Monday, 06 April 2015 08:23

የመጽሐፍ ቅኝት

Written by  ነቢይ መኮንን -
Rate this item
(0 votes)

የሃይለማርያም ወልዱ ያልተዘጉ ፋይሎች (መጋቢት 2007 ዓ.ም)

(በዕውነተኛ ታሪክ ላይ የተመሰረተ)
አንዳንድ ነጥቦች

ብዙ ቴክኒካዊ ሳልሆን ሃሳቤን መሰንዘር ስለፈለኩ ነው “አንዳንድ ነጥቦች” ያልኩት፡፡ አንድን መጽሐፍ የገባንን ያህል ካነበብን በቂ ነው ባይ ስለሆንኩ ነው፡፡
ሃይለማርያም ወልዱን ዱሮ ነው የማውቀው፤ በእኛ ዱሮ ለዛሬው ትውልድ ጥንት በሚባለው ዘመን - በ1966 ግድም፣ በነበረው አራት ኪሎ፡፡ በመፅሐፉ ገፅ 195 ላይ የጠቀሰውን ዓይነት የእስካውትነት፣ የቴያትርና ሙዚቃ ክበብ አባልነት፣ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በተማሪዎች እንቅስቃሴ ከፍተኛ ደረጃ ወቅት መግባት፣ ከሪቮዎች መቆራኘት፣ በፓናሎች መሳተፍ የUSUA ተካፋይነት፤ ከስብሰባ በኋላ የተናጋሪዎቹን ቃላት ለመፍታት ዲክሺነሪ ፍለጋ ኬኔዲ መፅሐፍት ቤት መሄድ … ከዚያ ካንዱ ፓርቲ ጋር ቃልኪዳን ማሰር… መመልመል… በሚለው አይደለም የማውቀው፡፡ እንዲያው አራት ኪሎ ነው የማውቀው፡፡ ኃይለማሪያም የሚያውቀውን በሆነ ዘዴ መናገር የሚፈልግ ሰው እንጂ ደራሲ ነኝ ባይ አይደለም። ለኔ ይሄ ይበቃኛል፡፡ ዘለግ ባለው ቁመቱ ላይ ረጋ ያለው ጥሞናውና የጠለለ አነጋገሩ የዛሬ ብቻ አይደለም፤ ያኔም የነበረ ነው፡፡
የብስለት ምልክት ይመስለኛል፡፡ ከማውቃቸው በሳል ረዣዥም ሰዎች፣ የያኔውን የተማሪዎች እንቅስቃሴ ደስኳሪ (Orator) ግርማቸው ለማን ያስታውሰኛል። ኃይለማርያም የኢሮብ ተወላጅ መሆኑን አሁን ነው ያወቅሁት፡፡ (እንደ ዕውነቴ ከሆነ ኢሮብ የሚባል አገር መኖሩን በ66 ዓ.ም አላውቅም፡፡ ዛሬማ ብዙ ወዳጅ ከኢሮብ አፍርቻለሁ - አንድም በኢህአፓ ምክንያት፣ አንድም በግሌ) በመጽሐፉ ውስጥ እንደተገለፀው፤ “ኢሮቦች’ኮ የዓጋመ ዋነኛ የዘር ግንድ ናቸው፡፡ ደግሞም አንድም የጣሊያንን እግር ያልረገጠው የዓሲምባ መሬት ባለቤቶች፡፡ ለዘመናት ራሳቸውን በራሳቸው ሲያስተዳድሩ የኖሩ ኩሩ ኢትዮጵውያን …” ይላቸዋል፡፡ ቀጠል አድርጎም፤ “ኢሮቦች አባቶቻችን በጣም ጠንቃቆች ነበሩ፡፡ የማያውቁት ሰው ባለበት ምስጢር ለማውራት ከፈለጉ፤ ‹ቤቱ ውሃ ያፈሳል እንዴ?› ይሉ ነበር፡፡ ማለትም ቋንቋችንን (ሳሆኛ) የሚችሉ በአጠገባችን አሉ ወይ? ለማለት…” ሃይሉ እንግዲህ የዚህ አገር ሰው ነው!
ያልተዘጉ ፋይሎች 203 ገፅ ያለው ደራሲው “ፖለቲካዊ ልብወለድ” የሚል መጠሪያ የሰጠው መጽሐፍ ነው፡፡ ተጨማሪ ቅጥያ (Index ማለቱ ይመስለኛል) ያዘሉት አራት ገፆች ሲጨመሩ 207 ገፅ ነው በድምሩ፡፡
“ተጨማሪ ቅጥያ” ያላቸው ገፆች የያዙት የ80 የኢሮብ ተወላጆች ስም ዝርዝር፤ ቅጥያ ሳይሆን ዋና ጉዳይ ይመስለኛል፡፡ ለምን ቢሉ፤
“በኢትዮ - ኤርትራ ጦርነት 1991 -1993 በኤርትራ ሠራዊት ታፍነው ከተወሰዱ በኋላ የት እንደገቡ የት እንዳሉ፣ ይኑሩ ይሙቱ የማይታወቁ የኢሮብ ተወላጆች” ከሚል አጀንዳ ሥር የተነቆጡ በመሆኑ ነው፡፡ የቡክናይታ፣ የሐሰበላ፣ የአድጋዳ ብሎ ለይቷቸዋል፡፡ የአፋልጉኝ ጥሪ ነው - የፖለቲካ አቤቱታ ነው፡፡
በአንደኛው ውይይት ላይ ገጸ-ባህሪያቱ ሲነጋገሩ (ገፅ 188) “… እንደምታውቃቸው እነሱ (ኢሮቦች) እንደሆኑ የሌላም አይፈልጉም፤ የራሳቸውንም ከፍቃዳቸው ውጪ ማንም እንዲነካባቸውም አይፈቅዱም፡፡ “የኢሮብ ሚሊሺያዎች በታንክ የታጀበውን ብርጌድ ለብቻቸው ተጋፍጠውታል፡፡ of course የተወሰኑት በክብር ተሰውተዋል፡፡
“ኢሮቦች የሚቆጫቸው … ባለፉት ሁለት ዓመታት ሻዕቢያ ልትወረን እየተዘጋጀች ነው ጥበቃው ይጠናከር እያሉ ሲያመለክቱም በጎ ምላሽ አላገኙም ነበር፡፡ ይብሱኑ እንደገመቱት ዋና ከተማቸው ዓሊተና በኤርትራ ካርታ ተካተተች፡፡ ክህደት ተፈፀመብን ያሉት ኢሮቦች በሁለቱም መንግሥታት ለእስራትና እንግልት ተዳረጉ፡፡
“ይህ አካባቢ የኢትዮጵያ አካል ነው ካሉት ተሰሚነት ከነበራቸው መካከል ከአንድ መቶ በላይ የሚሆኑ ወንዶች፣ ሴቶችና የሃይማኖት አባቶችን መርጠው ሌሊት ከየቤታቸው አፍነው ወስደዋቸው ደብዛቸውም ጠፍቶ ቀርቷል”!!
ደራሲው ጉዳዩን ተናግሯል፡፡ የሚሰማ ይስማ! የመጽሐፉ ገፀ - ባህሪያት ያሉም የሌሉም መሆናቸው ይመስለኛል መጽሐፉን “ፖለቲካዊ ልብወለድ” ያሰኘው። የዕውነት ፖለቲካ አለበት፡፡ ስለሆነም ፖለቲካዊ ነው፡፡ ልብ የወለደው ሃሳብ፣ ምኞት፣ ታሪክ፣ ተረት፣ ውይይታዊ ዕውነት፣ ህሊናዊ ፍላጐት አለበት፡፡ ልብወለድ የሚያረገው ያ መሆኑ ነው፡፡ እንጂ ምሉዕ በኩላሄ የሆኑ የልብ ወለድ አላባውያን ማለትም፡- ቅርፅ (Form)፣ ልብ - ማንጠልጠል (Suspense)፣ የታሪክ ሥሙር ፍሰት (Story – flow)፣ የሴራ ውስብስብነት (plot complexity)፣ (ለነገሩ የኢትዮጵያ ፖለቲካ በዚህ ረገድ ሴራንም ውስብስብነትንም በዕሙኑ ዓለም ያሟላ ነው)፤
የተሟላ መቼት (Setting)፣ ገፀ ባህርያት (Characters) መደምደሚያ ውሳኔ (Resolution) ወዘተ. ይኑርበት ብሎ ደራሲው የተጨነቀ አልመሰለኝም፡፡
እኔም ደራሲው በድርሰት ህግ ይመራም አይመራም ብዙ አልጠበኩበትም፡፡
ሁለቱ ዋና ዋና ተፈላጊ ነገሮች ውስጠ -ግፊት Motive እና ሥነ ውበት (aesthetics) ግን አሉት፡፡ ለእኔ ለጊዜው ይሄ በቂው ነው እላለሁ፡፡ በፖለቲካው ረገድ ሳስበው መጽሐፉ መረጃዊ Informative ነው፡፡ ለምሳሌ የታፈኑት ኢሮቦች የት እንደደረሱ ለመጠየቅ እግረ መንገዱን ሀ/ የኢትዮ - ኤርትርያ ጦርነት እንዴትና ለምን ተነሳ? ለ/ በማን ምክንያትና ፍላጐት ተነሳ? ሐ/የነማንን መሬት ቆረሰ? አስቆረሰ? መ/የነማንን ሰዎች አፈሰ? ከቀያቸው አፋለሰ? ሠ/ውጤቱ ለማን ጠቀመ? የሚለውን መረጃ በማስታወስ ይቀሰቅሰናል፡፡
ለአስረጅነቱ አንድ ነገር ልጥቀስ፡- “የዓሊተና ጉዳይ ምን ደረሰ?” አለ አንዱ፡፡
“በቅርብ ቀን የክልሉ ፕሬዚዳንት ለኢሮብ ወረዳ ዋና ከተማ ትሆን ዘንድ ተመርጣለች በተባለው ቦታ ላይ የመሰረት ድንጋይ አኑሮ ተመልሷል፡፡”
“ለምን?” አለ ሌላው፡፡
…“ዓሊተና ለኤርትራ ተሰጠች ነው የሚባለው፡፡”
“እንዴት? ተሰጠች ወይስ ተሸጠች?” አለ አንዱ ትግርኛው … የኢሮብ ተወላጅ መሆኑን የሚያሳብቅበት፡፡
“ህዝቡስ ምን ይላል?” ቀጠለ ሌላው፡፡
“ሽማግሌዎች መርጦ ወደ አዲስ አበባ ለመላክ በመዘጋጀት ላይ እንዳሉ… ጉዳዩን አራግበዋል ከተባሉት መካከል ሁለቱ ታዋቂ ሽማግሌዎች ታሰሩ፡፡ …” በፊት ሁለቱ ወዲ አፎምና ወዲ ዜናዊ ጫካ ውስጥ እያሉ የጨረሱት ጉዳይ ነው የሚሉ ሰዎች አሉ፡፡ የዓሊተና ህዝብ ብቻ አይደለም ሌላው የዓጋመ ህዝብም እጅግ አዝኗል፡፡
እነዚህ ከብዙ ጥያቄያዊ ዒላማዎች አንኳር አንኳሮቹ ናቸው ብል ከጉዳዬ አልርቅም፡፡ መጽሐፉ በልዩ ዕይታ የታሪክ መመሳሰሎችን ለማፀህየትም ይሞክራል (verify ለማድረግ እንደማለት፡፡) እራሱ ደራሲው በጋዜጠኛው ገፀ - ባህሪ አንደበት፤ “የዓድዋ ድል በባድመ ተደገመ” በሚለው መፈክር ዙሪያ እንዲህ ያናግረዋል፡-
የዓድዋ ድልና ባድመ “በጣም ይመሳሰላሉ” ለምን?
የምኒልክ ሠራዊት የጣሊያንን ሠራዊት አቸነፈ - ዓድዋ ላይ፡፡
የኢትዮጵያ ሠራዊት የኤርትራን ሠራዊት አቸነፈ - ባድመ ላይ፡፡
ምኒልክ በድሉ ሳይቀጥልበት ወደ አ.አ ተመለሰ፡፡
የኢትዮጵያ ሠራዊት በድሉ ሳይቀጥልበት ወደኋላ ተመለሰ፡፡
አቸናፊው ምኒልክ ከወራት በኋላ ከጣሊያን ጋር የሰላም ስምምነት ፈረመ፡፡
አቸናፊው ጠ/ሚኒስትር ከወራት በኋላ ከወዲ አፎም ጋር የሰላም ስምምነት ፈረመ፡፡
ጣሊያን መረብ ምላሽ ኤርትራን እንድትይዝ ተፈቀደላት፡፡
ኤርትራ የጠየቀችው የመሬት ይገባኛል ጥያቄ በፍርድ ዕውቅና አገኘላት፤ ስለዚህ አለ ጋዜጠኛው “አቸናፊው ተቸናፊ፣ ተቸናፊው - አቸናፊ የሆኑባቸው ጦርነቶች ናቸው፡፡ መመሳሰላቸው አይገርምም?”
“ቸ” ከ “ሸ” ይጠብቃል የሚለው የኢህአፓና የመኢሶን የፊደል (ሆሄ) ትግልም አይቼበታለሁ። ከላይ የጠቀስካትን የአቸናፊ ተቸናፊ መስመሮች ያስተውሏል።
ሃይለማርያም የህወሓትን ድርጅትና የሻቢያን ጦርነት በውስጥ ዐይን አይተን እንድንከልስ (Revise, Rethink እንድናደርግ) ያግዘናል፡፡ እግረመንገዱን የሻቢያንና የህወሓትን መሪዎች ነገረ - ሥራ ስብስብ ባለ መልኩ ያወዳድርልናል፡፡ አስረጅ፡- ወዲ አፎምና ወዲ ዜናዊ በሚል ያሳየናል፡፡
ህወሓትና ሻዕቢያ
ሁለቱ - “ከእኔ ሌላ… አይኖርም” የሚል መርህ ተከታዮች ናቸው፡፡ ሕወሓት በትግራይ ይንቀሳቀሱ የነበሩትን ፀረ ደርግ ኃይሎች በሙሉ አስወግዷል። የትግራይን መሬት በሙሉ በራሱ ለራሱ ብቻ አደረገው። ሻዕቢያም ኤርትራ ውስጥ ከራሱ ሌላ ተቀናቃኝ ኃይል እንዲኖር አልፈቀደም፡፡ ለዚህም ሲባል ከጀብሀ ጋር ለተከታታይ ግጭቶች ተዳርጓል፡፡ የብዙ ኤርትሪያውያን ደም ተገብሮበታል፡፡
ወድ አፎምና ወድ ዜናዊ
በሩሲያዊ ዲፕሎማት ገፀ-ባህሪ አንደበት እንዲህ ይገለፃሉ፡- “ይገርማችኋል “ኃያሏ አገር” (አሜሪካን መሆኑ ነው) ዛሬ ባወጣችው መግለጫ፤ አዲስ ራዕይ የሰነቁ ተስፋ የሚጣልባቸው የወቅቱ የአፍሪካ ወጣት መሪዎች ብላ አንቆለጳጵሳቸዋለች፡፡ ለነገሩ ከዚህ የበለጠ ዕድል ከየት ይመጣላታል? ባንድ ወቅት ሣይታወቃት ከእጇ ያመለጠው የአፍሪካ ቀንድ ተመልሶ መዳፉዋ ውስጥ ገብቶላታል፡፡ ከምሥራቁ መዳከምና መፍረስ በኋላ ብቸኛዋ ልዕለ - ኃያል ሀገር ሆናለች፡፡ Yankees go home እያሉ ሲጮሁ ትግላችን ፀረ ኢምፔሪያሊስትና ፀረ - ፅዮናዊነት ነው ብለው የኮነኗትን አገር፤ ማሪን እናታችን አባታችን ብለው በጥላዋ ሥር ተሰባስበዋል፡፡ የቀን ጉዳይ ሆኖ ተመልሳ ለአፍሪቃ ቀንድ ዕቅድ አዘጋጅና አስፈፃሚ ወደመሆን ደረሰች፡፡ “ቦ ጊዜ ለኩሉ” እንዲል መጽሐፍ፡፡”
… “የፖለቲካ መሸዋወድ እንዳይሆን” አለና ቀጠለ፡፡ “ሁለቱን (ወዲ አፎምንና ወዲ ዜናዊን) የሚያውቃቸው እንደነገረኝ ከሆነ፣ እጅግ የተለያየ ስብዕናና አቋም አላቸው፡፡ በእኔ (በሩሲያዊው ዲፕሎማት ዐይን) ቆይታዬ አጭር ቢሆንም የተገነዘብኩት ይሄንኑ ነው፡፡ ልሳሳት እችላለሁ፡፡ እንዳልኩት ያየኋቸው በኮንፈረንሱና በሪሰፕሽኑ ላይ ነው፡፡
አጭሩ (ወድ ዜናዊ)፤ ለንግግር የተፈጠረ የሚመስል Eloquent ነው፡፡ እንግሊዝኛውን ከዋነኞቹ በላይ ያቀላጥፈዋል፡፡ አማርኛውም አፍ መፍቻው አይደለም፤ ግን አማርኛውን የመጀመሪያ አፍ መፍቻ ከሆናቸው በላይ ይቀኝበታል፡፡ አይደለምንዴ? ስሜቱን የመደበቅና የማስመሰል ችሎታም ያለው መስሎኛል፡፡ በአቋም ጉዳዮች ቃላት እየቀያየረ መደራደር ይችልበታል፡፡ (ጉዳዩ) እውነት ባይሆንም እንኳን ለጊዜው እውነት ነው ብለህ እንድትቀበለው ያደርግሃል፡፡”
ረጅሙን (ወዲ አፎምን) እንዲህ ይገልጠዋል፡-
“የተለያዩ የአገር ውስጥና የውጭ ቋንቋዎችን ይችላል፡፡ ነገር ግን ቋንቋን ማወቅና መቻል የተለያዩ መሆናቸውን ከርሱ ታያለህ፡፡ አነጋገሩ audienceን (አድማጭን) አይስብም፡፡ አጭርና ቁርጥ ያለውን ወርውሮልህ ቁጭ የሚል ዓይነት ነው፡፡ ሲናገርም ስሜቱን መደበቅ አይችልም፡፡ የሚያስቆጣ ከሆነ ፀጉሩ ይቆማል፣ ፊቱ የታመመ ጉበት ሲመስል ታያለህ፡፡… ሰውዬው በቃ ሚሊታሪስት ሜንታሊቲውን አዳብሯል፡፡
ስለዚህ አሁን በሚያስመስሉት ወዳጅነት የሚዘልቁ አይመስለኝም፡፡
ስለ ወዲ ዜናዊ ቀጠለ፡፡ (ይሄን እኔም እራሴ የማውቀው ነው፡፡)
“አጭሩ ብልጣብልጥ፣ ባለብሩህ አዕምሮ ነው ይባላል፡፡ የመናገርና የማንበብ ችሎታው ከተማሪነቱ ይጀምራል፡፡ በወቅቱ የነበረው የቀ.ኃ.ሥ ሽልማት ስኮላርሺፕና የወርቅ ሰዓት ከንጉሱ ተሸልሞ ነበር ዩኒቨርሲቲ የገባው፡፡ በትግሉ ወቅት ምድቡ የፖለቲካ ሥራ ነበር፡፡ ላለፉት 17 ዓመታት ፖለቲካውን ሲፈታና ሲያስር፤ ሲመራመርበት ኖሯል፡፡
ተፈጥሮ ከሰጠችው ችሎታ በተጨማሪ ብዙ ልምድ አካብቷል፡፡ በውይይት ለማሳመን ይሞክራል፡፡ ይሳካለታልም ይባላል፡፡ የሚያውቁት ሰብዓዊ ባህሪውንም ያደንቁለታል፡፡ ተቃዋሚዎቹን ሳይቀር ስንቅ ሰጥቶ ሸኝቷል ይሉታል፡፡”
…“የወድ አፎም”ን ግን ከዚህ ባህሪያት በተቃራኒው ያስቀምጡታል -
ግትር፣ እልከኛና ጨካኝ በማለት፡፡ በተዋጊነቱና ወታደራዊ ስልቱ ግን ተደናቂ ነው ይባላል!”  
ማህበራዊ የሆኑ ጉዳዮችንም መጽሀፉ የሚያነሳበት መንገድ ደስ ብሎኛል፡፡ ያው ቀደም ብዬ እንዳልኩት በውይይት መልክ ነው የሚያስቀምጠው፡- (ገፀ 112) ሞቅ ብሎናል በጨዋታ መኸል ሳይታወቀን ብዙ ጠርሚሶች ገድለናል፡፡
“የዓጋመ ልጅ ማግባት አለብኝ” አለ አስራቱ፡፡
“ትችላለህ፡፡ አጋሜዎች ዘር፣ ቋንቋ፣ ምንትስ አይገድባቸው፡፡ አብሽር” አለው ወዲ አጋመ፡፡
“ግን እንዴት አገኛለሁ?” አስራቴ ጠየቀ፡፡
“የአዲግራት ልጅ የምትለይበትን ዘዴ እነግርህና ትሞክረዋለህ” አልኩት፡፡ “የምነግርህ ዘዴ እንደ ቀልድ ሲወራ የሰማሁት ነው፣ እሺ?”
“አንዷን ይፈትወኪ (እወድሻለሁ) ስትላት … አነለ (እኔም) ካለች - በቃ የመቀሌ ልጅ ናት፡፡
“ሌላዋን - ይፈትወኪ ስትላት … ‹ምእንታይ ለካ› (ምን አለህ) ካለች - የአዲግራት ልጅ ናት፡፡
“ሌላዋን - ይፈትወኪ ስትላት … ‹መገበሲካ› (መነሻህ) ካለች የአድዋ ልጅ ናት፡፡”
ከት ብሎ ሳቀ፡፡ .. “የአዲግራቷ ሚዛን ኢኮኖሚ ሆነ ማለት አይደለም? ድሮውንስ ከጉራጌ ይመሳሰሉብኛል አላልኩም?” አለና ተሳስቀን ቢሉ (ሂሳቡ) እንዲመጣ ጠየቀ፡፡
መጽሐፉ በንዑስ - ርዕሶች የተከፋፈለ ነው፡፡ ለንባብ ይመቻል፡፡ እያንዳንዳቸው ምን ርዕሰ - ጉዳይ አካትተዋል?
(ሳምንት ይቀጥላል)

Read 2482 times