Tuesday, 14 April 2015 08:22

7ቱ አስተማማኝ የአፍሪካ ፓስፖርቶች

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

     የዓለም አገራት ፓስፖርቶች ሁሉ ተመሳሳይ ናቸው፡፡ መጠናቸውም ቢሆን 125 ሚሜ x 88 ሚሜ ገደማ ነው፡፡ የየአገራቱ ፓስፖርት አንዱ ከሌላው የሚለየው በምን መሰላችሁ? ያለ ቪዛ ወደ ስንት የዓለም አገራት በቀላሉ ያስገባሉ በሚለው ነው፡፡ ሲሼልስ ዜጎቿ ያለ ቪዛ ውጣ ውረድ በርከት ወዳሉ የዓለም አገራት በቀላሉ እንዲገቡ የሚያስችል አስተማማኝ ፓስፖርት ያላት አፍሪካዊ አገር ናት። የኤርትራ ፓስፖርት ደግሞ የዓለም አገራትን ጉዞ አስቸጋሪ ያደርጋል ተብሏል፡፡
የአፍሪካ አገራት ፓስፖርቶች ያለ ቪዛ ወይም መድረሻ ላይ በሚመታ ቪዛ ወደ ስንት የዓለም አገራት ሊያስገቡ ይችላሉ የሚለውን በመፈተሽ “Good” መፅሄት 7 ቀዳሚ የአፍሪካ አገራትን ለይቶ ደረጃ ሰጥቷቸዋል፡፡ ጥናቱ እንደሚያሳየው፤ የሲሼልስ ፓስፖርት ያላቸው ዜጎች ለቪዛ ማመልከት ሳያስፈልጋቸው 126 አገራትን በነፃነት መጎብኘት ይችላሉ፡፡ ሞሪሽየስና ደቡብ አፍሪካ ደግሞ በሁለተኛና ሦስተኛነት ደረጃ የአፍሪካ አስተማማኝ ፓስፖርቶች ሆነዋል፡፡ የአፍሪካ ግዙፍ ኢኮኖሚ ባለቤት የሆነችው ናይጄሪያ ግን በዚህ ረገድ በ33ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች፡፡
በዓለም ደረጃ ፊንላንድ፣ ስዊድንና ዩናይትድ ኪንግደም የዓለማችን የመጀመሪያዎቹ ሶስት አስተማማኝ ፓስፖርቶች ባለቤት ሲሆኑ ዜጎቻቸው ወደ 137 አገራት ያለምንም ውጣውረድ በቀላሉ እንዲገቡ ያስችላሉ፡፡ አፍጋኒስታን ከዓለም የመጨረሻ ደረጃ ላይ ትገኛለች፡፡
በዓለም ላይ ቪዛ በከፍተኛ ደረጃ ከሚጠየቅባቸው ክልሎች አንዷ አፍሪካ ስትሆን በአፍሪካ አገራት መካከል ያለው ጥብቅ የቪዛ ቁጥጥር የኢኮኖሚ ዕድገቱን ክፉኛ እንደጎተተው ይነገራል፡፡ ከዚህ በታች “Good” መፅሔት “7ቱ አስተማማኝ የአፍሪካ ፓስፖርቶች” በሚል በደረጃ ያስቀመጣቸውን አገሮች እንመለከታለን፡፡
ሲሼልስ - ለ129 አገሮች ቪዛ አያስፈልግም
የሲሼልስ ዜጎች ወይም ፓስፖርት ባለቤቶች ያለ ቪዛ ወይም መድረሻቸው ላይ በሚመታላቸው ቪዛ ወደ 126 አገራት በቀላሉ መግባት ይችላሉ፡፡ የሲሼልስ ፓስፖርት ዜጎችን ከዓለም አገራት ጋር በቀላሉ በማገናኘት ከአፍሪካ የአንደኝነት ደረጃ ሲይዝ ከዓለም በ28ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡
ሞሪሺየስ - ለ125 አገሮች ቪዛ አያስፈልግም
በአፍሪካ ከሲሼልስ ቀጥሎ ወደ ብዙ የዓለማችን አገራት በነፃነት የሚጓዙት የሞሪሺየስ ዜጎች ናቸው፡፡ የዚህች አገር ፓስፖርት ያለ ቪዛ ወይም መድረሻ ላይ በሚመታ ቪዛ ወደ 123 አገራት ያስገባል፡፡ በዚህም በአፍሪካ 2ኛው አስተማማኝ ፓስፖርት ተብሏል፡፡
ደቡብ አፍሪካ - ለ94 አገሮች ቪዛ አያስፈልግም
ደቡብ አፍሪካውያን ለፓስፖርታቸው ምስጋና ይግባውና ከዓለማችን 194 አገራት ውስጥ ወደ 97 ያህሉ ያለ ቪዛ መግባት ይችላሉ፡፡ የደቡብ አፍሪካ ፓስፖርት ከሲሼልስና ሞሪሽየስ ቀጥሎ በአፍሪካ እጅግ አስተማማኙ ፓስፖርት በመሆን 3ኛ ደረጃን ይዟል፡፡
ቦትስዋና - ለ73 አገሮች ቪዛ አያስፈልግም
የአህጉሪቱ አራተኛው አስተማማኝ ፓስፖርት ያለው በቦትስዋና ዜጎች እጅ ሲሆን ከዓለም በ58ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች፡፡ የቦትስዋና ፓስፖርት ወደ 73 አገራት ያለ ቪዛ የሚያስገባ ቢሆንም ከዓለማችን 5 ቀዳሚ ፓስፖርቶች አስተማማኝነቱ በ57 በመቶ ዝቅ ያለ ነው፡፡ የፊንላንድ፣ ስውዲን፣ ዩናይትድ ኪንግደም፣ ጀርመንና አሜሪካ ዜጎች ቪዛ ሳይጠየቁ ወደ 174 የዓለማችን አገራት መግባት ይችላሉ፡፡
ጋምቢያ - ለ68 አገሮች ቪዛ አያስፈልግም
ጋምቢያ በአፍሪካ 5ኛዋ አስተማማኝ ፓስፖርት ያላት አገር ናት፡፡ የጋምቢያ ፓስፖርት ያለምንም ቪዛ 68 የዓለም አገራትን በነፃነት መጎብኘት ያስችላል፡፡
 ኬንያ - ለ68 አገሮች ቪዛ አያስፈልግም
የኬንያ ፓስፖርት በዓለማችን ላይ ወደሚገኙ 68 አገራት ያለ ቪዛ በነፃነት የሚያስገባ ሲሆን እንደ ጋምቢያ ሁሉ በ5ኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ አስተማማኝ ፓስፖርት ነው፡፡
ሌሴቶ - ለ67 አገሮች ቪዛ አያስፈልግም
የሌሴቶ ፓስፖርት በአፍሪካ 6ኛው አስተማማኝ ፓስፖርት ነው፡፡ የሌሴቶ ፓስፖርት የመግቢያ ቪዛ ሳያስፈልግ የዓለማችን 67 አገራትን ለመጎብኘት ያስችላል፡፡
(በነገራችን ላይ የአገራችን ፓስፖርት ያለ ቪዛ መግባት የሚያስችለው ጎረቤት አገር ኬንያ ብቻ ነው።)

Read 3713 times