Monday, 06 April 2015 08:18

ሁለት ባላ ትከል አንዱ ሲሰበር ባንዱ ተንጠልጠል

Written by 
Rate this item
(10 votes)

ከዕለታት አንድ ቀን አንድ ባላገር አንድ የማያውቀው ጫካ አቋርጦ ወደ መንገዱ ሊወጣ ሲጓዝ፤ አንድ የንጉሥ ልጅ በፈረስ ሆኖ ሲንሸራሸር ባላገሩን ያገኘዋል፡፡ ባላገሩ እጅ አልነሳም ልዑሉን፡፡ አልተሸቆጠቆጠም፡፡
ልዑሉ በጣም ገረመው፡፡ በአገሩ ደንብ ንጉሥን አክብሮ ለጥ ብሎ እጅ መንሳት ነበረበት፡፡ ባያውቅ ነው ብሎ በመገመት፤
“እንደምን ዋልክ?” ይለዋል፡፡
“ደህና እግዚሐር ይመስገን” ይላል ባላገሩ፡፡
“ለመሆኑ ንጉሥ ማለት ምን ማለት እንደሆነ ታውቃለህ?”
“አላውቅም” አለ ባላገር፡፡
“እንግዲያው ና ፈረሴ ላይ ውጣ፡፡ አፈናጥጬ ይዤህ እሄዳለሁ፡፡ ንጉሥ ማለት በሄደበት ሁሉ ሰው እጅ የሚነሳው፣ መንገደኛ ቆሞ የሚያሳልፈው የተከበረ ሰው ነው። ስለዚህ ቀስ በቀስ ንጉሥ ምንና ማን እንደሆነ ይገባሃል” አለና ያን ባላገር አፈናጠጠው፡፡
ወደ ከተማ እየተቃረቡ መጡ፡፡
“እንግዲህ አሁን ልብ ብለህ አስተውል” አለ ልዑሉ፡፡
የከተማው ሰው ልዑሉን ሲያይ ወዲያው የሚሄደው ቆመ፡፡ የቆመው ለጥ እያለ እጅ ነሳ፡፡ ልዑል  ዝም ብሎ መንገዱን ይቀጥላል፡፡ ህዝም እየቆመ እጅ እየነሳ ማሳለፉን ቀጥሏል፡፡ ይሄኔ ልዑሉ፡-
“አንተ ባላገር፤ ንጉሥ ማን እንደሆነ አሁን ገባህ?” ሲል የጠቀው፡፡
ባላገሩም፤
“አዎን አሁን ገብቶኛል” አለ፡፡
ልዑሉ ቀጥሎ፤
“ማን ነው ንጉሡ?” አለና ጠየቀ፡፡
ባላገሩም፤  
“እንግዲህ ወይ እኔ ወይ አንተ ነና!” አለና መለሰ፡፡
*       *      *
ስለተፈናጠጡ ብቻ የነገሡ የሚመስላቸው አያሌ አይተናል፡፡ በተሰጣቸው ትርጓሜ - ነገር (Definition) መሠረት ብቻ ጉዳዮችን እየተረጎሙ የሚጓዙ የዋሃንንም አስተውለናል፡፡ ግራ ቀኙን ሳያዩ በተሰመረው መስመር ላይ ብቻ የሚነጉዱ፣ ወቅት የሚለወጥ የማይመስላቸውና ወቅትም የማይለውጣቸው በርካታ መንገዶችን ታዝበናል፡ “ሳይማር ያስተማረንን ገበሬ አንረሳውም” ብለው ሲያበቁ ከተማ ገብተው ከተሜ ሲሆኑ፤ የሚገነቡትን ህንፃ ብቻ ዐይን ዐይኑን እያዩ መሰረታቸውን የረሱ ዕልቆ መሣፍርት የሌላቸው መሆናቸውንም ገርሞን አይተናል፡፡ ጥንት “ሠፊው የኢትዮጵያ ህዝብ ሆይ! የረሱህን አልረሳናቸውም” ብለው ጀምረው ከነመፈጠሩም ያላስታወሱት ባለጊዜዎችንም ተመልክተናል፡፡ በህዝብ የሚምል የሚገዘት ፓርቲ፣ ድርጅት፣ ማህበር አገራችን አጥታ አታውቅም!
የፖለቲካ አየር የኢኮኖሚውን ንፋስ መከተሉ በዓለም ታሪክ እንግዳ ነገር አይደለም። የኢኮኖሚ ብሶት ወደ ፖለቲካ ምሬት መለወጡና የፖለቲካ ጥያቄን መውለዱም ሁለንተናዊ ዕውነታ ነው፡፡ ይሄ የቆረቆረው ፓርቲ፣ ድርጅት፣ ቡድን ወዘተ… ጥያቄውን አንግቦ መነሳቱና መልስ መሻቱ አይቀሬ ነው፡፡
ከጭፍን ጥላቻ ውጪ ይሄን ጥያቄ ማንሳት ዲሞክራሲያዊ መብት ነው፡፡ መብቱን የሚያውቅ፣ የገባውና የሚገባውን የሚያውቅ ዜጋ ያላት አገር የታደለች ናት! ይህንን ዕድል ለመጠቀም የሚችል ንቃተ ህሊናው የበለፀገ ዜጋ ሀገሩን በቅጡ ይታደጋታል ተብሎ ይገመታል፡፡ እንዲህ ያለ ዜጋ የገዛ ዐይኑን ጉድፍ ሳያነፃ ከወንድሙ ዓይን ጉድፍ አወጣለሁ ብሎ አይፍረመረምም፡፡ ራሱን ከሙስና አያድንምያላፀዳ ዜጋ፤ አገሩን ከሙስና አያድንም፡
ራሱን ዲሞክራሲያዊና ፍትሐዊ ያላደረገ ታጋይ፤ ዴሞክራሲያዊና ፍትሐዊ ሥርዓትን እገነባለሁ ቢል ሐሳዊ ታጋይ ከመሆን አያልፍም፡፡ ራሱ ህገ - ወጥ የሆነ ኃላፊ፤ የህግ የበላይነትን ያስከብራል ብሎ ተስፋ ማድረግ ከእባብ ዕንቁላል እርግብ መጠበቅ ነው፡፡
የምርጫ ወቅት ላይ ብቻ ስለ ኢ-ወገናዊነት የሚሰብክ ሰሞነኛ ወይም የወረት መንገደኛ ፍሬው በቀላሉ አይጐመራም፡፡ ጧት የተነሳ ብቻ ነው የማታ አዝመራው የሚሰምርለት፡፡
ፀሐፍት እንደሚሉት፤
“የምርጫ ወቅት ሙስና፡- Fake የይስሙላ ፓርቲዎችን ተወዳዳሪ አስመስሎ ከማቅረብ፣ እስከ ድምጽ ስርቆት ሊሄድ ይችላል፡፡
“በዚህ ምክንያት ነው በብዙ የአፍሪካ አገሮች ምርጫ ከመነሻው እስከ መድረሻው በውዝግብ የታጀበ የሚሆነው!”
ይሄን ልብ ብሎ ያልተገነዘበ ዜጋ ቡድን፣ ድርጅት ለራሱም አይሆን፤ ለአገሩም አይበጅ፡ ይልቁንም ነቅቶ መጠበቅ፤ ድምፁን እንዳያጣ፣ እንዳይጭበረበር፣ ያግዘዋል፡፡ ያ ካልሆነ ህዝባዊ ገዥነቱን የሚያረጋግጥበትን ዋና አቅሙን፣ ሠረገላ ቁልፉን አጣ ማለት ነው፡፡ የሚከበርና የሚፈራ ህዝብ የሚኖረው መብቱን የሚያውቅና የሚያስከብር ሆኖ ሲገኝ ነው፡፡ መብቱን ሲሸራርፉበት እምቢ! ማለት ሲችል ነው፡፡ በደልን፣ ግፍን እያየ ዝም ሳይል ሲቀር ነው፡፡ የፖለቲካ ሙስናን አልቀበልም ማለት ሲችል ነው፡፡ አስተዳደራዊ ብልሹነትን አሻፈረኝ ማለት ሲችል ነው! ቢሮክራሲያዊ እንቅፋቶችን አልቀበልም ማለት ሲችል ነወ፡፡ ባላስደሰተኝ ነገር አላጨበጭብም ማለት ሲችል ነው፡፡ እስከዛሬ ባየናቸው የተቃውሞ ጉዞዎች ውስጥ አማራጭ የትግል ስልቶችን ሳይቀይሱ በአንድና አንድ ግትር ስልት ብቻ እንጓዝ ብለው ብቸኛ መንገድ የመረጡ ሰዎች ቢያንስ መጨረሻቸው አያምርም፡፡ ሁለተኛም ሶስተኛም መጓዣ መንገዶችን ገና በጠዋት ማዘጋጀት ይገባቸዋል፡፡ ፈረንጆቹ “ፕላን ቢ”፣ “ፕላን ሲ” እንደሚሉት ነው፡፡ በአማርኛ “ሁለት ባላ ትከል፤ አንዱ ቢሰበር ባንዱ ተንጠልጠል” እንደማለት ነው!



Read 4957 times Last modified on Monday, 06 April 2015 08:22