Saturday, 25 April 2015 10:43

የተገፉትን ማን ይጠይቅልን?

Written by  ባዩልኝ አያሌው
Rate this item
(2 votes)

     እኛ ላይ የሆነውንና እየሆነ ያለውን ሁሉ ሳስብ በታላቁ መጽሐፍ የሠፈረን አንድ አስገራሚ ታሪክ አስታወስኩ፡፡ ይኸውም ሙሴና እግዚአብሔር ስለእስራኤል ልጆች ያደረጉት ምልልስ ነው። በሙሴ እየተመሩ ከግብጽ የዘመናት ባርነት ነጻ የወጡት እስራኤላውያን በብዙ ምህረት ታድጎ ያወጣቸውን አምላካቸውን አብዝተው በደሉ፡፡ በዚህ የተቆጣው እግዚአብሔርም መሪያቸውን ሙሴን “ይህንን ህዝብ ላጠፋው ነው” አለው። ሙሴ ግን በታላቅ ቁጣ የተነሳውን አምላኩን እንዲህ አለው፤ “የህዝቡን ሐጢያት ይቅር በል፤ ያለዚያ ግን ከጻፍኸው መጽሐፍ እባክህ ደምስሰኝ” ዘይገርም! ስለሚመራው ህዝብ ራሱን አሳልፎ የሚሰጥ ታላቅ መሪ፡፡
ይህች ሀገርና ህዝቦቿ በረጅም ዘመናት ታሪካቸው እጅጉን ለስሜት የሚከብዱ ታላላቅ መከራዎችን አይተዋል፤ አሳልፈዋልም፡፡… ለነጻነታቸው እጅጉን ቀናኢ የነበሩት አባቶቻችን ድንበራችንን ደፍረውና አቋርጠው የእትብታችን ማረፊያ፣ የልጅነታችን ዓለም፣ የአዛውንትነታችን መተከዣ… የሆነውን ርስታችንን ሊነጥቁን፣ በባርነትም ሊገዙን ብረት ስለውና ቃታ ስበው ከመጡ ጠላቶቻችን ጋር ባደረጉት እልህ አስጨራሽ ትንቅንቅ እጅግ የበዛ መስዋዕትነትን ከፍለዋል፡፡
በአይበገሬነታችን ህልማቸው የጨነገፈባቸው ወራሪዎቻችንም እጃቸው የገቡትን አቅመ ደካማ ሽማግሌ፣ ሴት፣ ህጻን… ሳይሉ ቤት ውስጥ እያጎሩ በእሳት ፈጅተዋል፤ በጥይት ደብድበዋል። ማረክን ያሉትን ጥቂት ሠራዊትም አንገቱን ቆርጠው ሸልለዋል፡፡ በዚህም ሰልጥነናል ያሉት ነጮች፣ “ያልሰለጠነ ህዝብ ነው” ባሉት ህዝብ ላይ በፈጸሙት አረመኔያዊ ድርጊት ራሳቸው ከሰውም በታች እንስሶች መሆናቸውን ለዓለም አሳይተዋል፡፡
ተበዳዮቹ አባቶቻችን ግን በወቅቱ ይህንን አላደረጉም፡፡ የዚህች ሀገር መሪዎችና ህዝቦቿ ባህር ተሻግረው ለመጡትና በብዙ መስዋዕትነት ለማረኳቸው ወራሪዎቻቸው ያደረጉት በዚያን ዘመን እንኳንስ “አልሰለጠነም” ከሚሉት ህዝብ ቀርቶ በወቅቱ “ገናና ነን፤ ብዙ እናውቃለን” ከሚሉት ህዝቦች እንኳን የማይጠበቅ ነበር። የጠላቶቻቸውን ቁስል ጠርገውና አክመው፣ ስንቅ ቋጥረው… ሸኙ፡፡ በዚህም የሚዋጉት አስተሳሰብንና ርዕዮተ ዓለምን እንጂ ግለሰቦችን እንዳልሆነ ለዓለም አሳዩ፡፡ ሌላ ሌላውን ትተን የአድዋን ድል ብናነሳ እንኳን በጦር ሜዳ ከተገኘው ድል ባልተናነሰ በዲፕሎማሲው የተቀዳጀነው ድል ነው ወራሪዎቻችንን አንገት ያስደፋው፡፡ ኢትዮጵያዊ የሰው ልጅን ሰውነት የሚረዳና የሚያከብር ታላቅ ህዝብ!
በዚህም ጀግኖችና ቆራጦች፣ በነጻነታችን ላይ ለአፍታ እንኳን የማንደራደር ህዝቦች መሆናችንን ለዓለም አሳይተናል፡፡ ይህ ማንም ሊክደው የማይችለው ሀቅ ነው፡፡ ጠላቶቻችንም ሳይቀሩ እያነቃቸውም ቢሆን የሚመሰክሩት ሀቅ! ይህ እውነታችንም በየትኛውም ሥፍራ፣ ዘመንና ህዝብ ፊት በፍጹም የራስ መተማመን እንድንቆምና አንገታችንን ቀና አድርገን እንድንናገር አስችሎናል። “እኛ ማንም ሳንሆን ኢትዮጵያውያን ነን!” እስክንል ድረስ፡፡
ይህንን ማንነታችንን ለመንጠቅና እኛን አንገት ለማስደፋት ሠርክ የሚታትረው ድህነታችን ግን አባቶቻችን በከፈሉት ደማቅ መስዋዕትነት የቆመውን ክብራችንን ተገዳድሮ በዓለም ፊት የረሀብና ችግር ምሳሌ ተብለን እስክንጠቀስ አደረሰን፡፡ እናም ስለማንነታችንና ታሪካችን ልንናገር ስንቆም ብዙዎች ልናሸንፈው ያልቻልነውን ችግራችንን ቀድመው በመናገር ሊያሸማቅቁን ይተጋሉ፡፡… ሆኖም ግን ማንም ክብራችንን ሊደፍርም ሆነ ሊያዋርደን አይሞክርም፤ የሞከረም ሲቀጣ ኖሮአል፡፡
ቀደምት መሪዎቻችንም ቢሆኑ ሀገራቸውንና ህዛባቸውን ከውጭ ጥቃት በመጠበቅ ረገድ የነበራቸው ቁርጠኝነት የሚታማ አይደለም፡፡ ብዙዎቹ ከህዝባቸውና ከሠራዊታቸው ቀድመው ለመውደቅ ያልሳሱ ነበሩ፡፡ ስለሆነም ከፊሉ ስለሀገሩና ህዝቡ ነጻነት አንገቱን አስቆርጦአል፡፡ ከፊሉም ቃታ ስቦ፣ ጥይት ጠጥቶ… ወድቆአል፡፡ ስለ ኢትዮጵያና ስለ ህዝቦቿ!! በዚህም ኢትዮጵያዊ ሁሉ የትም፣ መቼም ተከብሮና ታፍሮ ኖሮአል፡፡ ዛሬስ?...
ይህ ህዝብ ድህነታችንና ሌሎች ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ሰበቦች በፈጠሩት ግፊት ከፊሉ ወዙን አፍሶ በመሥራት ጥሪት ሊቋጥር፣ ከፊሉም ከፍቶትና የተሻለ ጊዜን መምጣት ተስፋ አድርጎ ከእናት ምድሩና ከወገኑ ርቆ በባዕድ ሀገር ተጠልሎአል፡፡ ድሮ ህንዶች የማይኖሩበት የዓለማችን ክፍል የለም ይባል ነበር፡፡ አሁን ደግሞ ኢትዮጵያውያን የሌሉበት የዓለም ክፍል ያለ አይመስለኝም፡፡ የዚህች ምስኪን ሀገር ምስኪን ህዝብ እንጀራ ፍለጋ ከጽንፍ ጽንፍ በዓለም ተበትኖአል፡፡ ለምን? እንዴት?... ተጠያቂው ማንም ይሁን ጥያቄው መልስ ይሻል፡፡
መቼም (ሰበቡ ምንም ይሁን ምን) ማንም ያለምክንያት ከምድሩና ከወገኑ ተለይቶና ርቆ በባዕድ ሀገር አይኖርም፡፡ ይህንን በቅጡ አጥንቶ ማወቅ፣ በርግጥም ችግሩን ለመፍታት የመጀመሪያው ቁልፍ ነው፡፡… ያም ሆኖ ማንም ኢትዮጵያዊ (በምንም ምክንያት) የትም ይኑር የት ኢትዮጵያዊ ነው፡፡ ሌላውን ትተን ወንጀል ሠርቶና ሸሽቶ ቢሆን እንኳን የራቀው በወንጀሉ ይጠየቃል እንጂ ኢትዮጵያዊነቱ አይፋቅም፡፡ ምክንያቱም ዜግነቱና እሱን ተከትለው የሚያገኛቸው ከለላዎች እኛ ስለወደድን የምንሰጠውና ስለጠላነው የምንነጥቀው ቸሮታ አይደለምና፡፡
ከዚህም ሌላ ይህ ወገን በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ ተከፍቶም ይሁን ወዶ ትቷት ለሄደው ሀገር የሚያበረክተው አያሌ አስተዋጽኦ አለ። ሌላ ሌላውን ትተን ወዙን አፍሶና ጉልበቱን አድክሞ ከሚያገኘው ገንዘብ ላይ በእናት ምድሩ ለሚደረጉ ልዩ ልዩ ጉዳዮች የበኩሉን ያዋጣል፡፡ ለቤተሰቦቹና ለወዳጆቹ በሚልከው ገንዘብም መንግስትና ሀገሪቱ በልዩ ልዩ መንገዶች ይጠቀማሉ፡፡ ይህን ሁሉ ባያደርግ እንኳን ቅሉ ዜጋ ነውና የእናት ሀገሩ መንግስት ባለበት ሀገር ሊጠብቀውና ሊያስጠብቀው ግድ ነው፡፡ ይህንን ማድረግ የአንድ መንግስት ሥራው ነውና፡፡
የአንድ ሀገር መንግስት በሌላ ሀገር ቆንስላ ጽ/ቤትም ሆነ ኤምባሲ ከሚያቆምበትና አምባሳደር ከሚሾምበት ዋና ምክንያቶች አንዱ በዚያ ሀገር የሚኖሩ ዜጎቹን መብትና ደህንነት ለማስከበርና ጥቃቶችም እንዳይደርሱባቸው ለመከላከል ነው፡፡ እንደሱ ይመስለናል፡፡ ስለሚመስለንም እንጠይቃለን። መጠየቅስ መብት አይደል?!
በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ኢትዮጵያውያን ወዛቸውን አፍሰውና ጉልበታቸውን አድክመው በሚኖሩባቸው አንዳንድ ሀገሮች ያህላል የማይሉት መገፋትና እንግልት እየደረሰባቸው ነው፡፡ አልፎ ተርፎም በታላቅ ግፍ ህይወታቸውን እየተነጠቁ ነው። ባለፉት ጥቂት ዓመታት የሆነውን ብቻ እናውቃለን። በአረብ ሀገራት እጅግ ዝቅተኛውን ሥራ ሠርተው ይኖሩ በነበሩ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ላይ የደረሰውን እናስታውስ፡፡ አሁን ደግሞ በፍጹም ይሆናል ይደረጋል ተብሎ በማይታሰብባት አፍሪካዊ ሀገር በደቡብ አፍሪካ ወንድም እህቶቻችን በእሳት ተቃጥለው ተገደሉ። የቀሩትም ለዓመታት ለፍተው ያተረፉትን ንብረት ተዘረፉ፤ ተንገላቱም፡፡
በዚህ አንብተን እንባችን ከዐይናችን ላይ ሳይደርቅ፣ሠላሳ የሚደርሱ ኢትዮጵያውያን ወንድሞቻችን ተስፋን ሰንቀው እንጀራ ፍለጋ ሲደክሙ፣ የሰው ልጅ ሊባሉ በማይችሉ አረመኔዎች እጅ እጅግ አሰቃቂና ኢ-ሰብአዊ በሆነ መንገድ አንገታቸውን ተቀልተው ተገደሉ፡፡ የሆነውና እየሆነው ያለው ሁሉ የምር ልብን ይሰብራል፡፡
ይህን አረመኔያዊ ድርጊት እየፈጸሙብን ያሉት ህዝቦች (አረቦቹም ሆኑ አፍሪካውያኑ) ከኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ጋር የረጅም ዘመናት የክፉ ጊዜ ወዳጅነት የነበራቸው፣ ይህቺም ሀገር ባለውለታቸውና የክፉ ቀናቸው ናት፡፡ ሁለቱም ህዝቦች ከጠላቶቻቸው ሸሽተውና ይህቺን ሀገር ሀገራቸው አድርገው በክንፏ ስር ተጠልለዋል። ከማዕዷ ቆርሰውና ከመደቧ ጎናቸውን አሳርፈው ከእንግልቱ አርፈዋል። ጎልምሰውና ኃይላቸውን አፈርጥመው በጠላቶቻቸው ላይ ድልን እንዲቀዳጁ ይህቺ ሀገርና ህዝቦቿ ስለ እነሱ አብዝተው ደክመዋል። ይህንን ዓለም ያውቀዋል፤ ይመሰክረዋልም፡፡
ያም ሆኖ ይህንን ማየት የተሳናቸው አረመኔዎች የለኮሱት ጥፋት ለታሪክና እውነት በተለይም ለወንድማማችነት ግድና እውቀት በሌለው፣ ይልቁንም በባዶ እብሪትና ድንፋት በተሞላ “ጎረምሳ” እየተመራ የሆነው ሁሉ በእኛ ላይ ሆነብን። ይህ በኢትዮጵያውያን ላይ የደረሰ ግፍ ሁሉ ለእኛ ጥቃት፣ ቁጭትና ማነስ ሲሆን ለእነሱ ግን መቼም ሊፍቁት የማይችሉት ሃፍረት ነው፡፡ ታላቅ ሃፍረት! ስለ ጠላቶቻችን ከዚህ በላይ ምንም ማለት ምንም አይረባንምና ወደ ራሳችን እንመለስ፡፡ ልብ ካልን የሚረባን እሱ ነው፡፡
ማንም ተጠቂ ከደረሰበት ጥቃት በላይ የሚያመው መጠቃቱን የሚያይለትና የሚሞግትለት አካል ሲያጣ ይመስለኛል። ተጠቂው ህዝብ ሲሆን ደግሞ “መንግስቴ ወዴት አለ?” ብሎ ይጠይቃል። የበርካታ ኢትዮጵያውያንን ሀዘን ያከፋውም ስለሆነውና እየሆነ ስላላው ሁሉ ጠያቂ ማጣታችን ነው። እናም እንጠይቃለን፡፡ ማን ይገዳደርልናል?! እስከመቼስ እንዲህ እናንሳለን?!…
መሆን ያለበትና እየሆነ ያለው ፍጹም ከመለየቱ የተነሳ ምን እየሆነ ነው? ወይንስ እኛ ያልገባን ጉዳይ አለ? ብለን አብዝተን እንድንጠይቅ ሆነናል። (መልስ የሚሰጠን ባናገኝም፡፡) ደግሞስ መልስ አለመስጠት መነሻው ምንድን ነው? መልስ ማጣት ወይስ ማን አለብኝነት? ይህንንም እንጠይቃለን፡፡ ማንም ህዝብ በማንም የሚከበረውና የሚታፈረው ህዝቡን የሚመራው መንግስት ባለው ቁርጠኝነትና በሚወስዳቸው እርምጃዎች ነው፡፡ ይህንን ባሳለፍነው ታሪክ አይተናል፡፡ በሌሎች ሀገሮች ላይ በሆነውም ታዝበናል፡፡…
ዳተኝነቱ ለምን ሆነ? “የአፍሪካ አንደበት ሆነናል” እስከማለት ድረስ የምናሞካሸው ዲፕሎማሲያችን የኢትዮጵያና የህዝቦቿ አንደበት ለመሆን እንደምን ሰነፈ?! “የበርካታ ሀገራትን ሰላምና መረጋጋት እያመጣ ነው” እያልን ሠርክ የምናወድሰው ኃይላችንስ እንደምን ለዜጎቹ ደህንነት መከታ መሆን ተሳነው?! ይህንን መጠየቅ በደል አይደለምና እንጠይቃለን፡፡
እናውቃለን፡፡ በባዕድ ሀገራት በሚኖሩ ወገኖቻችን ላይ እየደረሱ ያሉት እንግልቶችና ህይወት ማጣቶች በኢትዮጵያውያን ላይ ብቻ የደረሱ አይደሉም፡፡ በአረብ ሀገራት በደረሰው ግፍ የፓኪስታን፣ ፊሊፒንስ፣ ህንድ… ሀገራት ዜጎችም የገፈቱ ቀማሾች ነበሩ፡፡ በደቡብ አፍሪካ ከተሞች በደረሰው ጥቃትም እንዲሁ የዚምባቡዌ፣ ማላዊ፣ ሱማሌና ናይጄርያ ዜጎች ተጠቅተዋል፡፡ በፅንፈኛው ቡድንም የአውሮፓ ሀገራት ዜጎችን ጨምሮ በርካታ የመካከለኛው ምስራቅና የአፍሪካ ዜጎች አንገታቸውን በስለት ተቀልተው ተገድለዋል፡፡ ሆኖም ግን የእነዚህ ሀገራት መንግስታት ቀድመው በወሰዷቸው ጥንቃቄዎችና ችግሩ ከተከሰተም በኋላ አፋጣኝ እርምጃዎችን በመውሰዳቸው በተወሰነ መልኩም ቢሆን ዜጎቻቸውን ለመታደግ ችለዋል።
መንግስታቱ ቀደም ሲል በኤምባሲዎቻቸው አማካይነት ለዜጎቻቸው የሚያደርጉት ከለላ እንደተጠበቀ ሆኖ ችግሩ ሲከሰትም እጅጉን አፋጣኝና ጠንካራ አቋሞችን ሲወስዱና ለችግር አድራሾቹ ሀገራት መንግስታት አስገዳጅ ምላሾችን ሲሰጡ ተስተውለዋል፡፡
የእኛ የኢትዮጵያውን መንግስትስ ምን ቀዳሚ  ጥንቃቄዎችን ወሰደ? ለክስተቶቹ የሰጣቸው ምላሾችስ ምንድን ናቸው? መከፋታችን ያህላል ያጣው በዚህ ነው፡፡ የምር ያስከፋል!  አንድ መንግስት ካሉበት ዋና ዋና ኃላፊነቶች አንዱ በየትኛውም ሥፍራና ወቅት የዜጎቹን ደህንነት መጠበቅ ነው፡፡ ይሄ እኮ መንግስት ለዜጎቹ የሚያደርገው ቸሮታ ሳይሆን ስራውና ኃላፊነቱ ነው፡፡
የሆነው ግን የተገላቢጦሽ ነው ማለት ይቀላል። እውነት ለመናገር ችግሩ ከተከሰተበትና አለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ከዘገቡበት ቅጽበት ጀምሮ ለጉዳዩ አስቸኳይ ትኩረት በመስጠት መረጃ ሲለዋወጥና ግፊት ሲያደርግ የነበረው ህዝቡ ነው። መንግስትስ? መንግስትማ አንዴ “እያጣራሁ ነው”፣ አንዴ  “ኢትዮጵያውያን መሆናቸው አልተረጋገጠም”… በማለት ዳተኝነት አሳይቶአል፡፡ ችግሩ እኮ ከፍተኛ አደጋ ነው፡፡
መንግስት አውቆም ይሁን ግራ ገብቶት የሚወስዳት የአንድ ደቂቃ መዘናጋት የሺዎችን ህይወት ለማስቀጠፍ በቂ ናት፡፡ ደግሞም በሰዓቱ እንጂ ካለፈ በኋላ የሚሰማ ድምጽ “ብያለሁ” ከማለት ያለፈ ፋይዳ እንደሌለው ለማወቅ ብዙም እውቀትን አይጠይቅም፡፡
ሌላው አሳዛኙ ነገር ደግሞ አሁንም ድረስ በመንግስት በኩል እየተወሰዱ ያሉት እርምጃዎች የምር ችግሩን ለማስቆም የሚያስችሉ አለመሆናቸው ነው፡፡ የችግሩ ሰበዝ እየተሳበ ወዴት እንደሚመጣ ስለሚታወቅ ይመስላል፣ የነገሩን አቅጣጫ ለማስቀየስና ይልቁንም ለፕሮፓጋንዳ መጠቀሚያ ለማድረግ እየተሞከረ ነው፡፡ (የሰሞኑን የመንግስት ሚዲያዎች ውትወታ ልብ ይሏል፡፡) ይህም እጅግ ያስከፋል። በሚሊዮኖች ሀዘን ላይ እንጀራን ለመጋገር እንደመሞከር ነው፡፡
ምን እየተደረገ ነው?... ከደረሰብን ግፍ በላይ ያዘነው ግፋችንን የሚጠይቅልንና የሚገዳደርልን በማጣታችን ነው፡፡ ባዕዳን ካደረሱብን ግፍ በላይ “አስተዳድራችኋለሁ” የሚለን “መንግስት” ዝምታ ነው ያስቆጨን፡፡ ማን ይገዳደርልናል?! እስከመቼስ እንዲህ እናንሳለን?!

Read 1818 times