Sunday, 10 May 2015 15:29

በሦስት የስልጣኔ ጠላቶች የታመመው የአውሮፓ ፖለቲካ

Written by  ዮሃንስ ሰ.
Rate this item
(3 votes)

1. አዛውንቱን አባት እና ሴት ልጃቸውን ያናከሰ የፈረንሳይ የፖለቲካ ‘ድራማ’
“[አባቴ] አገር ምድሩን ካላቃጠልኩ ሞቼ እገኛለሁ የሚል መንፈስ ተጠናውቶታል። ከፓርቲ መሪነት ከወረደ በኋላ ፓርቲያችን በፍጥነት እያደገ ነው። ይሄም በቅናት ስሜት ያሳርረዋል” - በፈረንሳይ የፒኤፍ ፓርቲ መሪነትን ከአባቷ የተረከበችው ሜሪን ለፔን የተናገረችው ነው። ከሰሞኑ አባቷን ከፓርቲ አባልነት እንዲባረሩ አድርጋለች።
“እዚህ ያደረስኳት እኔ እንደሆንኩ ዘንግታለች። ተቃናቃኝ ፓርቲዎች ፊትለፊት ነው ጥቃት ሲሰነዝሩብኝ የነበረው። ይህች ግን፣ ከጀርባ አድብታ ወጋችኝ። ካላስገደለችኝ በቀር ፈፅሞ ሰላም እንደማልሰጣትና እንደማልተኛላት ማወቅ አለባት” - የፓርቲው መስራች አዛውንቱ ለፔን፣ ስለ ልጃቸው የተናገሩት ነው።
2. ስልጣን ተቀራምተው አገር ለማመሳቀል የሚናቆሩ የግሪክ ኮሙኒስት ፓርቲዎች።
“የትምህርት ቤትና የዩኒቨርስቲ አስተዳደር፣ በተማሪዎች ስር መሆን አለበት። መምህራንና ሰራተኞች ለተማሪ ይታዘዛሉ” - የትምህርት ሚኒስትሩ።
“ወንጀል የፈፀሙ ሰዎች፣ ተበዳይ እንጂ አጥፊ አይደሉም። ጥፋቱ የሕብረተሰቡ ነው። ወንጀለኞች፣ መከሰስ ሳይሆን መካስ አለባቸው” - የፍትህ ሚኒስትሩ።    
3. ትልልቆቹ ፓርቲዎች በአቅመቢስነት የተብረከረኩበት የእንግሊዝ ምርጫ
በሰሞኑ የእንግሊዝ ምርጫ፣ ትልልቆቹ ፓርቲዎች (ቶሪ እና ሌበር) መላ ጠፍቷቸው ሲወራጩ ሰንብተዋል። “የማሸነፍ ተስፋ የላቸውም፤  ምን አይነት መንግስት እንደሚመሰርት ለማወቅ ያስቸግራል” የሚሉ መላምቶች ሊናፈሱ ከቆዩ በኋላ፤ በሐሙሱ ምርጫ የዴቪድ ካሜሮን ቶሪ ፓርቲ አሸንፏል፡፡ ከግማሽ በላይ የፓርላማ ወንበሮችን ተቆጣጥሯል፡፡ ከመራጮች ያገኘው የድጋፍ ድምፅ ግን 37% ብቻ ነው፡፡
እንዲያም ሆኖ፣ በምርጫው ላይ የሚሳለቅ ሰው በምድረ አውሮፓ አልታየም። ሰበብ እየፈለጉ በእንግሊዝ ላይ ለመሳለቅ የሚሯሯጡ አንዳንድ የፈረንሳይ ፖለቲከኞች እንኳ፣ እንደወትሯቸው  ለማፌዝ አልተሽቀዳደሙም። ወደው አይደለም። የፈረንሳይ ፖለቲካም እንደወትሮው አይደለም። እየተናጠ ነው።  
በእንግሊዝ ስልጣን ላይ የሚፈራረቁት ሁለቱ ተቀናቃኝ ፓርቲዎች (ግራ ዘመሙ ሌበር ፓርቲ እና ቀኝ ዘመሙ ኮንሰርቫቲቭ ቶሪ ፓርቲ)፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ተደማጭነታቸው ቀንሷል። የዛሬን አያድርገውና፣ 90 በመቶ ያህል መራጮች፣ ለቶሪ ወይም ለሌበር ፓርቲ ነበር የድጋፍ ድምፃቸውን የሚሰጡት። ዛሬ ግን፣ የሁለቱ ለዘብተኛ ፓርቲዎች ድጋፍ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሸረሸረ ከመምጣቱ የተነሳ፤ አንዳቸውም 35 በመቶ የሚደርስ የድጋፍ ድምፅ ለማግኘት ተስኗቸዋል።
የግል ማንነትንና የሚጠሉ የዘርና የ“ባህል” አምላኪዎች
በተቃራኒው ከ2% በላይ ድጋፍ ያልነበረው ‘ዩኬአይፒ’ የተሰኘው ብሔረተኛ ፓርቲ፣ የደጋፊዎቹን ቁጥር ወደ 13 በመቶ ገደማ አሳድጓል። በግል ነፃነት ላይ የተመሰረተ የካፒታሊዝም ስርዓት ላይ ፅኑ ተቃውሞውን ሲገልፅ፤ “ከግል ጥቅማችሁ በፊት የአገራችሁን ጥቅም አስቀድሙ” በማለት የፋሺዝም መፈክር ያስተጋባል - ዩኬአይፒ። “ኢትዮጵያ ትቅደም” ከሚለው የደርግ መፈክር ጋር ይመሳሰላል። “ጀርመን ትቅደም” የሚለው የናዚዎች መፈክርንም ማስታወስ ይቻላል፡፡ የሕዝብ ስሜት ለማነሳሳት “የውጭ ሃይሎች” ላይ ጣቱን የሚቀስረው ዩኬአይፒ፣ የአውሮፓ ህብረትንና ስደተኞችን በጠላትነት ይፈርጃል፡፡  ሁሉም ዘረኛ ፓርቲዎች ዘንድ የሚዘወተር የተለመደ ዘዴ ነው፡፡  ሰዎችን በግል ማንነታቸው ከመመዘን ይልቅ፤ በተወላጅነት የዘር ሃረግ እየቆጠርን “ባዕድ” እና “ወገን” በሚል እንድንቧደን ይፈልጋሉ።
የእንግሊዝ ፖለቲካ የተመሳቀለው ግን፣ በዚህ ብቻ አይደለም። የፓርላማ  ወንበሮችን ለማሸነፍ አቅም ያልነበረው ሌላ ብሔረተኛ ፓርቲም፣ በጥቂት አመታት ውስጥ ገናና እየሆነ መጥቷል - SNP፡፡ ስኮትላንድን ከእንግሊዝ የመገንጠል አላማ ያነገበው ይሄው ፓርቲ፤ እንደ አብዛኞቹ ብሔረተኞች ወደ ፋሺዝም ያዘነበለ ፀረ ካፒታሊዝም መፈክር ማራገቡ አይገርምም። “ከግል ጥቅማችሁ በፊት የስኮትላንድን ጥቅም አስቀድሙ” ይላል። “ብሔር ብሔረሰብ ይቅደም” እንደማለት ልትቆጥሩት ትችላላችሁ። የሕዝብን ስሜት ለማነሳሳትም፣ እንግሊዝንና ሌሎች “የውጭ ሃይሎችን” በጠላትነት ይፈርጃል። ለምን? ሰዎችን በግል ማንነታቸው ከመመዘን ይልቅ፣ በጅምላ “የብሔረሰብ ተወላጅ” እና “ባዕድ” እያሉ በማቧደን፣ የአንደኛው ቡድን ገዢ ለመሆን ይመኛሉ። በሰሞኑ ምርጫም  ፓርቲው ከ55 በላይ የፓርላማ ወንበሮችን ለማሸነፍ ችሏል፡፡
በጥረት መበልፀግንና የግል ንብረትን የሚጠሉ የምፅዋትና የዝርፊያ አምላኪዎች
በእንግሊዙ ምርጫ፤ ከፋሺስት ዘመም ብሔረተኛ ፓርቲዎች በተጨማሪ፣ ወደ ኮሙኒዝም የተጠጉ ፓርቲዎችም በተወሰነ ደረጃ ደጋፊዎችን ለማበራከት ችለዋል። “ከግል ጥቅማችሁ በፊት የሰፊውን ሕዝብ ጥቅም ወይም የብዙሃኑን ጥቅም አስቀድሙ” የሚል ዲስኩር በመለፈፍ የካፒታሊዝም ቀንደኛ ጠላት እንደሆኑ የሚገልፁት እነዚሁ ሶሻሊስት ፓርቲዎች፤ “ነፃነቴ ይከበር” ብሎ ለሚጋፈጣቸው ሰው ምን አይነት ምላሽ ይሰጣሉ? “ይሄ የግል ሃሳብ ነው” ብለው ያጣጥሉታል።
ምናልባት ገፍቶ የሚከራከራቸው ሊኖር ይችላል። “መቼም የሕዝብ የጋራ አእምሮ የለም፤ የግል ሃሳቤን እንጂ ሌላ ምን አይነት ሃሳብ ልገልፅ እችላለሁ? የጋራ አእምሮ ስለሌለ’ኮ ነው፣ ሰዎች በየግላቸው የምርጫ ድምፅ የሚሰጡት” ብሎ ቢከራከራቸውስ? ሶሻሊስቶቹ፣ በዚህ ክርክር ብዙም አይደናገጡም። የሕዝብን ስሜት ለማነሳሳት የሚረዳ የተለመደ ዘዴ ይጠቀማሉ - ባለሃብቶችንና የቢዝነስ ድርጅቶችን በጠላትነት መፈረጅ!
“የግል ሃሳብና አቋም መያዝ ትችላለህ፤ ግን የሰፊውን ሕዝብ ፍላጎትና የብዙሃኑን ጥቅም አይወክልም። የያዝከው ሃሳብ ከከበርቴው ቡድን የሚመነጭ እንጂ፤ ዝቅተኛውንና ድሃውን የሕብረተሰብ ቡድን አይወክልም” በማለት ዝም ያሰኙታል።
አንደኛ፣ በነሱ ቤት፣ አንድ ሃሳብ ትክክል ወይም ስህተት የሚሆነው፣ በቁጥር ብዛት ወይም በቡድን ትልቅነት ነው። የግሪኩ የትምህርት ሚኒስቴር፣ “የዩኒቨርስቲ አስተዳደር በተማሪዎች ስር መሆን አለበት” የሚሉትም በዚህ ምክንያት ነው - የተማሪዎች ቁጥር ብዙ ስለሆነ፣ “ተማሪ” በሚል አንድ ላይ ከተቧደነ ትልቅ ስለሚሆን ነው።
ሁለተኛ፣ በሶሻሊስቶቹ እምነት፣ የሰው ሃሳብና ድርጊት የሚቃኘው በእያንዳንዱ ሰው ዝንባሌና ምርጫ ሳይሆን፣ በኢኮኖሚና በኑሮ ደረጃው ነው - በ“መደብ”። የግሪኩ የፍትህ ሚኒስትር፣ “ወንጀለኞች ጥፋተኛ አይደሉም። ክስ ሳይሆን ካሳ ይገባቸዋል” የሚል ዲስኩር የሚለፍፉት ለምን ሆነና? ምን እያሉ እንደሆነ በጥንቃቄ አስተውሉ።
“ወንጀለኞች... በሰው ላይ ድብደባ፣ ዝርፊያና ግድያ የሚፈፅሙት... በክፋት ሳይሆን በድህነት ምክንያት ነዋ። በድህነት ውስጥ እንዲኖሩ ያደረጋቸው ማህበረሰብ ነው ጥፋተኛው። ስለዚህ ድሆችን ለመደጎም፣ በእያንዳንዱ ሰራተኛና አምራች ላይ መንግስት እንዳሻው የታክስ ሸክም መከመር ይችላል” ማለታቸው ነው፡፡ “በራሴ ጥረት ያፈራሁት ምርትና ንብረት የኔ ነው፤ የራሴንና የቤተሰቤን ኑሮ ላሻሽልበት” ብሎ መከራከርም ሆነ አማራጭ ሃሳብ ማቅረብ፣ አልያም በእምቢተኝነት መቃወም አይቻልም። ለምን?
አሃ፣ እንዲህ አይነት ክርክርና ተቃውሞ “ራስ ወዳድነት” ይሆናላ። ራስ ወዳድነት ደግሞ እንደሃጥያት ተቆጥሯል። እና ምን ትላላችሁ? አስታውሱ። “እያንዳንዱ ሰው ከየራሱ የግል ሃሳብና ጥቅም በፊት የሌሎችን ሃሳብና ጥቅም ማስቀደም አለበት። ከራስ ወዳድነት በመላቀቅ ራሱን ለሌሎች መስዋዕት ማድረግ ይገባዋል። የግል ማንነትንና ሰብእናን በማዋረድ፣ ለሌሎች መስገድና መገዛት ይኖርበታል” የሚሉ መፈክሮችን አትርሷቸው። መፈክሮቹን አሜን ብሎ የሚቀበል ሰው፣ አእምሮውንና የማሰብ ነፃነቱን፣ የስራ ፍሬውንና ንብረቱን፣ የግል ማንነቱንና የእኔነት ክብሩን ለማንም መንገደኛ አሳልፎ ለመስጠት ፈቃደኛ ይሆናል።
ራሱን ከበግ አሳንሶ ለመስዋዕትነት የተዘጋጀ ሰው ካለ ደግሞ፣ ሰውን ወደ መስዋዕት ቦታ ለመንዳት የሚቋምጡ ሶሻሊስቶች ይመቻቸዋል። ለዚህም ነው፤ የሶሻሊዝም ፖለቲካ በገነነ ቁጥር፣ በሃሳብ ነፃነት ፋንታ አፈናና ፕሮፓጋንዳ፣ በንብረት ባለቤትነት መብት ፋንታ የንብረት ውርስና የድህነት ራሽን፣ ከእኔነት ክብር ይልቅ ፍርሃትና ውርደት የሚስፋፋው። ለማንኛውም፤ የእንግሊዝ ሶሻሊስት ፓርቲዎች፣ እንደ ግሪክ አቻዎቻቸው ስልጣን እስከመያዝ ባይደርሱም፣ አምስት በመቶ ያህል ድጋፍ ለማሰባሰብ ችለዋል። ይህም ብቻ አይደለም።
አእምሮን የጠሉ የጭፍንነትና የሞት አምላኪዎች
አዎ፤ የባሰባቸው መጥተዋል። በአልቃይዳ ወይም በአይሲስ ቅኝት፤ “የምርጫ ፖለቲካን ከምድረ ገፅ እናጠፋለን” የሚሉ የሃይማኖት አክራሪዎች እንደ አሸን ፈልተዋል። እነዚህም እንዲሁ፣ በግል ነፃነት ላይ የተመሰረተውን የካፒታሊዝም ስርዓት አይፈልጉትም። ስህተታቸውን፣ ጥፋታቸውንና እኩይነታቸውን እየተነተነ የሚሞግታቸው ቢመጣስ? ከጭፍንነት ተላቅቀው አእምሯቸውን ለመጠቀም ባይፈቅዱ እንኳ የእያንዳንዱን ሰው ነፃነት ማክበር እንዳለባቸው የሚነግራቸውና “ነፃነቴ ይከበር” ብሎ የሚከራከር ቢያጋጥማቸውስ? እስካሁን ብርቱ ተከራካሪ ያጋጠማቸው አይመስልም። አልያም፣ ቀላል የማሸነፊያ ዘዴ ታጥቀዋል ማለት ነው። “ከግል አእምሮ በፊት የሃይማኖት እምነትን አስቀድም። ከግል ምድራዊ ሃሳብህና ጥቅምህ በፊት፣ የሃይማኖት ትዕዛዛትን አስቀድም” በማለት ማንኛውንም ተከራካሪ አፉን እንዲዘጋ ማድረግ እንደሚችሉ ያምናሉ።
“የእያንዳንዱን ሰው ነፃነት አክብሩ በሚል የሚያዘጋጅም ሆነ ሌላ ምድራዊ ሕግ ማክበር የለብንም፤ በፈጣሪ ለተሰየመ መሪ ተገዢ መሆን አለብን” ከሚል ስብከት ጎን ለጎን፣ ራሳቸውን የፈጣሪ ተወካይ አድርገው በመሾም በሰው ሕይወት ላይ ይጫወታሉ። በእርግጥም፤ ዓለማዊነትን እያጥላላ፤ ማለትም የዚህ ምድር አእምሮውን፣ ሕይወቱንና ማንነቱን እያንቋሸሸ፣ “ከሞት ወዲያ”ን የሚናፍቅ ጭፍን የሞት አምላኪ፣ የሌሎች ሰዎችን ሕይወት ለማጥፋት ይሯሯጣል።  በደርዘን የሚቆጠሩ አገራትን በደም ጎርፍ እያጨቀዩ ያሉት እነዚሁ የሃይማኖት አክራሪዎች፣ በእንግሊዝና በሌሎች የአውሮፓ አገራት ውስጥ እየተበራከቱ መምጣታቸው ሚስጥር አይደለም።
የክርስትና ሃይማኖት አክራሪነት በሰፈነበት የጨለማ ዘመን፣ በምድረ አውሮፓ በርካታ ጳጳሳት በአገር ገዢነት እየነገሱና የለየላቸው ሃይማኖታዊ መንግስታት እየተመሰረቱ፣ ስንት እልቂትና ስቃይ እንደደረሰ መለስ ብሎ የሚመለከት ሰው የጠፋ ይመስል፤ ዛሬ በእስልምና አክራሪነት ተመሳሳይ ሃይማኖታዊ መንግስት ለመመስረት ዘመቻ የሚያካሂዱ ነውጠኞችና አሸባሪዎች መግነናቸው ያሳዝናል። ይሄውና፤ በእንግሊዝና በሌሎች የአውሮፓ አገራት ዜግነት ያገኙ በሺ የሚቆጠሩ የመካከለኛው ምስራቅ ተወላጆች ወደ ኢራቅና ሶሪያ እየሄዱ፣ “እስላማዊ መንግስት (አይኤስ)” በሚል ስያሜ በሚታወቀው የሃይማኖት አክራሪዎች ቡድን ስር ተጠርንፈው እየተዋጉ ነው። ከአንድ ሺ የሚበልጡት ተዋጊዎች ከፈረንሳይ የሄዱ ናቸው። ወደ ፈረንሳይ እናምራ መሰለኝ።
የእንግሊዝን ፖለቲካ እየተፈታተኑ ያሉትን ሦስት የቀውስ ምንጮች አይተን የለ? ወደ ፈረንሳይ አቅጣጫ ስንዞርም፣ የተለየ ነገር አናገኝም። እነዚያው ሦስት ቀውሶች የአገሪቱን ፖለቲካ ሲያመሳቅሉ ነው የምንመለከተው። የፈረንሳይ ጠቅላይ ሚኒስትር በራሳቸው አንደበት የተናገሩትን መጥቀስ ይቻላል። ከስፔናዊ አባትና ከስዊዘርላንዳዊ እናት የተወለዱት የፈረንሳይ ጠ/ሚ ማኑኤል ቫልስ፣ በቅርቡ ለዎልስትሪት ጆርናል በሰጡት ቃለምልልስ የአገራቸው ዋና ዋና ፈተናዎችን ዘርዝረዋል። ቃለምልልሱ የጋዜጣውን ሰፊ ገፅ ከላይ እስከ ታች የሚሸፍን ረዥም ንግግር ቢሆንም፣ በሶስት ነጥቦች ላይ ብቻ ያተኮረ ነው።
አንደኛ፣ የሃይማኖት አክራሪነት... ሁለተኛ፣ ዘረኝነት (ብሔረተኝነት)... ሦስተኛ፣ ወደ ሶሻሊዝም ያጋደለ ኢኮኖሚ። ጠ/ሚ ቫልስ ሌላ ጉዳይ አልቀላቀሉም - የፈረንሳይን ፖለቲካ፣ ኢኮኖሚና ህልውና የሚፈታተኑ ሦስት በሽታዎች ብቻ።
እንግዲህ አስቡት፡፡ “በዝቅተኛ ገቢ የሚኖር ብዙሃኑን ሕዝብ ለመደገፍና ለመደጎም” በሚለው የሶሻሊዝም ቅኝት፣ የፈረንሳይ መንግስት በተለያዩ ታክሶች አማካኝነት ከዜጎች ገቢ ውስጥ 57 በመቶ ያህሉን ይወስዳል።  የመንግስት እጅ ውስጥ የገባ ገንዘብ፣ ከፊሉ ለሙስና እየተጋለጠ፣ ገሚሱ በዝርክርክነት እየባከነ ኢኮኖሚን ይጎዳል። ከፊሉ ደግሞ በድጎማ እየተከፋፈለ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች፣ ለአጭር ጊዜ ሳይሆን ለዘለቄታው የመንግስት ጥገኛና የድጎማ ተመፅዋች እንዲሆኑ ያደፋፍራል። በአንድ በኩል፣ አምራችና ሃብት ፈጣሪ ሰዎች በታክስ ጫና እየተዳከሙና ከአገር እየለቀቁ የአገሪቱ ኢኮኖሚ ይዳከማል፤ የስራ እድል ይቀንሳል፤ ስራ አጥነት ይባባሳል። በሌላ በኩል ደግሞ፣ በየጊዜው ከሚጨምረው የተደጓሚ ሰዎች ቁጥር ጋር፤ ከስራ ርቆ የመንግስትን ድጎማ የሚጠብቅ ስራ ፈት ይበራከታል።
ጠ/ሚ ቫልስ በራሳቸው ፓርቲ አማካኝነት እየተባባሰ የመጣውን ይህን ፈተና አድበስብሰው ለማለፍ አልሞከሩም። “ስራ ፈትነትን ስፖንሰር የምናደርግ መንግስት ሆነናል” በማለት ተናግረዋል ጠ/ሚ ቫልስ። በሌላ አነጋገር፣ “የሶሻሊዝም ዝንባሌ ከልክ አለፈ” እንደማለት ነው። እንዲህም ሆኖ፣ ሰውዬውና ፓርቲያቸው የካፒታሊዝም አቀንቃኝ ለመሆን ፈልገዋል ማለት አይደለም። ስልጣን ላይ የሚፈራረቁት ሁለቱ የፈረንሳይ ትልልቅ ፓርቲዎች፣ ራሳቸውን እንደለዘብተኛ ነው የሚቆጥሩት። ማለትም የቅይጥ ኢኮኖሚ አጋፋሪ ናቸው፡፡ በአንድ በኩል፣ ከካፒታሊዝም ይልቅ ሶሻሊዝምን ያከብራሉ። ግን፤ የሰውን ንብረት በሚወርስ የሶሻሊዝም መንገድ የአገሪቱ ኢኮኖሚ እንዲንኮታኮት አይፈልጉም። ስለዚህ ምን ያድርጉ?
ሃብትን ለመፍጠር እድል የሚከፍት የካፒታሊዝም አሰራርን በከፊል፣ ከተፈጠረው ሃብት ውስጥ ገሚሱን መንግስት እንዲወስድ የሚያደርግ የሶሻሊዝም አሰራርንም በከፊል ተግባራዊ ማድረግን ይመርጣሉ - ለዘብተኞቹ ፓርቲዎች። እውነትም፣ የቅይጥ ኢኮኖሚ ተከታዮች ናቸው ማለት ይቻላል። ግን ቅጥይ ኢኮኖሚ አላዋጣም። አሁን ፈተና የሆነባቸው፣ የሶሻሊዝሙ ዝንባሌ እየበዛና ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተለጠጠ፣ ማቆሚያ የሌለው የቁልቁለት ጉዞ መምሰሉ ነው።
ከዘጠና አመት በፊት፣ መንግስት ከዜጎች ገቢ ውስጥ 8 በመቶ ገደማ ነበር የሚወስደው። የታክስ ጫናው፣ ቀስ በቀስ ወደ ሃያ እና ወደ ሰላሳ በመቶ እየጨመረ፣ ከዚያም ወደ አርባ እና ሃምሳ በመቶ እያለ ከጊዜ ወደ ጊዜ ሲብስበት እንጂ ሲሻሻል አይታይም። የታክስ ጫና የበዛባቸው አምራቾችና ሃብት ፈጣሪዎች፣ እንደምንም ተቃውሞ ለማሰማት ቢሞክሩ እንኳ ተደማጭነት አያገኙም። “ከግል ጥቅማችሁ በፊት የሌሎችን ጥቅምና የብዙሃኑን ፍላጎት አስቀድሙ” ብለው የሚደሰኩሩ ሶሻሊስቶች ናቸው የድጋፍ ጭብጨባ የሚጎርፍላቸው። አሁን፣ መንግስት ከዜጎቹ የስራ ገቢ ውስጥ 57% ያህል ይወስዳል።
አባትና ልጅን ያናከሰ ዘረኝነት
የፈረንሳይ በሽታ፣ ሶሻሊዝምና የሃይማኖት አክራሪነት ብቻ አይደለም። “ከግል ጥቅም በፊት የአገር ጥቅም ይቅደም” የሚል መፈክር የሚያስተጋባ ፒኤፍ የተሰኘ ብሔረተኛ ፓርቲ፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየገነነ መጥቷል። በአማካይ ከአምስት በመቶ በላይ የድጋፍ ድምፅ አግኝቶ የማያውቀው ፒኤፍ ፓርቲ፣ ባለፈው አመትና ዘንድሮ በተደረጉ የተለያዩ ምርጫዎች 25 በመቶ ገደማ ድጋፍ አግኝቷል። ነባሮቹ ትልልቅ ፓርቲዎች ከዚህ የበለጠ ውጤት አላስመዘገቡም።
ሰዎችን በግል ማንነታቸው (እንደየተግባራቸውና ባህርያቸው) ከመመዘን ይልቅ፣ የሰውን ማንነት በጅምላ እየፈረጀ በተወላጅነት  ለሟባደን የሚጥረው ይሄው ፓርቲ፣ “ነባር የፈረንሳይ ተወላጅ” እና “ከሌላ የአውሮፓ አገር ሰዎች የተወለደ መጤ” በማለት ይፈርጃል። የፒኤፍ ፓርቲ ፖለቲከኞች፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩንም ጭምር፣ “መጤ” በማለት ያንቋሽሻሉ። ሌላ ጊዜ ደግሞ፣ “ነጭ” እና “ጥቁር” በሚል ለማቧደን ይቀሰቅሳሉ። አንዳንዴም፣ የአረብ ተወላጆች ላይ ወይም የቤተእስራኤል ተወላጆች ላይ የጥላቻ ጣታቸውን እየቀሰሩ ይዝታሉ። የአዶልፍ ሂትለር ናዚ ፓርቲ እንዳደረገው ነው፣ ሰዎች በተወላጅነት እየተቧደኑ በወዳጅነት መቀራረብና በጠላትነት መራራቅ ይኖርባቸዋል። ለምን? የሰው ማንነት የሚወሰነው በተወላጅነት ነው ብለው ያምናሉና። ከአርባ አመት በፊት፣ ለፔን የመሰረቱት የፈረንሳይ ብሔራዊ ግንባር (ፒኤፍ) የሚያራግበው መፈክርም ይሄው ነው።
ለበርካታ አመታት ፓርቲውን ሲመሩ የነበሩት ለፔን፣ የዛሬ ሦስት ዓመት ገደማ ነው ሃላፊነቱን ለልጃቸው ሜሪን ለፔን ያስረከቡት። ሜሪን ለፔን ከአዛውንት አባቷ በተሻለ ሁኔታ የአባላት ምልመላ እና ቅስቀሳ በማካሄዷ፤ የፓርቲው ተቀባይነት እየጨመረ መጥቷል። አባቷ ግን ደስተኛ አልነበሩም። “ደጋፊ ለማብዛት ብለሽ የፓርቲውን አቋም አለሳልሰሻል” በማለት ቁጣቸውን በተደጋጋሚ ገልፀዋል። የተለሳለሰውን አቋም መልሶ ማጠናከር አለብኝ በሚል ስሜትም፣ ለተለያዩ የሚዲያ ተቋማት ተከታታይ ቃለምልልሶችን ሰጥተዋል - እንደወትሮው  የዘረኝነት ስሜትን የሚያግለበልቡ ያፈጠጡና ያገጠጡ ጭፍን ንግግሮችን በማራገብ።
በአባቷ ድርጊት የተናደደችው ሜሪን ለፔን፣ በተደጋጋሚ ልታስታግሳቸው ብትሞክርም አልተሳካላትም። በየመሃሉ፣ ለአፍታ እርቅ ያወረዱ ቢመስሉም፣ ብዙም ሳይቆይ እንደገና የሚያጣላ ነገር ይከሰታል። በአባቷ ሰፊ ሕንፃ ውስጥ ከፍቅረኛዋ ጋር ትኖር የነበረችው ሜሪን ለፔን፣ ንዴቷ ሞልቶ የፈሰሰው የዛሬ ወር ገደማ ነው። የሜሪን ለፔን ድመት ሞተች - የአባቷ ትልቅ ውሻ ነው ድመቷን የገደላት። ያኔ ሜሪን ህንፃውን ለቅቃ ወጣች። ባለፈው ሳምንት፣ አዛውንቱ ለፔን እንደገና ለአንድ የሬዲዮ ጣቢያ ነውጠኛ ቃለምልልስ ለመስጠት ብቅ ሲሉ ግን፣ ሜሪን በጠሰች።
በቃ፤ አባቷ በፓርቲው የዲሲፕሊን ኮሚቴ ፊት ቀርበው ከፓርቲ አባልነት እንዲባረሩ ወሰነች። አባቷ ፓርቲውን እየጎዱ እንደሆነ የተናገረችው ሜሪን፣ “ይህንን የሚያደርገው፣ በክፋት ስሜት እየተገፋፋና በሕዝብ ዘንድ ስሙ የተዘነጋ ስለሚመስለው ዝናውን ለማስመለስ ነው” ብላለች። “በቃለምልልስ የሚናገራቸው ነገሮች ራሱንም ሆነ ፓርቲውን የሚጎዱ ናቸው። አገር ምድሩን ካላቃጠልኩ ሞቼ እገኛለሁ የሚል የአጥፍቶ ጠፊ መንፈስ ተጠናውቶታል። ከፓርቲ መሪነት ከወረደ በኋላ ፓርቲያችን በፍጥነት እያደገ ነው። ይሄም በቅናት ስሜት ያሳርረዋል” በማለትም አባቷን አውግዛለች።
ከፓርቲ አባልነት ከተባረሩ በኋላ፣ “እዚህ ያደረስኳት እኔ እንደሆንኩ ዘንግታለች” በማለት ቁጣቸውን የገለፁት ለፔን፣ “ከሁሉም የባሰች ጠላቴ እሷ ነች። ተቃናቃኝ ፓርቲዎች እንኳ ፊት ለፊት ነው ጥቃት ሲሰነዝሩብኝ የነበረው። ይህች ግን፣ ከጀርባ አድብታ ወጋችኝ” ብለዋል።
“በሚቀጥለው አመት በፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ልጅዎ እንድታሸንፍ ይመኛሉ?” ተብለው የተጠየቁት ለፔን፤ “እንደሷ አይነት ቅሌታም ተመረጠ ማለት፣ የአገር ውርደት ነው።
ደግሞም ካላስገደለችኝ በቀር፣ ፈፅሞ ሰላም እንደማልሰጣትና እንደማልተኛላት ማወቅ አለባት። የሆነ ቦታ ሬሳዬ ከተገኘ ራሴን ያጠፋሁ እንዳይመስላችሁ” በማለት ልጃቸውን በደመኛ ጠላትነት ፈርጀዋል።
ሰኞ እለት ገንፍሎ በአደባባይ የፈነዳው የአባትና የልጅ እንካሰላንቲያ፣ ገና አልተቋጨም። በጋዜጣና በኢንተርኔት፣ በሬዲዮና በቴሌቪዥን የተጋጋለው የነቆራ ጦርነት፤ በፍርድ ቤት ወደ መካሰስ ያመራል ተብሏል። አንዳቸው አንዳቸውን ሳያደባዩ እንቅልፍ የሚወስዳቸው አይመስሉም።
በዚያ ሁሉ እንካሰላንቲያ መሃል ትንሽ ለማሰብ ቢሞክሩ’ኮ፣ አንዳች የሚያስማማ እውነተኛ ነገር ማግኘት ይችሉ ነበር። ግን ፈቃደኞች አይመስሉም። “ለካ፣ የፓርቲያችን ዘረኛ አቋም የተሳሳተ ነው። ለካ ወዳጅነትና ጠላትነት... በተወላጅነት የሚመጣ አይደለም። ለካ በዘር መቧደን ከንቱ ነው” የሚል እውነት ብልጭ አላለላቸውም። እናም፣ በጋራም ይሁን በተናጠል የፈረንሳይን ፖለቲካ ለማመሳቀል መቀስቀሳቸውን አያቋርጡም።  በስልጣኔ ደህና የተራመዱት የአውሮፓ አገራት፣ በሦስቱ የስልጣኔ ጠላቶች (ማለትም በሾሻሊዝም፣ በሃይማኖት አክራሪነትና በብሔረተኝነት) እየተናጡ የሚቃወሱ ከሆነ፤ ሌሎቻችን ምን ይውጠናል? እንደምታዩት ነባሩ የለዘብተኛነትና የቅይጥ አስተሳሰብ አቅጣጫ አውሮፓን ለቀውስና ለበሽታ የሚያጋልጥ እንጂ ስልጣኔን ከአደጋ ለመከላከል የሚያስችል አልሆነም። አንደኛ፤ ለአእምሮ፣ ለሳይንስና ለግል ነፃነት፣ ሁለተኛ፤ ለምርታማነት፣ ለግል ንብረትና ለብልጽግና፣…ሦስተኛ፤ ለግል ማንነት፤ ለእኔነት ክብር፣ ለራስ ወዳድነት ትልቅ ዋጋ የሚሰጥ ጽኑ የካፒታሊዝም አፍቃሪ የተመናመነባት ዘመን ነው፡፡ እናም ዘመኑ ለአውሮፓም ጭምር የሚያሰጋ የቀውስ ዘመን ቢሆን አይገርምም፡፡
ከአውሮፓ ውጭስ? ያማ እያየነው ነው፡፡ ብዙዎቹ የአረብና የአፍሪካ አገራት ከቀውስ አልፈው፣ በእርስበርስ እልቂት እየተተረማመሱ ነው - በሦስቱ የስልጣኔ ጠላቶች አማካኝነት፡፡  Read 2777 times