Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 21 January 2012 10:51

የግጥም ጥግ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ግጥማዊ ምንባብ 2

ታሪክ

(ፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያም)

ያለፈው አለፈ፤

ሄደ እየከነፈ፡፡

ይረሳ፤ አይወሳ፤

ትናንትና ሬሳ

ከራስ በላይ ነፋስ ስንኩል ፍልስፍና

ደካማ አእምሮና ደካማ ሕሊና

መሆኑን አያውቁም ዛሬ ትናንትና፡፡

ትናንት መሠረት ነው ዛሬ የቆመበት

ዛሬም መሠረት ነው ነገ የሚያርፍበት

የትናንት መሠረት አይፈርስም በፀፀት

ለነገውስ ምኞት ዛሬን ማን ነጥሎት

የዛሬው ውሳኔ ሚዛን ነው ለነገው

ዛሬ ያልከበደ ነገ መቅለሉ ነው፡፡

ዛሬ እንደሠፈሩት ቢተርፍም፤ ቢጐልም፤

ነገ ይሰፈራል ታሪክ ፍርዱ አይቀርም፡፡

ትናንትና ነገ የተያያዙበት

ዛሬ ነው ሰንሰለት ውሳኔ ያለበት

ከባዱ ውሳኔ ትልቅ ኃላፊነት

የነገው ቅርፀ መልክ የሚታነጽበት፡፡

ትናንት ነገ፣ ዛሬ የሚለዩ አይደሉም

ድርና ማግ ናቸው የታሪክ ራስ ጥምጥም፡

ነገ ዛሬ ሲሆን ዛሬም ትናንትና

የዛሬ ቁራኛ ግልጽ ድንቁርና

ይሙት በቃ ብሎ ታሪክ ፍርዱ አይቆምም

የተቀበረውን ሬሳም አይምርም

ታሪክ ትዝብት ነው ፍሬው እንዲፋፋ

አረም እንክርዳዱን መርጦ የሚያጠፋ

ታሪክ ትምህርት ነው፤ የፀፀት አለንጋ

ትውልድን ለእድገት ገፍቶ የሚያስጠጋ

ታሪክ ፍርድ ቤት ነው የሕሊና ችሎት

ሕያው ከሙት ጋራ የሚሙዋገትበት

ታሪክ ማዕበል ነው፤ የሚዥጐደጐድ ጐርፍ

ሊታገድ አይችልም ገፍትሮ ነው የሚያልፍ

ይሄዳል፤ ይሮጣል፤ ኃይል እየጨመረ፤

ይንዳል፤ ይከባል፤ እያነጣጠረ፡፡

ጐረምሳና አሮጌው ዋና ልዩነቱ፤

አሮጌው ትናንትን የሙጥኝ ማለቱ

ዛሬ ለዛሬ ሲል ጐረምሳው ማርጀቱ

አንድነቱ ደግሞ ነገ መረሳቱ

ቂልነት ነው፤ ትዕቢት

ወይስ ደደብነት

ነገ የሚፈርሰው ዛሬ እሚካብበት

የማታ ማታ ታሪክ ይረታ፤

እንዴታ!

እንዴታ!

 

 

Read 4408 times Last modified on Saturday, 21 January 2012 10:58