Print this page
Sunday, 10 May 2015 15:26

3 ሰራተኞች ብቻ ያሉት አለማቀፍ ኩባንያ ተቋቋመ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

መስራቾቹ ትርፋማ እንደሚሆኑ እርግጠኛ ሆነዋል
ሶስቱ ሰራተኞች በሶስት ሽፍት ይሰራሉ
ታላላቅ ኩባንያዎች ምርቶቹን ለመግዛት ተመዝግበዋል


ክላውድ ዲዲኤም የተባለውና በባለሶስት አውታር ህትመት ዘርፍ ላይ ተሰማርቶ ለመስራት ዝግጅቱን ያጠናቀቀው  የአሜሪካ ኩባንያ፣ በ3 ሰራተኞች ብቻ በሚያከናውነው የምርት እንቅስቃሴ ትርፋማ ስራ እንደሚያከናውን መስራቾቹ በእርግጠኝነት መናገራቸውን ሲኤንኤን ዘገበ፡፡
በአይነቱ የመጀመሪያው የሆነውና ሙሉ ለሙሉ በማሽን አማካይነት የሚሰራው ይህ ኩባንያ፣ የዘመናዊ ቴክኖሎጂ ውጤት በሆኑ 100 ባለ ሶስት አውታር ማተሚያ ማሽኖቹ አማካይነት በሳምንት ለ 7 ቀናት ለ24 ሰዓት የማምረት ስራውን የሚያከናውን ሲሆን፣ እያንዳንዳቸው በሶስት ሽፍት ለ8 ሰዓታት የሚሰሩ 3 ሰራተኞች ብቻ እንዳሉትም ገልጽዋል፡፡
ከኩባንያው መስራች አንዱ የሆኑት ሚች ፍሪ ባለፈው ረቡዕ ለሲኤንኤን እንደገለጹት፣ ኩባንያው የምርት ስራውን በማተሚያ ማሽኖቹና በሶስቱ ሰራተኞች አማካይነት በተቀላጠፈ ሁኔታ እያከናወነ ሲሆን፣ ምርቶቹን የማሸግና ለደንበኞች የማድረስ ስራውን ደግሞ ዩፒኤስ የተባለ አጋር ድርጅት እያከናወነው ይገኛል፡፡
ኩባንያው የተለያዩ ቁሳቁሶችን በባለ ሶስት አውታር ማተሚያ ማሽኖች አማካይነት በማምረት ለደንበኞቹ የሚያቀርብ ሲሆን አሰራሩ የተቀላጠፈ በመሆኑ ለማምረት አንድ ሳምንት ያህል ጊዜ የሚወስዱ ዕቃዎችን በ24 ሰዓታት ውስጥ ሰርቶ ማጠናቀቅ የሚችልበት ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ሚች ፍሪ ገልጸዋል፡፡
ኩባንያውን ለማቋቋም 1 ሚሊዮን ዶላር ወጪ መደረጉን የጠቆመው ዘገባው፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ በርካታ ደንበኞችን ማፍራት መቻሉንና በቀጣይም የባለ ሶስት አውታር ማተሚያ ማሽኖቹን ቁጥር ወደ አንድ ሺህ ከፍ ለማድረግ ዕቅድ ይዞ በቅርቡ ወደ ስራ እንደሚገባ አስታውቋል፡፡
ተቀማጭነቱ በኒውዮርክ የሆነው ሁማንስኬል የተባለ የቤት ዕቃዎች አምራች ኩባንያ፣ ታዋቂው የቅንጦት የእጅ ሰዓቶች አምራች ኩባንያ ዴቮን ዎርክስ እንዲሁም ግዙፉ ፍሌክስትሮኒክስን ጨምሮ በርካታ ድርጅቶች ከዚህ በአይነቱ የተለየ ኩባንያ ምርቶችን ለመግዛት ደንበኝነት መመስረታቸውንም አስታውቋል።

Read 1752 times
Administrator

Latest from Administrator