Tuesday, 14 April 2015 08:11

የአከራይን የገንዘብ ፍቅር በድማሚት--

Written by  ተአምር ተክለብርሃን
Rate this item
(4 votes)

      ተከራይ ሆይ፤ የአዲስ አበባ አከራይ ሱዳናዊ እየመሰልነው መብራትና ውሃ ለእኛ ለተከራዮች መሸጥ ከጀመረ ከራርሟል፡፡ የኢትዮጵያ ዋና ከተማ በሆነችው አዲስ አበባ፣ አንድ ሰው ቤት ሊከራይ ሲሄድ የመሬት ዋጋ የሚያህል ወርሃዊ ክፍያ ይጠየቃል። ታዲያ ተከራይ ከድንጋጤው ሲመለስ ሳልበላ ባድርስ በቤቴ ማን ያየኛል ይሁን ብሎ ቤቱን ሲከራይ ባለቤቶቹ ምንም እንዳይቀረው አድርገው ገንዘቡን አጥልለው ይወስዳሉ፡፡
አዲስ አበባ ላይ የተከራዩት ቤት ተጨማሪ የመብራትና የውሃ ክፍያ እንደሚያስጠይቅዎት እስካሁን ያውቃሉ ብዬ አገምታለሁ፡፡ እንደ ስለት ብር ከሌላ ገንዘብ ጋር እንዳይቀላቀል ይሆን እንዴ የቤት ኪራይ እንዲሁም የመብራትና የውሃ ክፍያን ለየብቻ የሚቀበሉት? ከዚህ በላይ የመክፈል አቅም የለኝም የሚሉ ከሆነ ቀላል ነው። አከራይዎ በመብራት፣ እርስዎ በሻማ መኖር ትጀምራላችሁ፡፡ ለነገሩ ይሄም ቢሆን ለአከራይ ሌላ የስራ እድል ይፈጥራል፡፡ ሻማ ከውጭ ይዞ መግባት አይቻልም ይሉና ለእርስዎ ብቻ ሻማ በእጥፍ ዋጋ መሸጥ ሊጀምሩ ይችላሉ፡፡ (በገዛ ቤታቸው ንግስናውን ማን ይወስድባቸዋል?)
አከራይ ሌላው ብቃቱ ምን መሰላችሁ? በፈለገው ሰዓት ከውጭ ሀገር ዘመድ ማፍራት መቻሉ ነው። የቤት ኪራይ ላይ ዳጎስ ያለ ጭማሪ ማድረግ ባማረው ጊዜ፣ ከውጭ ሀገር ከፈለገ ልጅ አሊያም ወንድም ያመጣል። የፈጠራ ማለት ነው፡፡ የሆነ ጊዜ ላይም “ወንድሜ coming soon” የሚል ፕሮፓጋንዳ ማሰራጨት ይጀምራል።  በተዘዋዋሪ የደረስዎ መረጃ ላይ እርምጃ ካልወሰዱ ወዲያው በቀጥታ ይደርስዎታል፡፡ ቤቱ ለወንድም ማረፊያ እንደሚፈለግ ይነገርዎታል፡፡
እርስዎ ከለቀቁ በኋላ እዚያች ቤት የሚገባው ግን የተባለው ወንድም አይደለም፡፡ ከእርስዎ የበለጠ መክፈል የሚችል፣ በደላላ የተገኘ ሌላ “ብራም” ተከራይ ነው፡፡ ዕድገት ሲመጣ ግላዊነት የሚያይል፣ማህበራዊነት እንደ ተከራይ ተክለ ሰውነት የሚቀጭጭ ይመስለኛል፡፡
ድሮ ድሮ አንድ ሰው በአጋጣሚ የሚያውቀውን ሰው ውይ ወንድሜ ቸገረው ብሎ ደባል ያደርገው ነበር አሉ፡፡ ዛሬ ዛሬ የቤት ኪራይ ሂሳብ ዝንፍ ያደረገ ተከራይ፣በባለቤቱና አጋሮቹ ተደብድቦ ሁሉ ሊባረር  ይችላል፡፡ ባለመብት ነዋ!
ምን እሱ ብቻ--- አብሮ መኖር ያመጣውን ትውውቅ የረሳ አከራይ፤ ተከራዬ እቃ ገዛ፣ ደሞዝ ጭማሪ አሊያም የሆነ ገንዘብ አገኘ ብሎ ሲያስብ ያለምንም ሃዘኔታ  ኪራይ ይጨምራል፡፡
“ዘመነ እኔ” ላይ፣ አንድ ግቢ ውስጥ አብረኸው የኖርከው ሁሉ ዘመድ ነው፡፡ ጎረቤት ደሞ-- ለችግርህ ደራሽ፣ ደስታህን ተካፋይ ብቻ አይደለም፡፡ ግዴታም ጭምር ያለበት ሁነኛ ሰው ማለት ነው። አሁን አንተ አንድ ግቢ አብረኸው ከምትኖረው አከራይህ ጋ የሚያገናኝህ “ለአምጪው እንዲከፈለው ህግ ያስገድዳል” የሚል የተፃፈበት የአከራይና የተከራይ ገንዘባዊ ግንኙነት ነው። በማንኛውም ሰአት አከራይህ የተሻለ ነገር ካገኘ በጨረታው አይገደድም።
ሌላው ለአከራዮች የሱዳን ዜጋ ሆነን እንደምንታያቸው የሚያረጋግጥልን ነገር---እንግዳ የሚባል እንዲመጣብህ አለመፈለጋቸው ነው። ዘመዶቻችን ሁሉ ከሀገር ውጪ ያሉ እየመሰላቸው ይሆን? ከሱዳን ኢትዮጵያ ትራንስፖርት ውድ ነው፤ አይመጡባቸውም--- ብለው ያስባሉ መሰል። ሱዳናዊ የኢተዮጵያን ቋንቋ እስኪለምድ፣ ጓደኛ አይዝም ብለውም ሳይደመድሙም አይቀሩም፡፡ እቤታቸው ብቻህን ኖረህ፣ ብቻህን እንድትወጣ ነው ህልማቸው፡፡
በተለይ የውሃ ጉዳይ ሃሳብ ውስጥ ስለሚከታቸው ቦንድ ገዝተን እየገደብን ያለነውን አባይን ጨምሮ የብዙ ወንዞች ባለቤት መሆናችንን ይዘነጉታል፡፡ ውሃውን ያለአግባብ በማፋሰስ ዕዳ ይከተናል በሚል -- ያውም በግልፅ በምትከፍለው ውሃ ላይ መብት አይሰጡህም። “በዘመነ እኔ”፣ ውሃ አስክሬን ማጠቢያ ነው፤ ለማንም አይነፈግም ይባላል። እንደኔ ነገረኛ የሆናችሁ ሰዎች፣እቺ አባባል አትጠፋችሁም። እስከ ወገብ አያያዙ ብዙ ጊዜ ስለተጠቀማችሁባት።
ተከራይ ሆነው ጆርዳና ሾ ከተመለከቱ ሆዳምና ጥሩ ምግብ የሚበሉ መስሎ ስለሚሰማቸው፣ እንዴት በለጠኝ በሚል ክራይ ሊጨምርብዎ አሊያም ሊያስወጣዎ ስለሚችል--- እባክዎ የቴሌቪዥንዎን ድምፅ ይቀንሱ፡፡
አቤቱ ላንተ ስልጣን የባቢሎንን ቋንቋ የለያየህ አምላክ ሆይ! እባክህን የተከራዮችን ስቃይ ተመልከትና፣ የአከራዮችን የገንዘብ ፍቅር በድማሚት ብትንትን አድርግልን። እኛ ፀሎታችንን እንደ ዓባይ ግድብ  አጠንክረን እናደርሳለን። አሜን! አሜን! አሜን!  

Read 1671 times