Saturday, 02 May 2015 11:47

ተኝቶ ከማልቀስ በርትቶ መታኮስ!

Written by 
Rate this item
(3 votes)

   እንቅልፍ ከዓለም መሸሸጊያ ጥግ ነው፡፡ ከህይወት ተፋቶ፤ ከኑሮ ተለይቶ ሌላ ዓለም ውስጥ መግባት ነው፤ መተኛት፡፡
በእንቅልፍ ቡልኮ መጋረድ፣ ከዓለም ለተኳረፈ ምቹ ምሽግ ነው፡፡ ህይወት ጥልቅ ናት፤ በጥልቀትዋ ልክ መጥለቅና ከሁሉ በላይ መምጠቅን መታደል ቀላል አይደለም፡፡ ቀላል አይደለም ሳይሆን ከባድ ነው፡፡ ክብደቱ የሚሰማው ደግሞ ልብ ላይ ነው፡፡
መጥለቅና መምጠቅ የተለያዩ የሚመስሉ ነገር ግን ተመሳስሎን የታደሉ ቃላት (ወይም ሀሳቦች) ናቸው፡፡
ህይወት ጥልቅ ናት ብለናል፡፡ በህይወት ጥልቀት ልክ መጥለቅ ለሰው የሚቻል አይመስልም። የህይወት ጥልቀትዋና ርቀትዋ ሩቅ ነው፡፡ ወደ ህይወት ለመጥለቅ፣ በጥልቀት ተመልካችና አጥልቆና አርቆ አሳቢ መሆን ያስፈልጋል፡፡ ውጫዊ ገፅታን ለማሳመር ቀለም መቀባባት እና የላይ የላይ ኑሮ መኖር ወይም የለብለብ ዕውቀት ባለቤት መሆን ህይወት ላይ አያነግስም፡፡ ህይወት ላይ ለመንገስ ህይወትን በጥልቀትና በርቀት መገንዘብ የተገባ ነው።
እርግጥ ነው ይህን ሳያደርጉ የሆነ ደረጃ ላይ ደርሰው ወይም ስኬታማ መስለው የሚታዩ ሰዎች አሉ፡፡ ነገር ግን የአጭር ርቀት ተጓዦች እንጂ ከህይወት ጋር በማይሎች የሚጓዙ አይደሉም፡፡ ከጥቂት ርቀት ጉዞ በኋላ ዘሎ ወራጆች ናቸው፡፡
ህይወት ጥልቅና ውስብስብ የሆነች፤ እንደ ዕጢ የጠጠረች፤ በተፈጥሮ ንጥረ ነገሮች የተሞላች ግዙፍ ክስተት ናት፡፡ ኑሮ አድካሚና ለቀቢፀ-ተስፋ የሚድር፣ በቀላሉ ግን የማይሰበር ወይም የማይሞነጫጨር አለት ነው፡፡
የህይወትን የመምጠቅ ዓይነት ወይም የምጥቀት ደረጃ ለመገንዘብ ምጡቅ (ጂኒየስ) መሆን ሳያስፈልግ አይቀርም፡፡ ህይወት እንዲሁ ዝም ብላ መለስ ቀለስ የምትል፤ እንዲሁ ዝም ብላ የምትንጎራደድ ባልቴት አይደለችም፡፡ በርካታ ምርጫዎችን ከፊት ለፊታችን ታቀርብልናለች፡፡ የተሻለና የሚስማማኝ ነው የሚለውን መምረጥ የባለቤቱ ኃላፊነት ነው፡፡
ዓለም በተቃርኖ የተሞላች ናት፡፡ እያንዳንዱ ማንነት ወይም ክዋኔ አቻው የሆነ ሌላ ማንነት ወይም ክዋኔ አለው፡፡ ለወንድ ሴት፣ ለፀሐይ ዝናብ፣ ለመዓልት ሌሊት፣ ለብርሀን ጨለማ፣ ለህይወት ሞት፣ ለቅጥነት ውፍረት፣ ለርዝመት እጥረት፣ ለሀዘን ደስታ፣ ለለቅሶ ሳቅ … ወዘተ ….
ኑሮ ትግል ነው፡፡ እንደ በላይ ዘለቀ የበረታ፤ እንደ ማህተመ ጋንዲ ሰፊ ልቦና የታደለ፤ እንደ አብርሀም ሊንከን የፀና፤ እንደ ማርቲን ሉተር ኪንግ “በቃን!” ለማለት የደፈረ፤ እንደ ሶቅራጠስ በጥልቀት ያሰበ የሚረታው!
ያለበለዚያስ?!
ያለበዚያማ የሚሆነው ግልፅ ነው፡፡ ምርጫው ሁለት ነው፡፡ መርታት ወይም መረታት፡፡ መርታቱ ካልሰመረልን መርታት ዕጣ ፈንታችን ይሆናል፡፡ …
እውነት ነው፤ የኑሮ ጫና ከባድ ነው፡፡ እንደ ቀምበር ትከሻ የሚቆረቁር፤ እንደ ገጀራ አንገት የሚቀላ፤ እንደ ታቦት ስጋነ የሚያኮሰምን፤ እንደ ጅቡቲ በወበቅ የሚያፍን፤ እንደ ራስ ዳሽን ተራራ በቅዝቃዜ የሚያኮማትር ወዘተ …
የኑሮ ጫና ክብደት በቀላል ቃላት የሚገለፅ አይደለም፡፡ ጫናውን አጉልቶ አግዝፎ ለማሳየት የቃላት ኃይል ደካማ ነው፡፡
ለማንኛውም ህይወት እንዲህና እንዲያ ናት፡፡
* *  *
የሰው ልጅ ሸክላ ነው፡፡ በቀላሉ የሚሰነጠቅና በቀላሉ የሚሰበር! …
የየሰው ልጅ ሸክላ መሆኑን መረዳትና ለማስረዳት መሞከር ከንቱነትን መስበክ አይደለም። መሬት ላይ ያለውንና ስር የያዘውን እውነት ከመገንዘብ የሚመነጭ ራሱን የቻለ አንድ እውነት ነው፡፡ ሰው ሸክላ ነው ስል ተሰባሪ ነው ለማለት ብቻ አይደለም። ተሰባሪነቱ እንዳለ ሆኖ ከተሰበረ በኋላም በሌላ መልኩ ይሁን እንጂ ህልውናው መቀጠሉን ለመጥቀስ ጭምር ነው፡፡
በዕውቀቱ ስዩም እንዳለው ነው፡-
“ጋን ከጀርባ ወድቆ፣ ገል ሆኖ ቀጠለ
ከመሰበር ወድያም ሌላ ህላዌ አለ፡፡”
…ለመልማትም ለመጥፋትም መንገዱ ክፍት ነው፡፡ ማዕከላዊው ነገር ሰው ነው፡፡ ትልቁ ቁም ነገር ሰው መሆን ነው፡፡ ሰው ነን ካልን በኋላ ማንዴላን መሆንም ሆነ ሂትለርን መሆን የምርጫችን ጉዳይ ነው፡፡ ፈጣሪ ሰው አድርጎ ፈጥሮናል፡፡ ፈጥሮ ግን አልጨረሰንም፡፡ ትንሽ ዕድልና መጠነኛ ድርሻ ለ‘ኛ ትቷል፡፡ ሰው አርጎ ከፈጠረን ወዲያ ሰናይ ወይም እኩይ የሚባለውን ማንነት ለመጎናፀፍ ምርጫው ያለው በእጃችን ነው፡፡ ማንዴላንም ሆነ ሂትለርን ሰው አድርጎ የፈጠረው ፈጣሪ ‘ራሱ ነው፡፡ ማንዴላን ማንዴላ፣ ሂትለርን ሂትለር ያደረገው ሰብዕና የተፈጠረው ግን በ ‘ራሳቸው (በማንዴላና በሂትለር) ነው፡፡
ሁለቱም የ‘ራሳቸውን የተለያየ መንገድ ተከትለዋል፡፡ ማንዴላ ሰናይ፤ ሂትለር እኩይ!...
ህይወት ፈተና ናት፡፡ ደካማውና ጠንካራው በወንፊት የሚጠለልባት!... የብርቱው ብርታትም ሆነ የለፈስፋሳ ሰው ደካማነት በሰፌድ የሚበጠርባት!..
ህይወት ፈተና ናት፡፡ ህይወት ጦር ሜዳ ናት፡፡ ህይወት ፈተናና ጦር ሜዳ በመሆንዋ ምክንያት ብቻ ሁለት አማራጭ እንደ ጅግራ ከፊታችን ይገተራል፡፡ ተኝቶ ማልቀስ ወይም በርትቶ መታኮስ!
ውጣ ውረድ ያዘለው፤ ወድቆ መነሳት ያጣመነው ማንነት ላይ እንደ በቆሎ የተዘራን፤ እንደ ዛፍ የበቀልን፤ እንደ ፅጌረዳ ያበብን ሰዎች ነን፡፡ (ፅጌረዳ ስል ከአበባው ጋር እሾህም መኖሩን ጠቆም አድርጎ ማለፍ መልካም ነው!)…
ትግል የህይወታችን አንዱ ክፍል ነው፡፡ በአካባቢያችን ከሚገኝ ደንቃራ ጋርም ሆነ ከ‘ራስ ጋር ሳይታገሉ ውሎ ማደር፤ አንግቶ ማምሸት፤ አምሽቶም ማንጋት፤ የሚቻል አይደለም፡፡ ደደቢት በረሀ ባንገባም፤ አሲምባ ተራራ ላይ ዳስ ባንጥልም፤ ሁላችንም ታጋዮች ነን፡፡ በህይወት ናቅፋ፣ በኑሮ ሳህል ላይ የተሰማራን ተራ ዜጎች ነን፡፡
“ተራ!” አልኩ?! … ተራ ምንድን ነው?
እውነት ለመናገር “ተራ” የሚባል ሰው የለም፡፡ ዜግነትም በተራነት የሚገለፅ ነገር አይደለም፡፡
ከፍታና ዝቅታ በህይወት ውስጥ የሚፈራረቅ ነገር ስለሆነ፣ ባንዱ ረክቶና ሰክኖ ለሁሌው የሚዘልቅ፤ በአንድ ቦታ ተረጋግጦ ስር ሰዶ የሚገኝ ፍጡር፤ ከፍጡርም ሰው አይገኝም፡፡
ወርቅ በእሳት እንደሚፈተነው፤ ሰው በመከራ ይፈተናል፡፡ ፈተና የሚጥላቸው ሰዎች እንዳሉ ሁሉ፤ በፈተና የሚሰሩ፣ በፈተና የሚፈጠሩ ሰዎችም አሉ፡፡ ስንዴ ፈካ፣ ፀዳ የሚለው ከተፈተገ በኋላ እንደሆነው ሁሉ፤ ከፈተናው በፊት ምንም የሆኑ ከፈተናው በኋላ ግን እንደ አዲስ፣ አዲስ ሆነው የሚፈጠሩ ሰዎች አሉ፡፡
መሰናክል ብልሀት ለመፍጠር አዕምሮአችንን እንድናሰራው ያደርገናል፡፡ የሰው አዕምሮ ደግሞ ረቂቅና መጢቅ አይደል?! ከደንቃራው ለማለፍ በምናደርገው መፍጨርጨር ብርታትን እንጎናፀፋለን፡፡ መሰናክልን እናሰናክላለን፡፡
በፈተና የተገነባ ሰውነት በቀላሉ አይዝልም። በፈተና ያደገና የጎለመሰ ተክለ-ሰብዕና በቀላሉ አይዘምም፡፡ በፈተና የታሸ ልብ በቀላሉ ሊወድቅ ወይም ሊመታና ሊረታ አይችልም፡፡
ህይወት የትግል መድረክ ናት፤ ተኝቶ ያለቀሰ ሳይሆን በርትቶ የተታኮሰ የሚነግስባትና ዘውድ የሚጭንባት ልዕልት!... ችግርን በመሸሽ ሳይሆን ፊት ለፊት ተጋፍጦ በማሸነፍ የማይነቃነቅ፣ ፅኑና ብርቱ ማንነትን ልንገነባ እንችላለን፡፡ ይገባልም፡፡
በርትተን ከተታኮስን ዛሬን ብቻ ሳይሆን ነገንም የግላችን ማድረግ እንችላለን፡፡
ዛሬ ብቻ ሳይሆን ነገም የኛ ነው፡፡
በሮበርት ስቹለር ስንኞች ልሰናበት፡፡
“The sun is shining, the sky is blue!
There is a new day dawning for me and you.
With every dawning of the sun
New possibilities have just begun
With every breaking of the morn
Fresh opportunities are newly born.”

Read 3957 times