Saturday, 02 May 2015 10:35

ጎረቤትክን ሲያማ ለእኔ ብለህ ስማ!

Written by 
Rate this item
(12 votes)

   ከዕለታት አንድ ቀን አያ ጅቦ አራት ልጆቹን፤ ማለትም - መዝሩጥን፣ ማንሾሊላን፣ ድብልብልን እና ጣፊጦን ይዞ በለሊት መንገድ ይሄዳል፡፡ እየተጓዙ ሳለ ድንገት አንዲት ከቤቷ የወጣች አህያ ያገኛሉ፡፡
ይሄኔ አባት ጅብ፤
“ልጆቼ ሆይ! እንግዲህ እኔ በጣም አርጅቻለሁና ይቺን አህያ እኔ ነኝ የምበላት! እናንተ ራቅ ራቅ ብላችሁ ትጠብቁኛላችሁ” አለ፡፡
ይሄኔ መዝሩጥ፤
“አባዬ ኧረ አንድ ብልት እንኳን አጋራን?” ይለዋል፡፡
“አይሆንም! ምንም አላቀምስህም” ይላል ጅቦ፡፡
ይሄኔ ማንሾላ ይነሳና፤
“ለእኔስ አባቴ?” ይላል፡፡ አያ ጅቦም፤ “እንካ ጆሮዋን ብላው” ይለዋል፡፡
ቀጥሎ ድብልብል ይመጣና፤
“ለእኔስ አባቴ?” ይለዋል፡፡
“አንተ ሽሆና ይደርስሃል” ይላል አያ ጅቦ፡፡
ቀጠለና ጣፊጦ ጠየቀ፡-
“አባዬ የእኔንስ ነገር ምን አሰብክ?” አለ፡፡
“አንተ ቆዳዋን ካገኘህ ያጠግብሃል” አለ፡፡
ልጆቹ አባታቸው አህያዋን ዘርጥጦ ጥሎ ሲበላ ዘወር አሉ፡፡
አያ ጅቦ ዋና ዋናውን የአህያዋን ብልት እንደበላ፤ ድንገት የአህያዋ ጌታ ሲሮጥ መጣ፡፡
አያ ጅቦ ፈርጥጦ መውጫ የሌለው የጫካ ጥግ ውስጥ ገብቶ ይሰረነቅና እየጮኸ ልጆቹን ይጠራል፡፡ ልጆቹ ቀርበው ወደጫካው ይጠጉና፤
“አባታችን ምነው ትጮሃለህ?” ሲሉ ይጠይቁታል፡፡
አያ ጅቦም፤
“አድነን ልጄ መዝሩጥ?” ይላል፡-
መዝሩጥም፤
“አባቴ ምን ሰጥተኸኛል እንደበላህ እሩጥ!” ይለዋል፡፡
“አድነኝ ልጄ ማንሾለላ!” ይላል አያ ጅቦ፡፡
“ምን ሰጥተኸኛል ካንድ ጆሮ ሌላ!?” ይለዋል ማንሾለላ፡፡
“አድነኝ ልጄ ድብልብል?”
“አይ አባት! ሸሆና ለማን ውለታ ይሆናል?!”
ቀጥሎ አያ ጅቦ ጣፊጦን ጠየቀ፤
“አድነኝ ልጄ ጣፊጦ?!”
“ማን የጎረሰውን ማን አላምጦ?” አለ ጣፊጦ፡፡
መላወሻም አጋዥም ያጣው አያ ጅቦ፤ እዚያው ተወጋና ሞተ፡፡
*           *          *
ዛሬ  እኔ ነኝ ዋናው ጅብ ማለት አይሠራም! ቀድመው ያላሰቡበት ግለኝነትና ሆዳምነት ምን ላይ እንደሚጥለን አለማሰብ የማታ ማታ ያላጋዥ ያለመጠጊያ ያስቀራል፡፡ ከካፒታሊዝም ምርኮኛነታችን ጀምሮ ስግብግብነት፣ በዝባዥነት፣ ዘረፋና ግፍ ይበረክታል፡፡ ያላየነው የገንዘብ ትርፍ ማህበራዊ መልካችንን ያዥጎረጉረዋል፡፡ እንኳን ሊያተርፈን ራሳችንን ያጎልብናል፡፡ “አድነኝ ልጄ እገሌ?” ቢባል ምላሽ አይኖረውም፡፡ ዛሬ ከመቼውም ጊዜ በላይ እርስ በርስ መግባባትና መስማማት ያለብን ሰዓት ነው፡፡ የሃይማኖት መግባባታችን፣ ስለአንድነት መግባባታችን፣ ስለድንበር ጉዳይ መግባባታችን፤ ስለዓለም አቀፍ እንቅስቃሴዎች መግባባታችን፤ ከሁሉም በላይ ስለአይኤስአይኤስ መግባባታችን… ብርቱ ጥረት ማድረግን የሚጠይቅ ዘመን ነው፡፡ የሳሱ ድንበሮችና መንግስት አልባ አገራት ወደ አሰቃቂ እልቂት ሊያመሩ እንደሚችሉ፤ ሶማሊያም፣ የመንም፣ ሊቢያም፣ ኢራቅም ለመነሻ አስረጅነት የቆሙ ተጨባጭ ምሳሌዎቻችን ናቸው! ነገ በየአገሩ ይሄው ሁኔታ ላለመከሰቱ ምንም አስተማማኝ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ህልውና የለም፡፡ በትናንሽ የፖለቲካ አታካራ ተሞልተን፣ ትናንሽ ሙሾ በማውረድ ጊዜያችንን ከምናባክን፣ ትልቁን የዓለም አቀፍም አገር አቀፍም ስዕል (The Bigger Picture) የምናይበትን ዐይናችንን እንክፈት፡፡ ምዕራባውያን፤ ባህል፣ ሃይማኖት እና ጥናታዊ ታሪክ ያላቸውን አገሮች ኢራቅ፣ ኢራን፣ ሶርያ፣ የመን፣ ግብፅ፣ ህንድ፣ ጃፓን፣ ቻይና … አሁን ደግሞ የእኛው አገር ኢትዮጵያ ላይ ያነጣጠሩት ያለነገር አይደለም፡፡ ግሎባላይዜሽንን ይነቅፋሉ የሚለው አጀንዳ የዋዛ አይደለም፡፡ ባህል የሌላቸው ባለባህሎቹን እየገደሉ ነው፡፡ የቅርቦቹ ሶማሊያና ሊቢያ በመንግሥት-አልባ ሁኔታ ውስጥ መሆን፣ በማንም ይሁን በማን ለመጠቃታቸው ሰፊ በር ከፍቷል፡፡
ወደ ሊቢያ በጣሊያን አዛዥነት ስለዘመተው ያለዕዳው ዘማች የኤርትራ ወጣት (ደራሲው አበሻ ይለዋል) እንዲህ የሚል ሀሳብ ይገኝበታል፡፡ ስለሊቢያ በረሀ ነው፡-
“የመሸበር ስሜት፣ ሐዘን፣ ተስፋ ቢስነት እና ፀፀት ፊታቸው ላይ ይነበባል፡፡ የበረሀው ስዕል አሰቃቂ ነው፡፡ አንዲት ዛፍ አትታይም፡፡ አንዲትም የሳር አገዳ የለችም፡፡ የውሃ ነገርማ ባይነሳ ይሻለዋል፡፡ ወደየትም አቅጣጫ መንቀሳቀስ አይታሰብም፡፡ ግራ፣ ቀኝ፣ ወደ ፊት፣ ወደ ኋላ፣ ወደየትም መሄድ አይቻልም ምክንያቱም የትም ይሁን የት ህይወት በአሸዋ ተከባ ነው የምትገኘው፡፡ በየትም ቢዞሩ ጠጠር ኮረት ድንጋይ፣ እና የአቧራ ክምር!
ያ በረሀ እንደባህር ሰፊ፣ ግን በጥላቻ የተሞላ!  ባህሩ ውስጥ ቢያንስ ዓሣ ማየትና የማዕበል ድምፅ ማዳመጥ ይቻላል፡፡ እዚህ ሊቢያ በረሃ ግን አንዲትም ወፍ አትዘምርም፡፡ አትበርምም፡፡ ያ ክፍቱ ደመና አልባ ሰማይ የጋለ ምድጃ ነው፡፡ በዚያ ጠራራ ንደድ ውስጥ ያለ ሰው፣ ያ መሬት፣ የህይወት ይሁን የሞት መለየት ይሳነዋል፡፡ ይሄን መሬት ከአረንጓዴው፣ ከንፋሳማው እና ከለሙ የኢትዮጵያ ምድር ጋር ማነፃፀር ከንቱ ድካም ነው! የሲዖልና የገነት ነው ልዩነቱ!?”
ስለአበሻ የጦርነት ብቃት የሚገርም ትንተናም አለው - በሊቢያ በረሐ፡- አበሻ፣ ጣሊያንና አረብ የውጊያ መንፈሳቸው ምን ይመስላል?
“ለአበሻ፣ ጦርነት ውጤቱ ምንም ዋጋ ያስከፍል ወደፊት መግፋት ነው፡፡ (ግፋ በለው እንደማለት) ለጣሊያኖች፤ አዛዥህ እንዳለህ ተዋጋ ነው፡፡ ጠላት ግንባር ለግንባር ቢፋጠጥህም ካልታዘዝክ አትተኩስም፡፡ ካልታዘዝክ ብትታረድም ፀጥ በል ነው!
ለዐረቦች ወደ ጠላትህ ፈጥነህ ሩጥ፡፡ ሁኔታው የሚያዋጣ ከመሰለህ ነብስህን ለማዳን ፈርጥጥ ነው፡፡ የየተዋጊውን ባህሪ ለእኔ ብሎ መስማት የእኛ ፈንታ ነው፡፡ ጊዜው አስጊ ነው፡፡ ጎረቤቶቻችንን በቅጡ እናስተውል፡፡ ሩቅ የሚመስሉንን ዕጣ ፈንታ ስናይ፣ “ያንተ ቤት ሲንኳኳ ይሰማል እኔ ቤት!” እንበል፡፡ “ጎረቤትክን ሲያማ ለእኔ ብለህ ስማ!” ማለት የአባት ነው!! 

Read 5440 times