Sunday, 10 May 2015 15:28

የአፍሪካ ህብረት የብሩንዲ ፕ/ት በምርጫ መወዳደራቸውን ተቃወመ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

የብሩንዲው ፕሬዚዳንት ፔሪ ንኩሩንዚዛ የአገሪቱ ህገ-መንግስት ከሚፈቅደው ውጭ ለሶስተኛ ዙር በምርጫ ለመወዳደር መወሰናቸው ህገወጥነት እንደሆነና ውሳኔውን አጥብቆ እንደሚቃወመው የአፍሪካ ህብረት አስታወቀ፡፡
የፕሬዚዳንቱ ውሳኔ በአገሪቱ የቀሰቀሰው ህዝባዊ ቁጣ እየተባባሰ መምጣቱ፣ ምርጫውን በሰላማዊ መንገድ ለማካሄድ አመቺ አይደለም ያለው የአፍሪካ ህብረት፣ የምርጫ ታዛቢ ቡድኑን ወደ አገሪቱ እንደማይልክም አስታውቋል፡፡ከስልጣናቸው እንዲወርዱ በአሜሪካ እየተደረገባቸው ያለውን ጫና የተቃወሙት ፕሬዚዳንት ፔሪ ንኩሩንዚዛ በበኩላቸው፤ ቀጣዩ ምርጫ በሰላማዊ መንገድ መከናወን እንዲችል ህዝቡ ተቃውሞውን እንዲያቆም ጥሪ አቅርበው፣ ለአራተኛ ዙር አገሪቱን ለመምራት እንደማይፈልጉና ከዚህ በኋላ በምርጫ እንደማይወዳደሩ ቃል ገብተዋል፡፡
ፖሊስ የአገሪቱን ዜጎች ደህንነት ለመጠበቅ ሲል በተቃውሞው የተሳተፉትን ሰዎች በማሰር ላይ እንደሚገኝና፣ ዜጎች ከመሰል ድርጊታቸው የሚታቀቡና ተቃውሞው የሚቆም ከሆነ የአገሪቱ ፖሊስ በቁጥጥር ስር ያዋላቸው ዜጎች በሙሉ እንደሚፈቱም ፕሬዚዳንቱ አስታውቀዋል፡፡በብሩንዲ ያለው ሁኔታ አደገኛ ነው፡፡ ምርጫውን ለመታዘብ አንችልም፡፡ ፕሬዚዳንቱ ለሶስተኛ ዙር መወዳደራቸውም አግባብነት የለውም፤ የአገሪቱ ህገመንግስት ሊከበር ይገባል ብለዋል የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽነር ንኮዛና ድላሚኒ ዙማ፤ ከቻይናው ሲሲቲቪ ቴሌቪዥን ጣቢያ ጋር ከትናንት በስቲያ ባደረጉት ቃለ መጠይቅ፡፡አገሪቱን በመምራት ላይ የሚገኘው ሲኤንዲዲ-ኤፍዲዲ ፓርቲ ከሁለት ሳምንታት በፊት የወቅቱን የአገሪቱ ፕሬዚደንት ፔሪ ንኩሩንዚዛ በመጪው ምርጫ በዕጩነት ማቅረቡን ተከትሎ በተቀሰቀሰው ተቃውሞ ከ15 ሰዎች በላይ መሞታቸውንና በርካቶች መቁሰላቸውን ያስታወሰው ዘገባው፣ ተቃውሞው ተጠናክሮ መቀጠሉን ጠቁሟል፡፡ሮይተርስ በበኩሉ፤ ከትናንት በስቲያ በአገሪቱ መዲና ቡጁምቡራ ለተቃውሞ የወጡ ዜጎች የገዢው ፓርቲ የወጣቶች ክንፍ አባል ነው ያሉትን አንድ ግለሰብ በእሳት አቃጥለው መግደላቸውንና የተለያዩ ሱቆችን ማጋየታቸውን ዘግቧል፡፡
ፕሬዚዳንቱ ለሶስተኛ ዙር ምርጫ ለመወዳደር መወሰናቸው የህግ ጥሰት ነው ያሉት የአገሪቱ ተቃዋሚ ፓርቲዎችና የሲቪል ማህበረሰብ ቡድኖች፣ የአገሪቱ ህገመንግስት አንድ ፕሬዚዳንት በመሪነት መቆየት የሚችለው ለሁለት ዙር ብቻ እንደሆነ ቢወስንም፣ ፕሬዚዳንቱ ግን ህገመንግስቱን በጣሰ ሁኔታ በስልጣን ላይ ለመቆየት እየተዘጋጁ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
የፕሬዚዳንቱን የምርጫ ተሳትፎ አግባብነት በተመለከተ ጉዳዩን ሲመረምር የቆየው የብሩንዲ ህገመንግስታዊ ፍርድ ቤት በበኩሉ ባለፈው ሰኞ ይፋ ባደረገው ውሳኔው፣ ፕሬዚዳንቱ የመጀመሪያውን ዙር በፓርላማ እንጂ ቀጥታ በህዝቡ ተመርጠው ስልጣን ባለመያዛቸው እንደ አንድ ዙር አይቆጠርባቸውም፣ በዘንድሮው ምርጫ መወዳደር ይችላሉ ብሏል፡፡
የፍርድ ቤቱ ምክትል ፕሬዚዳንት ሳላይሬ ኒምፓጋሪትሴ ግን፣ ከመንግስት በተደረገ ጫና የተላለፈ ውሳኔ ነው በሚል ተቃውመው፣ ፊርማዬን አላስቀምጥም በማለት አገር ጥለው የተሰደዱ ሲሆን የአገሪቱ መንግስት ቃል አቀባይ በበኩሉ፤ ግለሰቡ ውሳኔውን እንዲያስተላልፉ ምንም አይነት ጫና እንዳልተደረገባቸው መግለጻቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
ለአመታት የዘለቀው ከ300 ሺህ በላይ ዜጎችን ለህልፈተ ህይወት የዳረገው የአገሪቱ ደም አፋሳሽ የእርስ በእርስ ጦርነት እ.ኤ.አ በ2005 ከተቋጨ ወዲህ አስከፊው የተባለውንና ከሰሞኑ የተቀሰቀሰውን ተቃውሞና አመጽ ተከትሎ፣ በአገሪቱ ውጥረት መንገሱንና 40 ሺህ የሚደርሱ የአገሪቱ ዜጎች ለደህንነታቸው በመስጋት ወደ ሩዋንዳ፣ ታንዛንያና ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኦፍ ኮንጎ መሰደዳቸውንም ዘገባው አስታውቋል፡፡
ለፕሬዚዳንትነት የሚወዳደሩት ኦዲፋክስ ንዳቢቶሪየ የተባሉ የተቃዋሚ ፓርቲ አባል ባለፈው ረቡዕ  አመጹን አነሳስተዋል በሚል በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ ከተደረገባቸው በኋላ መለቀቃቸውን እንዲሁም በአገሪቱ መዲና ቡጁምቡራ ከትናንት በስቲያ የተቀሰቀሰውን ተቃውሞ በቁጥጥር ስር ለማዋል ፖሊስ በወሰደው እርምጃ አንድን ግለሰብ ተኩሶ መግደሉንና ሶስት ዜጎችንም ማቁሰሉን አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘግቧል፡፡

Read 1342 times