Monday, 20 April 2015 15:40

ከትንሣኤ እስከ ዳግም ትንሣኤ ያሉት ቀናት

Written by  ተመስገን ዘገየ(አዲስ አበባ)
Rate this item
(6 votes)

እሑድ፦ በዓለ ትንሣኤ ሲሆን ። ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርሰቶስ ሦስት ሌሊት ሦስት መዓልት በከርሠ መቃብር አድሮ መነሳቱን የምናስታውስበትና የመስቀል መርገምነቱ ቀርቶ ትንሣኤነቱ የታወቀበት፤ ሙስና መቃብር የተሻረበት ትንሣኤያችንን በትንሣኤው ያረጋገጥንበት ዕለት ነው።
ሰኞ፦ ፩ኛ ማዕዶት ይባላል።
ማዕዶት ማለት (መሻገሪያ፣ መሻገር) ማለት ነው። ምሳሌው ቀድሞ እስራኤላውያን ባሕረ ኤርትራን ተሻግረው ምድረ ርስት ገብተዋል። ምሳሌውም ፈርዖን የዲያብሎስ፣ ሠራዊቱ የሠራዊተ ዲያብሎስ፣ ግብፅ የሲኦል፣ ባሕረ ኤርትራ የባሕረ ሲኦል፣ እስራኤል የምእመናን፣ ሙሴ የወልደ እግዚአብሔር፣ በትረ ሙሴ የመስቀል ምሳሌ እስራኤላውያን በሙሴ መሪነት ተሻግረው ምድረ ርስት እንደገቡ ነፍሳትም በክርስቶስ መሪነት ባሕረ ሲኦልን ተሻግረው ገነት የመግባታቸው ምሳሌ ነው። በዚህም ማዕዶት ይባላል።
፪ኛ ዕለተ አብርሃም (ዕለቱ ለአብርሃም) ይባላል። አብርሃም ዮርዳኖስን ተሻግሮ ከነዓን ገብቷል። በዚህም አንጻር ምእመናንም ባሕረ ሲኦልን ተሻግረው ገነት የመግባታቸው ምሳሌ ነው። አንድም አብርሃም ዮርዳኖስን ተሻግሮ ቢሄድ መልከጼዴቅ ኅብስተ አኰቴት ጽዋዐ በረከት ይዞ ተቀብሎታል። ነፍሳትም ባሕረ ሲኦልን ተሻግረው ቢሄዱ ኅብስተ በረከት ጽዋዐ አኰቴት ወልድን የማግኘታቸውና ወደ ቀድሞ የበረከት ርስት የመመለሳቸው ምሳሌ ነው። ስለዚህ ትንቢቱ ምሳሌው መድረሱን ለማጠየቅ ዕለቷ ማዕዶት ትባላለች።
ማክሰኞ፦ ቶማስ ይባላል።
ሐዋርያው ቅዱስ ቶማስ የጌታችንን ጐን የዳሰሰበትና እጁ የደረቀችበት እንደገና መልሳ የዳነችበት መታሰቢያ ነው። ለቶማስ ታሪክ መታሰቢያ ይሆን ዘንድ ዕለቱ ቶማስ ይባላል። ምንም እንኳን ታሪኩ የዳግማይ ትንሣኤ ቢሆንም አበው ታሪክ ከታሪክ እንዳይደራረብ ብለው ነው። ዩሐ20፤27-29
ረቡዕ፦ አልዓዛር ይባላል። ዮሐ ፲፩፥ ፵
አልዓዛር ጌታችን በጥንተ ስብከት ያስነሳው ሲሆን ታሪኩ በዮሐንስ ወንጌል በሙሉነት ተመዝግቧል። ከሞት የተነሳው መጋቢት ፲፯ ቀን ነው። በዚሁ ቀን መታሰቢያ እንዳያደርጉለት የግርግር ወራት ሆነ በ፳፪ም ሆሳዕና ሆነ፤ በ፳፫ም ርግመተ በለስ አንጽሖ ቤተ መቅደስ ሆነ በዓሉ ከበዓል ይዋል ብለው አበው የውኃ በዓል ከውኃ ብለው ቃና ዘገሊላን ከጥምቀት ጥግ እንዳዋሉ ትንሣኤው ከትንሣኤ ጋራ እንዲሄድ አደረጉ። አንድም አልዓዛር በትንሣኤ ሥጋ እንደተነሣ እኛም ትንሣኤ ልቡና፣ እንነሣለንና።
ሐሙስ፦ አዳም ይባላል። የአዳም ምሉዕ ተስፋ የተፈጸመለትን ምስጢር የምናስታውስበትና የምንዘክርበት ዕለት ነው። ምክንያቱም ለክርስቶስ ሰው መሆን ዋና ምክንያቱ ጸሎተ አዳም ወሔዋን ስለሆነ ርደተ ሲኦልን በሚጠታቸው፣ ርደተ መቃብርን በሙስና መቃብር፣ ጽልመተ ሲኦልን በብርሃነ መለኮት ለውጦ ሞተ ሥጋ ወነፍስ ተፈርዶባቸው የነበረው ሁሉ አልፎ “ኃጢአት ከበዛችበት ዘንድ ጸጋ እግዚአብሔር ትበዛለች” ብለው ያመሰገኑበት መታሰቢያ ስለሆነ፤ አዳምና ሔዋን ከሲኦል የወጡት ዓርብ ሲሆን እዚህ መከበሩ ለምንድ ነው ከተባለ ዓርብ ለበለጠው ለአምላካቸውና ለአዳኛቸው ለክርስቶስ ስቅለት ስለሆነ በዚሁ ዕለት ይከበራል። ያውስ ይሁን ሰኞ፣ ማክሰኞ፣ ረቡዕ አለመዋሉ ሐሙስ መዋሉ ለምንድ ነው ቢሉ፥ ከእሑድ እስከ ሐሙስ አምስት ቀን ይሆናል። አምስት ከእኩል ሲፈጸም አድንሃለሁ ብሎት ነበርና ያ እንደተፈጸመ ለማጠየቅ ነው።
ዓርብ፦ ቤተ ክርስቲያን ትባላለች። ጌታችን ከልደቱ እስከ ሞቱ ያደረገው የማዳን ጉዞ በሙሉ የተፈጸመው ዓርብ ነው። “ወይቤ ተፈጸመ ኵሉ” እንዲል። ዓርብ የቤተ ክርስቲያን ሁለመናዊ ምስጢር የተፈጸመበት ዕለት ስለሆነ ቤተ ክርስቲያን ትባላለች። ማለትም ዓርብ ለቤተ ክርስቲያን መሠረት የሆኑ ዋና ዋና ምስጢራት ተሟልተዋል። ለምሣሌ የመስቀል አዳኝነቱ ከእርግማንነቱ ተለይቶ ታውቋል፤ የሕንጻዋ መሠረት ቀራኒዮ ተተክሎላታል፤ ሥጋ መለኮት የምትፈትተው በቀራኒዮ ተቆርሶላታል፤ ልጆቿን ከማኅጸነ ዮርዳኖስ ከአብራከ መንፈስ ቅዱስ የምትወልድበት ማየ ገቦ ፈስሶላታል። ስብከት፣ ትምህርት፣ ተአምራት፣ ትንሣኤ ተደርጎላታል። ይህንን ሁሉ ምሥጢር ያገኘችው በዕለተ ዓርብ ስለሆነ ቤተ ክርስቲያን ተባለች። የዓርብ ትርጓሜው የሥራ መክተቻ፣ ምዕራብ፣ መግቢያ ማለት ነውና። ኤፍ2፤19፤ራዕ1፤6-8
ቅዳሜ፦ አንስት አንከራ ትባላለች። በዕለተ ትንሣኤ ሌሊቱን ሲመላለሱ ያደሩ ሴቶች የድካማቸውና ጌታን የመሻታቸው ዋጋ መታሰቢያቸው ነው።
አንስት አንከራ መባሉ ሌሊት ሲመላለሱ ሁለት መላእክት አይተው ከብሩህነታቸው የተነሳ የተደነቁበትና በመቃብሩ ያለውን መዓዛ ትንሣኤ አሽትተው የተመሰጡበት ዕለት ስለሆነ እንዲሁም ድካማቸው ከንቱ እንዳልሆነ ለማጠየቅ ነው። አንድም ጌታችን አስቀድሞ ለእነርሱ ታይቶ ትንሣኤውን ያረጋገጠበት ስለሆነ እነርሱ ከአምላክነቱ ግርማ የተነሳ ረቡኒ ብለው ያደነቁበት ዕለት መታሰቢያ ስለሆነ። አንድም በጠቅላላው ከሕማማቱ እስከ ትንሣኤው ብዙ የእንባ መሥዋዕት ያቀረቡ እናቶች የሚታሰቡበት ስለሆነ አንስት አንከራ ይባላል።
እሑድ፦ ዳግም ትንሣኤ ይባላል።
ዳግማይነቱ ጌታችን ሳምንቱን ተሰውሮባቸው ሰንብቶ በዝግ ቤት እያሉ ዳግመኛ ስለተገለጸላቸው ዳግም ትንሣኤ ይባላል። ውስጠ ምሥጢሩ ግን ከእሑድ ከቀዳማይ ትንሣኤ ጀምረው ቢቆጥሩ ስምንት ቀን ይሆናል። አንድ ቀን እንደ አንድ ሺሕ ቆጥሮ ስምንት ሺሕ ይሆናል። ዳግማይነቱ ለትንሣኤ ነውና በስምንተኛው ሺሕ ዘመን ዳግም በትንሣኤ ዘጉባኤ እንነሣለን ለማለት ዳግም ትንሣኤ ተባለ።

Read 6153 times