Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 21 January 2012 10:38

የጨፌ - ዓይን

Written by 
Rate this item
(2 votes)

ቡና የለም እንጂ ቡናማ ቢኖር

ወይ አገር ወይ አገር ወይ አገር ጐንደር፡፡

(የታወቀ አባባል)

ይመስገን ቡናዬ የዘለለው “ካፌ”

ዛሬ አለም አውቆኛል ብሎ ይርጋጨፌ፡፡

(ያልታወቀ አባባል)

የምን “ማፋሸግ ነው?” በዚህ ውብ ቀን ዓይንን ማጨናበስስ ምን ይሉታል? መደበሩንስ ምን አመጣው? ጌታዬ ይልቅ ቀልብዎን ይሠብስቡ፡፡ ቡና ተጠርተናል፡፡ ጌድኦ፡፡ እንደ ጋምቤላ ማንጐ ጁስ የወፈረ፡፡ በቅቤ እንደታሸ የጐራጌ ቆሎ የሚያብረቀርቅ፣ ሲቀዳ እንደ ዶሮ ዓይን የሚቀላውና ሲጠጡት ነቃ-ፈካ፣ ደስ የሚያሰኝ - የይርጋጨፌ ቡና፡፡ ካላመናችሁ የአሜሪካውን ስታር ባክስ ሀላፊዎችና ደንበኞች ጠይቁ፡፡ አለበለዚያ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ መረጃዎችን መርምሩ፡፡ ቡናው የምር ጉደኛ ቡና እንደሆነ ትሠማላችሁ፡፡ የራሡ መለዮ /brand/ እንደተሰጠውና ከ36 በላይ የዓለም ሀገራት መታወቁን ታደምጣላችሁ፡፡ ኦርጋኒክ መሆኑንም ትረዳላችሁ፡፡ የኢትዮጵያ ሬዲዮ ሁሌ ጧት “የገቢ ምንጫችን ቡና ቡና ..” እያለ የሚዘምረው ወዶ አይደለም ብላችሁ ራሣችሁን ከፍና ዝቅ ታደርጋላችሁ፡፡ እናም በትክክል ይገባዋል ትላላችሁ፡፡ ሳልቀምሠው አሉ እንዴ? የይርጋጨፌ እናቶች ዝግጅታቸውን አጠናቀዋል፡፡ እንደ ሙሽራ በሚያሳሳ ፈገግታቸው፣ እንደ ልጅ አፍ በሚጣፍጥ አንበደታቸው “ቡና ሀዌኤ”  ብለዋል፡፡ በሞቴ ግብዣ አይናቁ፤ ይከተሉኝ፡፡

የአቶ ቡሼ ጨፌ

የደቡብ መንገዶች እንደ ሠሜኖቹ አንጀት አይደሉም፡፡ ያፈቀሯት እንስት ሠፈር ያህል ቅርብ ናቸው፡፡ ከአስፓልቱ ይልቅ የኪሎሜትሩ ቁጥር ያስጨንቃል፡፡ ለምሣሌ ሀዋሳ ከአዲስ አበባ 275 ኪ.ሜ ትርቃለች፡፡ ወይ የአንድ ቀን መንገድ ነው ወይም የዘጠኝ ሠዓት ጉዞ ነው ብላችሁ እንዳትማረሩ በደረጃ አንድ አውቶቡስ የአራት ሠዓት መንገድ ነው፡፡

ከምንጊዜው ደሠርው በከተማዋ ውበት ተገረሙ፡፡ ሀዋሳ የምር እንደቡና ቤት ሴት ሽቅርቅር ናት፡፡ እንደፈነዳች ልጃገረድ ቅምድምድ ናት፡፡ ጧት መኳል ነው፡፡ ማታ መቀባት ነው፡፡  ሌሊት መዘነጥ ነው፡፡ አዙሪቷ በአጭሩ የሚቆም አይደለም፡፡ የሀምሳ አንድ ዓመቷ አዛውንት ከተማ የሁልጊዜ ልምዷ ነው፡፡ እውነት ለመናገር ሀዋሳ እርጅናን የምትፈራ ከተማ ናት፡፡ ሞትን የምትሸሽ ሀገር ናት፡፡ ባይሆንማ አስፓልታዊ ፊቷን ባለፀዳች፡፡ ሸፋፋ ቤቶቿን ባለደሠች፡፡ ታሪክ እንደሚነግረን ትላንት አባባ ጃንሆይ ለአቅመ ሠፈር አጯት፡፡ ደርጉ የሐረር ወታደሮችን አስፍሮ ካምፕ እንድትሆን ፈረደባት፡፡ ዛሬ ኢህአዴግ የደቡብ ክልል ርዕሠ ከተማ አድርጓታል፡፡ ሁኔታውም ተመችቷታል፡፡ እነ አባባ ጅማን፣ እነ እማማ ደሴን ጥላቸው ላሽ ብላለች፡፡ እነ ጋሼ  ናዝሬትን፣ እነ እትየ መቀሌን ትታቸው መርሻለች፡፡ ዙሩን አክራባቸዋለች ብሎኛል አንድ ጓደኛዬ፡፡

ከሀዋሳ 90ኪ.ሜ በኋላ ዲላ አለች፡፡ የጌድኦ ዞን ዋና ከተማ ነች፡፡ አሁን ዓይንዎን ከመኪናው መስኮት ባሻገር ይወርውሩ፡፡ ሰማያዊ ሠማይ፣ አረንጓዴ ጫካ፣ ዓይን የሚያፈዝ መልክዓ ምድር፣ ልብ የሚሠርቅ ልምላሜ ያስተውላሉ፡፡ እናም ቁጭት ቢጤ ይሠማዎታል፡፡ እዚህም እኮ ድርቅ አለ ብለው እጅዎን አገጭዎ ላይ ይጥላሉ፡፡ በሀሣብ ተክዘው 37 ኪ.ሜ ከተጓዙ ይርጋጨፌ ደረሱ ማለት ነው፡፡ መረጃዎች እንደሚጠቀሙት ይርጋጨፌ በ1926 ዓ.ም ነው የተቆረቆረችው - በአንድ ሰው፡፡ አቶ ቡሼ ጉመላ ይባላሉ፡፡ የተራራ ህይወት ሲሠለቻቸው ወደ ረግራጋማዋ ጨፌ ወረዱ፡፡ አካባቢውን ወደውታል፡፡ ሳሩ ሞልቷል፣ ቄጠማው ነፍ ነው፡፡ ምንጮቹ እንደጉድ ይንፎለፎላሉ፡፡ ደኑ የአውሬ መነሀሪያ ሆኗል፡፡ ቡናው እንደ አሸዋ በየቦታው ተበትኗል፡፡ የሚለቅማው አጥቷል፡፡ የሚያጥበው የለም፡፡ የሚፈለፍለው አላገኘም፡፡ የሚሸጠው ናፍቋል፡፡ ሽማግሌው ከዚች ለምለም ምድር ዓይናቸውን ሆነ እግራቸውን መንቀል አልፈለጉም፡፡ ስም ጠየቁ፡፡ ሠማሮ ሠዶ (ትክል ድንጋይ) እንደምትባል አወቁ፡፡ እርሳቸው ግን ይርጋጨፌ ብለው ለወጡት፡፡ በአሁኑ ወቅት አንድ የአንደኛ ደረጃ ት/ቤት በአቶ ቡሼ ስም ተሠይሟል፡፡ ጨፌ ለታላላቅ አባቶቿ ፊቷን አላዞረችም፡፡

የቡና ስባቱ መፋጀቱ

ዛሬ ዛሬ የአዲስ አበባ ካፌዎች ስለ ወንበራቸው እንጂ ስለ ቡናቸው ይጨነቃሉ? ስለ ስኒዎቻቸው ውበት እንጂ ስለስፕሬሶአቸው ያስባሉ? ስለ ዲኤስቲቪው እንጂ ማኪያቶው ጉዳያቸው ነው?

በቸርቸር ጐዳና ውረዱ፡፡ በብሔራዊ ቲያትር ጥላና በራስ ሆቴል ድባብ መካከል የሚዋልሉ ቡና ቤቶች አሉ፡፡ ወደ ስድስት ኪሎ ውጡና በአንበሳ ግቢ ጀርባ የተኮለኮሉ የአንብቦ አዳሪዎችን ፌርማታ ተመልከቱ፡፡ የቡና ሡስ የተጠናወታቸው ተማሪና ተመራማሪ አንድ ሁለት ሲሉ ትታዘባላችሁ፡፡ ወይም ፒያሳ ሂዱና እንደ አሸን የፈሉትን ካፌዎች ጣዕም የእውነት አጣጥሙት፡፡ አለበለዚያ በየሠፈሮቹ የተፈለፈሉትን ቡና ማደያዎችን ጐብኙ፡፡ በንፅፅር ቡናቸው እንደ ሠነፍ ሴት ጠላ ቀጭን ነው፡፡ ደግሞ ከንፈር ላይ ሲደርስ መቀዝቀዙ፡፡ የምር “እባክህ ባሬስታው ሞቅ አድርገው እንጂ” ብለው  ተነጫንጨው አያውቁም? እሺ ገብስ እንደ ወረደ አላጣጣሙም?  ወደ ይርጋጨፌ እንመለስ፡፡ የእነ አለም፣ መስታወት እና እናት ቡና ዝነኛ ነው፡፡ ቡናው ሲቀዳ የታሸ ደማከሴ ይመስላል፡፡ ሲጠጡት ያልባል፡፡ ውፍረቱ እንደ ደጋ ማር ነው፡፡ ደጋግመው ሲጠጡት ደግሞ ያፈካል፡፡ በቡናው ትኩስነት እጅና ምላሴ ሲቃጠል የታዘበች አንዲት አስተናጋጅ፤ የቡና ስባቱ መፋጀቱ ስትል ስቃብኛለች፡፡ በተጨማሪም “ገበያ ፈጣሪዋ” እየተባሉ የሚሞካሹት ዶ/ር እሌኒ ከአንዴም ሁለት ጊዜ ወደ አካባቢው ብቅ ብለው አቦል ቡና ቀምሠው መመለሳቸውን ሰምቻለሁ፡፡

በነገራችን ላይ የይርጋ ጨፌ ወረዳ ስፋት 30,000 ሄክታር ሲሆን ከ20,000 ሄክታር በላዩ መሬት በቡና የተሸፈነ ነው፡፡ በአሁኑ ሠዓት አንድ ኪሎ እሸት ቡና 25 ብር ብቻ ነው፡፡

ስጋ ለስጋ

ኑሮ እንዲህ ጣራ ቢነካም፣ በይርጋጨፌ የስጋ አምሮቱም ገበያውም፣ ቆረጣውም አልቀነሰም፡፡ እንድ ጉድ ስጋ ይበላል፡፡ ብዛት ያላቸው ሰንጋዎች ይጣላሉ፡፡ አያሌ ልኳንዳ ቤቶች ያከፋፍላሉ፡፡ ነዋሪው “ስጋ ለስጋ” ተገቢ ነው እያለ ይመገባል፡፡ በከተማዋ የሚዘጋጁ የተለያዩ ባህላዊና ዘመናዊ ምግቦች አሉ፡፡ “ቸስ ቸስ” እና “ቢፒ አር” የተሰኙት ግን ፈገግ አሰኝተውኛል፡፡

የጨፌ ቦጨ

ቦጨ ማለት ሙስና ነው፤ በይርጋጨፌ ቋንቋ፡፡ ይርጋጨፌ እንደ ቡና ገበያዋ መሠረተ ልማቶቿ አላደጉም፡፡ ነዋሪዎቿ “እየተቦጨቅን ነው” ይላሉ፡፡ የከተማው የቧንቧ መስመር ዝርጋታ ተጀምሮ ቆሟል፡፡ የውስጥ ለውስጥ መንገድ ግንባታው ባለበት ፈዟል፡፡ ዓመት የፈጀችውም የመቶ ሜትር  የኮብል ስቶን መንገድ ስራ፣ እሳት አስነስታ የከተማውን አመራር አውጥታ አውርዳቸዋለች፡፡ አስገራሚው ነገር ግን የአካባቢው ትራፊኮች ነገር  ነው፡፡ እኛን በሚኒባስ ጨፌ የወሠደን ሾፌር ስለ እነሡ አምቶ አይጠግብም፡፡ እነሡ እኮ በቦጨ ላይ እስፔሻላይዝድ ያደረጉ ምሁራን ናቸው ሲል ይቦጭቃቸዋል፡፡ “ምነው ጨፌን በዓየር ላይ በዘለልናት” ብለው ቅኔ የሚዘርፉም ብዙ የስራ ባልደረቦቼ አሉኝ ይላል እየሳቀ፡፡ በእርግጥ አያስቅም፡፡ይሄ ቀልድ አይደለም፡፡ ሠው እንደ ዶሮ በላይ ላይ እየጫነ  የሚበርን ሚኒባስ ዝም የሚሉ አንዳንድ ትራፊኮች እኔንም ገጥመውኛል፡፡ ግን ለማን አቤት ይባላል? ለተሳፋሪ፣ ለሹፌር፣ ለትራፊክ፣ ለመንግስት፣ ለፈጣሪ …?

 

 

Read 4101 times Last modified on Saturday, 21 January 2012 10:41