Saturday, 21 January 2012 11:06

በ28ኛው የአፍሪካ ዋንጫ

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

ለሻምፒዮኑ 2ሚ.ዶ ይበረከታል

ጋና ና አይቬሪኮስት በዋንጫ ግምት ይመራሉ

ሱዳን ከሪፍረንደም፣ ሊቢያና ቱኒዚያ ከአብዮቶቻቸው ማግስት ይሳተፋሉ

ዝሆኖቹ በሚሊዮነሮች ብዛት ብልጫ አላቸው

ካፍ የገቢ  አቅሙን ማጠናከሩ ይታያል

የአውሮፓ ክለቦች በወሳኝ ተጫዋቾቻቸው መነጠቅ ተማርረዋል

28ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ኢኳቶርያል ጊኒ ከሊቢያ ጋር በሚያደርጉት የመክፈቻ ጨዋታ ዛሬ ምሽት 3 ሰዓት ላይ ይጀመራል፡፡ ውድድሩ መደበኛ ተሳታፊዎቹንና ሃያላን ብሄራዊ ቡድኖችን ባያሳትፍም የአህጉሪቱንና የመላው ዓለም ስፖርት አፍቃሪዎችን ትኩረት ስቧል፡፡ በአፍሪካ ዋንጫው ለሽልማት ከቀረበው 10 ሚሊዮን ዶላር ተካፋይ የሆኑት 16 ብሄራዊ ቡድኖች በተሳትፎ ብቻ እያንዳንዳቸው 150ሺ ዶላር እንደሚታሰብላቸው ሲታወቅ  አሸናፊው ብሄራዊ ቡድን ከዋንጫው ጋር የ2 ሚሊዮን ዶላር የገንዘብ ሽልማት ይሰጠዋል፡፡

ከተሳታፊ 16  ብሄራዊ ቡድኖች መካከል አምስቱ ብቻ  በታሪካቸው ዋንጫውን ወስደው የሚያውቁ ሲሆን  3 አገራት ደግሞ ከአዘጋጆቹ አንዷ ኢኳቶርያል ጊኒ፤ በማጣርያው ግብፅና ደቡብ አፍሪካ የነበሩበትን ምድብ ያለፈችው ኒጀርና አስደናቂ ብቃት እያሳየች የምትገኘው ቦትስዋና  በመጀመሪያ ጊዜ ጊዜ ይሳተፋሉ፡

ለዋንጫው እነማን ይጠበቃሉ? የ4 ጊዜ ሻምፒዮኗ ጋና እና አንዴ ብቻ ሻምፒዮን የሆነችው አይቬሪኮስት ለዋንጫው ድል ከፍተኛ ግምት በማግኘት ይመራሉ፡፡ ማሊ፤ ሴኔጋል ፤ሞሮኮና ቱኒዚያ በ2ኛ ደረጃ የአሸናፊነቱ ግምት ተሰጥቷቸዋል፡፡ የቱሬ ወንድማማቾችን ከማን ሲቲ፤ ዲዲዬ ድሮግባና ሰሎሞን ካሉን ከቼልሲ፤ ጀርቪንሆን ከአርሰናል በቡድን ስብስቧ ያቀፈችው አይቬሪኮስት  በወቅታዊ ብቃቷ ከፍተኛ ጥንካሬ ይኖራታል፡፡ በአፍሪካ ምድር ለመጀመርያ ጊዜ ተካሂዶ በነበረው 19ኛው የዓለም ዋንጫ እስከሩብ ፍፃሜ በመድረስ አስደናቂ ስኬት ያስመዘገበችው ጋና ደግሞ እነ አሳሞሃ ጊያን፤ሱሊ ሙንታሪ፤ ማይክል ኢሴዬን፤ አንድሬ አየውን የመሳሰሉ ምርጥ ተጨዋቾችን በማሰማራቷ ዋና ተቀናቃኝ ትሆናለች፡፡ ከአፍሪካ ምርጥ ተጨዋቾች ሶስቱን ሰይዱ ኪዬታ ከባርሴሎና፤ ፍሬደሪክ ካኑቴ ከሲቪያ እና መሃመዱ ዲያራን የያዘው የማሊ ብሄራዊ ቡድንም ከባድ ግምት ይሰጠዋል፡ የሴኔጋል ብሄራዊ ቡድንም በምርጥ አጥቂዎቹ የኒውካስትሉ ዴምባ ባ፤ የማርሴዩ ማመዱ ኒያንግ፤ ሙሳ ሶውና ፓፒስ ሲሴ መደራጀቱ ያስጠብቀዋል፡፡ ይሄው ሁኔታም የምእራብ አፍሪካ ብሄራዊ ቡድኖች ለ28ኛው የአፍሪካ ዋንጫው ድምቀት መሆናቸውን እንዳመዘነ ያመለክታል፡፡

የውድድሩ ልዩ ገፅታዎች፡- ምስራቅ አፍሪካን የወከለችው ሱዳን በአፍሪካ ዋንጫ መስራችነት ብትታወቅም ዘንድሮ ለመሳተፍ የበቃችው ከ30 ዓመታት በኋላ ነው፡፡ የአፍሪካ ዋንጫው ማጣርያ ሲጀመር አንድ አገር የነበረችው ሱዳን ማጣርያው ሲያልቅ  ወደ ሁለት አገሮች ተቀይራለች፡፡ በሱዳን ብሄራዊ ቡድን ከሰሜንና ደቡብ የአገሪቱ  ክፍሎች የተገኙ ተጨዋቾች የተሰባሰቡ ሲሆን በውድደሩ የሚያስመዘግቡት ውጤት የተለያዩትን ህዝቦች ህብረት በመፍጠር ከፍተኛ ሚና ሊኖረው እንደሚችል ተጠብቋል፡፡ የሰሜን አፍሪካዎቹ ሊቢያና ቱኒዚያ ደግሞ በአፍሪካ ዋንጫው ማጣርያ ወቅት በየአገራቸው በፈነዱ ትልልቅ የለውጥ አብዮቶች መሃል ተሳትፏቸውን ያረጋገጡ ናቸው፡፡ ሁለቱ ብሔራዊ ቡድኖች በ28ኛው አፍሪካ ዋንጫ የሚሰለፉት ከእነዚህ አብዮቶች ማግስት መሆኑ የሚኖራቸውን ስኬት ታሪካዊ ገፅታ ያላብሰዋል፡፡ በተለይ የሊቢያ ብሄራዊ ቡድን በጋዳፊ ዘመን የነበረውን አረንጓዴ መለያ ሳይቀይር በውድድሩ መሳተፉ እያነጋገረ ነው፡፡

የሚሊዬነሮቹ ዝሆኖች ብልጫ፡- የአይቬሪኮስት ብሄራዊ ቡድን ከፍተኛ ክፍያ የሚያገኙና በሚሊዬነር ደረጃ በሚጠሩ ፕሮፌሽናል ተጨዋቾች በብዛት የያዘ መሆኑ ልዩ ያደርገዋል፡፡ በ28ኛው አፍሪካ ዋንጫ ከሚሰለፉ የ16 ብሄራዊ ቡድኖች ምርጥ ተጨዋቾች መካከል ከዓመታዊ ገቢው በደሞዝ ብቻ 13.5 ሚሊዮን ዶላር የሚታሰብለት የ28 ዓመቱ አይቮሪያዊው የ2011 የአፍሪካ ኮከብ ተጨዋች ያያ ቱሬ አንደኛ ደረጃ ይሰጠዋል፡፡ ያያ ቱሬ በማን ሲቲ ተጨዋችነት ሳምንታዊ ደሞዙ 320ሺ ዶላር ሲሆን በገፅታ መብቱና በሌሎች ጥቅማጥቅሞች በዓመት 2.5 ሚሊዮን ዶላር የሚያገኝ ከመሆኑም በላይ በክለቡ ባለው የኮንትራት ውል ለሻምፒየንስ ሊግ ውድድር በበቁበት የውድድር ዘመን 1.3 ሚሊዮን ዶላር ቦነስ ይከፈለዋል፡፡ በተመሳሳይ በማን ሲቲ ክለብ ያለው ታላቅ ወንድሙ ኮሎ ቱሬ ዓመታዊ ክፍያው 10.3 ሚሊዮን ዶላር ሆኖ በ2ኛ ደረጃ ይቀመጣል፡፡ ከአዲዳስ ጋር ባለው ስፖንሰርሺፕ ተጨማሪ ገቢ ያለው ኮሎ ቱሬ በማን ሲቲ የሚከፈለው ሳምንታዊ ደሞዝ 190ሺ ዶላር ነው፡፡ የማሊው ፍሬደሪክ ካኑቴ ደግሞ በስፔኑ ክለብ ሲቪላ ሲጫወት ዓመታዊ ክፍያው 8.6 ሚሊዮን ዶላር ስለሚያገኝ በ3ኛ ደረጃ ላይ ነው፡፡ የ33 ዓመቱ ካኑቴ በሲቪላ በሳምንታዊ ደሞዙ 180ሺ ዶላር ይከፈለዋል፡፡ ሌላው የአይቬሪኮስት ተጨዋች ዲዲዬር ድሮግባ በቼልሲ በሚያገኘው 8 ሚሊዮን ዶላር የዓመት ክፍያው 4ኛ ነው፡፡ የ33 ዓመቱ ድሮግባ ከናይክ፤ፔፕሲ፤ሳምሰንግና ኦሬንጅ ፍራንስ ከተባሉ ኩባንያዎች ጋር የስፖንሰርሺፕ ውል ያለው ሲሆን ከሃብቱ 5 ሚሊዮን ዶላር አውጥቶ በትውልድ ከተማው አቢጃን የህፃናት ማሳደጊያ ማዕከል መክፈቱ ይወሳለታል፡፡ የጋናው ማይክል ኤሲዬን ደግሞ በቼልሲ ክለብ በየዓመቱ በሚከፈለው 5.5 ሚሊዮን ዶላር በ5ኛ ደረጃ የሚቀመጥ ነው፡፡ በ2005 እኤአ ከፈረንሳዩ ክለብ ኦሎምፒክ ሊዮን ወደ ቼልሲ ሲዛወር 38 ሚሊዮን ዶላር የተከፈለበት ኤስዬን ከኤምቲኤን፤ ከሳምሰንግና ከፔፒሲ ኩባንያዎች በስፖንሰርሺፕ ተጨማሪ ገቢዎችንም ያገኛል፡፡

አዳዲሶቹ ክዋክብት፡- ከ2 የውድድር ዘመናት በፊት ለማንችስተር ዩናይትድ የተጫወተው የ28 ዓመቱ አንጎላዊ ማኑቾ፤ ኪውፒአር ወደ እንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ እንዲያድግ ከፍተኛ ሚና የተጫወተው የ22 ዓመቱ ሞሮካዊ አዴል ራባት፤ (ቤቢ ጀት) ተብሎ የሚጠራውና የሰንደርላንድ ክለብ አጥቂ የሆነው ጋናዊው አሳሞሃ ጊያን፤ ባለፈው የውድድር ዘመን ለፈረንሳዩ ክለብ ሊል ሲጫወት 15 ጎሎች አግብቶ ቡድኑ ከ47 ዓመታት በኋላ የፈረንሳይ ሊግ 1 ሻምፒዮን እንዲሆን ያበቃውና ዘንድሮ አርሰናልን በመቀላቀል በአጥቂ መስመር ድንቅ ብቃት እያሳየ የሚገኘው የአይቬሪኮስቱ ጀርቪንሆ፤ ለፈረንሳዩ ክለብ ሊል ኮከብ ግብ አዳኝ የሆነው ሴኔጋላዊ ሙሳ ሶው እና የኦሎምፒክ ማርሴዩ ጋናዊ ተጨዋች አንድሬ አየው በአፍሪካ ዋንጫው ይደምቃሉ ተብለው የተገመቱ አዳዲስ ክዋክብቶች ናቸው፡፡

የካፍ ገቢ መጠናከር :- 28ኛው የአፍሪካ ዋንጫ የአዘጋጁን የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን የፋይናንስ አቅም መጠናከርንም የሚያመለክት ሆኗል፡፡ ካፍ ካለፉት 5 ዓመታት ለየውድድሮቹ በቂ ስፖንሰሮች በማግኘት ገቢው እየጨመረ ሲሆን በሚቀጥሉት ሰባት ዓመታት በቴሌቭዝን ስርጭትና በማርኬቲንግ የስፖንሰርሺፕ ገቢው 140 ሚሊዮን ዶላር እንደሚደርስ ታውቋል፡፡ ከአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን ጋር በስፖንሰርሺፕ እየሰሩ ካሉ ኩባንያዎች እስከ 2016 የሚቀጥል ስምምነት ያለው የፈረንሳዩ የቴሌኮም ኩባንያ ኦሬንጅ ፍራንስ፤ ለዘንድሮው ውድድር ስፖንሰር የሆነው ሳምሰንግ፤ እስከ 2016 ከኮንፌደሬሽኑ ጋር በስትራቴጂካዊ የእድገት ስራዎች እየተሳተፈ ያለው ፔፕሲኮና የአፍሪካ ኮንፌደሬሽን ካፕና ሻምፒዮንስ ሊግ ውድድሮችን  ለሚቀጥሉት 4 ዓመታት ስፖንሰር ያደረገው ስታንዳርድ ባንክ ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡ ካፍ ከፍተኛውን ገቢ ሊያገኝ የበቃው በዋናነት ከፈረንሳዩ ስፖርት ኤጀንሲ ስፖርትፋይቭ ጋር የፈፀመው ውል  ሲሆን ኤጀንሲው 6 የተለያዩ የካፍ ውድድሮችን ስፖንሰር በማድረግ 137.45 ሚሊዮን ዶላር ይከፍላል፡፡ ከ2010ሩ የአንጎላ 27ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ጀምሮ በተከታታይ  በ2015 ሞሮኮ እስከምታስተናግደው 30ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ድረስ ስፖርትፋይቭ በስፖንሰርሺፕ ተጨማሪ 46.8 ሚሊዮን ዶላር ለካፍ ይሰጣል፡፡ ካፍ ከ2008 ወዲህ ባስተናገዳቸው የአፍሪካ ዋንጫዎች ውድድሮች በስፖንሰርሺፕ መብቱ በእያንዳንዱ 5.5 ሚሊዮን ዶላር እያገኘ ነው፡፡ የካፍ ዓመታዊ ውድድሮች በሆኑት ሻምፒዮንስ ሊግና ኮንፌደሬሽን ካፕ በ7 ዓመታት የስፖንሰርሺፕ ውል እስከ 2017 እኤአ 71.4 ሚሊዮን ዶላር ይገኝባቸዋል፡፡ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን በሚያስተዳድራቸው ውድድሮች ዓመታዊ ገቢው 15.53 ሚሊዮን የደረሰ ሲሆን ከሁለት ዓመት ወዲህ ዓመታዊ ተንቀሳቃሽ ትርፉ 1 ሚሊዮን ዶላር እንደደረሰ ታውቋል፡፡

የአፍሪካውያን ኤክሶዶስና የአውሮፓ ምሬት በየሁለት ዓመቱ የአፍሪካ ዋንጫ ሲካሄድ ግን ፊፋ፤ዩኤኤፍኤ፤ የአውሮፓ ክለቦችና አሰልጣኞቻቸው ለየብሄራዊ ቡድኖቻቸው በሚለቋቸው ተጨዋቾች ሳቢያ  ምሬት ማብዛታቸው የተለመደ ሆኗል፡፡ የአፍሪካ ዋንጫ የአውሮፓን የክለብ ውድድሮች በማያቃውስ ሁኔታ እንዲካሄድ ግፊት ተደርጎም ውድድሩ ከሚቀጥለው የ2013ቱ 29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ጀምሮ በጎዶሎ ቁጥር አመታት እንዲከናወን ግድ ሆኗል፡፡

በ28ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ሳቢያ በተለይ የእንግሊዝ ክለቦች በወሳኝ ምዕራፍ ትልልቅ ተጨዋቾቻውን መነጠቃቸው በከፍተኛ ደረጃ አሳስቧቸዋል፡፡ ማን ሲቲ ወንድማማቾቹን ያያ እና ኮሎ ቱሬ፤ አርሰናል ጀርቪንሆና  ቻማክን፤ ቼልሲ ድሮግባ ፣ ካሉና ኢሲዬንን  ቢያንስ ለወር ያህል ማጣታቸው በሊግ ውድድራቸው ላይ ከፍተኛ ጫና ይፈጥርባቸዋል፡፡ በእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ኮከብ ግብ አግቢዎች ደረጃ ሁለተኛ የሆነው የኒውካስትሉ ዴምባ ባም በ19 የሊግ ጨዋታዎች 15 ጎል ከማስቆጠሩ አንፃር ለሴኔጋል ለመጫወት መጠራቱ የክለቡን ተፎካካሪነት ያወርዳዋል በሚል ተሰግቷል፡፡ ተጨዋቾች በአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፏቸው ሳቢያ በአውሮፓ የሚገኙ ክለቦቻቸው በየሊጋቸው የሚያደርጓቸው 5 ጨዋታዎች ያመልጣቸዋል፡፡

 

 

Read 2714 times Last modified on Saturday, 21 January 2012 11:09