Saturday, 25 April 2015 10:45

የጨለማው መሰላል

Written by  ብርሀን ጌታ
Rate this item
(1 Vote)

     አየር ማረፊያ ልቀበላት ይገባኝ ነበር፡፡ ግን አልቻልኩም፡፡ ለዚህ ነበር ቀድሜ ከቤት ልጠብቅ ማቀዴ፡፡ እሱም እንዳልተሳካልኝ የተረዳሁት በር ላያ የሚኪን መኪና ሳይ ነበር፡፡ እሱ እንዲያመጣቸው ስለነገርኩት እንደቀደሙኝ እርግጠኛ ሆንኩ፡፡ እንዴት ቶሎ ደረሱ? ከአሜሪካ የገቡት ጠዋት ነበር፡፡ በእርግጥ እንዳይጉላሉ ወደ ባህር ዳር የሚያመጣቸው ትኬትም ቀድሜ አስይዤላቸው ነበር፡፡ ቸልተኛ የሆንኩ እንዳይመስላቸው ሰጋሁ፡፡ እርግጥ ቤት ውስጥ ተገቢው ነገር ሁሉ እንዲዘጋጅ አድርጌአለሁ፡፡ እናቴና የህፃኗ እናትም መጥተው ስላደሩ የጎደለ ሊያሟሉ ይችላሉ፡፡ ኧረ ሰራተኞቼም ለዚህ አይሰንፉም፡፡ ብቻ ባታስብበት ነው ጥላን ስራ የሄደችው እንዳይሉኝ፡፡ እኔ ደግሞ በህይወት እያለሁ ሥራዎቼን በጠዋት ካላየሁ ደስታ አይሰማኝም፡፡
ሹፌሬ መኪናውን አቆሞ ፈጠን ብሎ በመውረድ ከኋላ የጫነውን ዊልቼሬን ፈጥኖ አቀረበልኝ፡፡ እግሮቼ እንዳይራመዱ ሆነው የተልፈሰፈሱት ገና ህጻን እያለሁ ነው፡፡ እናቴ “ስትወለጅ ደህና ነበርሽ፤ በአራስነትሽ ወድቀሽ ጀርባሽ ተጎድቶ ነው” ትላለች፡፡ ብቻ እኔ ግን በእግሬ የሄድኩበትን ጊዜ አላስታውስም፡፡ ሹፌሬ ለመቀበያ ያስጋገርኩትን ኬክ ይዞ ከኋላዬ እየተከተለ እኔ ዊልቸሬን እየገፋሁ ሳሎን ገባን፡፡ ቤቴ በሰው ተሞልቷል፡፡ አስፈላጊው ነገር ሁሉ ቀርቦ ግብዣው ደርቷል፡፡ በከንቱ ተሳቀቅኩ! ቤቴ ሲመጡ በመጥፋቴ ጓጉቼ ባለመቀበሌ አልተቀየሙኝም፡፡
እንደውም ከሞት ተርፌ ከውጭ የመጣሁትና እኔ እስኪመስለኝ ድረስ ሁሉም ቆመው በክብርና በደስታ ተቀበሉኝ፡፡ ደነገጥኩ! የማየው የራሴን እህቶችና ወንድሞች ስለመሆኑ ተጠራጠርኩ፡፡ እናትና አባቴ ሳይቀሩ ልጃቸውን፣ ያውም እኔን! ሳይሆን አንድ ባለስልጣን የሚቀበሉ መስለዋል፡፡ ወንድሜም ገና ሲያየኝ በሮ እቅፌ ውስጥ ገባ፡፡
“ውይ አፈር በበላሁ! ስራ አቋርጠሸ መጣሽ አለሜ? በርግጋ እንደተነሳች የተናገረችው እናቴ ነበረች፡፡
“ምን አንገላታሽ ልጄ! የት እንኸድ ብለኝን ያው እንቆይሻለን? ነይ ነይ እስቲ ግቢ! አባቴም ተከትሏት እየተነሳ ተናገረ፡፡
“እንዴዬ ኧረ ቁጭ በሉ? በገዛ ቤቴ እንግዳ አደረጋችሁኝ እኮ?” እውነትም ግራ እየተገባሁ አሳልፌ እንጉዳይን አቅፌ ሳምኳት፡፡ እንጉዳይ የታላቅ ወንድሜ ልጅ ናት፡፡ ከህጻንነቷ ጀምሮ በሽተኛ ነበረች፡፡ የልብ ችግር እንዳለባትና ውጭ ካልታከመች እንደማትድን ያወቅነው ግን ከፍ ካለች በኋላ ነው፡፡  
“ተመስገን! ሁኔታዋን ሳይ ፈጣሪየን ቀና ብዬ አመሰገንኩት፡፡ የወንድሜ ሚስት ልጇን ትታ እኔን መሳም ጀምራለች፡፡ “ምን መናገር እንደፈለገች እንጃ እውነት…እው… እያለች ሳግ ሲያቀርጣት ይታያል፡፡ ወላጆቼም የምርቃቱን ናዳ ያሸክሙኝ ጀምረዋል፡፡ እኔ ግን የሁሉንም ሁኔታ ሳይ ‘ልብሴን ነውር በለው እንጅ እኔስ የቅድሙ ነኝ’ አሉ የሚባለው የአባ ገብረ ሃና ቀልድ መጣብኝ፡፡ ዛሬ አፈር አይንካሽ የሚሉ ዘመዶቼን እንዴት እንዳሳደጉኝ ጭራሽ ትዝ የሚላቸው አይመስሉም፡፡ ለካ የሰው ልጅ ክብሩንም ውርደቱንም የሚፈጥረው ራሱ ነው፡፡ እንዳስቀመጡኝ ቀርቼ ቢሆን አሁን የሚኖረኝን ሁኔታ ማሰብ አንገሸገሸኝ፡፡
የተወለድኩት ደቡብ ጉንደር ጋሳይ ከምትባል የገጠር ከተማ ውስጥ ነው፡፡ የስምንት ልጅ ጌታ ለሆኑት ወላጆቼ ሦስተኛ ነኝ፡፡ የበታቾቼም ሆነ የበላዮቼ የችሎት የችሎታቸውን ያህል ተምረዋል፡፡ የትምህርት ቤት ነፃነት ቀርቆ የግቢዬ ፀሃ እየናፈቀኝ ያደኩት እኔ ብቻ ነኝ፡፡ መራመድ ያልቻልኩት በእኔ ስንፍና ወይም በፍላጎት ገዝቸው አልነበረም፡፡

እነሱ ግን መነሳት፣ መራመድ አቅቶኝ ምድር ላይ ስጥመለመል እንደልዩ ፍጡር አዩኝ፡፡ ስወለድ እንደማንኛውም ልጅ ጤነኛ እንደነበርኩ የምትናገረው እናቴ እንኳን አፈረችብኝ፡፡ የእኔ መውጣትና መኖሬን ማሳወቅ የእሷንም የጤነኛ ልጆቿንም ክብር እንደሚነካ አሰበች፡፡ እናም እኔ ከቤት ውስጥ ከቤትም ጓዳ! እንድቀመጥ ተፈረደብኝ፡፡ ስለመኖሬ እንኳ የሚያውቁት ጓዳ ድረስ ዘው ማለት የሚችሉ የቅርብ ሰዎች ብቻ ናቸው። ለዛውም ተቀምጬ በእህቶቼና አስታዋሽ በሌለው በራሴ ጸጉር የተለማመድኩትን የጸጉር ስራ አገልግሎት ሲፈልጉ። ሁኔታው ቢያናድደኝም ያቺን ደቂቃም ሰው ማግኘት ብርቄ ስለሆነ እታዘዛለሁ፡፡ ያውም በሚስጢር ገብተው አለመኖሬን እያወጁ እንደሚሰሩ እያወኩ፡፡
ወላጆቼ የውጭ ሰው እኔ መስራቴንም ሆነ መኖሬን አውቆ እንዲመጣ አይፈለጉም፡፡ ስለዚህ እኔ ከእነ አለሁበት ሁኔታ መጣወቅ የወዳጆቻቸውን ክብር እንደሚነካ ስለተረዱ ለመጠበቅ ሚስጥሩን ያከብሩታል፡፡ አዎ የእኔ ነገር ውሾን ያነሻ ውሾ ነበር፡፡
በዚህ ሁኔታ ተቀምጨ እያለ ነው የቤታችን የመጨረሻዋ ልጅ የአስራ ሁለተኛ ክፍልን ማትሪክ የወሰደችው፡፡ ምክንያቱን ባላውቀውም የእሷ ፈተና ባለውለታዬ እንደሆነ ይሰማኛል፡፡ እግሬ እንጅ ጭንቅላቴ ስላልታመመ ስለመጨረሻዬ ዘውትር እጨነቅ ነበር፡፡ ለመሞት ያደረኳቸው ጥረቶች ታውቆም ሆነ ሳይታወቅ ተሰናክለውብኛል፡፡ በዚህም መኖር እየጠላሁ የኖርኩባቸው አመታት ቀላል አልነበሩም፡፡ ሞት እንኳን እንዲህ በቀላል ላገኘው የማልችለው ብርቅ ነገር ሆነብኝ፡፡ አንዳንዴ በራሴ አቅም ማጣት ሳይሳካ ይቀራል፡፡ በተለይ አንድ ቀን ራሴን ለማነቅ ያደረጉት ሙከራ ከንቱ የቀረው አቅም በማጣቴ እንጅ ሰው ደርሶብኝ አልነበረም፡፡ አንገቴን በቢለዋ አርጀ ለመግደል የሞከርኩበት ጊዜም ነበር፡፡ ብቻ ለጉዳት የሚጥል ደም ከመፍሰሱ በፊት እናቴ ደርሳ አዳነችኝ። ለምንም እንደማልጠቅም፣ እንደውም ለእነሱ ውርደት እንደተፈጠርኩ እያሰቡ ስለምን ተከታትለው እንደሚያድኑኝ ሳስብ ይገርመኛል፡፡ እንዲህ እየሆንኩ እያዩ እንኳን ተጎልታ ከምትውልበት ሰይጣን ቀረባት እንጅ አንድም ቀን ህይወት አሳስቧት ብለው አያውቁም፡፡ በቃ የማስብም ከንቱ መቀመጤ የሚቆጨኝም አይመስላቸውም፡፡ ያን ቀን ግን በአመጽ ራሴን ይፋ አወጣሁ፡፡
“ወይ ግደሉኝ! ካልያም ልኑርበት አትከልክሉኝ! እኔ ለእናንተ ስል መስዋዕት መሆን አለብኝ?” በመጀመሪያ ከእናቴ ላይ ነበር እንደብራቅ የጮህኩት፡፡
“ኧረ ኧረ ኧረበጉዴ ወጣሁ እናንተ! ኧረገኝ! ኧረ ምን ውሃው በላኝ ሰዎች! ምን ሆነሻል፡፡ እንደልማዷ አመማት ብላ እዛው ጸበል ልታረሰርሰኝ እንደሆነ ሲገባኝ “አዎ እኔ የእናንተ እብድ! ቆይ! እግሬ እንጅ ጭንቅላቴ የታመመ መሰላችሁ እንዴ? እንዳትነኪኝ ነግሬሻለሁ እኔ ምንም አልነካኝም ልታሳብዱኝ የምትጥሩት እናንተ ናችሁ፡፡ እጄን እያወናጨፍኩ ተከላከልኩ፡፡
“ውሃው በልቶኝ ዛሬ ኧረ እባክችሁ ድረሱልኝ!” ጠበሉን እንደያዘች እጀን ለመያዝ ሞከረች፡፡
“ክፉ ነሽ እሽ ክፉ ነሽ ደግሞ እናቴ አይደለሽም አሁን እንዳላመመኝ ጠፍቶሽ ነው በህመም እያመካኘሽ እዚሁ ለማፈን ነው እንጅ! አዎ ልጆችሽ እንዳይዋረዱ እኔ ጓዳ ታፍኜ እሞታለሁ ልቀቂኝ ልቀቂኝ!” ጎረቤት እስኪሰማ ጮህኩ፡፡
ኧረ በጉዴ ወጣሁ ዛሬ እናንተ ሆዬ! እኛ ደግሞ ምን አደረግንሽ ልጀ!? እሽ ወተሸስ ምን ትሆኝ? አሁን የሰው መፈራረጃ ልታደርጊን እንጅ በምንሽ ልትሄጅው ነዋ? እንደ አህያ ትንከባለይ ነገር!” ሁኔታየ አስደንግጧት ይሁን አሳዝኛት ባላውቅም እያለቀሰች ነበር የመለሰችልኝ፡፡ እሷን እምባ ሳይ እንደገና ደነገጥኩ፡፡ ቢሆንም ወደኋላ ማፈግፈግ አልፈለኩም፡፡
“በቃ ማንም ይወቀኝ እወጣለሁ! ጸጉርም ከአሁን በኋላ ያለ ሳንቲም አልሰራም፡፡ ይሄው ጸጉር ቤት የሚሰሩት እንኳን እንደሷ አይሆንም እየተባለ እየሰማሁ! ሁኔታውን ሳስበው ነው መሰለኝ እንደገና ቁጣየን አናረው፡፡
“እንደው ምናለ ብትተይኝ ልጄ፡፡ አሁን የሰው መፈራረጃ ልታደርጊን እንጅ እውነት አንች ሰርተሸ ሕይወትሽን ልትለውጭ ነው? በምንሽ ተንቀሳቅሰሽ? እንደው ይልቅ የሰጠሸን ብትቀበይውና እንዳመጣብኝ እስካለሁ ብጦርሽ ምነው? ‘አርሶ ያልጠገቡ ራስ ሰርቶ’ አሉ የእኔው ሃጢያት ነው እንጅ! ቢያድለኝማ መች እንዲህ… አቋርጣ ለቅሶዋን ጀመረች፡፡ ብታሳዝነንም መለሳለስ አልፈለኩም፡፡ በተለይ ‘..ብጦርሽ…’ የምትለዋ ቃል ስለት ሆና ከላይ እስከታች ስትቀደኝ ራሴን መቆጣጠር ተሳነኝ፡፡ እየተጎተትኩ ወጥቼ የሰፈር ልጆች በመሰብሰብ ሹርባ ለመስራት ታገልኩ፡፡ ዓላማዬ እንደምሰራ ማሳየት ነው፡፡ አንዳንዶቹ ግን ምን ጉድ ናት ብለው ፈሩኝ መሰል እምቢ አሉ፡፡
ከፍ ከፍ ያሉትና ምን አልባትም ስለ እኔ በሹክሹክታ የሰሙት ግን እየቀረቡ መሰራት ጀመሩ፡፡ ነገሩ ግን ከየዋሉበት የመጡትን ቤተሰቦቼን ሁሉ አስቆጣ፡፡ ተማርን ያሉት እህትና ወንድሞቼ ሳይቀሩ ተናደደቡብኝ፡፡ ለማስቆም ግን መግደል የሚጠይቅ ነበርና ሳይሞክሩት ቀሩ፡፡ እኔም በየቀኑ እንደ እባብ እየተሳብኩ እየወጣሁ ወንበሬ ላይ በመቀመጥ የሃገሩን ቁንዳላ ሁሉ ስቆነድል መዋልን ተያዝኩት፡፡
ስጀምር ፀጉር ቤቶች ያስከፍላሉ ከተባለው ዝቅ ብዬ ነበር፡፡ በኋላ ግን እንደውም የእኔ ጨመረ፡፡ እውነትም ለዚህ የተሰራሁ ሳልሆን አልቀረሁም፡፡ የትኛውም ፀጉር ቤት የእኔን ያህል ማሳመር ባለመቻሉ ሴቱ ሁሉ እኔን መርጦ መሰብሰብ ጀመረ፡፡
ይህን ዝና ሰምታ ክረምቱን በሚያምር ሹርባ ለማሳለፍ የመጣች አንዲት አዲስ ደንበኛ ነበረች አዲስ ህይወት የከፈተችልኝ፡፡ ገና ከመጀመሯ በፊት ነው የተለያዩ ነገሮችን ስትጠይቀኝ የነበረችው፡፡ የልብስ ነጋዴ ናት፡፡ ለሱቋ የሚሆን የተለያ ልብስ ለማምጣት ብዙ ከተሞች እንደምትሄድ ትናገራለች፡፡ ይህን የፀጉር ሥራ ሞያዬን በተመቻቸ ሁኔታ መስራትና እኔም ዊልቼር ገዝቼ እንደፈለኩ መንቀሳቀስ እንዳለብኝ የመከረችኝም ፍጹም ተቆርቋሪ በሆነ ስሜት ነበር፡፡ እንዳለችው ከተመቻቸ ቦታ ሰፋ ባለ መልኩ መስራትን ባልጠላም፣ ቀድሞ ልቤን ያንጠለጠለው ግን ዊልቸሩ ነበር፡፡
“በፈጠረዎ ከቻሉስ የሚረዱኝ ይሄኛውን ነው፡፡ የተለያየ ቦታ ማየት እንደናፈቀኝ መሞት አ…አ..” ድሮም አስተዛዝኘ ለመንግር አቅጀ ነበር፡፡ በየምክንያቴ መቅደም የለመደው እምባዬ ግን አንደበቴን ጭምር ተቆጣጠረብኝ፡፡ እሷን ግን ከማሳዘን ይልቅ አበሳጫት መሰለኝ፡፡
“በይ በይ በይ! አድናቆቴን እንዳታጠፊው! የምን ማልቀስ ነው? በማልቀስ የሚፈታ ችግር የለም፡፡ ጭንቅላቱን እስካላሰራ ድረስ ሁሉም አካል ጉዳተኛ ነው፡፡ ጭንቅላትሽን ከተጠቀምሽበትና አደርገዋለሁ ብለሽ እስከተነሳሽ ደግሞ አንችም ምንም የሚጎድልሽ ነገር የለም፡፡ ታይኛለሽ አይደል እኔን? ለሰው ስታይ ሙሉ ጤነኛ ነኝ፡፡ ግን እስካሁን ድረስ ወገን ዘመድ ያሰለቸሁ ትልቅ ጡረተኛ ነበርኩ፡፡ … ስትል የቁጣ ናዳ ካወረደችብኝ በኋላ፤ ውጤት አልመጣልኝም ብላ አሮጊት እናቷ ጋር በመቀመጥ እንዴት ድህነትን ስታራባ እንደኖረች፤ አሁን ብድር ወስዳ ንግድ በመጀመሯ እናቷንም እሷንም የለወጠችበትን ሁኔታ በማንሳት፤ ጭንቅላቱን አሰርቶ በህይወቱ ለውጥ እስካላመጣ ድረስ ሁሉም አካል ጉዳተኛ እንደሆነ እየተበሳጨች ነገረችኝ፡፡ ብዙዎቹን ማነሳሻዎቿንም በጣም ወደድኩላት፡፡
ከዚህች ግቢ ታጥሬ በተራ ነገር እንዳልቀርና ትልቅ ራዕይ መቋጠርና ለዚያ መጣር እንዳለብኝ ደጋግማ መከረችኝ። ማውራት ብቻ ሳይሆን ቁም ነገረኛ ሴትም ናት። ከምኑ ገብታ የት አግኝታ እንዳመጣቻቸው እንጃ ዊልቼሩን አንድ ድርጅት በራሱ መኪና ሰጥቶኛና አበረታቶኝ ሄደ፡፡ አዎ ያች ሴት ህይወቴን በጣም ረጅም እርምጃ እንዲራመድ ትልቁን ምርኩዝ አቀብላኛለች፡፡
እውነትም ዊልቸሬ ወደ ፈለኩት ቦታ ሁሉ መራኝ፡፡ መጀመሪያ የሄድኩት ወደ ቀበሌ ነበር፡፡ መስሪያ ቦታ ስጡኝ አልኳቸው፡፡ ወላጆቼ የእኔን ገንዘብ ማጥፋት እንደሃጢያት ይቆጥሩት ስለነበር መጠነኛ ገንዘብ አጠራቅሜ ነበር። እናም ብድር መግባት አልፈለኩም፡፡ ከዚህ ይልቅ ቦታ በመፍቀድ ልታበረታቱኝ ይገባል ስል ወተወትኳቸው። እነሱ ሲሰጡኝም በቂ የሚባል ዕቃ ያሟላች ጸጉር ቤት ከፈትኩ። ገቢው ግን ከድሮው የሚሻል አልሆነም፡፡ ከተማችን ትንሽ በመሆኗ ሰው ወደ ሹሩባው ያደላል፡፡ እኔ ደግሞ ከፍ ያለ ገቢና ለውጥ ማየት እፈልጋለሁ፡ ስለዚህ የተወሰነ ጊዜ ከሰራሁ በኋላ ያገኋትን ቦታ ለባለቤቶቹ አስረክቤ እቃዎቼን ጭኜ ባህር ዳር ገባሁ፡፡
ለካ ጀመሪያ ቤትም ሱቅም መከራየት ነበረብኝ፡፡ ደግነቱ ብቻዋን ወድቃ ትሞታለች ብላ የፈራችው እናቴ ውጤቷ ተበላሽቶባት ከቤት የዋለችውን ታናሽ እህቴን አያይዛ ልካኝ ነበር። አሁን በእኔ ማፈር ቀርቷል። እንደውም የቀበሌውም የድርጅቱም ሰዎች ያሳዩኝን ክብር ማየት በራሳቸው እንዲያፍሩ ያደረጋቸው ይመስለኛል። እውነትም እያገዘችኝ ተሯሩጠን ቤት ተከራየን፡፡ ስራችንም በአዲስ መንፈስ አጧጧፍነው፡፡ የገባነው ሰኔ አጋማሽ ነበር ባህር ዳር በእኔ አዲስ ዲዛይን ሹርባ ተሞላች፡፡ ፀጉር ቤታችን የተለያየ መዋቢያዎችንና ዊጎችን ማቅረብ ጀመረች፡፡ ድሮም ሁለት ሰዎችን ቀጥረን ነበር የጀመርነው። እረፍት ማጣታችን ግን ሌላ ሁለት ሰራተኞች አስፈለገን፡፡ በዚህ ላይ የእህቴ ለስራው ፍላጎት ማጣት ሌላ አማራጭ እንድፈልግ አስገደደኝ፡፡ እምቡሽ እምቡሽ እየተባለች ስላደገች. የሰውን ጸጉር ማገላበጥን እንደ ትልቅ ውርደት ቆጠረችው፡፡ እኔ ደግሞ በችግሬ የተከተለችኝን እህቴን እንዲሁ ልሸኛት አልፈለኩም፡፡ እናም ሌላ ሱቅ ተከራይቼ የመዋቢያ እቃዎች ቤት ከፈትኩ፡፡ የማሰራት ግን እንደሁሉም በደመወዝ ነበር፡፡ አላማዬ ማደግ በመሆኑ ያለምክንያት የሚባክን ነገር የለኝም፡፡ በዚህ ጉዳይ ድሮም ጠንቃቃ ብሆንም የክልሉ ነጋዴ ሴቶች ማህበር የሚሰጠን ሞያዊ ድጋፍ ይበልጥ አጎብዞኛል፡፡
ከዚህ መሃል እንዳለሁ ይህን ችሎታሽን ለሰው ማካፈል ይገባሻል የሚሉ አስተያየቶች ይመጡልኝ ጀመር፡፡ ይህም አንድ ሃሳብ ፈጠረልኝ፡፡ የጸጉር ስራ ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት መክፈት፡፡ ቦታና ብድር ለማግኜት ወደ ቀበሌ አመራሁ፡፡ ጥሩ አጋጣሚ ላይ ነበር፡፡ የተለያዩ ወጣቶችን እያደራጁ ቦታና ብድር የሚሰጡበት ወቅት፤ እኔንም ብዙ ሳያንገላቱ ተባበሩኝ፡፡ ሁሉም ስኬታማ ነበር። አመታትን ተቀምጬ አሳልፌአለሁና ለማካካስ ያለ እንቅልፍ ታተርኩ፡፡ በተለይ ትምህርት ቤቱ ካሰብኩት በላይ ትርፋማ ሆነ፡፡ ፀጉር ቤቱና መዋቢያ ሱቁም ቢሆን ቀላል የማይባል ትርፍን ያስገቡልኝ ጀመር፡፡ በርካታ ሰራተኞችንም ቀጠርኩ፡፡ አግዙኝ አግዛችኋለሁ ብሎየለም? ጥረቴን ያየው አምላክ ባለሶስት መኝታ ቤት ኮንደሚንየም እጣ ቀድሞ መዘዘልኝ፡፡ በቃ ሃብትና ክብር አቅጣጫቸውን ወደኔ አዞሩ፡፡  
እንዲህ ገቢዬን ከየቦታው ማካበት በጀመርኩበት ወቅት ነበር ወንድሜ እንጎዳይን ለምርመራ ወደ አዲስ አበባ ይዞ የሄደው፡፡ ወንድሜ ደብረታቦር የሚኖርና በማስተማር ስራ የሚተዳደር ነው፡፡ ወደ አዲስ አበባ ሲሄድም አንዳንድ ነገሮችን ላግዘው ጥርት አድርጌ ነበር፡፡ እሱ ግን ከእኔ ምንም መውሰድ አልፈለገም፡፡ እኔም ብሆን ያላቸውን ስሜት ስለማውቅና መረዳት እንጅ መርዳት የማይገባኝ ሰው እንደሆንኩ ማሰባቸው ስለሚያስጠላኝ ትልቅ ጉዳይ ካልተፈጠረ በቀር አልቀላቀላቸውም፡፡ ያኔም ካልፈለገ ይተወው ስል በግዴለሽነት ሸኘሁት፡፡
ሲመለስ ግን በነበረው አልተመለሰም፡፡ ምክንያቱም እንጉዳይ ውጭ ሄዳ ካልተከመች በቅርቡ ልትሞት እንደምትችል ተነግሮታል፡፡ ከህጻንነቷ ጀምሮ ስቃይ ያየባት ለተንኮሏ ደግሞ እውነትም እንጉዳይ የሆነች የምታሳሳ ህጻን፡፡ እንኳን ወላጅ ማንም ቢሆን እንዲህ አይነቱን ጉድ የሚችል አቅም አይኖረውም፡፡ ወንድሜም ቢሆን ይህን ተሸክሞ ስለክብር ለማሰብ ጊዜ አልነበረውም። የሚሰጠው ካገኘ እንኳን ከእኔ ከመንገደኛም ይቀበላል፡፡
አስተማሪ ደመወዙ ከእለት ሆድ አልፎ ለእንዲህ አይነት ትልቅ ጉዳይ የሚጠበቅ አልነበረም፡፡ ሚስቱ የቤት እመቤት ናት፡፡ በደህና ጊዜ የገዛው ከደብረታቦር ከታማ ወጣ ብሎ የሚገኘው መኖሪያ ቤቱም አወጣ ተብሎ ሃምሳሽ ሽህ ብር ብቻ ሆነ፡፡ ሃምሻ ሺ ይዞ አሜሪካ ልብ ለማሳከም መሞከር፤ የማይታሰብ ነበር፡፡ አሉኝ ካላቸው ሁሉ ተሯሩጦ መቶ ሽህ እንኳን መሙላት አልቻለም። ሁሉንም ካጠናሁ በኋላ ነው ከአካውንቴ ስምንት መቶ ሽህ ብር አውጥቼ የሸኘሁት፡፡ ለነገሩ እስከሚመጣ የላኩትም ከዛው የሚዳረስ ነው፡፡ የልጅቷ መዳን ትልቁ ዓላማዬ ቢሆንም ዋናው ሃሳቤ ግን እኔ የታፈረብኝ እንዴት መከታ ልሆናቸው እንደቻልኩ ማሳየት ነበር፡፡ ሁኔታው ንግዴን የሚያነጋ፣ ትልዕ እዳ ውስጥ የሚከተኝ ቢሆንም ማነነቴን እስካሳየልኝ ድረስ ግድ አልነበረኝም፡፡ ከሁሉም በላይ ትልቁ ድል እንዳረባ ሰው በጣሉኝ ቤተሰቦቼ መሃል ይህን ያህል ክብር ማግኘት ነው፡፡

Read 3654 times