Tuesday, 14 April 2015 08:15

ትንሳኤ

Written by  መኳንንት አስፋው
Rate this item
(0 votes)

ልጄን ሌላ ሆቴል ውስጥ አስቀምጨ ነው የመጣሁት። ሰዓቱ ከመሸ ብደርስም ግቢው በግርገር እንደተሞላ ነበር። ሰራተኞቼ ሙሉ ጊዜያቸውን ሰጥተው ዝግጅቱን አጧጡፈውታል፡፡
“ዋው! ጥሩ ሰዓት ደረሳችሁ! ባቢስ?” ሃላፊው እየሳቀ መጥቶ ጨበጠኝና ሻንጣየን ከሹፌሩ ጋር ማውረድ ጀመረ። ህንጻው ዙሪያውን  በተለያዩ ዲኮሮች አጥሩ በባንዲራ አጊጧል፡፡ ምስቅልቅል ያለ ስሜት እየተሰማኝ እዛው ቆሜ ትንሽ ካየሁ በኋላ ወደ ውስጥ ገባሁ፡፡ በስመአብ! ይበልጥ የደመቀው ትልቁ አዳራሽ ነው፡፡ ከዚህ በፊት ያላየሁት እስኪመስል እዛው ቆሜ ቀረሁ፡፡ ሙሽራ ሊቀበል የተዘጋጀ ነው የሚመስለው፡፡ ለነገሩ ለእኔ የነገዎቹ እንግዶች ከምንም ሙሽራ በላይ ናቸው፡፡ በተለይ ባብዬ! አምላክ በዚህ ሁሉ አውጥቶ ለዚህ አበቃልኝ፡፡ እና ከዚህ በላይ ምን ሙሽራ አለኝ? አዎ! ነገ ከእኔና ከልጄ በላይ ሙሽራ የለም፡፡ ብዙ ታላላቅ ሰዎችንና ባለስልጣናትን ብንጠራም፣ ሙሽራዎቹ ግን እኛ ነን፡፡ የምናምር፣ ሌላ ተጓዳኝ ያልጨመርን እናትና ልጅ ሙሽሮች፡፡ ለነገሩ ለማያውቅ ሰው የእውነት ባልና ሚስት ነው የምንመስለው፡፡ ባብዬ ሰውነቱ ግዙፍ ስለሆነ አንድም ሰው እናትህ ብሎት አያውቁም፡፡ ቀረብ ያላሉ ጓደኞቹ ሁሉ እህትህ እያሉ ነው የሚጠሩኝ፡፡
ተፈጥሮዬ አጭር ባልባልም ብዙ ነገሮችን የተሸከምኩበት አካሌ የባቢ እናት ለመባል የሚያበቃ ግዝፈት የለውም፡፡ ለነገሩ በእድሜም ቢሆን የምበልጠው አስራ አራት አመት ብቻ ነው፡፡ ባብዬ የመጀመሪያ ልጄ ነው፡፡ ምን መጀመሪያ፤ መጨረሻም እንጅ! ከእሱ አባት ወዲህ ወንድ!... በማለቴ ልጄም አንድ ብቻውን እንዲቀር ፈርጀበታለሁ፡፡ ለባቢ አባት የነበረኝ ፍቅርም ሆነ ደግነቱ አልነበረም ከሱ ሌላ ያሰኘኝ፡፡ ወላጆቹና ወላጆቼ ተነጋግረው ያጋቡን ገና በስምንት አመቴ ነው፡፡ ከዛ የሚያጋጥመኝ አቀባበል ብቻ ሳይሆን ከእናቴ መለየቴ ጭምር ከብዶኝ በየጊዜው መኮብለል ሥራዬ ሆነ፡፡ እሱ ደግሞ እንደልጅ ከማባበል ይልቅ እየተከታታለ በመግረፍ አሰቃየኝ፡፡
ወላጆቼም በርበሬ አጥነውና ገርፈው ስላልቻሉ “እንግዲህ ሰው ልጁን አይገድል! ካልሆነ ትቅርብህ እንጅ ማለት ጀመሩ፡፡ በዚህ ላይ እንዳለን ነው ባብዬ የተረገዘው። አሁን የወላጆቼም ፊት እንደገና ተቋጠረ፣ “እንግዲህ ልጅ አይደለሽም! ኮስተር በይና ልጅሽን አሳድጊ!” አሉኝ፡፡ ባሌ ደግሞ በእጁ እንዳረገኝ ስላረጋገጠ ነው መሰል ባህሪው በጣም ከፋብኝም፡፡ አማራጭ ግን አልነበረኝም፡፡ ዘጠኝ ወሩን ከብዙ ስቃይ ጋር አሳልፌ ለመውለድ ወደ እናቴ ቤት ሄድኩ፡፡ ስቃዩም ልጅነቴም ተዳምረው ምጥን ብቻ ሳይሆን ሞትን አሳይተው መለሱኝ፡፡ እራሴም ልጅ እስሆንኩ ለልጁ ደንታ ባይኖረኝም፡፡ የፈጣሪ ፈቃድ ግን ሁለታችንም ከሞት አተረፈን፡፡ እናትነት ልዩ ሃይል አለው፡፡ ቁልቁልጭ እያለ ሳየው የልጅ አምሮዬ ሃላፊነትን ለመቀበል ተዘጋጀ፡፡ ቢሆንም ከዚህ በኋላ ከአባቱ ጋር እንደማልቀመጥ ቆርጬ ነበር፡፡
ልጄን ክርስትና አስነስቼ ከአራስ ቤት ከወጣሁ በኋላ ባለቤቴ ካልወሰድኩ ብሎ ይመላለስ ጀመር፡፡ አሁን እናትና አባቴ እንደድሮው ገርፈውና ተቆጥተው ሊልኩኝ አልሞከሩም፡፡ ምክንያቱም ከሞት የከፋ ውሳኔዬን ቀድሜ አስረድቻቸው ነበርና “ከእንግዲህ አይሆንም!” ሲሉ ሸኙት። ያን እለት ቢበሳጭም እኔን እንደሚያጠፋኝ ነበር የዛተው፡፡ አባቴ በህይወት እያለ ይህን ማድረግ ግን ቀላል አልሆነለትም። በውድ እንጅ በግድ ሊወስደኝ እንደማይችልም ደጋግሞ አረጋገጠ፡፡ “እልህ መርፌ ያስውጣል” ነው የሚባለው? አዎ እሱም አባቴን ለመግደል ከእልህ ይለፈ በቂ ምክንያት እንደሌለው ይሰማኛል፡፡ ምድር ያበቀለችው እኔን ብቻ አልነበረም፡፡ አባት ለልጁ ደህንነት መቆሙም በእኔ አባት አልተጀመረም፡፡ ብቻ መጥፎ ዕድል ሆነና የምወደውን አባቴን በእኔ ምክንያት በልጄ አባት አጣሁት፡፡ ሃዘኔም፣ መከራየም፣ ያን ቀን ጀመረ፡፡
የወንድሞቼ ቤት ከአባቴ ቤት ፈንጠር ፈንጠር ያለ ነበር። ተኩሱን ቢሰሙም የት እንደሆነ አውቀው የደረሱት ጠላት ተብየው ካመለጠ በኋላ ነው፡፡ ለነገሩ ወዲያው የገነፈለው ጎረቤትም ቢሆን አልደረሰበትም፡፡ የልቡን ሰርቶ ወዲያው ተሰወረ፡፡ በላይ በታች ብሎ ጠላቱን ማግኘትና መበቀል ያልቻለው ቤተ ዘመድ ደግሞ እኔንና ልጄን እንደሁለተኛ ጠላት አድርጎ ቆጠረን፡፡ ወንድሞቼ ትናንት ተንከባክበው ያሳደጉኝ እህታቸው መሆኔን እንኳን ማስታወስ አልፈለጉም። ልጄን ከጉያዬ ነጥቀው መግደል እኔን እንደጠላት ሚስትነቴ ማሰቃየት አማራቸው፡፡ ከጅምሩም ሁኔታው ስላላማረኝ የወላጆቼን ቤት ለቅቄ የወጣሁት ወዲያው ነበር፡፡ ወዴት መሄድ እንዳለብኝ እንኳን አላውቅም፡፡ ልጄን ይዤ ከአገር መጥፋት እንዳለብኝ ባስብም እንኳን አገር፣ የማውቀው ራቅ ያለ ቀበሌ አልነበረም፡፡ ቢሆንም የጭንቄን እግሬ እስኪደክመኝ ተጓዝኩ፡፡
*   *   *
“ያስደምማል አይደል? በጣም የሚገርም ጥበብ ነው! እንዴት ጎበዝ ሰዎች መሰሉሽ?” ቆሜ መቅረቴን ያው ሃላፊ ነበር ከሃሳቤ ያናጠበኝ፡፡ እንደመበርገግ ብዬ የሃፍረት ፈገግታ ፈገኩለትና፣ “አመሰግናለሁ! ይሄ የሁላችሁንም ብርቱ ጥረት ነው የሚያሳው!” አልኩት እውነትም ዝግጅቱ ሰራተኞቼ ሁሉ ምን ያህል ከልባቸው እንደተንቀሳቀሱበት የሚያሳይ ነው፡፡ እንደ አንቺ አየነት ብርቱ አለቃ ያለው ሰራተኛ ከዚህ ውጭ ሊሆን አይችልም፡፡ በእውነት በህይወቴ ከማደንቃቸው ብርቱ ሴቶች የመጀመሪያዋ ነሽ! ከወዲሁ እንኳን ለዚህ አበቃሽ እልሻለሁ፡፡ ሲል በአክብሮት ጎንበስ ብሎ ጨበጠኝ፡፡
“አመሰግናለሁ ግን ይሄ የሁላችንም ውጤት…” ለምን እንደሆን ባላውቀውም ንግግሬን ሳግ አቋረጠው፡፡ ከፊቱ ማልቀስ ግን አልፈለኩም እቃ እንደረሳ ሰው ተጣድፌ ወደ ቢሮዬ ገባሁ፡፡ ጸሃፊዬ ነገ የማደርገውን ንግግር ተይባ ጠረጴዛዬ ላይ አስቀምጣለች፡፡ ላነበው ግን አልቻልኩም። ለምን እንደሆን እንጃ ሆዴ ተረብሾብኛል፡፡ አልቅሽ የሚል ስሜት ነበር የተናነቀኝ፡፡ ለምን እንደማለቅስ ግን አልገባኝም፡፡ እስቲ በድሌ ቀን፤ ድሌን በማከብርበት ዋዜማ ምን ያስለቅሳል? ራሴን ጠየኩ እንጅ ስሜቴን መግታት አልቻልኩም ቢሮዬን ቆልፌ ስቅስቅ ብዬ አለቀስኩ፡፡ በዚህ ቀን ችግሮቼን ለምን እንደማስታወስ ባላውቅም ጭንቅላቴ የኋሊት እየራቀ እምቢ ብሎኛል፡፡ በዚህ ምቹ የቆዳ ወንበር ላይ ተቀምጨ አራስ ልጅ አዝየ የተንከራተትኩበት ተራራና ገደል ትውስታ እረፍት ነሳኝ፡፡


*   *   *
አባቴ ሲገደል ልጀ ገና ወር ከአስራ አምስት ቀኑ ነበር፡፡ ከዛ በኋላ የቆየሁት አስር ቀን እንኳ የሚሞላ አልነበረም፡፡ ልጄን እንደ አራስ ነብር ሁሉንም ለመንከስ ከሚሯሯጡት ወንድሞቼ ለማዳን ወገቤ ሳይጠና አዝየው ወጣሁ፡፡ የራቅኩት ግን ሁለት ቀበሌ ብቻ ነበር፡፡ ደከመኝ፣ መንገድ ላይ ተዝለፍልፌ ወደኩ። የአካባቢው ሰው ከእነልጄ ሰብስቦ ከአውሬ ያተረፈኝ፡፡ አብልተው አጠጥተው ቀና ስል የደረሰብኝን ጠየቁኝ፡፡
የገዳይ ልጅ በመገደሉ ላይ በተመሳሳይ እምነት ስላላቸው በደረሰብኝ መከራ አዘኑ እንጂ በሁኔታው አልተደነቁም፡፡ ሆኖም “ቢሆንስ እስኪያድግ የተብቃሉ እንጅ አራስ ልጅ ላይ ቃታ አይስቡ፣ ኧረ ይልቅ ዝም ብለሽ ተቀመጭና ልጅሽን አሳድጊ!”  ሲሉ ሌላ ስደት እንዳላስብ አበረታቱኝ፡፡
አንዳንድ ቤተዘመድ ለአራስ መጠየቂያ መቀነቴ ስር ከሸጎጠልኝ ብሮች በቀር ምንም ይዠ አልወጣሁም፡፡ ነገሩ ይዤስ ልውጣ ብል ማን ሊሰጠኝ፡፡ የጠላት ገንዘብ ባይወስዱት እንኳን ወፍ ይበላዋል እንጅ በምን መብቷ ሚስት ታዝበታለች። አይ! እርጉም ሥራ! ታዲያማ ሴት አይገደልም! ይሉናል፡፡ ሞት ከዚህ በላይ ምን አለ? በደከመ አካል ሃዘን፣ ረሃብ፣ ችግር፣ ስጋት… ተሸክሞ ከመኖር ሞት አስር እጅ አይሻልም? ዳሩ ለእኛ ግልግል ነገር አልተፈቀደም፡፡ እኔም እነዛን በሮች ቋጥሬ ለስቃይ ወጣሁ። ለጊዜው ያስጠጉኝ አንዲት በጠላ ንግድ የተሰማሩ ሴት ነበሩ፡፡ በነዛው ብሮች ገብስ ግዥና አብረን እንነግድ አሉኝ። ለጊዜው ደስታውን አልቻልኩትም ነበር፡፡ የተከፋሁት ትርፉ ስቃይ ብቻ መሆኑን ስረዳ ነው፡፡ የጠላ ስራ ስቃይ ነው፡፡ በራሴ ገዝቼ እኔው መከራ አይቼ የሰራሁትን ጠላ የሚያዙበት እሳቸው ነበሩ፡፡ ለፈለጉት ይሰጣሉ፣ ለፈለጉት ይሸጣሉ፡፡ እሳቸውም ቢሆን እንደ እንስራቸው ጠላ ለምደዋል፡፡ ትርፉ ውሃ ቅዳ ውሃ መልስ የሆነብኝ ለእኔ ብቻ ነው፡፡ እንደልጅ ቆጠሩኝ መሰል ያለይሉኝታ አንገላቱኝ፡፡ በጣም ያቃጠለኝ ግን የልጄ መሰቃየት ነበር፡፡ ያን ሁሉ እየለፋሁ ለእሱ አንዲት ነገር የምገዛበት እንኳን አጣሁ፡፡ በልብስም፣ በምግብም፣ በአያያዝም ተጎዳ፡፡
ይሄኔ ነው የጠላውን ንግድ ለማቆም የተገደድኩት፡፡ ሴትዮዋ አይሆንም ቢሉም እምቢ ብዬ እህል ንግድ ጀመርኩ። ፈተናው ግን ቢብስ እንጅ የሚሻል አልነበረም፡፡ በጀርባዬ ልጅ በጭንቅላቴ ሃያና ሃያ አምስት ኪሎ እህል ይዠ ተራራ ገደል መጓዝ፡፡ ከንግዱ በላይ መጠጡን በትርፍነት ይዘውት የነበሩት ባለቤቷ ጠላውን ካቆምሽ ልጅሽን አልይዝም ስላሉኝ ከእኔ ጋር መንከራተት ግዴታው ሆነ፡፡ አንድ ቀን ከታችኛው ገባያ እገዛለሁ፡፡ ከቤቴ አድሬ በሌላው ቀን ወደ ላኛው ገበያ ወስጀ እሸጣለሁ፡፡ በቃ ከሚቀንሰው መግዛት፣ ተሸክሜ ወደሚጨምርበት ማጓጓዝ፡፡ በዚህ አይነት ለቀናት ተመላላስኩ፡፡ ስቃዩን ቃላት አይገልፁትም፡፡ ትርፉ ግን የተሻለ ሆነ፡፡ ልጀም ብርዱና ፀሃዩ ቢፈራረቅበትም ወተትና ጥብቆ አገኘ፡፡ በዚህ ሁኔታ እንዳለሁ ነበር የማስረክበው የእህል ነጋዴ አጠራቅመሽ ትወስጃለሽ እያለ ብሬን ማቆየት የጀመረው፡፡ ሁለት ሶስት አራት… ቢቸግረን እየተደበኩ ለሌላ ነጋዴ እየሸጥኩ የእለት ማገላበጫ ማግኘት ጀመርኩ፡፡ ቢሆንም እሱንም አልተውኩትም፡፡ እንዳለው ጠርቀም ብሎልኝ አህያ ለመግዛት አስቤአለሁ፡፡ አንድ ቀን ቁጭ በዬ ሳስበው እውነትም ለአህያ መግዣ የሚሆን አጠራቅሜአለሁ፡፡ እየተደሰትኩ ሄጀ አስረከብኩትና ለሚቀጥለው ቅዳሜ አዘጋጅቶ እንዲጠብቀኝ ስል ያሰብኩትንና ወደፊት ጨመር አድርጌ እንደማቀርብለት ነገርኩት፡፡ ለእለቱ በደስታ ተቀበለኝ፡፡በተባለው ቀን ግን ምንም ብር ሊሰጠን አልቻለም፡፡ ለካስ ለእሱም ስጋት ሆኘበት በፍርሃት ኖሯል የሚያስተናግደኝ፡፡
“ጠላታችን ለማሳደግ እሷን ትተባበራለህ ብለው እንዳስፈራሩትና ብሩን እንደቀሙት!” ነገረኝ፡፡ “አሁንም እየተከታተሉሽ ስለሆነ ልጁ ከፍ ብሎ ሳያውቁት ይዘሽው ብትጠፊ ይሻላል፡፡” ሲልም እያዘነ ምክር ቢጤ ለገሰኝ፡፡ ልጄን ከላዬ ላይ የነጠቀኝ ያህል ነበር የደነገጥኩት፡፡ ተሸክሜ የመጣሁት እህል ሳይገለበጥ መንገሩ ጠቀመኝ፡፡ ምን አልባትም ሆን ብሎ ያደረገውም ይመስለኛል፡፡ እንደደነገጥኩ እህሌን አንስቼ ሮጥኩ፡፡ ቢሆንም እንደሌባ ተሹለክልኬ ሸጥኩ እንጅ ወደ ቤቴ አልተመለስኩም፡፡
*   *   *
“እ እ.. እራት እዚህ ይቅረብልሽ እንዴ? መስቲ!” አዲሷ ልጅ ነበረች ጠያቂዋ፡፡ ሆቴሉ ስራ ከጀመረ ሰንበት ቢልም የተወሰኑት ገና የቅርብ ጊዜ ተቀጣሪዎች ስለሆኑና ባህሪዬን ስላላወቁ ይፈሩኛል፡፡ ስትገባ ባለመስማቴ እንደመበርገግ ብዬ መሸ እንዴ? ኧረ መኖሪያ ቤት እሄዳለሁ! እንደበረገኩ ተነሳሁ፡፡
“ስራ በዝቶብሽ ማደር የፈለግሽ መስሎን እንጅ እኮ መሽቷል” አለችን ለመውጣት ወደ በሩ እየተመለሰች፡፡ ግራ ገብቶኝ ሞባይሌን አንስቼ ሰዓት አየሁ፡፡ ገረመኝ የገባሁት ከመሸ ቢሆንም ይህን ያህል እቀመጣለሁ ብዬ አላሰብኩ፡፡ “ወይጉድ! ምን ነካኝ እባክሽ! በይ አንድ ሹፌር ጥሪልኝ አድርሰውኝ ይመለሱ፡፡ እውነትም በድርጊቴ እየተበሳጨሁ ቦርሳየን አንጠልጥዬ ወጣሁ፡፡ በቅርቡ ተጠናቆ የገባሁበት አዲሱ መኖሪያ ቤቴ ከከተማው ፈንጠር ስለሚል ከመሸ ብቻዬን እያሽከረከርኩ ለመሄድ እፈራለሁ፡፡ እሽ ብላ በፍጥነት ሄደች፡፡ ቢሮየን ቀልፌ እየተጣደፍኩ ሊፍት ጠራሁ፡፡ አልተያዘም፤ ፈጥኖ ሲደርስልኝ ገብቼ ቁጥሩን ነካሁ፡፡ ይዞኝ ቁልቁል ሸመጠጠ፡፡ ወደ መኪና ማቆሚያው እየተራመድኩ ግቢውን ቃኘሁ፡፡ እውነትም ሬስቶራንቱ አካባቢ ጭር ብሏል፡፡ ወዲያ የመኪና ማሞቅ ድምጽ ሰማሁ እሰይ! ሾፌር ተዘጋጅቶ እየጠበቀኝ ነው፡፡ ፈጠን ብዬ ገባሁና ቶሎ አድርሶኝ መመለስ እንዳለበት ነገርኩት፡፡ እሽታውን በአንገቱ ገልጾልኝ መኪናውን አስጓርቶ ከግቢ ወጣ፡፡ እሱም ፈራ መሰል እንደ በፍጥነት እያበረረ አድርሶኝ ተመለሰ። ቤቴ ስገባ ከዘበኛው በቀር ሁሉም ተኝተዋል፡፡ ለነገሩ እኔም የምግብ ፍላጎት አልነበረም፡፡ ቀጥታ ወደ መኝታ ቤቴ አመራሁ፡፡ ነገርን የኋሊት እያጠነጠነ ያለው ጭንቅላቴ ቢያርፍልኝ መተኛት ይኖርብኛል፡፡
*   *   *
የልጄን ነፍስ ለማዳን ነፍሴን ስቼ ያመለጥኩት ወደ ባህር ዳር ነበር፡፡ በእኔ ሸክም የመጣችው እህል ዋጋ ከትራንስፖርት ብዙ አልተረፈም፡፡ ቢሆንም ሁሉም ባለቆርቆሮ ሃብታም እንደሆነ ስላሰብኩ ከአንዱ ቤት የመጠጋት ሃሳብ ነበረኝ። ከተማ ሳይ የመጀመሪያዬ ነው፡፡ ከእኛ ገጠር ጋር ሲነፃጸር ብዙ ልዩነት እንዳለው ገብቶኛል፡፡ የነዋሪውን ልዩነት ያህል ግን አይሰፋም፡፡ እኔ ባገሬ መንገደኛ ሁሉ መሸብኝ ብሎ ሲጠለል ነው የማውቀው፡፡ እኔንም አቅፈው ደግፈው ያሳደሩኝ የማላውቃቸው የገጠር ሰዎች ነበሩ፡፡ እዚህ ግን እንዲያ የለም። የሰው ልጅ በየአስፋልቱ ተኝቶ ማየቱን ተላምደውታል፡፡ እኔም ያለኝ አማራጭ ከአንዱ ፌርማታ ስር ላስቲክ መከለል ነበር። ሁለታችንም እረሃብ ቢያዳክመንም የቀረችኝን ትንሽ ብር ለእለቱ በልቼ መጨረስ አልፈለኩም፡፡ ከሱቅ የተለያየ ነገር ገዝቼ በየመንገዱ እየተዘዋወርኩ መሸጥ ጀመርኩ፡፡ ለስቃይ ሆነ እንጅ ቆንጆ አድርጎ ነበር የፈጠረኝ፡፡ ገበያውን የሚያደራው ግን ካላቅሜ ልጅ አዝዬ መንከራተቴ ይመስለኛል፡፡ ብቻ ሁሉም እየጠሩ የሚፈልጉትንም የማይፈልጉትንም ይገዙኛል። እንዲህ እየዞርኩ በመነገድ ላይ እንዳለሁ ነው አንድ ሰው ለልጄም ለራሴም ደህንነት ባለው ሁኔታ እንድነግድ ቦታ በመስጠት የሚረዳኝ እንደሚፈልግልኝ ቃል የገባልኝ፡፡ ማንም ለማንም ይሰጣል ብዬ ስላልጠበኩ አላመንኩትም፡፡ ሰውየው ግን ቁምነገረኛ ነበር፡፡ በቀጠረኝ ቀን መጥቶ “እስቲ የአማራ ነጋዴ ሴቶች ማህበር የሚባል አለ ብለውኛል ልውሰድሽና የሚረዱሽ ካለ…”ሲናገር ለራሱም እርግጠኛ አይመስልም፡፡ ለዚህ ነው መሰል ሥራ እንዳያስፈታኝ እያሰብኩ በይሉኝታ የተከተልኩት። ግን ተሳስቼ ነበር፡፡ ያኑ እለት የሙያም የብድርም ድጋፍ እንደሚደርጉልኝ ቃል ገቡልኝ፡፡ መንገድ ላይ በሸጥኳትም ከልጄና ከእኔ ሆድ አትርፌ ትንሽ በቋጠርና ቤት መከራየት ችዬ ነበር፡፡ የተሰጠኝ የብድርና የሙያ ድጋፍ ግን ቤት ተከራይቼ የተለያዩ ነገሮችን እንድሰራ አበረታታኝ። እንጀራ ምግብ ባልትና ሁሉ አይቅረኝ አልኩ፡፡ ሃያ አራት ሰዓቱንም ሳልሸራርፍ ተጠቀምኩበት፡፡
በዚህ ላይ ተቀናቃኞቼ እንደሚሉኝ በመተት ባይሆንም ለገበያ ጥሩ እድል ያለኝ ይመስለኛል፡፡ የአማራ ነጋዴ ሴቶች ማህበርም በጥረቴ ተደሰተ መሰል ድጋፉን አበዛልኝ፡፡ በተለይ በሙያ አለመማሬ ጥፋት እንዳያመጣ አገዙኝ፡፡
“ቁልቁል ሲሄዱማ ሞልታል አዋራጅ እኛን የቸገረን የሚያዋጣው እንጅ!” ነበር ያለች ዘፋኟ መሬቱ ይቅለላትና አሁን ሳስበው ግን የተሳሳተች ይመስለኛል፡፡ ምክንያቱም ወደላይ ለመውጣት ለፈለገም አዋጭ እንደማያጣ አይቻለሁ። ቁም ነገሩ እኛ የምንይዘው አቅጣጫ ነው፡፡ እኔም ለመውጣት የማደርገውን ጥረት ስላዬ ነበር የክልሉ ጥቃቅንና አነስተኛ ተቋም እነሆ የመስሪያ ቦታ ያለኝ፡፡ እንኳን ዘንቦብሽ.. ነበር የሚባለው? እንኳን የቤት ኪራይ ሳልከፍል? ገቢዬ ሌላ ሆነ። የትናንቷ ጎዳና ተዳዳሪ ከሃያ በላይ ሰራተኛም ቀጠርኩ፡፡ ባልትናውም ሆቴሉም ጎን ለጎን አደጉ! በተለይ ልጀ ከተማይቱ አለኝ ከምትለው የግል ትምህርት ቤት መማር ጀመረ፡፡ በየጊዜው የሚሰጠኝ የሙያ ምክር ሳልማር ንቁ አድርጎኛል። ልጄም ነፍስ እያወቀ በሚችለው ሁሉ ይደግፈኝ ጀምሯል፡፡
ቢሆንም ይህን ባለ አምስት ኮኮብ ሆቴል ለመገንባት ቦታ ስጠይቅ ያመነኝ አልነበረም፡፡ “ደፋር ገጠሬ! በጭቃ የምትለቁጠው መሰላት እንዴ?” ያሉኝ እንደነበሩም በኋላ ሰምቻለሁ፡፡ እኔ ግን ጠንክሬ ገባፋሁበትና ጠየኩ፡፡ እነሱም እግዜር ይስጣቸው እንደሁሉም አክብረው የሚሟላውን አሟልቼ እንዳቀርብ በመጠየቅ ከእነሱም የሚገባውን አደረጉልኝ፡፡ እግዚአብሄር የሚጥሩትን ያግዛል፡፡ ይሄው ከግማሽ ሚሊየን ያነሰ ብድር ይዞ ሥራ ለመጀመርና ለምረቃ ተዘጋጅቷል፡፡ ከዚህ በላይ ትልቁ ድሌ ግን የባብዬ ምርቃት ነው። ከትናንት ወዲያ ከአዲስ አባባ ዩንቨርሲቲ ያውም በመዓረግ ተመርቋል፡፡ ጥህ ብቻም አይደል፣ የተመረቀበት ሕግ ይተገበር ዘንድ ታች ገጠር ድረስ ወርዶ እንደሚሰራ ቃል ገብቶልኛል፡፡ ይህን ሳስብ ነው እኔን የመሰሉ ብዙ ሴቶች እንዳይንገላቱ ትልቅ አስተዋጽኦ ማድረጌ የሚሰማኝና የሚያረካኝ፡፡
*   *   *
ደንግጨ እንደተነሳሁ ነበር መለባባስ የጀመርኩት፡፡ ይህን ያህል አረፍዳለሁ የሚል ግምት አልነበረኝም፡፡ በሃሳብ ስባዝን አድሬ ለካስ እስኪረፍድ ተኝቻለሁ፡፡ ጉድ ነው! ያች ጅል ልጇን ድራለች! ያለው ሰውዬ አይነት? እስቲ አሁን በራሴ ጉዳይ ላይ ማርፈድ! እየተበሳጨሁ ፈጥኜ ለበስኩ። ደግነቱ ልብስ አዘጋጅቻለሁ፡፡ ለነገሩ ምን አዘጋጃለሁ አዲስ አበባ ለልጄ ምርቃትና ለዚሁ ጉዳይ የሚያምር ሃበሻ ቀሚስ ከነጫማውና ጌጣጌጡ ገዝቼ ነው የመጣሁት፡፡ እናም አሁን በፍጥነት ጠለቅ ጠለቅ አድርጌ ወጣሁ፡፡ እውነትም ስደርስ አዳራሹ በሰው ተሞልቶ ነበር፡፡ ደግነቱ ባብየ አልቀደመኝም። ከውስጥ የቆየሁ ለማስመሰል ከጣርኩ በኋላ አዳራሽ ገባሁ፡፡ ገና ከመቀመጤ እንዲመርቁ የተጠሩት ባለስልጣን ስለመጡ እንድቀበል የሆቴሉ ሃላፊ ጠጋ ብሎ ሹክ አለኝና ወጣሁ። ቀድሜ ያየሁት ግን ባብየን ነበር፡፡ በገዋን ደምቆ በጓደኞቹ ታጅቦ እየገባ ነው፡፡ ሳየው አልቅሽ አልቅሽ የሚለኝ መጣ፡፡ እንዴት አምሮበታል! አባቱ ባህሪ የለውም እንጅ ቆንጅዬ ነበር፡፡ እሱ ግን ከሁለታችንም አዋጥቶ ልዩ ስራ ሆኗል፡፡ ሌላውን ጥዬ ሄጀ እቅፍ አደረኩት፡፡ ባለስልጣኑ በሌሎች እንግዶቼና በአማራ ነጋዴ ሴቶች ማህበር አመራሮች ተከበው ለምረቃ የተዘጋጀውን ሪቫን መቁረጥ ጀምረዋል፡፡ ይህን ተከትሎ እልልታው ደመቀ፡፡ እኔ ግን ባብዬ ላይ እንደተጠመጠምኩ ነኝ፡፡ እሱን እንዳቀፍኩ እልል ለማለት ብሞክርም የደስታ እምባዬ ከለከለኝ፡፡ እምባ የደስታ መግለጫ ይሆናል ለካ? አነባሁት፡፡

Read 1924 times