Sunday, 10 May 2015 15:15

አይሠግሩም ተብሎ ፈረስና በቅሎ አይሮጡም ተብሎ ፈረስና በቅሎ እንዲያው በጥላቻ፤ ትመረጥ ይሆናል ኤሊ ለኮርቻ!! (አገርኛ አባባል)

Written by 
Rate this item
(13 votes)

ከዕለታት አንድ ቀን አንድ አውራዶሮና ሚስቱ በአንድ ቄስ የእህል መጋዘን አጠገብ ሲጓዙ አውራዶሮው አንድ ባቄላ አግኝቶ ሲውጥ፤ አነቀውና፤ ውጪ ነብስ ግቢ ነብስ ሆነ፡፡ ሚስቲቱ ዶሮ የምታደርገው ብታጣ ውሃ ፍለጋ ወደ ወንዝ ወረደች፡፡
“ወንዝ ሆይ! እባክህ ባለቤቴ ባቄላ አንቆት፣ መተንፈስ አቅቶት ሊሞትብኝ ነው፡፡ ትንሽ ውሃ ስጠኝና ነብሱን ልታደገው?” አለችው፡፡
ወንዝም፤ “ወደ ሎሚ  ዛፍ ሄደሽ አንድ የሎሚ ቅጠል ካመጣሽልኝ ውሃ እሰጥሻለሁ” አላት፡፡
ዶሮይቱ ወደ ሎሚ ዛፍ ሄደችና፤
“ሎሚ ዛፍ ሆይ! ባለቤቴ ባቄላ አንቆት መተንፈስ አቅቶት፣ ሊሞትብኝ ነው ብዬ ወንዝን ውሃ ስጠኝ ብለው፤ “የሎሚ ቅጠል ካመጣሽ እሰጥሻለሁ” አለኝ፡፡ እባክህ አንዲት ቅጠል ስጠኝ?” አለችው፡፡
የሎሚ ዛፍም፤
“ወደ ቄሱ ቤት ሠራተኛ ሄደሽ የመርፌ ክር ካመጣሽልኝ እሰጥሻለሁ” አላት፡፡
እመት ዶሮ ወደ ቄሱ ቤት ሠራተኛ ሄዳ ጉዳይዋን አስረዳች፡፡
የቤት ሠራተኛዋም፤ “ወደ ላም ሄደሽ ትንሽ ወተት ካመጣሽልኝ ክሩን እሰጥሻለሁ” አለቻት፡፡
እመት ዶሮ ወደ ላም ሄዳ “ትንሽ ወተት ስጪኝ ባክሽ” ብላ ጉዳይዋን ሁሉ ዘረዘረችላት፡፡
ላምም፤ “ወደ አጫጆቹ ዘንድ ሄደሽ ትንሽ ጭድ ካመጣሽልኝ እሰጥሻለሁ” አለቻት፡፡
እመት ዶሮ እንደፈረደባት ወደ አጫጆቹ ሄዳ “እባካችሁ ትንሽ ጭድ ስጡኝ” አለቻቸው፡፡
አጫጆቹም “ወደ ቀጥቃጮች ሄደሽ ትንሽ ማጭድ ከሰጡሽ ጭዱን እንሰጥሻለን” አሏት፡፡
እመት ዶሮ ወደ ቀጥቃጮቹ ሄዳ ለመነቻቸው፡፡
ቀጥቃጮቹ ደግሞ “ወደ ከሰል አክሳዮቹ ጋ ሄደሽ አንድ አራት ራስ ከሰል አምጪልንና የጠየቅሽንን እንሰጥሻለን” አሏት፡፡
ወደ ከሰል አክሳዮቹ ላዕያውያን (Laians) ምርር ባለ ምስኪን ቃና አስተዛዝና፤
“ከሰል አክሳዮቹ ሆይ፤ ባለቤቴ አውራዶሮ ባቄላ አንቆት፣ መተንፈስ አቅቶት ሞት አፋፍ ቢደርስ፣ አንድ ጉንጭ ውሃ ወንዝን ብጠይቀው፣ የሎሚ ቅጠል ከሎሚ ዛፍ አምጪ፤ የሎሚ ዛፍ ጋ ብሄድ ከቄሱ ሠራተኛ የመርፌ ክር አምጪ፤ የቄሱ ሠራተኛ ከላም ወተት አምጪ፤ ላም ጋ ብሄድ ከአጫጆቹ ጭድ አምጪ፤ አጫጆቹ ጋ ብሄድ ከቀጥቃጮች ማጭድ አምጪ፤ ቀጥቃጮቹ ዘንድ ብደርስ ከላዕያውያን ከሰል ካመጣሽ እንሰጥሻለን አሉኝ፡፡ እባካችሁ እናንተ እንኳ እሺ በሉኝ፡፡”
ከሰል አክሳዮቹ ራሩላትና ከሰሉን ሰጧት፡፡
እመት ዶሮ እየከነፈች ከሰሉን ይዛ ለቀጥቃጮቹ ሰጠች፡፡ ማጭድ ተቀብላ ለአጫጆች፤ ከነሱ ጭድ ተቀብላ ለላም፤ ከላም ወተት ወስዳ ለቄሱ ሰራተኛ፤ ከሷ የመርፌ ክር ተቀብላ ለሎሚ ዛፍ፤ ከሎሚ ዛፍ ቅጠል ተቀብላ ወደ ወንዙ በረረች፡፡ ከወንዙ ውሃ ተቀብላ ወደ አውራ ዶሮ ባሏ ከነፈች፡፡
አውራ ዶሮ ባሏ ግን ለአንዴም ለሁሌም ፀጥ ብሏል፡፡ ሞት ቀድሟታል፡፡
*   *   *
ችግር ሠንሠለቱን ሲተረትር ሰው በማህል ያልቃል፡፡ አያድርስ ነው፡፡
ገጣሚ ደበበ ሰይፉ፤ በ “አክሱም ጫፍ አቁማዳ” ግጥሙ ትግራይ ለሸዋ፣ ለአርሲ ለሲዳሞ፣ ለወለጋ፣ ለጐንደር፣ ለኤርትራ እህል ተለማምነው፤ የተላከችው አቁማዳ አንዳችም እህል ሳይገባባት ተመልሳ ለባለቤቱዋ ለትግራይ ባዶዋን ትመጣለች፡፡
“…አክሱም ላይ ሠቀላት
ከባዶ አቁማዳ ነው፣ እሚዛቅ ፍቅራችን” ብሎ ይደመድማል፡፡ አንድምታው ብዙ ነው፡፡ የችግሩ መጠን ይለያያል እንጂ በየሠንሠለቱ ቀለበት ላይ ችግር አለ፡፡ ቢሮክራሲያችንም እንደዚያው ነው! ሁሉም ለየግብዓቱ ጥሬ ዕቃውን ይጠይቃል፡፡ ይሄን ሠንሰለት ሙስና ብንለውም፤ ወይም የቅብብሎሽ ሂደት፤ አሊያም ዱላ ቅብብሎሽ፤ ዞሮ ዞሮ የታነቀው ህዝብ ለአንዲት ፍሬ መሞቱ አሳዛኝ ሀቅ ነው!
የችግሮቻችን ብዛት የመፍትሔዎቻችንን ውስብስብ ገፅታ ከወዲሁ ጠቋሚ ነው፡፡ የቆዩ ችግሮች መፍትሔ ሳያገኙ፤ አዳዲሶቹን ለመፍታት መጣራችን ራሱ አንድ ተጨማሪ ችግር ይሆንብናል፡፡ የሀገራችን ቁልፍ ጉዳይ ችግርን በሌላ ችግር መፍታት መሆኑ አሳሳቢ ከሆነ ቆይቷል፡፡ አብሮ መታየት ያለበት ግን ችግርን የመገንዘብ አቅማችንም አናሳ መሆን ነው፡፡
አንድ ፈላስፋ እንዳለው፡-
“The Problem is us; the Solution us” (ችግሩም እኛ፤ መፍትሔውም እኛ እንደማለት) ስለዚህ “እንዳልተመለሰው ባቡር” ያልተመለሱ ጥያቄዎች ሲደመሩ አዲስ ጥያቄ እያረግን ማሰብ ይበጃል፡፡
ሀ+1= ለ
ሀ= የዱሮ ችግር፣ “1” = አዲሱ ችግር፤ “ለ” = ያሁኑ ሁኔታ፤ እያልን ማስላት ነው፡፡ የዱሮ ችግር ብለን በመዝገብ የተያዙ ሂሳቦችን ካላወራረድን ነገ ኦዲተር አይለቀንም!
ከዲሞክራሲ ምን ጐሎ ነበር? ከፍትሕ ምን ጐሎ ነበር? ከሙስና መፍትሔ ምን ጐሎ ነበር? ከመልካም አስተዳደር ምን ጐሎ ነበር? ከሹምሽር ሥራ ምን ጐሎ ነበር? ህዳሴውስ ተመርምሯል ወይ? ከምርጫ ዝግጅት አሁን ምን ጐሎዋል? ከዱሮ ምርጫዎችስ ምን ጐሎ ነበር? በዚህ ሁሉ ድምር ሂሳብ ዛሬ ምን ላይ ነን? በአየር ጊዜ ክርክር አድማጩ ህዝብ እየረካ ነው? ምርጫው የተበላ ዕቁብ ነውን? የሚለው አስተሳሰብ መክኗል ወይስ በየልቡ ያኮበኩባል፡፡
በተፅዕኖ ከመምረጥ ጀምሮ አንዳንዱን ጠፍቶ ድንገት የመጣ ተመራጭ “አፋልጉኝ” እስከማለት የደረሰ፤ በስላቅ በሚኖር ህብረተሰብ ውስጥ ምርጫው አድሎ የሌለውና ዕውነተኛ (ነፃ) [Fair and Free] ነው ብሎ ለመኩራት፣ ለመተማመንና “አሹ!” ለማለት ከባድ ነው፡፡ “ዐባይን ጭብጦዬን ከወሰደብኝ በኋላ አላምነውም!” ያለውን ባላገር ደግመን ደጋግመን እንድናስብ የሚያደርገን ፖለቲካዊም ባህላዊም ተፈጥሮ ያለን ነንና እንዴት ይሆን ወደፊት የምንገፋው ማለት አመላችን ነው!
“አይሠግሩም ተብሎ
ፈረስና በቅሎ፤
አይሮጡም ተብሎ
ፈረስና በቅሎ፤
እንዲያው በጥላቻ:-
ትመረጥ ይሆናል ኤሊ ለኮርቻ!” የሚለው አገርኛ አባባል፤ ጥቂት ቆም ብለን እንድናስብ ዐይናችሁን ክፈቱ ይለናል፡፡

Read 4593 times