Monday, 06 April 2015 08:34

ሆሣዕና በአርያም፤ ሆሣዕና … ሆሣዕና… ሆሣዕና…!!

Written by  በዲ/ን ክንፈ ገብርኤል
Rate this item
(2 votes)

    ሆሣዕና ቃሉ የዕብራይስጥ ሲሆን ትርጓሜውም “አሁን አድን” ማለት ነው፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እምነትና ሥርዓት ከፋሲካ/ከትንሳኤ በፊት ያለው እሑድ “የሆሣዕና እሑድ” በመባል ይታወቃል፡፡ በዚህ ዕለትም በቤተ ክርስቲያናችን የሚዘመረው መዝሙር፣ ማኅሌቱ፣ ቅዳሴው፣ ምንባቡና ማንኛውም አገልግሎት ሁሉ ዕለቱን በታላቅና እጅግ ደማቅ በሆነ መንፈሳዊ ሥነ - ሥርዓት የሚዘከርበት፣ የሚታሰብበት ነው፡፡ ይህ በዓል እጅግ በደማቅና ልብን በሚመስጥ መንፈሳዊ ሥነ-ሥርዓትና ድምቀት ከሚከበርባቸው ቅዱሳን ገዳማትና መካናት መካከል የአክሱሟ ርዕሰ አድባራት ጽዮን ማርያም እና በዚህ በአዲስ አበባችን የእንጦጦ ማርያም በዋናነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡
ሆሣዕና የእግዚአብሔር ልጅ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ በአህያ ውርንጭላ ላይ ሆኖ ወደ ኢየሩሳሌም በታላቅ ድል የገባበት ዕለት መታሰቢያ ነው፡፡ አስቀድሞ በቅዱስ መጽሐፍ በነቢዩ ዘካርያስ፡- “ለጽዮን ልጅ እነሆ ንጉሥሽ የዋህ ሆኖ በአህያ ላይና በአህያይቱ ግልገል በውርንጭላይቱ ላይ ተቀምጦ ወደ አንቺ ይመጣል በሉአት፡፡” ተብሎ የተነገረው ትንቢት ይፈጸም ዘንድ ይህ ሆነ፡፡ ጌታ፣ አምላክና መድኀኒት የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስም በአህያ ውርንጭላ ላይ ሆኖ ወደ ኢየሩሳሌም በድል ገባ፡፡
እንደ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት፤ በብሉይ ኪዳን ዘመን የእግዚአብሔር ነቢያት መልካም የሆነ ትንቢት ከፈጣሪ ዘንድ ይዘው ሲመጡና መጪው ጊዜ ሰላምና ብልጽግና የሞላበት መሆኑን ለማብሰር በአህያ ላይ ተቀምጠው ነበር እየዞሩ ትንቢት የሚናገሩት፡፡ ዘመኑ የጦርነት፣ የረሃብ፣ የግዞት ዘመን ከሆነ ደግሞ በፈረስ ላይ ተቀምጠው ትንቢት ይናገሩ እንደነበረ ከብሉይ ኪዳን መጻሕፍት በመጥቀስ፡- “እግዚእነ ወመድኃኒነ ኢየሱስ፣ የሰላም አለቃ ለኢየሩሳሌምና ለዓለም ሁሉ ሰላምንና ፍቅርን ያውጅ ዘንድ በአህያ ላይ ተቀምጦ ወደ ኢየሩሳሌም ገብቷል፡፡” ሲሉ ያመሠጥራሉ።
የዋህና ትሑት ሆኖ በአህያው ውርንጭላ ላይ በታላቅ ድልና ክብር ወደ ኢየሩሳሌም የገባው የዓለም መድኃኒት ኢየሱስ ክርስቶስ፣ ለታላቅ ክብሩና ማዳኑ ሰዎች ሁሉ ኢየሱስ በሚያልፍበት መንገድ ልብሳቸውን፣ የዘንባባ፣ የወይራና የዛፍ ቅርንጫፎች በማንጠፍ ለክብር ጌታ ምስጋናን፣ ውዳሴን አቀረቡለት፡፡ በመቅደስም ሳለ ሕፃናቱ፡- “ሆሣዕና ለዳዊት ልጅ በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው፣ ሆሣዕና በአርያም!” እያሉ በታላቅ ድምፅ እየጮኹ አመሰገኑት፡፡ አስቀድሞም በንጉሥ ዳዊት አፍ እንደተነገረው፡- “ከሕፃናትና ከሚጠቡት አፍ ምስጋናን ለራስህ አዘጋጀህ፡፡” የሚለው ትንቢትም ይፈጸም ዘንድ ይህ ሆነ፡፡ የቤተክርስቲናችን አባት የሆነው ሊቁ አባ ጎርጎሪዮስም በቅዳሴው፡-
የካህናት አለቃ ወደ መጋረጃ ውስጥ በገባ ጊዜ በጸሎት ቤት የተደረገውን ድንቅ ነገር ታዩ ዘንድ ኑ፡፡ ሁሉም መለኮትን የምትሸሽግ ሕሊናትንም የምትሰውር ናት ይሏታል፡፡ የአጋዕዝትና የመናፍስት ጌታ በተዋረደ አህያ ውርንጭላ ተቀምጦ ወደርስዋ ገባ፡፡ በእግዚአብሔር ስም የሚመጣ ብሩክ ነው፡፡ አንተም የአማልክት የእስራኤልም ንጉሥ እግዚአብሔር ብሩክ ነህ እያሉ ለሚያመሰግኑ ሕፃናት ሁሉ ጌትነቱን አሳየ፡፡ ከመድኀኒትነቱ የተነሣ ከቤቱ መሰረት ሳይናወጥ ከልዑል መንበሩ ወርዶ ጸጋንና ኃይልን አሳየ፡፡ ሆሣዕና በአርያም፣ ሆሣዕና በአርያም፣ ሆሣዕና በአርያም፡፡ ብሎ እንዳመሰገነ፡፡
የክብርን ጌታ፣ የሕይወትን ራስ ሆሣዕና … ሆሣዕና… ሆሣዕና በአርያም፣ በእግዚአብሔር ስም የሚመጣ ብሩክ ነው! እያሉ በአናታቸው ጀርባና እቅፍ ያሉ ሕፃናትና የቢታንያ ድንጋዮች ሁሉ ሳይቀሩ በታላቅ ደስታና ሐሴት ሆነው መድኃኒት፣ አዳኝና ቤዛ ለሆነው ለኢየሱስ ክርስቶስ በአንድ ድምፅ በንጹሕ አንደበት ዘመሩለት፣ አመሰገኑት። ምድርምና ሞላዋ፣ ውቅያኖሶች፣ ባሕሮችና ተራሮች፣ ሰማይ፣ ሰማየ ሰማያት፣ ከሰማይም በላይ ያለ ሰማይ፣ የእግዚአብሔር ፍጥረታት ሁሉ በዚህ ልዩ የህፃናት የምስጋና ጥዑም ዜማ ተሞሉ፣ በደስታም እንደ እንቦሳ ዘለሉ፡፡
በዚህ ልዩ ሰማያዊ ቅኔ የሰማይ ሰራዊት፡- መላዕክት፣ ሊቃናት፣ አጋእዝትና መናብርት ሁሉ በአንድነት በሐሴትና በደስታ ታደሙ፡፡ በዚህ ታላቅ የምስጋና፣ የፍቅር ዜማ ምድርም በሐሴትና በደስታ ተናወጠች፣ መሰረቶቿም ተነቃነቁ፡፡ የፍቅር አምላክ፣ የሰማይና የምድር ሁሉ ፈጣሪ ዝቅ ብሎ፣ የዋህና ትሑትም ሆኖ በአህያ ውርንጫ ላይ ሆኖ በግልጽ መጥቷል፣ ተገልጧል፡፡
ወንጌላዊው ማቴዎስ በወንጌሉ እንደጻፈልን፡- ኢየሱስ በአህያ ላይ ተቀምጦ ወደ ኢየሩሳሌም በቀረበ ጊዜ መላው ከተማ ይህ ማነው ብሎ ተናወጠ፡፡ ይለናል፡፡ ዛሬም ይህ ማነው ለሚሉ፡- ሊቀ ሐዋርያ ቅዱስ ጴጥሮስ እንደተናገረ፣ እንዲህ እንመሰክራን፡- “እርሱ ክርስቶስ፣ መሢሕ፣ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ነው፡፡” በእውነትም እርሱ፡- “የሕያው የእግዚአብሔር ልጅ፣ ድንቅ፣ መካር፣ ኃያል አምላክ፣ የዘላለም አባት የሰላም አለቃ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው!!”
በዕለተ ሆሣዕና ሕፃናት፣ ሕዝቡና የተከተሉት ሁሉ ቃላት በማይገልጸው ደስታና ሐሴት ውስጥ ሲዘምሩና ሲያመሰግኑ፣ ክርስቶስ ኢየሱስ ግን ቅድስቲቱን ከተማ ኢየሩሳሌም በበደሏና በኃጢአቷ ምክንያት ከእግዚአብሔር ዘንድ የተቀጠረላትን የመዓት፣ የጥፋትና የመፍረስ ቀን አሻግሮ አይቶ አለቀሰላት፣ እንዲህ ሲል በማለት ይለናል ሐኪምና ታሪክ ጸሐፊው፣ ወንጌላዊው ቅዱስ ሉቃስ፡-
“ለሰላምሽ የሚሆነውን በዚህ ቀን አንቺስ ብታውቂ አሁን ግን ከዓይንሽ ተሰውሮአል…” የሰላሟን አምላክ፣ የሕይወትን ራስ የገፋችው፣ አሳልፋ በመስጠትም የሰቀለችው ኢየሩሳሌም፤ ጌታ እንደተናገረ ቅጥሮቿ ፈርሰው፣ ሕዝቧ እርስ በርሱ ተራርዶ፣ ልጆቿም ያለ እናት ተበትነው፣ እንዲያ የሚያከብሩትና የሚፈሩት፣ የሚኮሩበትና የሚኮፈሱበት መቅደሳቸውም በአሕዛብ ተረግጦና ተዋርዶ፣ ድንጋይ በድንጋይ ሳይቀር በፈራረሰበት፣ ህዝቦቿም በታላቅ ሀፍረትና ውርደት ተሸማቀው፣ በዓለም ሁሉ ዙሪያ እንደ ጨው ዘር ተበትነው፣ ለ፲፰፻/ከአንድ ሺህ ስምንት መቶ ዓመት በላይ እስራኤል የምትባል ሀገር ከምድረ ገጽና ከካርታ ላይ ከጠፋች በኋላ ነበር እንደ ገና እንደ አዲስ ሙሽራ ጎጆ በመውጣት እ.ኤ.አ በ1948 ዓ.ም ዳግም ዓለም ሁሉ እንደ ሀገር የተቀበላት፡፡
ይሁን እንጂ ያቺ ምድር ዛሬም ቢሆን መሽቶ በነጋ ቁጥር የጥይት፣ የባሩድና የሮኬት አረር ጭስን የምትታጠን፣ ፍጹም ሰላምና መረጋጋት የራቃት የዓለም ሁሉ ዜና መክፈቻና መነጋገሪያ፣ የጣርና የጭንቅ ምድር እንደሆነች ይኸው አለች። የእርሷ ሰላም ማጣት የዓለም ሀገራት ሁሉ የሚታወኩበትና የሚጨነቁበት፣ የሌት ተቀን ጉዳያቸው እንደሆነ ዘወትር እየሰማን፣ እያየን ነው፡፡
የእስራኤልና የዐረቡ ዓለም ፍጥጫ፣ የፍልስጤማውን የልዑላዊነትና የነፃነት ጥያቄ፣ በአካባቢው ሀገራት የሚገኙ ISIS፣ የሃማስና የሂዝቦላ ጽንፈኞች ታጣቂ ኃይላት፣ የኢራን የኑክሌየር ባለቤትነት የጦፈ ክርክር፣ አገራት የጅምላ ጨራሽ ኬሚካልና ባይሎጂካል መሳሪያዎች የማምረት ሽር ጉድ በአሜሪካና በምዕራባውያኑ ሀገራት መካከል ያነገሰው ውጥረትና ጥርጣሬ፣ ለእስራኤል ታላቅ ስጋት ነው በሚል አሜሪካና የምዕራቡ ዓለም ከኢራንና ከዐረብ አገራት ጋር የገቡበት ውዝግብና ክስ… ከአፍሪካ እስከ አሜሪካ፣ ከኤዥያ እስከ አውስትራሊያ፣ ከአውሮፓ እስከ ሩሲያ፣ ከቻይና እስከ ፓሲፊክ ሀገራት ድረስ የተዘረጋ ትልቅ የዓለማችን የመነጋገሪያ አጀንዳ፣ መፍትሔ ያጣ አንዴ ቦግ አንዴ እልም እያለ ያስቸገረ፣ የምድሪቱ የፖለቲካ የተዳፈነ ፍም፣ የሚንቦገቦግ እሳት እንደሆነ ቀጥሏል፡፡
እናም የዓለማችን የታሪክ ሒደት የሚነግረን ሀቅ በእውነትም የእስራኤል ሰላም ያለው በገፋችው በሰላሟ ጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ እጅ ነውና ወደ እርሱ ፊቷን እስካላዞረች ድረስ እንደታወከች፣ እንደተናወጠችና ለዓለም ሁሉ ጭንቀትና ውጥረት እንደሆነች ትዘልቃለች። ዛሬም እንደ አገረ እስራኤል ሁሉ በዘመናችን ሰላም የሁሉም ሰው አንገብጋቢ ጥያቄ ሆኗል። ሰላም በቤተሰብ፣ ሰላም በሀገራት፣ ሰላም በመንግስታት፣ ሰላም በባልና ሚስት፣ ሰላም በአብያተ ክርስቲያናት እና በሃይማኖት ተቋማት፣ ሰላም በሁሉም ስፍራ በሁሉ ዘንድ በመብራት የምትፈለግ ዕንቁ ሆናለች፡፡ ስለሆነም ሀገራት ከፍተኛ ወጪ የሚያወጡት ለውስጥ ሰላማቸው፣ ጸጥታና የደህንነት ጉዳያቸው ከሆነ ውሎ አድሯል፡፡
ዓለማችን በተደጋጋሚ ስለ ሰላም የዘንባባ ዝንጣፊን በማወዛወዝ ዘምራለች፣ ስለ ሰላምም ሲባል ነጫጭ ርግቦችን በሰማይ ላይ ለቃለች። ግን ዓለማችን የተመኘችው ሰላም ዛሬም የሰማይ ያህል እንደራቃትና እንደሸሻት ነው፡፡ በውስጣቸው ሰይፍና ጠብ ያለባቸው ሀገራትና ሰዎች በአፋቸው ሰላም ሰላም በማለት ቢሰብኩም የሰላሙ አለቃ ኢየሱስ ክርስቶስ ከልባቸው ዙፋን ተሰዷልና ሰላምን በተግባር ሊያረጋግጡ፣ ዕውን ሊያደርጉት አልቻሉም ወይም አልተቻላቸውም፡፡
የጥበብና የሕይወት ምንጭ የሆነው መጽሐፍ ቅዱስ ግን ለምድራችን፣ ለዓለም፣ ለሀገራትና ለሰዎች ሁሉ ሰላምና እረፍት መፍትሔው የሰላም አለቃ የሆነው የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ክርስቶስ ኢየሱስ ነው ይለናል፡፡ ኢየሱስም በወንጌል፡- ሰላምን እተውላችኋለሁ፣ ሰላሜን እሰጣችኋለሁ፣ እኔ የምሰጣችሁ ሰላም ዓለም እንደሚሰጥ አይደለም፡፡ በማለት ለደቀመዛሙርቱ ነግሮአቸዋል፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም ለኤፌሶን ክርስቲያን በጻፈላቸው መልዕክቱ፡- እርሱ ሰላማችን ነውና! እንዲል፡፡
በመጨረሻም በበዓለ ሆሣዕና በቤተ ክርስቲያን፣ አባቶቻችን ዘንድ ተባርኮ በሚሰጠን፣ በግንባራችን በእጆቻችን በምናስረው የዘንባባ ዝንጣፊ ስለ ሰላም የምንዘምርበት፣ ፍቅር የምናጸናበት ታላቅና የተቀደሰ በዓል መታሰቢያ ምልክት ነው፡፡ በዚህ ቀን የሁሉ አምላክ፣ ጌታና መድኃኒት የሆነው አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የዋህና ትሑት ሆኖ፣ ራሱን ዝቅ አድርጎ ለሰው ልጆች ሁሉ ፍቅርን እንዳሳየ፣ ሰላምን እንዳበሰረ ኹሉ ሕዝበ ክርስቲያን ሁላችንም ለሰው ልጆች ሁሉ ሰላምን የምንሰብክ፣ ፍቅርን በተግባር የምንገልጽበት መልካም የሆነ መንፈሳዊ ሕይወት ይኖረን ዘንድ የፍቅር ቃል ኪዳናችንን የምናድስበት የሰላም፣ የፍቅር፣ የምስጋ፣ የውዳሴ ዕለት ነው - በዓለ ሆሣዕና!!
ሆሣዕና በአርያም! ሆሣዕና ለወልደ ዳዊት! ሰላም በምድራችን ይሁን!! 

Read 5493 times