Monday, 06 April 2015 08:34

የፖለቲካ ጥግ

Written by 
Rate this item
(7 votes)

ወፍራም ደሞዝ ተከፋይ የአፍሪካ ፕሬዚዳንቶች!!

የደቡብ አፍሪካው ፕሬዚዳንት ጃኮብ ዙማ መደበኛ ትምህርት እንዳልተከታተሉ “አፍሪካ ክራድል” የተባለው ድረገፅ ሰሞኑን ይፋ ያደረገ ሲሆን “7 ቀለም ያልዘለቃቸው የአፍሪካ ፕሬዚዳንቶች” በሚል ባወጣው ዝርዝር ውስጥ ዙማን በአንደኝነት ነው ያስቀመጣቸው፡፡  ሰውየው ያልተማሩ መሆናቸው እምብዛም አልጐዳቸው፡፡ እንደውም ሳይጠቅማቸው አልቀረም፡፡  የዙማ ዓመታዊ ገቢ 270ሺ ዶላር (5ሚ.400ሺ ብር ገደማ) ሲሆን በአሁኑ ሰዓት በአፍሪካ ከፍተኛ ተከፋይ  ፕሬዚዳንት ናቸው፡፡ ዙማ ከዓለማችን 10 ከፍተኛ (Top 10) ተከፋይ ፕሬዚዳንቶች ውስጥ አንዱ ናቸው፡፡
አልጄሪያን እ.ኤ.አ ከ1999 ጀምሮ በመምራት የአገሪቱ አምስተኛ ፕሬዚዳንት የሆኑት አብደላዚዝ ቡቴፍሊካ ዓመታዊ ደሞዛቸው 168ሺ ዶላር ነው፡፡ ቡቴፍሊካ ሁለተኛው፤ ከፍተኛ ተከፋይ የአፍሪካ ፕሬዚዳንት ናቸው፡፡
ኡሁሩ ሙይጋይ ኬንያታ አራተኛው የኬንያ ፕሬዚዳንት ሲሆኑ ሥልጣን የተቆናጠጡት እ.ኤ.አ በ2013 ዓ.ም ነበር፡፡ ኬንያታ በዓመት 132ሺ ዶላር ያገኛሉ፡፡ በ2014 ዓ.ም በወር ይከፈላቸው የነበረውን 14ሺ ዶላር ወደ 11ሺ ዶላር እንዲቀነስ በማድረግ አርአያ ለመሆን ሞክረዋል፡፡ እንዲያም ሆኖ ግን ሶስተኛው የአፍሪካ ከፍተኛ ተከፋይ ፕሬዚዳንት ከመሆን ያገዳቸው ነገር የለም፡፡
ኮሞሮስን ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ በመምራት ላይ የሚገኙት አይኪሊሎ ዲሆይኒኔ፤ በ115ሺ ዶላር ዓመታዊ ገቢ 4ኛው ከፍተኛ ተከፋይ ፕሬዚዳንት ሆነዋል፡፡ ሰውየው ስልጣን ሲይዙ ሙስናን ከአገሪቱ ለማጥፋት ቃል እንደገቡ ተዘግቧል፡፡ ዲሆይኒኔ ያጠኑት ፋርማሲስትነት ነው፡፡
ዴኒስ ሳሶ ንግዩሶ፤ ከ1997 ዓ.ም ጀምሮ የኮንጎ ሪፐብሊክ ፕሬዚዳንት በመሆን አገሪቱን  እየመሩ ይገኛሉ፡፡ በቅርቡ  “ግሎባል ዊትነስ”  እንደዘገበው፤ የፕሬዚዳንቱ ልጅ ዴኒስ ክሪስትል የአንድ ወር የግል ፍጆታ፣ የ80ሺ የኮንጎ ህፃናትን የኩፍኝ መከላከያ ክትባት ወጪ ይሸፍናል፡፡ የኮንጐው መሪ ዓመታዊ ክፍያ 110ሺ ዶላር ሲሆን 5ኛው ከፍተኛ ተከፋይ የአፍሪካ ፕሬዚዳንት ናቸው፡፡

Read 3161 times