Monday, 06 April 2015 08:26

“የጥበብ ሆቴል” ንግድ ስንት ጭንጋፍ ጥበብ አስታቅፎን ይሆን?

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

      የዚህን ሚሲዮናዊ ታሪክ ሳነብ ወደ ዘመኔ እና ወደ እኔ ተተረጎመልኝ፡፡ እንዴት? እንጃ!!...
…ሚሲዮናዊው ክራፕፍ ይሰኛል፡፡ የChurch Missionary Society ተልዕኮ ተቀብሎ፤ በኢትዮጵያ የዕምነት “ተሃድሶ” ለማምጣት ከሌሎች ሁለት ሚሲዮናውያን ጋር ወደዚህ እንደመጣ ይነገራል፡፡ ታዲያ ክራፕፍ ካተኮረባቸውና ከሚተቻቸው የኛ ጉዳዮች ውስጥ የመሸበት እንግዳ ማሳደር አንዱ ነበር፡፡ “ምዕንተ ማርያም” ብለው ማደሪያ ለሚሹ መንገደኞች መጠጊያ የመስጠት ባህልን፤ የሆቴል ኢንዱስትሪ እንዳይስፋፋ ያደረገ የኢኮኖሚ ዕድገት ዕክል ነው በማለት በማስታወሻው ላይ አስፍሮ ነበር፡፡
የሚገርመው ከዚህ በኋላ ያለው የክራፕፍ ታሪክ ነው። የራስ ወርቅ አድማሴ “ባሕልና ልማት፤ ምንነታቸውና ትስስራቸው” በሚል ጥናት ላይ እንዳሰፈሩት፤ ክራፕፍ የኢትዮጵያ ቆይታውን ጨርሶ ወደ ምፅዋ ወደብ በሚጓዝበት ወቅት የመዘረፍ አደጋ ይደርስበታል፡፡ ለህይወቱ ማቆያ ዋስትና የሆነው ያ የጠላው “ምዕንተ ማሪያም አሳድሩኝ” የሚለው ነባር ባህላችን ነበር፡፡ “ምዕንተ ማርያም አሳድሩኝ” እያነበነበ፣ ለኢትዮጵያ ባህል ያለውን ንቀትና ማስታወሻ ደብተሩን እንደጨበጠ ምፅዋ ገባ አሉ፡፡
ይሄ ታሪክ ከዚህ ዘመንና ከእኔ ጋር እንዴት ተተረጎመልኝ?--- “ምዕንተ ማርያም አሳድሩኝ” የሚባለው የግድ ሥጋ ሲራብና ሲደክም ብቻ አይደለም፡፡ የነፍስ መራብና መድከምም በየሰው “ደጅ” ያንከራትታል፡፡ በአንድ ወቅት የእኔ ነፍስ የቆሎ ተማሪ ቁመናና ዋስትና ነበራት፡፡ የጥበብ ቁራሻቸው ያደነደነኝ፤ የደነበቁልኝ ያረሰረሰኝ ነኝ፡፡ ደምሴ ፅጌ፣ ስብሐት ገብረእግዚአብሔር፣ አብደላ ዕዝራ፣ ዶ/ር ፍቃደ አዘዘ፣ አስፋው ዳምጤ… ፍካት ወጣት ደራሲያን ማኅበር ውስጥ ሳለሁ ጊዜና ጉልበታቸው ወደ እኔ ያለፈ ሰዎች ናቸው፡፡ አንዳንዶቹም ሳይንቁኝ እንደወገዝ በሬ አብረውኝ ተጣምደው፣ በጊዜ ሂደት ጥበባዊ ተሞክሯቸውን ያጋቡብኝ ባለውለታዎቼ ናቸው፡፡
ወቅቱን በደንብ አላስታውሰውም፡፡ ብቻ እኔ፣ ደምሴ ፅጌና ክብሩ ክፍሌ አምባሳደር መናፈሻ ተቀምጠን እናወጋለን። እኔ ደምሴን ለማግኘት እንዴት ወደሱ እንደሄድኩ እያወጋሁ ነው፡፡
ደምሴ በመሐል፤ “እኔ ነኝ ወዳንተ የመጣሁት” አለኝ።
“ኧረ እኔ ነኝ” እያልኩ በወቅቱ ውስጠ ምስጢሩ ሳይገባኝ ተሟገትኩ፡፡ በኋላ ላይ ሳስበው ግን እርሱ ትክክል ነበር፡፡ እኔ “ጉርባውን” ሳይንቀኝ ማቅረቡ ወደ እኔ መምጣቱ ነበር፡፡
ይሄ ዘመንና እኔስ? …
… ይሄ ዘመንና እኔ በክራፕፍአዊ አስተሳሰብ ተተብትበናል፡፡ “ምዕንተ ማሪያም” ያሉ የጥበብ ተጠራሟቾች ላይ ቤታችንን ዘግተናል፡፡ ሆቴላዊ መንፈስ አስፍነናል፡፡ በነፃ ተገልግለን፣ በነፃ የማገልገል ወርተራችን ላይ “ወገቤን” ብለናል፡፡ የጥበብን “መባ” ለገንዘብ ለውጠን አርክሰናል፡፡ በእኛ ላይ ያልሆነውን ሁሉ አድርገናል፡፡
… ረቂቅ  አምጥቶ የአርትኦት ሥራ እንዳከናወንለት ከሚጠይቀኝ ሰው ጋር በገንዘብ ስደራደር ዘወትር ያመኛል፡፡ ያለክፍያ የሰበሰብኩትን እየቸረቸርኩ እንደሆነ ይሰማኛል፡፡ ግን ደግሞ ኑሮ ስንዝር ጥርሱን ገላዬ ላይ ቀብቅቧል፡፡ የገዛ ጉልበቴንና ጊዜዬን ተመፅዋች አድርጎኛል፡፡ ኑሮ ሲከብድ መጀመሪያ የሚደፈጥጠው ታማኝነትና ሰብአዊነትን እንደሆነ ከእኔና ከጊዜዬ እንድማር አድርጎኛል…
በቀድሞ ጊዜ ግን እንዲህ እንዳልሆነ እንጥፍጣፊው የደረሰኝ እኔ እመሰክራለሁ፡፡ ጊዜ እና ጉልበት እንደ እንቅብና ሰፌድ ከወዲያ ደራሲ ቤት፤ እወዲህ አርታኢ ቤት ይመላለሱ ነበር፡፡ ክቡር ዶክተር ሀዲስ ዓለማየሁ አንድ ረቂቅ ልቦለድ አንብበው አስተያየት የሰጡበት የእጅ ፅሁፋቸው እኔ ዘንድ አለ፡፡ ልቦለዱ የደራሲ እና ሐያሲ አስፋው ዳምጤ “አንድ ለአምስት” ነው፡፡ በየካቲት 17 ቀን 1978 ዓ.ም የተፃፈው ደብዳቤ እንዲህ ይላል፡-
“ወዳጄ አቶ አስፋው ዳምጤ፣
’አንድ ለአምስት’ በተባለ ስም ሳይመህ የጻፍኸው ልብ-ወለድ ድርሰት ደስ ደስ እያለኝና ሌላ ስራዬን አስትቶ እየሳበኝ ባጭር ጊዜ አንብቤ ጨረስሁት፡፡ አስተያየቴን ከማመልከቴ አስቀድሜ፣ ከመታተሙ በፊት እንዳነብበው ፈቃድህ ስለሆነ፣ እውነተኛ ምስጋናየን ላቀርብልህ እወዳለሁ፡፡ …”
ክቡር ዶ/ር ሀዲስ፤ 455 ገፆች ያሉትን ልቦለድ አንብበወ ገንቢ አስተያየት የሰጡት እንደ እኛ ዘመን ኪስና ልብስ አይተው አልነበረም፡፡ ነፍስና መንፈስ እንጂ፡፡ በዚህ ዘመን ሥነ ፅሑፍ ውስጥ “እንዘፍ” የበዛው ባለመደጋገፍ ሳይሆን ይቀራል?
“ሀዲስ” የበዓሉ ግርማ ልቦለድ ነው፡፡ በመጀመሪ “የህሊና ደወል” በሚል ርዕስ የታተመ ቢሆንም በዓሉ የቀረው ነገር እንዳለው ስለተስማሙ ዳግም ጻፈው። በፃፈበት ፍጥነት ወደ ማተሚያ ቤት ቢሰድደው ኖሮ አሁን ያለውን መልክ ባልያዘ ነበር፡፡ በዓሉ ግን ለሶስት ሰዎች ሰጠ፡፡ ለአብዱራህማን ሙዘይን፣ ለአስፋው ዳምጤ እና ለስብሐት ገብረእግዚአብሔር። ውይይት የተካሄደው አብዱራህማን ቢሮ ውስጥ ነበር፡፡ ከሦስቱ ሰዎች ብዙ አስተያየቶች ጎረፉ፡፡ በዓሉ አስተያቶቹን ለመቀበል አላመነታም ነበርና “ሀዲስ”ን ድጋሚ ፃፈው፡፡ አሁን ያለው ልጨኛ ሥራ በመደጋገፍ ተወለደ፡፡
ስብሐት ነገሮኝ ከጋሽ አስፋው እንዳረጋገጥኩት ከሆነ “ሀዲስ” ውስጥ ያሉት አቶ ጣሴ ደጉ የተፈጠሩት በዚያ የበዓሉ አጋዥ ቡድን ነበር፡፡ ሀዲስ ሳህሌ የተሰኘው ዋና ገፀ ባህርይ ያለ ጣሴ እርቃኑን መሸፈኛ እራፊ ያጣ ግንፍልተኛ ሆኖ ይቀር ነበር፡፡ አቶ ጣሴ የሀዲስ ሳህሌ መጪ ህይወት መጠቆሚያ ብቻ ሳይሆኑ መነሻውን አመላካች ጭምር ናቸው። አቶ ጣሴ እንደ ሀዲስ ሳህሌ ሁሉ የማስተማር ተልዕኳቸውን በአንድ ዓመት ትልም ገድበው ወደ ሱጴ ከተማ የመጡ መምህር ነበሩ፡፡ አቶ ጣሴ እንደ ሀዲስ ሳህሌ ሁሉ ውጥንቅጡን የትምህርት ሁናቴ ለማደራጀት ወጣታዊ ግንፍልታ ግድ ያላቸውም ነበሩ። ታዲያ ምን ሆነ? አቶ ጣሴ ሰላሳ ዓመታት ሙሉ እስከ አንገታቸው ድረስ በአረንቋ ተውጠው ወደ መጥፊያቸው የተቃረቡ የሀዲስ ሳህሌ መጪ ህይወት መሆናቸው ታየ፡፡ ፍርሃት! አቶ ጣሴ እና አብዮቱ ይሄን የሀዲስ ሳህሌን መጪ የሰላሳ ዓመት አይቀሬ ህይወት ጎምደው ድንገተኛ መፍትሄ አመጡ፡፡ ሁሉም ነገር በኃይል ባይበጣጠስ ኖሮ ሀዲስ ሳህሌና ጣሴ ደጉ የዳግም ልደት ውጤት ሆነው በእሽክርክሪት ጢንቢራው የዞረ መፍትሄ አልባ ትግል ያካሂዱ ነበር፡፡
ታዲያስ? የዚያ ዘመን የጊዜ ልግስና “ሀዲስ”ን ከአካለ ስንኩልነት አልታደገውም? የእኔ ዘመን ክራፕፍአዊ “የጥበብ ሆቴል” ንግድ ስንት ጭንጋፍ ጥበብ አስታቅፎን ይሆን? …
… ደራሲ ኃይለመለኮት መዋዕል ወደ ትግርኛ የመለሰው የሼክስፒር ተውኔት ነበረው፡፡ ይሄን ተውኔት ዘወትር ሐሙስ ይሁን አርብ ለሎሬት ፀጋዬ ገብረመድህን ያነብለት ነበር፡፡ ጸጋዬ “ኮ ትግሪኛ አይችልም፤ ነገር ግን ወጣቱና ፍሬው ያልታየው ደራሲ ኃይለ መለኮት መደመጥ ስለነበረበት በፕሮግራም ጊዜውን ሰውቶ ይሰማው ነበር፡፡ በመጨረሻ የሰጠው አስተያየት ለዛሬው ኃይለመለኮት መሰረት የጣለ ሆነ፡፡
“አንተ ፀሐፌ ተውኔት ሳትሆን የልቦለድ ደራሲ ነህ”
ታዲያስ? የዚያ ዘመን የጊዜ ልግስና ኃይለመለኮትን ከከንቱ የበረሀ ላይ ጉዞ አልታደገውም? እኛስ እንደ ሙሴ እርሱን እየተከተልን አርባ ዓመት ሙሉ አንድ ተራራ ስንዞር መኖራችንም አልነበር? የእኔ ዘመን ክራፕፍአዊ “የጥበብ ሆቴል” ንግድ ስንት አላስፈላጊ ጉዞ፣ ስንት ጥማት፣ ስንት እንግልት .. ጨምሮብን ይሆን?
አንድ ወጣት ፀሐፌ ተውኔት ደግሞ አዲስ ቴአትር መክፈቻ ላይ ሎሬት ፀጋዬ ገብረመድህን እንዲገኝለት ጋበዘው አሉ፡፡ ጸጋዬ አልቀረም፤ ቴአትሩ ሲያልቅም ምንም አላለም፡፡ ወደ ቤቱ ለመሄድ ከቴአትር ቤቱ ግቢ ሲወጣ ወጣቱ ፀሐፌ ተውኔት ከኋላ እየሮጠ ደረሰበት፡-
“ጋሽ ፀጋዬ ቴአትሬን እንዴት አየኸው?”
ፀጋዬ ብስጭት ብሎ በመዞር እንዲህ አለው አሉ፡
“‘እንትንሽን’፣ መድረክ ጥግ “እንትን’ነው ያልሽው”
ወጣቱ ፀሐፌ ተውኔት ቢሸማቀቅም አልተኮላሸም። እንደውም በእልህ ፀጋዬ የሚታወቅበትን፣ የሼክስፒር ቴአትር በፀጋዬ ጉልበት ተርጉሞ እንዲዘጋጅ በማድረግ ሎሬቱን ጋበዘው፡፡ ቴአትሩ ሲያልቅ ፀጋዬ ቆሞ እያጨበጨበ ነበር፡፡
“ታዲያስ?” አለ ወጣቱ ፀሐፌ ተውኔት
“አሁን ሰርተሻል!” አለው አንጋፋው ፀሐፌ ተውኔት፡፡
እልህ የወለደው ወጣቱ ፀሐፌ ተውኔት መስፍን ዓለማየሁ ነበር፡፡ የትርጉም ሥራው ደግሞ “የቬኑሱ ነጋዴ”፡፡
ታዲያስ? …

Read 2201 times