ከዩናይትድ ኪንግደም፣ ከምዕራብ አፍሪካ፣ ከሮዴሽያ፣ ከደቡብ አፍሪካ፣ ከኬንያ፣ ከሱዳን እና ከህንድ የተውጣጡ ወታደሮች በጦርነቱ እንዲሳተፉ አድርጓል፡፡ እንዲሁም፤ የቤልጀም ቅኝ ከነበረችው ኮንጎ እና ነፃነት ከተቀዳጁ የፈረንሳይ የአፍሪካ ቅኝ ሐገራት የተውጣጡ ወታደሮችም ነበሩበት፡፡
የ‹‹አላይድ ፓወር›› ለኢትዮጵያ አርበኞች እገዛ አደረገ እንጂ፤ ዋና መመኪያ ኃይል የነበሩት፤ የኢትዮጵያ አርበኞች ናቸው፡፡ የ‹‹አላይድ ፓወር›› በመልሶ ግንባታ ሂደት ለተከተሉት ፖሊሲ አንድ መነሻ ሆኖ ያገለገለውም ጉዳይ ይኸው ነበር፡፡ ሌላው ጃንዋሪ 2፣ 1942 ዓ.ም (እኤአ) የተመድ አባል ሐገራት በአሜሪካ ዋሽንግተን ተፈራርረመው ያወጡት መግለጫ ነው፡፡
ይህን የጋራ መግለጫ መሠረት አድረገው ከኢትዮጵያ ጎን ከተሰለፉ ሐገራት በተጨማሪ፤ የፋሽስት ጣሊያን በሀገሪቱ ላይ የከፈተውን ጦርነት በመቃወም ከኢትዮጵያ ጎን የተሰለፉ፤ ፀረ ኢምፔሪያሊስት አቋም ያላቸው (ጥቁር አሜሪካውያን ጨምሮ) በዓለም ዙሪያ የሚገኙ በርካታ ጥቁሮች  ነበሩ፡፡
ከዚህ ሌላ፤ አሜሪካ ‹‹ቃኘው ሻለቃ›› የተባለ ወታደራዊ ጣቢያ በኤርትራ በመገንባቷ የኢትዮጵያ ጉዳይ ያሳስባት ነበር፡፡ ‹‹ቃኘው ሻለቃ›› የተገነባው ለ‹‹አላይድ ኃይሎች›› የጦር መሣሪያ ለማቅረብ እና የጥገና አገልግሎት ለመስጠት ነበር፡፡ እንግሊዝ እንደገና በቆመው የአፄ ኃይለ ስላሴ መንግስት ላይ የምትከተለው ፖሊሲ ለአሜሪካ ትርጉም የሚሰጣት ከዚህ የተነሳ ነው፡፡
ቤኒቶ ሙሶሎኒ ጁን 10፣ 1940 ዓ.ም (እኤአ) የጦርነት ነጋሪት ሲጎስም፤ አዲስ ያቀናውን የምሥራቅ አፍሪካ ኤምፓየር ለአደጋ አጋልጦ ነበር፡፡ ዱቼ ሞሶሎኒ፤ በጊዜው የያዘው አንድ የተሳሳተ ስሌት ነበር፡፡ ሙሶሎኒ፤ ‹‹የፈረንሳይ ኃይል እየተዳከመ ሲመጣ፤ እንግሊዝም ወደ አዘቅት ትወርዳለች›› የሚል የተሳሳተ ግምት ነበረው። ይህም በሰሜን-ምሥራቅ አፍሪካ ሰፊ የጣሊያን ግዛት ለመመስረት የሚስችል አዲስ ዕድል እንዲከፈት ያደርጋል የሚል እምነት ነበረው፡፡ ሆኖም፤ ይህ ስሌት የተሳሳተ ነበር፡፡ የፋሽስት ጣሊያን መንግስት፤ የምሥራቅ አፍሪካ ግዛቱ ከጣሊያን የራቀ እና በቀላሉ ግንኙነት ለማድረግ የማያስችል በመሆኑ፤ ለማስተዳደር ማስቸገሩ አይቀርም።
የእንግሊዝ መንግስት በ1938 ዓ.ም (እኤአ) ኢትዮጵያ የጣሊያን ቅኝ ስለመሆኗ ዕውቅና ሰጥቶ ነበር። የእንግሊዝ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት፤ አፄ ኃይለ ስላሴ በስደት ሎንዶን እንዲኖሩ የፈቀደላቸው እንደ አንድ ስደተኛ ግለሰብ እንጂ፤ የስደት መንግስት እንዳለው መሪ ቆጥሯቸው አልነበረም፡፡
ይሁንና ውሎ ሲያድር እንግሊዝና ጣሊያን ተቃቃሩ። ስለዚህ እንግሊዝ በምሥራቅ አፍሪካ የፋሽስት ኃይል ላይ እርምጃ የምትወስደው መቼ ይሆን? ከሚል ጥያቄ በቀር፤ እርምጃ መውሰዷ የማይቀር መሆኑ ተረጋገጠ። ያልታሰበው ሆኖ፤ ሁለቱ ሐገራት ወደ ጦርነት ገቡ፡፡ በዚህ ጊዜ፤ እንግሊዝ እንደ ተራ ስደተኛ ታያቸው የነበሩት ንጉሥ፤ ትልቅ ዲፕሎማሲያዊ እና ወታደራዊ እሴት ያላቸው ሰው ሆኑ፡፡ ስለዚህ አፄ ኃይለ ስላሴን በእንግሊዝ አውሮፕላን ወደ ሱዳን እንዲበሩ አደረገች፡፡
እርሳቸው ስደት ከገቡበት ከ1936 ዓ.ም (እኤአ) ጀምሮ፤ በዱር በገደሉ ከጣሊያን ፋሽስታዊ ኃይል ጋር ሲፋለሙ የነበሩት የኢትዮጵያ አርበኞች ከአፄ ኃይለስላሴ ጋር ተቀላቀሉ፡፡ ጣሊያን፤ በምስራቅ አፍሪካ 200 ሺህ የሚደርስ እና በደንብ የታጠቀ እና የተሟላ አቅርቦት የሚያገኝ ኃይል ነበራት፡፡ የፀረ ፋሽስት ጦርነቱ በአብዛኛው በእንግሊዝ የጦር መኮንኖች ይመራ ነበር፡፡ በንጉሡ የሚመራው ጦር በተለይ ጎጃምን ነፃ በማውጣት ትልቅ ሚና የተጫወተ ሲሆን፤ አፄ ኃይለስላሴም ጃንዋሪ፣ 15፣ 1941 ዓ.ም የኢትዮጵያን ባንዲራ በኢትዮጵያ ምድር ላይ አውለበለቡ፡፡
ሆኖም አፄ ኃይለስላሴ፤ በእንግሊዝ ከሚመራው ጦር ቀድመው መዲናዋን የመቆጣጠር ክብር እና ዕድል አላገኙም፡፡ ይህን ክብር ያገኘው፤ ከሶማሌ የጁባ ወንዝ ምንጭ አካባቢ ከኪሲማዩ ተነስቶ፤ ከፌብሩዋሪ 14 እስከ ኤፕሪል 5 ባሉት ሰባት ሣምንታት ጉዞ መቋዲሾን አቋርጦ፣ ሐረርን ተሻግሮ አዲስ አበባ የገባው የደቡብ፣ የምዕራብ እና የምሥራቅ አፍሪካ ጥምር ጦር ነው፡፡
በሰባት ሣምንታት 1 ሺህ 850 ኪሎ ሜትር ተጉዞ አዲስ አበባ የገባው ጦር፤ በየቦታው ያገኘውን በርካታ የጣሊያን ጦር እየደመሰሰ፤ በርካታ የስንቅ እና ትጥቅ መጋዘኖችን እየተቆጣጠረ ዘለቀ፡፡
የኦስታው ዱክ አምባላጌ ላይ ተሸነፈ፡፡ በዚህ ጊዜ፤ እዛም - እዛም ያሉ የማዘዣ ጣቢያዎችን ከመቆጣጠር በቀር፤ ጦርነቱ በወሳኝ መልኩ ተጠናቅቆ ነበር፡፡ ይህ ፈጣን የድል ግስጋሴ፤ የዚህ ዘመቻ ወታደራዊ እንቆቅልሽ ሆኖ በታሪክ ተመዝግቧል፡፡ በቁጥር ትንሽ የሆነ ኃይል፤ በርካታ ቁጥር በነበረው የጦር ኃይል ላይ በአጭር ጊዜ እንዲህ ያለ ከፍተኛ ድል እንዴት ሊጎናፀፍ ቻለ? የሚለው ጥያቄ፤ በርካታ ኃይል እና አስተማማኝ አቅርቦት ያለውን፤ እንዲሁም ስፍር ቁጥር የሌለው ለመከላከል ጦርነት ምቹ የሆነ መሬት የተቆናጠጠው የፋሽስት ጣሊያን ኃይል እንዲህ እንደ ቀላል የመበታተኑ ምስጢር የሞራል ውድቀት መሆኑን ወታደራዊ ጠበብት ይናገራሉ፡፡ የፋሽስት ጣሊያን ጦር፤ ከግማሽ ልብ ከፍ ባለ ወኔ ጦርነት ሲገጥም የታየው፤ ከረን ላይ በተካሄደው ጦርነት ብቻ ነበር፡፡ በመጨረሻ፤ ሙሶሎኒ ኢትዮጵያን ለመቆጣጠር ከወሰደበት ጊዜ በጣም ባጠረ ጊዜ ተፈረካክሶ ከጥቅም ውጭ ሆነ፡፡
በድል ማግስት
ከዚህ በኋላ፤ አፄ ኃይለስላሴ ከእንግሊዝ መንግስት ጋር ያላቸውን ግንኙነት አጠበቁ፡፡ ፌብሩዋሪ 4፣ 1941 ዓ.ም (እኤአ) የእንግሊዝ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኤደን በፓርላማው ፊት ቀርቦ፤ የእንግሊዝ መንግስት ነፃ የኢትዮጵያ መንግስት ዳግም እንዲመሰረት ፈቃደኛ መሆኗን እና የዚህ መንግስት ዙፋን የኃይለስላሴ መሆኑን ዕውቅና መስጠቷን ገለፀ፡፡ አፄ ኃይለስላሴ የውጭ መንግስታት ዕርዳታ እና ምክር ለመቀበል ዝግጁ መሆናቸውንም ገለፀ፡፡
የእንግሊዝ መንግስት የንጉሡን የዕርዳታ እና ምክር ጥያቄ የተቀበለ መሆኑን ኤደን ጠቅሶ፤ እንዲህ ዓይነት የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ስምምነት ለማድረግ የተለያዩ ሐገራት የሚሳተፉበት ዓለም አቀፍ ስምምነት ማድረግ እንደሚያስፈልግም አስታወቀ፡፡ እንግሊዝ በኢትዮጵያ ውስጥ ግዛት የማስፋፋት ፍላጎት እንደ ሌላት አመልክቷል። ከዚህ ሌላ፤ በኢትዮጵያ የሚካሔደው ወታደራዊ ዘመቻ፤ እንግሊዝ ወታደራዊ አመራር እና ውሳኔ የመስጠት ጊዜአዊ ሥልጣን እንዲኖራት ማድረግን የሚጠይቅ ሥራ እንደሆነ ገልጦ፤ ይህም ሥራ ከንጉሡ ጋር በመመካከር የሚፈፀም እና ሁኔታው በፈቀደ ፍጥነት እንግሊዝ ራሷን ከዚህ ኃላፊነት እንደምታወጣ አስታውቆ ነበር፡፡ እንግሊዝ ይህን ቃል የገባችው፤ ከጦርነቱ በፊት ሲሆን የጣሊያን የምሥራቅ አፍሪካ ቅኝ ግዛት እንደሚፈርስ በመገመት የወሰደችው ውሳኔ ነበር፡፡
አፄ ኃይለስላሴ ስደት ከወጡ ከ5 ዓመታት በኋላ መናገሻ ከተማቸው ከሆነችው አዲስ አበባ ገቡ፡፡ ወዲያው ሚኒስትሮቻቸውን ሰይመው፤ በመዲናዋ እና በጠቅላይ ግዛቶቻቸው የመንግስት አስተዳደራቸውን እንደገና ለመመስረት ደፋ ቀና ማለት ያዙ፡፡ ከዚህ ጎን ለጎን፤ እንግሊዝ የራሷን አስተዳደር ለማፅናት ከፍተኛ ጥረት አደረገች፡፡ አንዳንዴም ከኢትዮጵያ መንግስት የበላይ የመሆን ሁኔታ ታሳይ ነበር፡፡
እንግሊዝ፤ በአስተዳደር ሥራው ተሳታፊ እንዲሆኑ ያደረገችው ሰዎች ወታደሮች ብቻ መሆናቸውን ለማሳየት ብትሞክርም፤ ቁጥራቸው ቀላል የማይባል በእንግሊዝ የቅኝ ግዛት አስተዳደር ውስጥ ተሳታፊ የሆኑና ከፍተኛ ልምድ ያላቸው ሰዎች ወደ ኢትዮጵያ እንደላከች ግልፅ ነበር፡፡ ስለዚህ ነገሩ ያላማራቸው የኢትዮጵያ ወዳጅ የሆኑ እንግሊዛውያን ስጋታቸውን መግለፅ ያዙ፡፡ በተለይ በቅኝ አገዛዝ አስተዳደር ልምድ ያላቸው ባለሥልጣናት በማስተዳድሩ ተሳታፊ መሆናቸው፤ የእንግሊዝን ጉዳይ አሳሳቢ አድርጎት ነበር፡፡ ለረጅም ዘመን የዘለቀ ራስን በራስ የማስተዳደር እና የመንግስት አመራር ልምድ ባለው ወዳጅ ህዝብ ላይ የቅኝ አገዛዝ አስተዳደር ልምድ ያላቸውን ሰዎች መሰየሟ ሥጋት ያሳደረባቸው በርካቶች ነበሩ፡፡ በመሆኑም፤ በእንግሊዝ ፓርላማ ከሚነሱ ጥያቄዎች መካከል፤ ‹‹የእንግሊዝ መንግስት ለኃይለስላሴ ዕውቅና የሚሰጠው እና የነፃ ሐገር መሪ መሆናቸውን ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያ በፀረ ፋሽስት ትግሉ የእንግሊዝ መንግስት አጋር ሆና በጦርነቱ የተሰለፈች ሐገር ስለመሆኗ ዕውቅና የሚሰጠው መቼ ነው?›› የሚል ጥያቄ ይነሳ ጀመር፡፡ ‹‹ከጦርነቱ በፊት፤ የመጨረሻው ድል እስኪገኝ ድረስ እርሳቸውም ሆኑ የኢትዮጵያ ህዝብ የፋሽስት ኃይልን በጦር ለማንበርከክ ዝግጁ መሆናቸውን አፄ ኃይለስላሴ መግለፃቸው መዘንጋት የለበትም፡፡ የእንግሊዝ መንግስት ይህን መርሳት አይገባውም›› በማለት የፓርላማ አባላት ጥያቄ ያነሱ ነበር፡፡
በመጨረሻም፤ የእንግሊዝ መንግስት ጃንዋሪ 19፣ 1942 ዓ.ም (እኤአ)፤ ለሁለት ዓመታት የሚቆይ ስምምነት ከኢትዮጵያ ጋር መፈራረሙን አሳወቀ። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ኤደን ፌብሬዋሪ 3፣ 1942 ዓ.ም (እኤአ) በሰጠው መግለጫ እንዳሳወቀው፤ የዚህ ስምምነት አጠቃላይ ይዘት፤ የእንግሊዝ መንግስት ለኃይለስላሴ መንግስት ኦፊሴላዊ ዕውቅና የሰጠ መሆኑን፤ የ2.500.000 ፓውንድ ዕርዳታ መሰጠቱን፤ በወታደራዊ ተልእኮ ረገድ እና በሌሎች የተለያዩ መስኮች ምክር ለመለገስ ዝግጁ መሆኑን የሚያመለክት ነበር። ይህም እርዳታ ለኢትዮጵያ መንግስት የተሰጠው፤ እንግሊዝ በጦርነቱ ሂደት የኢትዮጵያን የጦር ማዘዣዎች እና የግንኙነት አውታሮች የተጠቀመች በመሆኑ፤ ይህን ውለታ ለመክፈል ታስቦ እንደሆነ ተነግሯል፡፡
ከእንግሊዝ ሌላ በዚህ ታሪክ ሁነኛ ሥፍራ ያላት ሐገር አሜሪካ ናት፡፡ አሜሪካ ለፋሽስት ጣሊያን የኢትዮጵያ ቅኝ ግዛት ዕውቅና አልሰጠችም፡፡ እንዲያውም የአሜሪካ መንግስት፤ ከአፄ ኃይለስላሴ መንግስት ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት መመስረት ይፈልጋል። አሜሪካ ይህን ማድረግ የፈለገችው፤ ነገሩን በፍትህ ሚዛን አስልታ ብቻ አልነበረም፡፡ ይልቅስ በአዲስ አበባ እና ቤሎች የኢትዮጵያ ከተሞች የዲፕሎማቲክ መቀመጫ ማግኘት እና የቆንስላ ጽ/ቤቶችን በመክፈት ወኪሎቿን ማስቀመጥ፤ አካባቢውን የተመለከተ መረጃ ለማሰባሰብ በር እንደሚከፍትላት በማሰብ ነበር፡፡ አሜሪካ፤ በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ጥሩ ከበሬታ ነበራት፡፡ ስለዚህ በኢትዮጵያ መቀመጫ ማግኘት ‹‹ከአላይድ ፓወር›› ጋር መልካም ግንኙት ለመመስረት ምቹ ሁኔታ እንዲሚፈጥርላት ተረድታለች፡፡
ፀሐፊው ሮበርት ጋሌ ውልበርት፤ ‹‹ኢትዮጵያ፤ የተመድ አባል ሐገር እና የዋሽንግተን ስምምነት ፈራሚ (ጃንዋሪ 2፣ 1942) ነች፡፡ ኃይለስላሴ እና የኢትዮጵያ አርበኞችም የፀረ-ፋሽስት ኃይልን ትግሉን አስቀድመው የተቀላቀሉ ናቸው፡፡ በወቅቱ የተመድ አባል የሆኑት ሃያ ስድስቱ ሐገራት፤ ‹‹ጦርነቱ የእኛም ጦርነት ነው›› የሚል አቋም ከመውሰዳቸው አስቀድሞ ኢትዮጵያ ጦርነት ውስጥ ገብታለች፡፡ ስለሆም፤ እነዚህ ሐገራት የኢትዮጵያን ውለታ በትንሹም ቢሆን ሊመልሱ የሚችሉት፤ እሷም እንደነሱ ነፃ ሐገር መሆኗን በመቀበል ነው፡፡ ይህን ማድረግም ብልህ ዲፕሎማሲያዊ ስትራተጂ ነው፡፡ ይህን በማድረግ ‹‹የአላይድ ፓወር›› የጥቁር ህዝቦችን እና በቅኝ ግዛት የሚማቅቁ ሐገሮችን ልብ ለማሸነፍ ይችላሉ›› ብሎ ነበር፡፡
አሜሪካ፤ እነጣሊያንን (አክሲስ ፓወርን) የሚያጠናክር ነገር እንዲፈጠር አትፈልግም፡፡ እንዲሁም፤ ሌላ ጦርነት ሊቀሰቅስ የሚችል ቅሬታ እንዲፈጠር አትሻም፡፡ በዋሽንግተን ለተፈረመው ስምምነትም ተገዢ መሆን ትፈልጋለች፡፡ ይህ የዋሽንግተን ስምምነት ኢትዮጵያ ነፃ ሐገር መሆንዋን የሚደግፍ ስምምነት ሲሆን በወቅቱ ‹‹የኢትዮጵያ የወደፊት ሁኔታ ምን ይሁን?›› የሚለው ጥያቄ ሲመጣ፤ አነጋጋሪ ነጥብ ሆኖ የወጣው የድንበር ጉዳይ ነበር፡፡
በዚህ ረገድ በእንግሊዝ የተንፀባረቀው አስተሳሰብ በሦስት ዋና ዋና ጎራዎች የተከፈለ ነበር፡፡ አንደኛው ወገን፤ ሊበራል እና ፀረ ኢምፔሪያሊስት አቋም አራማጆችን የያዘ ነው፡፡ በዚህ ጎራ ያሉ እንግሊዛውያን፤ የኢትዮጵያ ድንበር ከ1935 ዓ.ም (ከጦርነቱ በፊት) የነበረውን ግዛት የሚያካትት ብቻ መሆን የለበትም፡፡ ይልቅስ፤ ኤርትራን፣ ምናልባትም የፈረንሳይ ሶማሌላንድን (ጅቡቲን) እንዲሁም የጣሊያን ሶማሌላንድን (ሰሜን ሶማሊያን) የሚያካትት ግዛት ሊሆን ይገባል የሚል አቋም ነበራቸው። ይህን አቋም የያዙት ወገኖች፤ ምክረ ሐሳባቸውን ሊደግፉ የሚችሉ በርካታ ጅኦግራፊያዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ብሔረሰባዊ ጉዳይን በመጥቀስ ይከራከራሉ፡፡ በሌላ በኩል፤ ‹‹ከፍተኛ ቁጥር ያለው ደጋፊ እና ከፍተኛ ተፅዕኖ የማሳደር አቅም ያለው›› በሚል የሚጠቀስ ቡድን ደግሞ፤ ‹‹ኢትዮጵያ ተስፋ በሚያሳጣ ሁኔታ እጅግ ኋላ ቀር ሐገር በመሆኗ፤ ከ1935 በፊት በነበረው ግዛቷ ላይ ሌላ ይጨመርላት የሚለው ሐሳብ ተቀባይነት የሌለው ነው። ይህ ሊሆን አይገባም፡፡ እንዲያውም፤ አማርኛ ተናጋሪ እና ክርስቲያን ያልሆነውን ህዝብ ለብቻ በመነጠል፤ ነባር የአቢሲኒያ ግዛት በሆነው የሐገሪቱ ክፍል ለሚኖረው ህዝብ የይስሙላ ነፃነት ሰጥቶ በእንግሊዝ ሞግዚትነት እንዲተዳደር ማድረግ ያስፈልጋል›› የሚል አቋም የሚያራምድ ነበር፡፡ ይህ ምክረ ሐሳብ፤ ‹‹Hoare-Laval Plan›› በሚል የሚታወቀውን ዕቅድ እንደገና የሚጎትት እና መልሶ የሚያፀና ቢሆንም፤ ይህን አቋም የሚያራምዱ ወገኖች አፄ ኃይለስላሴ ‹‹ምክር እና ዕርዳታ›› ሊቀበሉ ይገባል የሚል አስተያየት በአፅኖት ያስተገባ ነበር፡፡ ሦስተኛው ወገን ደግሞ፤ ልቡ ለጣሊያን የሚራራ ነበር። እንደ ሻለቃ ፖልሰን ኒውማን ያሉ ለጣሊያን የቅኝ ግዛት ታሪክ ትልቅ ግምት የሚሰጡ ወገኖች፤ ‹‹ከጦርነቱ በኋላ ቢያንስ ኤርትራ እና ሶማሊያ እንደማስተዛዘኛ ለጣሊያን ሊመለስላት ይገባል›› ባዮች ነበሩ፡፡ ዋና ዋናዎቹ የሐሳብ ቡድኖች እነዚህ ቢሆኑም፤ ከሦስቱ ወደ አንዱ ሊደመሩ የሚችሉ አስተያየቶች ነበሩ፡፡
ከዚህ ሌላ፤ ከሰሃራ በታች ያለውን የአፍሪካ ምድር አንድ አድርገው የሚመለከቱ እና ከሰሃራ በታች ያለው የአፍሪካ ምድር፤ የደቡብ አፍሪካ ኢምፔሪያሊስታዊ ኃይል ግዛት ሊደረግ ይገባል የሚል አቋም የያዙም ነበሩ፡፡ ከዚህ ሌላ፤ ‹‹የተባበሩት የአፍሪካ መንግስታት›› (United States of Africa) ይመስረት፤ ኢትዮጵያም የዚህ ግዛት አካል ትሁን የሚል አመለካከት የነበራቸው ወገኖች ነበሩ። አሁን ወደ እንግሊዝ እንመለስ፡፡
አንዳንዶች፤ እንግሊዝ የኢትዮጵያን ነፃ መንግስትነት ለመቀበል እንዲያ ያቅማማችው፤ ከጦርነቱ በፊት (1935) የነበረውን የኢትዮጵያ ግዛት እንዳለ ለመቀበል ባለመፈለጓ ነበር ይላሉ፡፡ አስቀድማ የጣሊያንን የኢትዮጵያ ቅኝ ግዛት ስለተቀበለች፤ ‹‹እኔ ኢትዮጵያ ነፃ መንግስት ትሁን ስል፤ ቀደም ሲል የነበራትን ግዛት እንደ ያዘች ማለቴ አይደለም›› የሚል ማደናገሪያ ለማቅረብ ትችላለች፡፡ አሜሪካ እንዲህ የማድረግ ሐሳብ አልነበራትም፡፡ ከዚህ በተጨማሪ፤ በወቅቱ የተመድ አባል ሐገራት የነበሩት ሁሉ በፊርማቸው ያፀደቁት ‹‹አትላንቲክ ቻርተር›› የተሰኘው ሰነድ፤ ፈራሚዎቹ ሐገራት ምንም ዓይነት የግዛት ማስፋፋት እንቅስቃሴ እንዳያደርጉ የሚከለክላቸው ነበር። የድንበር ለውጥ የሚደረግ ከሆነም፤ ለውጡ በባለጉዳዩ ህዝብ ሙሉ ፈቃድ ላይ የተመሠረተ መሆን እንደሚገባው የሚያዝ ስምምነት ነበር፡፡
የማትከፈል አንድ
አንደ መፅሔቱ ዘገባ፤ በወቅቱ የኢትዮጵያን ህዝብ በሐይማኖት እና በብሔር መስመር ከፋፍሎ አዲስ ካርታ የመፍጠር ፍላጎት ነበር፡፡ ሆኖም፤  የህዝቡ ስብጥር ሐይማኖት እና ብሔርን መሠረት ያደረገ ድንበር ለመፍጠር የሚያመች አልሆነም፡፡ ሌላው ቀርቶ በካርታ እንኳን ለመሳል እስኪያቸግር ድረስ ህዝቡ ተቀላቅሎ የሚኖር በመሆኑ መቸገራቸው አልቀረም፡፡ ታዲያ በወቅቱ በ‹‹ፎሪን ፖሊሲ›› መጣጥፍ ያቀረቡት ፀሐፊ፤ የብሔር እና የሐይማኖት ልዩነት በኢትዮጵያ ታሪክ ያላቸውን ሚና ከጠቀሰ በኋላ፤ የኢትዮጵያ ሁኔታ በምኒልክ፣ በይበልጥም በአፄ ኃይለስላሴ ዘመነ መንግስት እየተለወጠ መምጣቱን ያመለክታል፡፡ እንደ አብነት የጠቀሰውም፤ የልጅ ኢያሱን ጉዳይ ነው፡፡
የምኒልክ የልጅ ልጅ የሆኑት የልጅ ኢያሱ አባት (የወሎው ንጉስ ሚካኤል) መሠረታቸው ኢስላም መሆኑን የጠቀሰው ይኸው ፀሐፊ፤ ‹‹ልጅ ኢያሱ ወደ እስልምና አዘነበሉ በሚል ከሥልጣን የወረዱበት ሁኔታ ቢፈጠርም፤ በኢትዮጵያ የእስልምና እምነት መሠረት ያለው ሰው ከዙፋን መውጣቱ፤ ነገሮች እየተለወጡ መምጣታቸውን የሚያመለክት ነው›› ይላል፡፡
አያይዞም፤ በተለይ የኦሮሞ ብሔር ተወላጆች የመንግስት ሥልጣን መያዝ መጀመራቸውን የሚጠቅሰው ይህ ፀሐፊ፤ የኢትዮጵያ መድህን የሚገኘው በዚህ ጎዳና እንደሆነ ይናገራል፡፡ ጠቅላላውን የኢትዮጵያ ግዛት የሚያቅፍ የኢትዮጵያዊነት ስሜት ገና እንዳልዳበረ ጠቅሶ፤ የፋሽስት ጣሊያን ወረራ ይህን ስሜት በመፍጠር ረገድ ጉልህ ሚና መጫወቱን ይገልፃል፡፡
ፀሐፊው፤ ጣሊያን ከምሥራቅ አፍሪካ መባረሯን ተከትሎ፤ የድንበር ጉዳይ በኢትዮጵያ ዙሪያ የሚገኙ (እንደ ኤርትራ እና ሶማሊያ ያሉ የጣሊያን ነባር የቅኝ ግዛት) ሐገሮችን ጉዳይ እንደሚጎትት በመግለፅ፤ የጅቡቲም ጉዳይ ምላሽ የሚጠይቅ ነገር መሆኑን ያወሳል። የተጠቀሱትን ሐገራት ጨምሮ ህዝቡ በተበታተነ አኳኋን በሰፈረባት እና በእንግሊዝ ሞግዚትነት የምትተዳደረውን ‹‹ሱማሌ - ላንድ›› የሚያካትተው ጅኦግራፊያዊ ክልል፤ መልክዐ ምድራዊ እና ብሔረሰባዊ ትስስር ስላለው፤ አካባቢው እንደ አንድ ሰፊ ግዛት ሊታይ የሚችል እንደሆነ በመጠቆም፤ ከሞላ ጎደል ‹‹ጎነ - ሦስት›› የሆነ ቅርፅ የሚይዘው ይህ ክልል፤ ኩታ ገጠም ሆኖ ከሚገኘው አካባቢ ተለይቶ ሊታይ የሚችል ልዩ ባህርይ እና መልክ ያለው ግዛት ነው ይላል፡፡ ከመልክዐ ምድራዊ አንድነት በተጨማሪ፤ ይህ ግዛት ከፍተኛ ብሔረሰባዊ (?) ወጥነት (ethnic homogeneity) የሚታይበት እንደሆነ ያስረዳል፡፡ ከሱዳን ጋር ያለውን ድንበር ተከትሎ ከሚኖሩ ህዝቦች በስተቀር፤ በዚህ ግዛት የሚኖሩት ህዝቦች፤ አንትሮፖሎጂስቶች ‹‹ኢትዮፒክ›› (Ethiopic type) የሚሉት ዓይነት አካላዊ ገፅታ ያላቸው ህዝቦች የሚኖሩበት መሆኑን በማንሳት፤ ይህ ክልል በአንድ አንዲጠቃለል ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ያስረዳል፡፡
ፀሐፊው በማያያዝ፤ ‹‹ከጦርነቱ በኋላ ለአፍሪካ የድንበር ጉዳይ እልባት ለመስጠት ሙከራ ሲደረግ፤ የኢትዮጵያ መንግስት ከጦርነቱ በፊት ከነበራት ግዛት ሰፋ ያለ የድንበር ጥያቄ እንደምታቀርብ አይጠረጠርም›› ይላል፡፡ አክሎም፤ ‹‹ንጉሡ ገና አዲስ አበባ ከመግባታቸው በፊት፤ በሎንዶን የኢትዮጵያ ሚኒስትር (?) ሆነው ሲያገለግሉ የቆዩት ዶ/ር ወርቅነህ ማርቲን፤ የበፋሽስት ጣሊያን ጦር በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ላደረሰው የከፋ ጭፍጨፋ ካሳ ይሆን ዘንድ፤ የአሰብ እና የምፅዋ ወደቦች እንዲሁም በሁለቱ ወደቦች መካከል ያለው የባህር ዳርቻ፤ አሁን ኤርትራ በሚል የሚጠራውን የሐማሴን ግዛት ጨምሮ ለኢትዮጵያ ሊሰጥ ይገባል፡፡ በእርግጥ፤ የህዝቡ ፍላጎት ተጠይቆ፤ የኢትዮጵያ ኤምፓየር ነፃ እና እኩያ አባል ለመሆን እንፈልጋለን የሚል ውሳኔ ካሳለፉ የጣሊያን ሱማሌ - ላንድ ግዛት በኢትዮጵያ ውስጥ እንዲካተት መደረግ አለበት ሲሉ ፅፈዋል›› በማለት አትቷል፡፡
እንዲያውም፤ አንዳንድ የእንግሊዝ የአደባባይ ሰዎች (publicists) ‹‹የፈረንሳይ ሱማሌላንድ የተባለችው ጅቡቲ፤ ለማዕከላዊ እና ደቡባዊ ኢትዮጵያ ክልሎች ምቹ የባህር በር ሆና የምታገለግል ስለሆነ፤ ለኢትዮጵያ ልትሰጥ ይገባል›› የሚል ሐሳብ ያራምዱ እንደ ነበረ ገልጧል፡፡
‹‹ኤርትራን ወይም ቢያንስ የኤርትራን ተራራማ ክፍሎችን በተመለከተ ኢትዮጵያ የምታቀርበውን የይገባኛል ጥያቄ ውድቅ ማድረግ አስቸጋሪ ነው›› የሚለው ፀሐፊው፤ ‹‹Round Table›› የተሰኘ አንድ ‹‹ሦስት - ወራዊ›› መፅሔት፤ የሴፕቴምበር 1941 ዕትም፤ ‹‹የቀይ ባህር እና የህንድ ውቂያኖስ ዳርቻዎች በኢትዮጵያ ዘንድ አመኔታ ሊፈጥር እና ለወጪ-ገቢ ዕቃዎች አስፈላጊውን አገልግሎት ሊሰጥ በሚችል አንድ መንግስት ሥር እንዲተዳደር ማድረግ ይገባል›› በሚል ያሰፈረውን ሐሳብ ይቃወማል፡፡
ተቃውሞውን ሲገልፅም፤ ‹‹ይህ ምክረ ሐሳብ ቢያንስ ቢያንስ ቀይ ባህርን በተመለከተ የተሳሳተ ምክር ይመስላል፡፡ የቀይ ባህር ዳርቻ፤ ከምፅዋ፣ ከአሰብ ከሌሎች ጥቂት ትናንሽ የሆኑ መንደሮች በቀር ሰው የማይኖርበት ነው፡፡ አሰብ እና ምፅዋ ትርጉም የሚኖራቸው ለደጋማው የኢትዮጵያ ክፍል ወደብ ሆነው ማገልገል ከቻሉ ብቻ ነው፡፡ ምፅዋን ከመሐል ሐገር መለየት ኢኮኖሚያዊና ጅኦግራፊካል ሐጢያት ነው (geographic and economic absurdity)፡፡ ኢትዮጵያ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ትርጉም እንዲኖራት ከተፈለገ፤ ወደብ ሊኖራት ይገባል፡፡ ኢትዮጵያ የባህር በር እንዲኖራት አለማድረግ ሊያሳካው የሚችለው ትርጉም ያለው ግብ፤ ሐገሪቱን ከፊል የቅኝ ግዛት ሁኔታ ውስጥ ማኖር ብቻ ነው›› በማለት አትቷል፡፡
‹‹የጅቡቲም ነገር ከዚህ የተለየ አይደለም›› የሚለው ይኸው ፀሐፊ፤ ‹‹ ፈረንሳይ በፓስፊክ እና በህንድ ውቂያኖስ ያላትን ግዛት ይዛ መቀጠል ከቻለች ጅቡቲ ምናልባት entrepôt ሆና ማገልገሏን ትቀጥላለች። ከወደቡ ውጭ ያለው የፈረንሳይ ሶማሌላንድ ምድር ወደ ኢትዮጵያ ሊጠቃለል ይችላል፡፡ ምክንያቱም በዚህ አካባቢ የሚኖረው ህዝብ በአጎራባች ከሚኖሩ የኢትዮጵያ ብሔሮች (አፋር እና ሶማሌ) ጋር አንድ ዓይነት ባህል ያላቸው ናቸው›› ይላል፡፡
ይህን ባህላዊ፣ ብሔረሰባዊ እና መልክዐ ምድራዊ አንድነት አንዲነጣጠል ማድረግ፤ ፖለቲካዊ ብልህነትን የማያንፀባርቅ፤ እንዲሁም ከመልክዐ ምድር አኳያ የማይሞከር ተግባር መሆኑን በመጥቀስ፤ ተፈላጊውን አንድነት ለማምጣት ይህን ተፈጥሮአዊ አንድነት በፖለቲካዊ አንድነት ማጠናከር እንደሚያስፈልግ ያትታል፡፡
ይህ ዓላማ እንዲሳካ አስተዋይ እና በሳል አመራር እንደሚጠይቅ፤ ለዚህም የኢትዮጵያ መንግስት የውጭ ዕርዳታ እና ምክር እንደሚያስፈልገው የሚናገረው ፀሐፊው፤ ‹‹በቅርቡ በኢትዮጵያ እና የእንግሊዝ መንግስታት መካከል ለሁለት ዓመታት የሚቆይ ስምምነት ተፈርሟል፡፡
በዚህ ስምምነት የእንግሊዝ ዳኞች በኢትዮጵያ ፍ/ቤቶች ያስችላሉ፤ የእንግሊዝ አማካሪዎች ለንጉሱ አስተዳደር ምክር ይለግሳሉ፤ የእንግሊዝ የጦር መኮንኖች ለጦር ሠራዊት እና ለፖሊስ ሠራዊት ስልጠና ይሰጣሉ። ስምምነቱ ተፈጻሚ በሚሆንበት ጊዜ በሐገሪቱ ግዛት ለሚከሰት ጦርነት የእንግሊዝ መንግስት ሙሉ ሥልጣን እንዲኖረው ተደርጓል፡፡ ይህ ሰፊ የአድራጊ ፈጣሪነት ሥልጣን፤ ኢትዮጵያን የእንግሊዝ ዲፋክቶ የሞግዚት አስተዳደር ያደርጋታል›› ሲል ፅፎ ነበር፡፡
ሆኖም ፀሐፊው እንደ ገለፀው፤ ‹‹በቅኝ ግዛት ከቆዩ ወይም ለረጅም ዘመን በውጭ አስተዳደር ሥር ከቆዩ ህዝቦች በተለየ ሁኔታ፤ የኢትዮጵያ ህዝብ ትዕግስት የሚኖረው፣ ልቡ የሚሸነፈው እና የሚተባበረው ከራሱ በተውጣጡ ሰዎች ለተቋቋመ መንግስት ብቻ ነው›› በማለት ፅሁፉን አጠቃሏል፡፡  

Read 2549 times