Tuesday, 14 April 2015 11:20

የአልሻባብ ጥቃት የኬንያን ኢኮኖሚ እየጎዳው ነው ተባለ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

በሽብር ጥቃቱ የተጠረጠሩ ግለሰቦች ፍ/ቤት ቀርበዋል
መንግስት 13 የገንዘብ አስተላላፊ ተቋማትን ዘግቷል፤ 86 የባንክ ሂሳቦችን አግዷል
   አልሻባብ ባለፈው ሳምንት በኬንያዋ በጋሪሳ ከተማ ውስጥ በሚገኝ ዩኒቨርሲቲ ላይ ከፈጸመውና 148 ያህል ተማሪዎችን ለህልፈተ ህይወት ከዳረገው የሽብር ጥቃት ጋር በተያያዘ የአገሪቱ ኢኮኖሚ እየተጎዳ እንደሚገኝና የመገበያያ ገንዘቧ የመግዛት አቅም እየቀነሰ መሆኑን ሮይተርስ ዘገበ፡፡
ባለፈው ሳምንት ሃሙስ የተፈጸመውን የሽብር ጥቃት ተከትሎ በአገሪቱ ኢኮኖሚ ቁልፍ ሚና በሚጫወተውና ዋነኛ የውጭ ምንዛሬ ምንጭ በሆነው የቱሪዝም መስክ እንቅስቃሴ ላይ መዳከም መታየቱን የጠቆመው ዘገባው፤ ጥቃቱ ከተፈጸመ በኋላ በርካታ የውጭ አገራት ቱሪስቶች ወደ ኬንያ ለመሄድ የያዙትን ፕሮግራም ሰርዘዋል ብሏል፡፡
የአገሪቱ የመገበያያ ገንዘብ የሆነው ሺልንግ የመግዛት አቅም፣ ከዶላር ጋር ሲነጻጸር በዚህ አመት ብቻ 2 ነጥብ 5 በመቶ ቅናሽ እንዳሳየ ዘገባው ጠቁሞ፣ ቅናሹ በመጪዎቹ ቀናትም ይቀጥላል ተብሎ እንደሚገመት ገልጿል፡፡
አልሻባብ በ2013 በኬንያ ርዕሰ መዲና ናይሮቢ በሚገኝ የገበያ አዳራሽ ላይ ጥቃት ከፈጸመ ጊዜ አንስቶ፣ የቱሪስት ፍሰቱ እየቀነሰና አገሪቱ ከቱሪዝም ዘርፍ የምታገኘው ገቢ በከፍተኛ ሁኔታ ማሽቆልቆሉን ያስታወሰው ዘገባው፤ የኬንያ ማዕከላዊ ባንክ የመገበያያ ገንዘቡን የመግዛት አቅም ለማሻሻል ጥረት ሲያደርግ ቢቆይም ይህ ነው የሚባል ለውጥ አለመምጣቱንም ጠቁሟል፡፡
ካለፈው ሳምንት የሽብር ጥቃት ጋር በተያያዘ ተጠርጥረው በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋሉ አምስት ግለሰቦች ማክሰኞ ዕለት ናይሮቢ በሚገኝ ፍርድ ቤት መቅረባቸውን የዘገበው ደግሞ አሶሼትድ ፕሬስ ነው። ፖሊስ ተጠርጣሪዎቹ ጥቃቱን ለፈጸሙት አራት ግለሰቦች የጦር መሳሪያ አቅርበዋል በሚል በቁጥጥር ስር ያዋላቸው ሲሆን ፍርድ ቤቱም ፖሊስ በተጠርጣሪዎቹ ላይ ተጨማሪ ምርመራ ለማድረግ ያቀረበውን ጥያቄ ተቀብሏል፡፡ ከአምስቱ ተጠርጣሪዎች በተጨማሪ አንድ ታንዛኒያዊ በሽብር ጥቃቱ ተሳትፏል በሚል በቁጥጥር ስር እንደዋለ የጠቆመው ዘገባው፤ ፖሊስ ግለሰቡ ላይ ምርመራ ለማድረግ ተጨማሪ ጊዜ ይሰጠኝ ባለው መሰረት እንደተፈቀደለትም አክሎ አስታውቋል፡፡
የኬንያውን “ዴይሊ ኔሽን” ጋዜጣ ጠቅሶ ሮይተርስ እንደዘገበው ደግሞ፣ የአገሪቱ መንግስት ለሽብር ተግባር የሚውል ገንዘብ ያስተላልፋሉ ብሎ የጠረጠራቸውን 13 የሶማሊያ ገንዘብ አስተላላፊ ተቋማትን የዘጋ ሲሆን በግዛቷ ውስጥ የሚፈጸሙ የሽብር እንቅስቃሴዎች በገንዘብ ይደግፋሉ ያላቸውን የ86 ግለሰቦችንና ድርጅቶችን የባንክ ሂሳብ እንዳይንቀሳቀስ አግዷል፡፡
የመንግስት ውሳኔ በኬንያ በሚኖሩ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ሶማሊያውያን ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ይፈጥራል ያሉት የሶማሊያ ማዕከላዊ ባንክ ገዢ በሽር አሊ፤ ኬንያውያኑ ኑሯቸውን የሚገፉት ከተለያዩ የአለም አገራት ከዘመዶቻቸው በሚላክላቸው ገንዘብ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
በኬንያ መንግስት እንዲዘጉ የተወሰነባቸው የገንዘብ አስተላላፊ ተቋማት ሃላፊዎችም ውሳኔውን በመቃወም፣ በዚህ አካሄድ ሽብርተኝነትን መዋጋት አይቻልም ብለዋ።
የኬንያ አየር ሃይልም ባለፈው እሁድ በሶማሊያ በሚገኙ ሁለት የአልሻባብ ካምፖች ላይ በፈጸመው የአየር ድብደባ ጥቃት ካምፖቹን ሙሉ ለሙሉ ማውደሙን ቢያስታውቅም፣ አልሻባብ በበኩሉ፤ ጥቃቱ አልተፈጸመብኝም ሲል አስተባብሏል፡፡
አልሻባብ ባለፉት ሁለት አመታት ብቻ በኬንያ በፈጸማቸው የሽብር ጥቃቶች ከ400 በላይ ሰዎችን ለህልፈተ ህይወት እንደዳረገም ቢቢሲ ሰሞኑን ባወጣው ዘገባ አስታውሷል፡፡

Read 1937 times