Saturday, 02 May 2015 11:10

“የኛ” እና የስኬት ጉዞው

Written by 
Rate this item
(6 votes)

     የቲያትር ትምህርቷን በከፍተኛ የትምህርት ተቋም ለመከታተል ከትውልድ አገሯ ባሌ፣ አጋርፋ አካባቢ የመጣችውን ለምለም ኃይለሚካኤል (ሚሚ)፣ በጥልቅ የሙዚቃ ፍቅሯ የተነሳ በ“ኢትዮጵያን አይድል” ለመወዳደር የትውልድ ቀዬዋን ጅማን ለቅቃ አዲስ አበባ የገባችው ጠሪፍ ካሣሁን (ሜላት) እንዲሁም እዚሁ አዲስ አበባ ተወልደው ያደጉት ራሔል ጌቱ (ለምለም)፣ እየሩሳሌም ቀለመወርቅ (ሣራ) እና ዘቢባ ግርማ (እሙዬን) ያገኘኋቸው እንደ ብርቅ ከሚታዩበት የአማራ ክልል ደብረታቦር ከተማ ውስጥ ነበር፡፡
“የኛ” በሚል ስያሜ የሚታወቀው ፕሮጀክት፤ በኢመርጅ ሊደርስ ኮንሰልታንሲ ትሬይኒንግ፣ በማንጐ ፕሮዳክሽንና በዴሎይት ኮንሰልቲንግ በተቋቋመው ኮንሰርቲየም የሚተዳደር ሲሆን በእንግሊዝ መንግስት የልማት ድርጅት (ዲኤፍአይዲ) እና በናይክ ፋውንዴሽን ትብብር በገርል ሀብ ኢትዮጵያ የገንዘብ ድጋፍ የሚከናወን ነው፡፡ ፕሮጀክቱ እነዚህ አምስት ወጣት ሴቶች የተወኑበትን አዲስ ፊልም ሰሞኑን በጥንታዊቷና ታሪካዊቷ የደብረታቦር ከተማ አስመርቋል፡፡ ከአዲስ አበባ በ666 ኪሎ ሜትሮች ርቀት ላይ የምትገኘው የደብረታቦር ከተማ ነዋሪዎች በ11 ሰዓት ላይ ለሚከናወነው የፊልም ምረቃ ፕሮግራም ገና በስምንትና ዘጠኝ ሰዓት ላይ ሥፍራውን አጨናንቀውት ነበር፡፡
የአካባቢው ህብረተሰብ ሣምንታዊውን የ “የኛ” የሬዲዮ ድራማና የአምስቱን ወጣቶች ሙዚቃ አጥብቀው የሚከታተሉና በእጅጉ የሚወዱ እንደሆኑ ሁኔታቸው ይመሰክራል፡፡ እስካሁን በሬዲዮ ድራማቸው የሚያውቋቸውና የሚያደንቋቸው ገፀባህሪያት፡- ሚሚ፣ እሙዬ፣ ለምለም፣ ሣራና ሜላት ፊልም ሲሰሩ ደሞ ለማየት እጅግ የጓጉ ይመስላሉ፡፡ ህፃን አዋቂው በሁለት ትላልቅ የፊልም ማሳያ ስክሪኖች ለእይታ የሚበቃውን ፊልም ለማየት አሰፍስፏል፡፡ የሁለትና የሶስት ሰዓታት የእግር ጉዞ አድርገው ከሥፍራው የደረሱ ወጣቶችም ነበሩ፣ እነዚህ አምስት ወጣቶች በአካባቢው ያተረፉትን እውቅናና በህብረተሰቡ ላይ የፈጠሩትን ስሜት ማወቅ እምብዛም አስቸጋሪ አይደለም፡፡ ይህም ፕሮጀክቱ የተቀረፀበትን ዓላማ ተግባራዊ እያደረገ ለመሆኑ ማሳያ የሚሆን ነው፡፡ በሥፍራው እየተዘዋወርኩ ያነጋገርኳቸው ወጣቶች፣ ታዳጊዎችና አዋቂዎች ስለየኛ፣ ስለድራማዎቹና ዘፈኖቻቸው በሚገባ ያውቃሉ፡፡ ፕሮጀክቱ ትኩረት አድርጐ በሚንቀሳቀስባቸው የሴቶች ጥቃት፣ ያለዕድሜ ጋብቻና አስገድዶ መድፈር በስፋት በሚታይባቸው የአማራው ክልል አካባቢዎች ሴቶች ልጆችን ወደኋላ ከሚያስቀሩ አስተሳሰቦችና ተግባራት አላቆ ማህበራዊ ለውጥን ለማምጣት የተቀረፀ ሲሆን የሬዲዮ ፕሮግራሙ በአካባቢው እጅግ ተደማጭ መሆኑን ለማወቅ ችያለሁ፡፡
በአምስቱ ወጣት ሴቶች የተሠራው ፊልም ምረቃ ሲጠናቀቅ ወጣቶቹን ለማየት፣ ከተቻለም በእጅ ለመንካት የአካባቢው ወጣቶችና ህፃናት ያሳዩት የነበረው ሁኔታ እጅግ ስሜት የሚነካ ነበር፡፡ የዩኒቨርሲቲ ተማሪ የሆኑ ወጣት ሴቶችም አምስቱ ወጣቶች ያረፉበት ሆቴል ድረስ በመሄድ ለወጣቶቹ ስሜታቸውን የገለፁበት ሁኔታ አስገራሚ ነው፡፡
ሰሞኑን በሊቢያ በወገኖቻችን ላይ የደረሰውን አሰቃቂ ግድያ ተከትሎ በመገናኛ ብዙሃን በተደጋጋሚ የሚሰማው  በእነዚህ አምስት ወጣቶች የተሰራው የስደት ዘፈን የፊልሙ አካል ሲሆን የተመልካቹን ስሜት  በእጅጉ የነካ ነበር፡፡
እሩቅ ማዶ እሩቅ አገር ሄዳለች
እታበባ ውብ አለሜ የት አለች
በእኔ እድሜ ነበር የተላከችው
ከማታውቀው አገር የተሸኘችው
እንኳን ጠረኗ ጠፍቶ ትንፋሿ ነው
የእሷ እጣ ታሰበ ለእኔ ለታናሿ፡፡
የሚል ስንኝ ያለው ዘፈኑ፤ የስደትን አስከፊነትና መራራነት አጉልቶ የሚያሳይ ነው፡፡ ከፈልም ምረቃው በኋላ ከ5ቱ ወጣቶች ጋር በጅማሬያቸው፣ በህልሞቻቸው፣ በተስፋዎቻቸውና በገጠመኞቻቸው ዙሪያ ጥቂት አውግተን ነበር፡፡
    
      ለፕሮጀክቱ እንዴት ታጫችሁ?
ለፕሮጀክቱ የታጨነው የተሰጠውን ፈተና ተወዳድረንና አልፈን ነው፡፡ አምስታችን ከመመረጣችን በፊት ለውድድር የቀረብነው 69 የምንሆን ልጆች ነበርን፡፡ ውድድሩ በ3 ዙሮች የተሰጠ ሲሆን ይህንን ሁሉ አልፈን ነው የተመረጥነው፡፡
ወደ ሥራው ስትገቡ እንዲህ አይነት ዓላማ ያለው ሥራ እንደሆነ ታውቁ ነበር?
ሥራው ሲጀመር እንዲህ ዓይነት ፕሮግራም መሆኑን አናውቅም ነበር፡፡ አንድ ተከታታይ የሆነ የሬዲዮ ድራማ እንደሚሰራ ነበር የምናውቀው፡፡ ሥራው የሴቶችን አቅም ለማጎልበት የሚያስችል ፕሮጀክት እንደሆነና ሙዚቃ ያለው ድራማ ያለው እንደሆነ የተነገረን ወደ ሥራው ከገባን በኋላ ነው፡፡ ከዛ ሥራውን በሚገባ ተገንዝበን እኛም እራሳችን የፕሮጀክቱ አባል ሆንን፡፡
የ“ኛን” ከተቀላቀልን በኋላ የመጀመሪያዎቹ 6 ወራት ከምንሰራው ነገር ጋር በደንብ እንድንተዋወቅና እንድንዋደድ የተደረግንበት ጊዜ ነበር፡፡ ይህም የምንሰራውን ሥራ በሚገባ እንድናውቀው፣ እርስ በርሳችንም በደንብ እንድንተዋወቅ ረድቶናል፡፡ የስድስት ወራት የልምምድ ጊዜያችን ሲጠናቀቅ ሁላችንም ቀደም ሲል ከነበረን አስተሳሰብ በእጅጉ ተለወጥን ነበር፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የትወና፣ የሙዚቃና የድምፅ ስልጠናዎች በብቁ ባለሙያዎች ይሰጠን ነበር፡፡ በድራማው ላይ ወክለን የምንተውናቸውን ገፀ ባህሪያት በድንብ እንድናውቃቸውና እንድንለምዳቸው ለማድረግ ከገፀባህርይው ጋር ተመሳሳይነት ካላቸው ሰዎች ጋር እንድንውል ተደርገናል፡፡ ይህ ደግሞ እጅግ የቀየረንና ሥራው በድንብ ስሜት ሰጥቶን እንድንሰራው አድርጐናል፡፡
ስለሴቶች ጥቃትና ችግር የነበረን ግንዛቤ እንደአብዛኛው የህብረተሰብ ክፍል ነበር፡፡ ስለጉዳዩ በየሚዲያው የሚነገረው አሰልቺ በሆነ መልኩ ስለነበር፣ ጆሮ ሰጥተን ለማዳመጥና ግንዛቤ ለመጨበጥ አልቻልንም ነበር፡፡ ነገር ግን “የኛ” ይህንን ቀየር አድርጎ ሳቢና አዝናኝ በሆነ መልኩ፣ የሰዎችን አስተሳሰብ ሊለወጥ የሚችል ፕሮግራም ቀርፆ ወደ ሥራ በመግባቱና እኛም የዚህ ፕሮጀክት አባል በመሆናችን እጅግ ደስተኞች ነን፡፡
የፕሮግራሙን ዓላማ ምን ያህል ተረድተነዋል ብላችሁ ታስባላችሁ?
ሴት ልጆችን ወደ ኋላ የሚያስቀሩ አስተሳሰብና ተግባራት በስፋት በሚታይባቸው አካባቢዎች እነዚህን ተግባራት ለማስቀረት የሚችልና ሴቶችን በማስተማር ማህበራዊ ለውጥ ለማምጣት የሚያስችል ዓላማን ይዞ የተጀመረ ፕሮጀክት መሆኑን እናውቃለን፡፡ ማህበረሰቡ የአስተሳሰብ ለውጥ በማምጣት፣ ሴት ልጆችን ማበረታታት መደገፍና ማስተማር እንደሚገባው የማስተማርን ዓላማ ይዞ የሚንቀሳቀስ ነው፡፡ ሴት ልጆች የሚገጥማቸውን እንቅፋት ስናስወግድና እነሱን ስናበረታታ የምንለውጠው የእነሱን ህይወት ብቻ ሳይሆን የማህበረሰቡንም ጭምር ነው የሚል ዓላማ ያለው መሆኑን እናውቃለን፡፡
ይህንን ዓላማ ለማሳካት ጥረታችሁ ምን ያህል ነው? የእናንተስ አመለካከት ምን ያህል ተለውጧል?
ወደ ሥራው ከመግባታችን በፊት ባሉት ስድስት ወራት ጊዜ ውስጥ ያገኘነው ልምድና ትምህርት እኛን ሙሉ በሙሉ የቀየረንና ስራው ወደ ውስጣችን ገብቶ እንዲዋሃደን ያደረገ ነበር፡፡ የስልጠናና የልምምድ ጊዜው ሲጠናቀቅ ሁላችንም በደንብ ነው የነቃነው፡፡ ጉዳቱ በቅድሚያ ለእኛ ሊሰማን ይገባል፡፡ እኛ በደንብ ሲሰማን ነው መልዕክቱን በሚገባ ለማድረስ የምንችለው፡፡ በዚያ የስድስት ወር ጊዜ ከምንሰራቸው ገፀ ባህርያት ጋር እንድንዋሃድ መደረጉ ለዚህ በጣም ጠቅሞናል፡፡ እያንዳንዱን ነገር አውቀነው ውስጣችን ተዋህዶ ነው የምንሰራው፡፡ እያንዳንዷ ከአፋችን የምትወጣው ቃል ምን ስሜት ይዛ አንደምትወጣ መገመቱ ከባድ ነው፡፡ አንድ ሥራ ስንሰራ ስንት ሚሊዮን ሴቶችን መቀየር እንደሚችል እያሰብን ነው የምንሰራው፡፡ የተሸከምነው ኃላፊነት ምን ያህል ከባድ እንደሆነም ይገባናል፡፡
በግላችሁ ከዚህ ፕሮጀክት አገኘነው የምትሉት ዕድልና በህይወታችሁ ላይ ያመጣው ለውጥ  ምንድነው?
ፕሮጀክቱ በግል ለእያንዳንዳችን ትልቅ እድል ነው፡፡ መንገድ ጠራጊያችን ነው፡፡ አስተሳሰብና አመለካከታችንን በሚገርም ሁኔታ ለመለወጥ እንድንችል ያደረገንም ነው፡፡ “የኛ” ከትልቅ ግንድ የተነሳና በርካታ ቅርንጫፎች ያሉት ዛፍ ነው፡፡ ሰፊ ቤተሰብ ያለው፣ ሁሉም በኃላፊነት ስሜት ሥራውን በመከባበርና በፍቅር የሚሰራበት ቤት ነው፡፡ ከዚህ ፕሮጀክት አባላት ጋር አብሮ መስራት በራሱ ትልቅ ዕድል ነው፡፡ ሲቀጥል ደግሞ በህይወታችን ህልም የሆኑብንና እንኳንስ አብረናቸው ልንሰራ ቀርቶ ለማየት እንጓጓላቸው ከነበሩ ታላላቅ ሙያተኞች ጋር ለመስራት መቻል የማይታመን እድል ነው፡፡ እንደ አይዳ አሸናፊ፣ ሰሎሜ ታደሰ፣ አስቴር አወቀ፣ አብርሃም ወልዴ፣ ፍቃዱ ተክለማርያም፣ ዓለማየሁ ታደሰና ኃይሌ ሩትን ከመሳሰሉ ታላለቅ ሙያተኞች ጋር ለመስራት መታደል ቀላል ነገር አይደለም፡፡ እነዚህ ሰዎች‘ኮ ህልሞቻችን ነበሩ፡፡ በተረፈ የሙዚቃና ትወና ችሎታችንን በማዳበር፣ ከሰዎች ጋር እንዴት ተግባብቶ መስራት እንደሚቻል ስለተማርንበት ቀላል የማይባል ጠቀሜታን ሰጥቶናል፡፡ ከዚህ ሁሉ በላይ ግን የራሳችን አስተሳሰብ እንዲቀየርና ስሜቱ እንዲሰማን በማድረጉ ረገድ ትልቅ ጠቀሜታ አለው፡፡ በቃላት ሊገለፅ የማይችልና ከአዕምሮ በላይ የሆነ ዕድል ነው ያገኘነው፡፡ ከዚህ በኋላ ምን ሊያቆመን ይችላል፡፡ ምንም አያቆመንም፡፡ ችግሩ የት ጋ እንዳለ፣ መንስኤና ምክንያቱ ምን እንደሆነና ችግሩን እንዴት መፍታት እንደምንችል እናውቃለ፡፡ እንዲህ ሙሉ እንድንሆን ያደረገን ደግሞ ይህ ፕሮጀክት ነው፡፡
እስከዛሬ በስፋት የምትታወቁት በሬዲዮ ድራማና በዘፈናችሁ ነው፡፡ አሁን ደግሞ ፊልም ሰርታችሁ አስመረቃችሁ፡፡ እንዴት ነው አዲሱ ሥራ አይከብድም?
ምንም አይከብድም፡፡ ፊልሙ ላይ የመጡት ያው የሬዲዮኖቹ ገፀባህሪያት ናቸው፡፡ ለእኛ አዲስ አይደሉም፡፡ ከሬዲዮ ድራማው ውስጥ ተቆርጦ የወጣ ታሪክ ነው ፊልም ሆኖ የተሰራው፡፡ እናም ብዙም አዲስ ነገር ሆኖ አላስቸገረንም፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ሥራውን የሰራነው ከበቂ በላይ ዕውቀትና ልምድ ካላቸው ታላላቅ ባለሙያዎች ጋር በመሆኑ፣ ለእኛ ነገሮች እንዲቀሉና ሥራውን በአግባቡ እንድንሰራው አድርጎናል፡፡ ምንም የተቸገርንበት ነገር የለም፡፡
በሲኒማው ውስጥ የሚታየው ዘፈን ሰሞኑን በአገራችን ከተፈጠረው አስከፊ ሁኔታ ጋር ተገጣጥሟል፡፡ ይህ ለእናንተ ምን ስሜት ሰጣችሁ? ብዙ ሰዎች ዘፈኑ በቅርቡ በኢትዮጵያውያን ላይ በተፈፀመው አስከፊና ዘግናኝ ድርጊት መነሻነት እንደተሰራ ያስባሉ፡፡ እንዴት ነበር ሙዚቃውን የሰራችሁት?
ሙዚቃው የተሰራው በድራማው (በየኛ ድራማ) 4ኛ ሲዝን ላይ እሙዬ የተባለችው ገፀ-ባህርይ ኑሮ ከአቅሟ በላይ ሆኖባት፣ የቤተሰቧን ህይወት ለመለወጥ ወደ አረብ አገር ስደት የምትሄድበት ታሪክ አለ፡፡ በእሱ ምክንያት ነው ሙዚቃውን የሰራነው፡፡
ግን ፊልሙ ውስጥ እንዲካተት ተስማማንበትና አስገባነው፡፡ ለፊልሙ የተሰራው ሌላ ሙዚቃ ነበር፤ እኛ ግን ይህንን መረጥነውና እነሱም ተስማምተውበት ነው የገባው፡፡ ዘፈኑ በእያንዳንዳችን ቤት ውስጥ ያለ ኑሯችን ነው፡፡ ሲከፋሽ ብድግ አድርገሽ የምትሰሚው አይነት ነው፡፡ ስቱዲዮ ውስጥ ዘፈኑን ስንዘፍነው የምር “ፊል” እናደርግ ነበር፡፡ ሙዚቃው ሀዘንን ብቻ አይደለም የሚናገረው፤ ተስፋን፣ ራዕይን ሁሉ የሚያወራ ነው፡፡ ዘፈኑ አሁን ከተፈጠረው ነገር ጋር ሲገጣጠም ወይም ታሪኩ ውስጥ ገብቶ ስክት ሲል እንደ አዲስ ነው ያለቀስነው፡፡ ግጥምጥሙ በጣም አስገራሚ ነው፡፡ አገራችን አሁን የገጠማት ሀዘን ልብ የሚሰብር ነው፡፡ ግጥምጥሙ በደስታ ቢሆንና ዘፈናችን ተደማጭነትን ቢያገኝ ደስ ይለን ነበር፡፡
በዚህ ሥራ ላይ ከተሰማራችሁ በኋላ ወደተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የመጓዝና ከፕሮግራሙ (ድራማችሁ) ተከታታዮች ጋር የመገኘትና ዕድሉን አግኝታችኋል፡፡ በየሥፍራው ስትዘዋወሩና ከአድማጮቻችሁ ስትገናኙ የገጠማችሁ ለየት ያለ ነገር ነበር? ስሜታቸውስ ምን ይመስላል?
በአማራ ክልል የተለያዩ ሥፍራዎች ተዘዋውረናል፡፡ በዚህ ቦታ ያገኘነውን የህዝብ አስተያየትን ለመናገር ቃላት ያጥረናል፡፡ ህብረተሰቡ ሲወድሽ የእውነቱን ነው የሚወድሽ፡፡ የጆሮ ጌጥ፣ ሻሽ፣ የእጅ አምባር እየገዙ ስጦታ ይሰጡናል፡፡ እንጅባራ ውስጥ የእኛን ዘፈን ግማሹን በአገውኛ ቀይረውና ሚክስ አድርገው መድረክ ላይ ሲያቀርቡት ማመን ነው ያቃተን፡፡ የአምስትና የሰባት ሰዓት የእግር መንገድ እየተጓዙ ያለንበት ድረስ ይመጡም ነበሩ፡፡ እስቲ ልንካሽ፣ እስቲ ልንካሽ እስቲ ልቀፍሽ… ሲሉ ስሜት ይነካሉ፡፡ ፍቅራቸው ከምር ነው፡፡ “አንቺን መስማት ከጀመርኩ በኋላ ተስፋ ማድረግ ጀምሬ ህይወቴ ተቀየረ” ሲሉን በጣም ደስ ይለናል፡፡ “መንገድ ላይ ነው አይደል የምታድሪው?” ብሎ ሻርፕ ገዝቶ የሰጠን አድማጭም አለ፡፡ በደብረማርቆስ፣ በአንኮበር፣ በቡሬ ያጋጠመን የተመልካች አቀባበልና ስሜት በቃላት ሊገለፅ የሚችል አይደለም፡፡
ክፍያችሁ ከፍ ያለ እንደሆነ ይነገራል፡፡ ምን ያህል ነው?
 ስለክፍያ የተጋነኑ ነገሮች ሊወሩ ይችላሉ፡፡ ግን እውነታው እንደማንኛውም ጥሩ ተከፋይ ኢትዮጵያዊ አርቲስት፣ በጥሩ የወር ደመወዝ ተቀጥረን መስራታችን ነው፡፡ እኛ የየኛ” ብራንዶች ነን፡፡ ከዚህ የተለየ ሥራ መስራትም አንችልም፡፡ የተመረጥነው ትልቅ ዓላማ ላለው ሥራ ስለሆነ ማለት ነው፡፡ ስለዚህም ውጭ ያለው ሥራ እንዳያጓጓን የሚያደርግ ጥሩ ክፍያ እየተከፈለን እንሰራለን፡፡
ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ ምን የመስራት ዕቅድ አላችሁ?
ለማህበረሰቡ ሊጠቅሙ የሚችሉ ነገሮችን መስራት፣ የአስተሳሰብ ለውጥ እንዲያመጡ ማገዝ፣ ሴቶችን ማስተማርና መደገፍ እንደሚገባና ይህም ዓለማችንን በመቀየር ረገድ ያለው አስተዋፅኦ ቀላል እንዳልሆነ እናስተምራለን፡፡ አንድ እናት ሳትማር ፕሮፌሰርና ዶክተር ሊሆኑ የሚችሉ ልጆችን ማፍራት ከቻለች፣ ብትማርማ ምን ልትፈጥር እንደምትችል እንሰብካለን፡፡ ከዚህ በኋላ ምንም አያቆመንም፡፡ አብረናቸው ከሰራናቸው ሰዎች የተማርነው የስራ ዲሲፒሊን ቀላል ነገር አይደለም፡፡ በደንብ ቀርፆናል፡፡ ከእነዚህ ሰዎች ጋር ስንሰራ ቆይተን፣ ወጥተን የማይረባ ነገር ለመስራት አንችልም፡፡ ስለዚህም የፕሮጀክቱ መጠናቀቅ አሁን ካለንበት አስተሳሰብና አመለካከት አይለውጠንም፡፡ የህብረተሰባችን አመለካከት ተለውጦ፣ ሴት ልጆች ተምረው የተሻለ ደረጃ ላይ መድረስ የሚችሉበትን ጊዜ ለማየት እጅግ እንናፍቃለን፡፡

Read 3465 times