Tuesday, 14 April 2015 08:21

(የትምህርት ቤት ትዝታ) “የሺደብር አምላክ ያውቃል”

Written by  መንክር - ከጉባያ ሠፈር
Rate this item
(2 votes)

     በ1964፣ 65 እና 66 ዓ.ም በደጀን ትምህርት ቤት በተማሪዎች ዘንድ በእጅጉ ተወዳጅ የነበሩ መምህራንን ሳስታውስ በተለይ እነ ወ/ት ይደነቁ ምትኩ፣ ወ/ት ዘነበች ሥዩም ዋዲሎ ዋዳ፣ አህሙ ደረሩ (የስፖርት መምህር)፣ አበራ ኃይለ ሚካኤል፣ ገብርኤል እምሩ፣ ገበየሁ መንግስቴ፣ ጋሽ ሐሰን፣ ጋሽ ብሩና ጋሽ ንጉሡ ውቤ ተጠቃሾች ናቸው፡፡
በተለይ የሰባተኛና የስምንተኛ ክፍል የሳይንስ አስተማሪዬ የነበረውን መምህር ንጉሡ ውቤን በቅጽል ስሙ “ጋሽ ዝለቀውን” ምንጊዜም አስታውሰዋለሁ። ከትምህርት ቤት ጓደኞቼ ጋር አልፎ አልፎ ስንገናኝም ስለእርሱ ማውራት እንወዳለን፡፡ “ጋሽ ዝለቀው” የተባለውም ጥያቄ ሲጠይቅ፤ “እስቲ ዝለቀው” የሚል ልማድ ስለነበረው ነው፡፡
በ1966 ዓ.ም የ8ኛ ክፍል የሂሳብ አስተማሪ በመጥፋቱ ባዮሎጂ ላይ ደርቦ እንዲያስተምር ተመደበልን፡፡ የክፍላችንም ተጠሪ እርሱ ሆነ፡፡ ጋሽ ንጉሡ አጭርና ወፍራም ሲሆን ፊቱም ክብ ነው፡፡ ሲናገርም በጣም ፈጣን፣ ሳቂታ፣ ቀልደኛም ግልጽም ሰው ነው፡፡ ከቀድሞው የሐረር ጦር አካዳሚ ገብቶ በገዛ ፈቃዱ የወጣ ይመስለኛል፡፡ ብዙ ጊዜ “What is Biology?” እያለ ሲያስተምር፣ ተማሪ ሁሉ ፀጥ ረጭ ብሎ ማዳመጥ አለበት፡፡ በሚያስተምርበት ጊዜ ተማሪ ከተንጫጫ፣ ወይም ከረበሸ አንዴ ወደ መሬት፣ አንዴ ወደ ክፍሉ ጣሪያ፣ አንዴ ወደ እኛ ትላልቅ አይኖቹን እያጉረጠረጠ ብስጭትጭት ይላል፡፡
“…ወይኔ አንበሳው! ይኼኔ ብርጋዴር ጄኔራል ንጉሡ ውቤ በምባልበት ሰዓት የናንተ መቀለጃ ልሁን?” ብሎ ቆጣ በማለት ይናገረንና ወዲያው ሳቅ ይላል፡፡ ጋሽ ንጉሡ አስተምሮ አስተምሮ ጥያቄ መጠየቅና የቤት ስራም ሰጥቶ መቆጣጠር ይወድዳል፡፡ እኛም ማለት አንዳንዶቻችን የእርሱን ሥነ ልቡና በደንብ  እናውቅ ነበር፡፡ ሁልጊዜ እርሱ የሚጠይቀው “እኔ” ብሎ እጅ የማያወጣውንና የማይመልሰውን ነው፡፡ የቤት ሥራ ካልሰራን አውቀን “እኔ እኔ…” ብለን ጥያቄ ለመመለስ እንጫጫለን፡፡ “የለም እናንተማ ጎበዞች ናችሁ፤ እኔ የምጠይቀው እጅ ያላወጡትንና ያደፈጡትን ነው” ይልና ከወንዶች ጥላሁንንና ባንቴን፣ ከሴቶች ደግሞ ዘውድነሽን፣ ኢዛምንና ሺደርብ ጫኔን ይፈልግና “እስቲ እናተ ዝለቁት” ይላል፡፡
የባዮሎጂ ይሁን የሂሳብ ክፍለ ጊዜ ትዝ አይለኝም፤ አንድ ቀን እንደልማዱ ወደ ክፍል በችኮላ እንደገባ፤ “Matter is anything that occupies space….” እያለ ሲያስተምር ቆይቶ፤ “ሺደብር አር ዩ ማተር? (Are you matter?) እስቲ ዝለቂው” ሲል ጠየቃት። ሺደብር የምትቀመጠው እኔ አጠገብ ነበርና “ምንድነው ማተር? ኖ ልበለው ወይስ የስ ልበለው?” ብላ ጠየቀችኝ፡፡ እኔም ተመራመርኩና፤ “መቼም ማተር መጥፎ ወይም ቆሻሻ ነገር ይመስለኛልና ኖ አይ አም ኖት ማተር በይው” አልኳት በለሆሳስ፡፡
“አንችንኮ ነው? ዝለቂው እንጂ” አለ ጋሽ ንጉሡ፤ ፊቱን ከሚጽፍበት ጥቁር ሰሌዳ ወደኛ አዙሮ፡፡ ሺደብርም፤ “ኖ አይ አም ኖት ማተር (I am not matter)” ብላ መለሰችለት፡፡ “እኔን እኔን! ምን ትከፊ ሰው ነሽ አደራሽ፡፡ እንኳን አንቺ ትልቂቱ ሴትዮ ይቅርና ይህች የያዝኳት ጠመኔ እንኳ ማተር ናት” እያለ ስለማተር ምንነት ያስተምረን ጀመር። መምህር ንጉሡ ማስተማሩን ቀጠለና፤ “ነጋቲቭ ኤንድ ነጋቲቭ ሪፔል ኢች አዘር፡፡ ነጋቲቭ ኤንድ ፖዘቲቭ አትራክት ኢች አዘር (Negative plus negative repel each other. Negative and positive attract each other…)” እያለ ሲያብራራ፤ “ጋሸ አልገባንም” አልነው፡፡ ከዚያም ከልጃገረዶች ሺብርን፣ እትየ ይመኑን፣ አስናቀችን፣ ኤልሳቤጥንና ዘውድነሽን፤ ከወንዶች ደግሞ ጥላሁንና፣ ሲሳይን፣ ዘውዱን፣ ፈጠነንና እኔን ተነሱ አለና፤ “በሉ እንግዲህ ሁላችሁም ተመራረጡና ከሴቶች ጋር ተቃፈፉ” አለ፡፡ እኔም በጣም ደስ የምትለኝንና የምወዳትን ኤልሳቤጥ አበበን አቀፍኳት፤ ሌሎችም ወንድና ሴት ሆነው ተቃቀፉና እንደ መደነስ ይቃጣን ጀመር፡፡
“አያችሁ ጎበዝ፤ ነጋቲቭና ፖዘቲቭ አትራክት ኢች አዘር የሚባለው ይኸው ነው፡፡ እርስ በርስ የሚሳሳቡና የሚፈላለጉ ነገሮች ሁሉ አትራክሽን /ስበት/ አላቸው” አለና፤ ወንድ ከወንድ፣ ሴት ከሴት ጋር ደግሞ እንድንተቃቀፍ አደረገ፡፡ “አሁን ደግሞ ሙቀት የለም፤ መሳሳብ የለም፤ መፈቃቀር የለም፤ አለመጣጣም እንጂ” እያለ በመቀለድ ትምህርቱን አስተማረን፡፡
በወቅቱ የሂሳብ መምህርነት የሰለጠነ የ8ኛ ክፍል የሂሳብ አስተማሪ ስለአልተመደበልን መምህር ንጉሡ ሂሳብ ጭምር እንዲያስተምር ተደረገ፡፡ የሂሳብ ትምህርቱ ግን ለአብዛኛው ተማሪ ሊገባን ስለአልቻለ፤ “አንፈልግም ይቀየርልን” ብለን ለርዕሰ መምህሩ ለአቶ ገላጋይ ትርፌ አቤት አልን፡፡ ጋሸ ንጉሱ ወደ ክፍላችን 8ኛ ኤ ገብቶ ሂሳብ ሊያስተምረን ሲል “ውጣልን” አልነው፡፡
“ይህችን ይወድዳል ንጉሡ ውቤ” ብሎ ወደ ዲሬክተሩ ቢሮ ተንደርድሮ በመሄድ፣ አቶ ገላጋይ ትርፌን ይዞ መጣና፤ “እስቲ የኔን የሂሳብ አስተማሪነት የማትፈልጉ እጃችሁን አውጡ! የማትፈልጉ ከክፍሉ መውጣት ትችላላችሁ” አለ፡፡ ወዲያው “ያንተን የሂሳብ አስተማሪነት አንፈልግም” እያሉ አሳምነው አበራ፣ ዳንኤል ታምሩ፣ አብዱ መሐመድ፣ ዘውዱ ዑመርና መዓዛ ታፈሰ ከክፍል ሲወጡ፣ በቁመቱ ረጅምና በዕድሜ ታላቅ የሆነው ባንቴ ጥሩነህ፤ ቀውለል ቀውለል እያለ ሊወጣ ሲል፤ “አንተ ደግሞ የምትወጣው ምን ተበደልኩ ብለህ ነው? ይኼኔ’ኮ ሞሱ ባንቴ የሚባል ልጅ ታደርስ ነበር፡፡” አለው ጋሽ ንጉሡ፡፡ ባንቴ ገራገርና የዋህ ስለነበር ዝም ብሎ ወጣ፡፡
ከዚያ እኔ በእድሜዬም በሰውነቴም ግዙፍነት የተነሳ ከፈጠነ ባንታምላክ ስልጣን ተቀብዬ የ8ኛ ክፍል አለቃ ሆኜ ስለነበር ለመውጣት ስነሳ፣ የቀረውና በቁጥር ስድሳ የሚደርሰው ተማሪ አንዴ ብድግ አለ፡፡ ይህን ጊዜ፤ “አያ ገላጋይ፤ አሁን ገና ያድማው መሪ ተገኘ፡፡ አሳምነው ቢወጣ ማንም አልወጣ፣ አብዱ ቢወጣ ማንም አልወጣ፣ ዘውዱ ቢወጣ ማንም አልወጣ፣ መዓዛ ቢወጣ ማንም አልወጣ፣ አለቃው ሲነሳ ሁሉም ተነሳ፡፡ አቆራኙ እጅ ከፍንጅ ይያዝልኝ” አለ፡፡ ሽደብር ጫኔ አጠገቤ ቆማ ነበርና ወደ እርስዋ እየተመለከተ፤ “አያ ገላጋይ፤ ሺደብር እንኳ ነገሩ አልገባትም፡፡ አሁን ለምንድነው የተነሳሽ? ቢሏት ‹እኔ እንጃ አለቃችን መንክር ስለተነሳ (Because he is the father of the class)› ትላለች እንጂ ሌላ መልስ የላትም” ብሎ ቀለደባት፡፡
ከዚያም የአድማው “መሪዎች” የተባልን ሰባት ተማሪዎች ተመርጠን ስንቀር ሌሎች ወደ ክፍላቸው እንዲገቡ ተደረገ፡፡ እኛም በሰኔ ላይ ለሚተከለው ባሕር ዛፍ አገልግሎት የሚውል መሬት ለሁለት ሳምንታት ያህል በቅጣት መልክ ቆፍረን አለሰለስን፡፡ በመጨረሻ በተሰጠን ምሕረት ወደ ክፍላችን ገባን፡፡ ያን ጊዜ የተማሪ ቅጣቱ “ሥራ” ነበር፡፡
እናም የጋሽ ንጉሱ የሂሳብ አስተማሪነት በርዕሰ መምህሩ ተቀባይነት አገኘና ማስተማሩን ቀጠለ። አንዴ፤ “ኤፍ ኦፍ ኤክስ ፕላስ ኤፍ ኦፍ ኤክስ (F Of X + FOFX) ስንት ነው?” ብሎ በተለይ በሂሳብ ትምህርት ደከም ያሉትን ጥላሁንንና ሺደብርን ሲጠይቅ፤ “እኔጃ” እያሉ መለሱለት፡፡ “አይ የናንተ ነገር፣ ሶስት እንጀራ ሲደመር ሶስት እንጀራ ስንት ነው? ማለት’ኮ ነው፡፡ ኧረ ተዉ ነቃ ነቃ በሉ! የ8ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተናም’ኮ እየተቃረበ ነው” አለ፡፡ እንደአጋጣሚ በዚያው ዓመት የ8ኛ ክፍል ማለፊያ ማርክ 30% ሆነና ጥላሁንና ሺደብር እቅጩን አምጥተው አለፉ፡፡ ጋሽ ንጉሡ ማለፋቸውን እንዳወቀ፤ “ሺደብርና ጥላሁን ጥሩ አምላክ አላቸው” እያለ ያስቀን ነበር፡፡ በዘመኑ በከተማው ውስጥ ፎቶ ቤት ስለአልነበረ ካሜራ ያለው ሰው እንደብርቅ ይታይ ነበር፡፡ በ1966 ዓ.ም ሰኔ ወር ላይ ከደብረ ማርቆስ ፎቶ አንሺ /ፎቶ አምዴ/ ትምህርት ቤታችን ድረስ ስለመጣ፣ ፎቶ መነሳት ብርቃችን ነበር፡፡ ጋሽ ንጉሡም ለማስታወሻ ይሆን ዘንድ የ8ኛ ኤ ተማሪዎች ከአስተማሪዎቻችን ጋር እንድንነሳ አደረገ፡፡ እኛም የእርሱን ትክሻ ተደግፈን የማስታወሻ ፎቶግራፍ ስንነሳ፣ ከሴቶች በጣም ቆንጆዎች የሚባሉት አስናቀች ውብእሸትንና ኤልሳቤጥ አበበን መርጦ ወደራሱ አቀራረባቸው። ሺደብርም አብራቸው ለመነሳት ጠጋ ስትል፤ “ሺደብር አንቺ ቆይ… ፎቶግራፍ ታበላሻለሽ” አለና ቀለደባት፡፡
እርስዋም፤ “እኔ ከማን አንሳለሁ ጋሽ! ቆንጆ ነኝኮ” እያለች በመጠጋት አብራት ተነሳች፡፡ በዚያው በ1967 ዓ.ም ንጉሡ የ8ኛ ክፍል የባዮሎጂና ሂሳብ አስተማሪ ሆኖ ተመድቦ፤ ሸዋየ ታሪኩ የተባለችው ሙዝ ለመንገደኞች እየሸጠች የምትማር ልጅ የሂሳብ ትምህርት ይከብዳታል፡፡ “ኤፍ ኦፍ ኤክስ ፕላስ ኤፍ ኦፍ ኤክስ ስንት ነው?” ሲላት ደንግጣ፤ “ጋሽ ንጉሡ ያንተ ትምርት ከባድ ነው፤ በዚህ ዓይነት 8ኛ ክፍል አልፍ ብለህ ነው!” ትለዋለች፡፡
“ሸዋየ ያንቺ ጠላት’ኮ ኤፍ ኦፍ ኤክስ የሚለው ቃል ነው፡፡ በቀላል አማርኛ 8 ሙዝ ሲደመር 8 ሙዝ ስንት ነው ቢሉሽ መልሱን ቁጭ ነው የምታደርጊው። ስለማለፉ ደግሞ አትጨነቂበት፡፡ አይዞሽ ’የሺደብር አምላክ’ ያውቃል፡፡ ደጉ መንግሥታችን ዘንድሮ ደግሞ የ8ኛን ክፍል ማለፊያ 15% ሊያደርገው ይችላል፡፡ ማን ያውቃል?” ብሎ አስቋታል፡፡
ነፍሱን ይማረውና ጋሽ ንጉሡን አዲስ አበባ አግኝቼው፤ “ጋሽ፤ ምነው ጸጉርህ ሸበተ?” አልኩት፡፡
“አይ ታደለ፤ በእውነቱ አንተም ያንተን ነገር፣ እኔም የእኔን ሽበት አለማየታችን ነው፡፡ እኔም ሽበቴን አንተም መላጣህን የምናይ ቢሆን ኖሮ እንናደድ ነበር፡፡ ደግነቱ ራሳችንን አናየውም፤ ዝንጀሮ የራስዋ መላጣ አይታያትም እንዲሉ” አለና የበለጠ አሳቀኝ፡፡  

Read 3606 times