Tuesday, 14 April 2015 08:29

ትልቅ ስህተት - ከትልቅ ደራሲ

Written by  ኑርሁሴን እንድሪስ
Rate this item
(28 votes)

     ሰሞኑን የወጣውን የዳንኤል ክብረት “እኛ የመጨረሻዎቹ እና ሌሎች” የተሰኘ መጽሐፍ አንብቤ ስጨርስ ነው ይህን ጽሑፍ ለመፃፍ የተነሳሁት፡፡ በዚህ መፅሐፍ ውስጥ የተለያዩ ወጐች ተካትተዋል። ከነዚህ ወጐች መካከልም በገፅ 133 የሚገኘው “እስከ ሰባት ትውልድ” የሚለው ይገኝበታል፡፡
ዳንኤል ክብረት በሌሎች መጽሐፍቱ የምናውቀው ትልቅ ደራሲ ነው፡፡ “እኛ የመጨረሻዎቹ እና ሌሎች” በተባለው አዲሱ መጽሐፍ ውስጥ ያገኘሁት የታሪክ ግድፈት ግን ከትልቅ ደራሲ የማይጠበቅ ትልቅ ስህተት ሆኖብኛል፡፡ በዚህ መጽሐፍ ውስጥ በርካታ የታሪክ ግድፈቶች ቢኖሩም በዚህ ጽሑፍ ግን በጣም ጐልቶ የታየውን አንዱን ብቻ እነግራችኋለሁ፡፡
“እስከ ሰባት ትውልድ” የሚለው ወግ አጠቃላይ ጭብጡ መጪውን ዘመን አስበን ካልሰራን የትውልድ መበላሸት እንደሚፈጠር የሚያስገነዝብ ነው፡፡ ለዚህ ጭብጥ ደራሲው የተለያዩ አጫጭር ታሪኮችን በመጥቀስ መልእክቱን ሲያጠናክር እናስተውላለን፡፡ ለምሳሌ በመስቀሉ ጦርነት ወቅት አውሮፓውያንን አሸንፎ እየሩሳሌምን ስለተቆጣጠረው ሳላሐዲን ይናገራል፡፡ ዳንኤል ክብረት እንደሚለው፤ ሳላሐዲን እየሩሳሌምን ከተቆጣጠረ በኋላ የክርስቶስን መቃብር ለማየት ወደ ጐለጐታ ይሄዳል፡፡ በጐለጐታ የነበሩ ቄሶች ሳላሐዲንን እያስጐበኙት ሳለ የስግደት ሰዓት ደረሰበት፡፡ ሳላሐዲንም ጉብኝቱን አቋርጦ ወጣ። በወቅቱ የነበሩት መነኮሳት እዚያው እንዲሰግድ ቢነግሩትም ሳላሐዲን ግን፤ “እኔ የሰገድኩበትን ቦታ መጪው የሙስሊም ትውልድ ሊነጥቃችሁ ይችላል” በማለት ከጐለጐታ ወጣ ብሎ ሰገደ። ሳላሐዲን ያለው አልቀረም፤ ያ ቦታ በኋላ ዘመን መስጊድ ተሰራበት፡፡ ሳላሐዲን በጐለጐታ ቢሰግድ ኖሮ በክርስቲያኖች እና በሙስሊሞች መካከል ጊዜ ጠብቆ የሚፈነዳ ቦንብ ይኖር ነበር… በማለት ዳንኤል ክብረት በመጽሐፉ አውግቶናል፡፡
ውድ አንባቢያን ሆይ፤ እኔን የገረመኝ በክርስትናም ሆነ በእስልምና ሃይማኖት ውስጥ የክርስቶስ መቃብር የሚባል አለመኖሩ እየታወቀ ደራሲው ግን ይህንን ማስፈሩ ነው፡፡ እንደ ክርስትና እምነት ከሆነ፣ የክርስቶስ አካል ያረፈበት ዋሻ ነበር። ከሶስት ቀን በኋላ ግን ክርስቶስ ተነስቶ ማረጉን ሐይማኖቱ ይነግረናል፡፡ ዳንኤል ክብረት ይህን ማለት ፈልጐ ከሆነ በግልጽ ማስቀመጥ ነበረበት፡፡ ሁለተኛ ነገር ደግሞ ሳላሐዲን ሙስሊም መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ በእስልምና አስተምህሮት ደግሞ ክርስቶስ ከነህይወቱ አርጓል የሚል እንጂ ተቀብሯል የሚል እምነት የለም፡፡ አይሁዶች እየሱስን ለመግደል ወይም ለመያዝ ወደ እርሱ ዘንድ ሲሄዱ፣ አምላክ እየሱስን ወደ እርሱ ዘንድ እንዲያርግ አድርጐታል ነው የሚለው እስልምና። ታዲያ ክርስቶስ አልተቀበረም ብሎ የሚያምነው ሳላሐዲን፤ የቱን መቃብር ነው የጐበኘው? የትኛው ታሪክ ውስጥ ነው የክርስቶስን መቃብር ለማየት ሳላሐዲን ወደ ጐለጐታ መጣ ተብሎ የተፃፈው?
ውድ አንባቢያን ሆይ፤ እኔ በዋናነት ለማንሳት የፈለግሁት ይህን አይደለም፡፡ ዳንኤል ክብረት ያነሳው ይህ ታሪክ የሳላሐዲን አልነበረም፡፡ ትልቁ ስህተትም እዚህ ላይ ነው፡፡ ይህ ታሪክ በ638 ዓመት የተፈፀመ የካሊፍ ኡመር ታሪክ ነው፡፡ ሳላሐዲን በ11ኛው ክ/ዘመን የኖረ የጦር ሜዳ ጀግና ሲሆን ኡመር ደግሞ በ6ኛው ክ/ዘመን የነበረ የሙስሊሞች ሁለተኛው ካሊፍ (ንጉስ) ነው፡፡
ከነብዩ ሙሐመድ ሞት በኋላ ከአቡበከር ቀጥሎ የንግስናውን መንበር የጨበጠው ኡመር ነበር። እስልምና በርካታ ግዛቶቹን ያስፋፋው በኡመር ዘመነ መንግስት ነው፡፡ እየሩሳሌምም በሙስሊሞች እጅ የወደቀችው በዚሁ ዘመን ነበር፡፡ እየሩሳሌምን ከሌሎች ግዛቶች የሚለያት ምንም ደም ሳይፈስ የኢስላም ግዛት አካል ለመሆን መቻሏ ነው፡፡
ግዛቶችን እያስፋፋ የመጣው የሙስሊሞች ጦር፣ ወደ እየሩሳሌም ሲገሰግስ ባዛንታይኖች ሶሪያን ለመልቀቅ ተገደዱ፡፡ በኡመር ኢብን አል አስ የሚመራው የሙስሊሙ ጦር ሰተት ብሎ እየሩሳሌም ገባ፡፡ በወቅቱ የእየሩሳሌም ፓትሪያርክ ሶፍሮኒያስ ነበር፡፡ ቄስ ሶፍሮኒያስ በካቶሊክ እና በምስራቅ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ዘንድ እንደ ቅዱስ የሚታይ ሰው ነው፡፡ ሶፍሮኒያስ የሙስሊሞቹን ጦር መቋቋም እንደማይችል በተገነዘበ ወቅት ህዝቡን ከእልቂት ለመታደግ እየሩሳሌምን ለኡመር አገዛዝ ለማስረከብ ወሰነ፡፡ ይህን ለማድረግ የጠየቀው ቅድመ ሁኔታ ግን ነበር፤ ንጉስ ኡመር እየሩሳሌም ድረስ መምጣት አለበት የሚል፡፡ የከተማዋን ቁልፍ የሚያስረክበው ለማንም ሳይሆን ለንጉስ ኡመር ብቻ መሆኑን አሳወቀ፡፡
ይህ መልዕክት የደረሰው ከሊፋ ኡመር አጠገቡ የነበሩትን ሰዎች ካማከረ በኋላ ከመዲና (ሳኡዲ አረቢያ) ተነስቶ ወደ እየሩሳሌም ተጓዘ፡፡ ከሊፋ (ንጉስ) ኡመር እየሩሳሌም በፈረስ እንደገባ አቀባበል ተደረገለት፡፡ በዲንጋ ቆሽሸው የነበሩ የቤተ - መቅደሶቹን አካባቢ ልብሱን ተጠቅሞ አፀዳቸው። (በወቅቱ አይሁዶች ቤተ መቅደሱ ዘንድ እንዳይገቡ በመከልከላቸው ሮማውያኖች ቦታውን በቅጡ አልያዙትም ነበር)፡፡ የኡመርን ተግባር የተመለከቱት የሙስሊሞቹ ጦር ልክ እንደሱ አደረጉ፡፡ ከዚያም እየሩሳሌምን መጐብኘት ጀመረ፡፡ ከሊፋ ኡመር ቤተ - መቅደሶቹን እና ቤተ - ክርስቲያናትን በመጐብኘት ላይ ሳለ የሶላት (ስግደት) ሰዓት ደረሰበት፡፡ ኡመርን የሚያስጐበኙት ቄሶች እዚያው እንዲሰግድ ቢነግሩትም ኡመር ግን እንቢ አለ፡፡ “እኔ እዚህ ከሰገድኩኝ መጪዎቹ የሙስሊም ትውልዶች ኡመር የሰገደበት በሚል ቦታውን ይነጥቋችኋል።” በማለት ከቤተ - ክርስቲያኑ ራቅ ብሎ ሰገደ፡፡ ኡመር ያለው አልቀረም፤ እርሱ በሰገደበት ቦታ ላይ በኋላ የመጡ የሙስሊም ትውልዶች መስጊድ ገነቡበት፡፡ ይህ መስጊድ አሁን ድረስ በእየሩሳሌም ውስጥ የሚገኝ ሲሆን “ኡመር መስጂድ” በመባል ይጠራል፡፡
እየሩሳሌም በሰላማዊ መንገድ በሙስሊም አገዛዝ ስር ከወደቀች በኋላ ንጉስ ኡመርና ቄስ ሶፍሮኒያስ ስምምነት አደረጉ፡፡ ምንም አይነት ግድያ እንደማይፈፀም፣ የክርስቲያኖች ንብረት እና የፀሎት ቦታ እንደማይነካ፣ ማንኛውም የክርስትና አማኝ እምነቱን በነፃነት የማራመድ መብት እንዳለው እና ሌሎችንም ስምምነቶች ኡመር በፊርማው ለሶፍሮኒያስ አረጋገጠለት፡፡
በወቅቱ አይሁዶች ወደ እየሩሳሌም እና ቤተ - መቅደሶቹ ዘንድ እንዳይገቡ በሮማውያን ተከልክለው ነበር፡፡ ይህ ህግ እንዲከበር ሶፍሮኒያስ ጠየቀ፡፡ ንጉስ ኡመር የሶፍሮኒያስን ጥያቄ የተቀበለ ቢሆንም በኋለኛው የሙስሊሞች ዘመን ግን አይሁዶች መግባት ተፈቅዶላቸዋል፡፡
በአጠቃላይ በእስልምና አገዛዝ ስር ክርስቲያኖችም መብት እንዳላቸው ኡመር ካረጋገጠላቸው በኋላ ወደ መዲና (ሳኡዲ አረቢያ) ተመለሰ፡፡ ያን ዘመን ተከትሎ ነበር እየሩሳሌም የሶስቱ ታላላቅ ሐይማኖት ተከታዮች የጋራ መኖሪያ የሆነችው፡፡ ለእስልምና፣ ክርስትና እና ለአይሁድ እምነቶች፡፡
ከላይ የገለፅነው የኡመር ተግባር በሐይማኖት ውስጥ መቻቻል እና አብሮ መኖር ሲወሳ፣ እንደ ተምሳሌት ተደርጐ አብሮ ይጠቀሳል፡፡ ይህ ታሪክ “Jerusalem is ours: The Centuries old Christian, Islam and Struggle for Holy Land”  በተባለው መጽሐፍ ውስጥ ሰፍሮ ይገኛል። በሌሎች የኢንተርኔት ፅሁፎች ውስጥም በብዛት አለ፡፡ ውድ አንባቢያን ሆይ፤ በዳንኤል ክብረት ወግ ውስጥ ሳላሐዲን በሚል የቀረበው ታሪክ የእርሱ ሳይሆን የንጉስ ኡመር ታሪክ ነው፡፡ ትልቅ ስህተት - ከትልቅ ደራሲ ይሏችኋል ይህ ነው፡፡ ሰላም!!

Read 12355 times